10 Jun, 2017 

 ሰለሞን ጐሹ 

 ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/)፣ የሚዲያ ኤክስፐርት

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/) መቀመጫቸውን በደቡብ አፍሪካው ዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉ የሚዲያ ኤክስፐርት ናቸው፡፡ ኢጂኒዮ ተነፃፃሪ የሚዲያ ሕግና ፖሊሲ ላይ በማተኮር ይሰሩበት ከነበረው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሴንተር ፎር ሶሽዮሌጋል ስተዲስ ለቀው ዊትስ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉት እ... 2016 ነው፡፡ ይሁንና አሁንም የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ አሶሼት ሪሰርች ፌሎው ናቸው፡፡ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ከኦክስፎርድ በፊት በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ጥናቶች የትምህርት ክፍል ሠርተዋል፡፡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም ለጣሊያን ኢኖቬሽን ሚኒስቴር በሮም ይሠሩ ነበር፡፡ የኢጂኒዮ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮችን የተመለከቱ የሚዲያና የፖለቲካ ለውጥ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በመላው ዓለም እየተመነደጉ ያሉ ልዩ የሆኑ የኢንፎርሜሽን ማኅበረሰብ ሞዴሎች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ ኢጂኒዮ በርካታ የጥናት ፕሮጀክቶችን የመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በምሥራቅ አፍሪካ፣ የሰላም ግንባታና በአገር ግንባታ ላይ ያለውን ሚና የሚገመግመው፣ እንደ ቻይና ያሉ በመመንደግ ላይ የሚገኙ ኃይሎች በአፍሪካ ሚዲያና ቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ እየጨመረ የመጣውን ሚናቸውን ለመረዳት የተካሄደው፣ እንዲሁም ከምርጫ በፊት በኢንተርኔት አማካይነት የሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮች ባህሪና ተፅዕኖን ለመተንተን የተካሄደው ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የኢጂኒዮ የፒኤችዲ ጥናት በኢትዮጵያ ልማትና አለመረጋጋት ያላቸውን ግንኙነት የሚመረምር ሲሆን፣ በአገሪቱ ላይ ከ12 ዓመታት በላይ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ኢጂኒዮ በቅርቡ በግብፅ ካይሮ የናይል ቤዚን ካፓሲቲ ቢዩልዲንግ ኔትወርክና የዩኔስኮ ወተር ኤዱኬሽን ኢንስቲትዩት በመተባበር አዘጋጅተውት በነበረ ሥልጠና ላይ በአሠልጣኝነት ተሳትፈው ነበር፡፡ ሥልጠናው በናይል ላይ የሚሠሩ ሳይንቲስቶችና ጋዜጠኞች እየተመጋገቡ በሚሠሩበት መንገድ ላይ ግንዛቤ ለመስጠት ያለመ ነበር፡፡ በሥልጠናው የተሳተፈው ሰለሞን ጐሹ በኢትዮጵያ ስላለው የሚዲያ ነፃነትና የሥልጠናውን ጭብጥ በተመለከተ ኢጂኒዮን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡ በአፍሪካ ስላለው ወቅታዊ የሚዲያ ይዞታና የትኞቹ አገሮች የተሻለ አፈጻጸም እያሳዩ ስለመሆኑ ምን ይላሉ? ኢትዮጵያስ በአንፃራዊነት የት ትገኛለች?

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/)– አንዱን አገር ከሌላው አገር ጋር በማነፃፀር ደረጃ በማውጣት አላምንም፡፡ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በሶማሊላንድ፣ በሩዋንዳና በተለያዩ አገሮች ካካሄድኩት ጥናቶች መረዳት የቻልኩት እነዚህ አገሮች ኮሙዩኒኬሽንን በተመለከተ የራሳቸው በጎ ጎን ያላቸው ቢሆንም፣ ይህን በዓለም ላይ ካለ የትኛውም አገር ኮሙኒኬሽን መዋቅር ጋር በቀላሉ ማነፃፀር እንደማይቻል ነው፡፡ በኬንያ ላይ በሠራሁት አንድ ጥናት ከታዘብኳቸው ጉዳዮች አንዱ በአገሪቱ የራዲዮ ቶክሾውስ በጣም ተወዳጅ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመጣው እንደ ጣሊያንና እንግሊዝ በመሳሰሉ ሌሎች ቦታዎች ባልተለመደ ሁኔታ በፕሮግራሞቹ በሚስተናገዱ በንቁ ተሳትፎ የታጀቡ ክርክሮች የተነሳ ነው፡፡ ንቁ ተሳትፎው ደግሞ የመጣው በፕሮግራሞቹ የግለሰቦች ድምፅ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡም መሰማት አለበት ከሚለው እምነት ነው፡፡ ሁሌም ግንዛቤ ውስጥ የማንከተው አንዱ ነገር በሚዲያ የሚነገሩ ነገሮች በመንግሥት ዝቅተኛ መዋቅር የሚገኙ አካባቢዎች ላይ ለውጥ ሊያመጡ የመቻላቸውን ዕድል ነው፡፡ በአፍሪካ እንዳየሁት  በብሔራዊ ደረጃ በአብዛኛው ተግዳሮትና ክፍተት ነው የሚሰማው፡፡ ነገር ግን በተዋረድ መዋቅሮች የሚዲያ ለውጥ የማምጣት ኃይል ይታያል፡፡

የአፍሪካ ሚዲያ ምን እንደሚመስልና ምን መምሰል እንዳለበት፣ እንዲሁም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ጨምሮ በሕግ ማዕቀፍና በተግባራዊ አፈጻጸም መካከል ያለውን ተቃርኖ በተመለከተ ትልቅ ክርክር ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የካሜሩናዊው ምሁር ፍራንሲስ ንያምኖህ ሥራዎች የአፍሪካ ሚዲያ ልዩ ባህሪያት ምን እንደሚመስሉ ለማስገንዘብ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ ምሁር ኸርማን ዋሰርማን በኢንተርኔት ምንነት ላይ ተፈጥሯል ከሚባለው ዓለም አቀፋዊ ስምምነት በተቃራኒ፣ የአፍሪካን የኢንተርኔት ታሪክ ለመገንባት መጠየቅ ያሉብንን ጥያቄዎች ለማሳየት ይሞክራል፡፡ ስለዚህ አገሮቹን ከማነፃፀር ይልቅ በተጫባጭ በየአገሮቹ ያለውን ሁኔታ ማሳየት ይመረጣል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ አስደናቂ ለውጥ በማምጣት ላይ ብትሆንም፣ ለክርክር ምኅዳር ከመፍጠርና ሁሉም ወገን የሚያርፍበት መካከል ላይ ያለ ከባቢ ሁኔታ ከመፍጠር አንፃር ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነች፡፡ ሚዲያው ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እጅግ ጽንፍ የያዘ ነው፡፡ ከጋዜጠኝነትና ከተለያዩ ሙያዎች የመጡ ግለሰቦች በአገሪቱ ተቃራኒ ጫፍ ላይ የሚገኙ አካላት ተገናኝተው የሚያወሩበት አማካይ ሥፍራ ለመፍጠር በርካታ ሙከራዎች ሲያደርጉ አይቻለሁ፡፡ ይኼ በጣም ቅር የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ እርግጥ ነው ጉዳዩ አወዛጋቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በውስጡ ያሉ ግለሰቦች ይኼ አማካይ ሥፍራ እንዲኖር ዕድል የሰጡ መስለው ሁኔታው ለጊዜው እንዲኖር ካደረጉ በኋላ መልሰው በከፍተኛ ሁኔታ ሲዘጉት ይታያል፡፡ ሰዎች ማንም ጋዜጠኛ ወደ እስር ቤት ሊገባ አይገባም ሲሉ እሰማለሁ፡፡ እኔ በግሌ የምቃወመው እስሩን ሳይሆን ዓላማውን ነው፡፡ ማንም ቢሆን ባይታሰር ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ጽንፍ የያዙ ጋዜጠኞች ላይ መንግሥት የሆነ ዕርምጃ ቢወስድ እረዳለሁ፡፡ ሆኖም ለእኔ ልብ የሚሰብር ሆኖ ያገኘሁት ድልድይ የሚገነቡና ከኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም እስከ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ እንዲሁም የመንግሥትን ልማታዊ መንግሥት ነኝ ጨምሮ የአገሪቱን ተቋማዊ አደረጃጀት የሚያከብሩትንም ጭምር ሲዘጋ ማየቴ ነው፡፡ ይኼ አገሪቱን ወደ ኋላ የሚያስቀር ነው፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱን ጥቂት ባለ ብሩህ አዕምሮና ምርጥ ወንድና ሴቶች ልጆችን እየተከታተሉ ዕርምጃ መውሰድ ለረጅም ጊዜ ዘላቂ አይሆንም፡፡      

ሪፖርተር፡ከኢንተርኔት መስፋፋት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ በሠሩት አንድ ጥናትዎ በከፍተኛ ወጪ የሚገነባው የኢንተርኔት መሠረተ ልማት የፖለቲካ መሣሪያ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ይኼ ከኢትዮጵያ ጋር በተለይ የተያያዘ ችግር ነው? ወይስ በአኅጉሩ በስፋት የተለመደ ጉዳይ ነው

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/)– በአኅጉሩ ቴሌኮሙዩኒኬሽንን በሞኖፖሊ የያዙ አገሮች ኢትዮጵያና ጂቡቲ ብቻ ናቸው፡፡ የኢትዮዽያ ፖሊሲ በጣም ግልጽ ነው፡፡ ቢያንስ በአጭር ጊዜ የመቀየር ሐሳብ የለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት መሞገስ ያለበት አንድ ጉዳይ ቢኖር ዜጎችን እስከ መጨረሻው ተዋረድ ዘልቆ ለመድረስ ያለው ቁርጠኝነት ነው፡፡ ከተሜና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ብቻ ሳይሆን የተገለሉ ማኅበረሰቦችንም ለማካተት ይሞክራል፡፡ በአገሪቱ ካለው ብዝኃነትና አስቸጋሪ መልክዓ ምድር አንፃር ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደዚህ ግብ ለመድረስ የተመረጠው ስትራቴጂ በሞኖፖል የሚፈጸም በመሆኑ ማንንም አሸናፊ የሚያደርግ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን፣ የኢትዮ ቴሌኮም የቴክኒክ ተቀጣሪዎችን፣ እንዲሁም ፈንድ ያደረገውንና ሥራው ላይ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች ተወካዮችና ሌሎች ሰዎችን ቃለ ምልልስ በማድረግ እንደተረዳሁት የትኛውም ወገን ደስተኛ አይደለም፡፡ ውድድር ባለመኖሩና ጫና ስለሌለ የቴሌኮም አገልግሎትን የማሻሻል ፍላጎት የለም፡፡ የአገልግሎት ጥራቱ እጅግ የወረደ በመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሕዝብ ግን ቅሬታውን እያቀረበ ነው፡፡ ይህ አገልግሎት እንዲሻሻል በተለይ ከቴክኒክ አንፃር ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ ውድቀትንም ሆነ ስኬትን በታማኝነት መግለጽና መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረግ የማድረግ ዕቅድ ከሌለ ቢያንስ ባለው ሥርዓት ውስጥ አማራጮችንና ማትጊያዎችን በማምጣት፣ ሁሉም ወገኖች እንዲወዳደሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ እስካሁን ይኼ እየሠራ አይደለም፡፡   

ሪፖርተር፡መንግሥት ኢንተርኔት የምዘጋው በዚሁ አማካይነት የሚንሸራሸሩ ጽንፍ የረገጡ ሐሳቦች የአገሪቱን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው በሚል ምክንያት ነው፡፡ አንዱ የምርምር ሥራዎ በኢንተርኔት የሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮችን የተመለከተ ነው፡፡ የጥናቱ ግኝቶች ምንድን ናቸው? የባለድርሻ አካላትስ አስተያየት ምን ይመስላል?

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/)– ጥናታችን በሌሎች አገሮች እንዳለው ሁሉ በኢትዮጵያም የጥላቻ ንግግርና የጽንፈኝነት መገለጫዎች እንዳሉ ያሳያል፡፡ ይህ ‹‹መቻቻል››የሚል ርዕስ የሰጠነው ጥናት በዓይነቱ ለየት ያለ ስለሆን እንኮራለን፡፡ አማርኛ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባሉ ኢትዮጵያዊያን የሚነገር በመሆኑ በፌስቡክ የሚንሸራሸሩ አደገኛ ንግግሮችን በቁጥር መግለጽ መቻላችን፣ በኢትዮጵያም ሆን በመላው ዓለም የተለየ ጥናት አድርጎታል፡፡ ውጤቱ ለሁሉም በግልጽ ተደራሽ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም የተገኘው ቁጥር 0.7 በመቶ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ጥናታችን በመጠኑም ቢሆን ጽንፈኝነት እንዳለ የሚያሳይ ቢሆንም መንግሥት ኢንተርኔት ለመዝጋት ሰበብ ሊሆነው አይችልም፡፡ ሌላው በጥናቱ ይፋ የሆነው ነገር ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች በአብዛኛው የሚመጡት ከተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አለመሆኑን ነው፡፡ በተቃራኒው ጥቂት ተከታይ ሰዎች ናቸው ይህ አዝማሚያ ያላቸው፡፡ ለዚህ በሰጠነው ትርጉም መሠረት ይህን የሚያደርጉት የመገለል ስሜት ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የመጡ ናቸው፡፡ በአገሪቱ መፃኢ ዕድልና በሕይወታቸው ላይ ተፅዕኖ ባላቸው ፖሊሲዎች ላይ የመካተት ስሜት የላቸውም፡፡

ስለዚህ ኢንተርኔት የጥላቻ ንግግርን ከማንሸራሸር በላይ ሌሎች ንቅናቄዎችን ለመፍጠር ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የተለየ የፖለቲካ አቅጣጫ ላላቸውና አገሪቱ በምን መንገድ መሄድ እንዳለባት የተለየ ሐሳብ ላላቸው ሰዎች መድረክ ሆኖም ያገለግላል፡፡ ይኼ አግባብነት ያለው አጀንዳ በመሆኑ በመንግሥት ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል፡፡ አንዳንድ ድምፆች ጽንፈኛ ቢሆኑም ሌሎች ድምፆች ተገቢ ጥያቄ ያላቸው በመሆኑ ሊሰሙ ይገባል፡፡ በዚህ ሒደት የትውልድ ለውጥ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ በተማሪዎች ንቅናቄ ጊዜ የተፈጠረው ጽንፍ የያዘ ልዩነት ሳቢያ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ተገቢ የሆኑ ክርክሮች እንዳይደረጉ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በጥናታችንም የዚያ ትውልድ አባላት የፖለቲካ ሐሳባቸውን ሲገልጹ የጠብ አጫሪነት አዝማሚያ እንደሚታይባቸው ተገንዝበናል፡፡ በተቃራኒው የአዲሱ ትውልድ አባላት ከመንግሥት ጋር ወይም ሥልጣን ላይ ካለው ኃይል ጋር አተካሮ ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ ለውይይት ክፍት በመሆን አማራጭ ሐሳቦችን በማቅረብ ላይ እንደሚያተኩሩ ነው ያየነው፡፡

ሪፖርተር፡የናይል ቤዚን አገሮች ሚዲያ የናይል ጉዳይን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ እንደ ሚዲያ ባለሙያ የናይል ጉዳይ የሚዲያ ሽፋንን እንዴት ያዩታል?

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/) በአንፃራዊነት ለናይል ጉዳይ አዲስ ነኝ፡፡ ስለዚህ የምሰጠው አስተያየት በመማር ላይ ያለ ሰው አስተያየት ነው የሚሆነው፡፡ በአብዛኛው በሚዲያ እንደተለመደው ለናይል ጉዳይ የሚሰጠው ሽፋን ከግጭት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ግጭት እስካለ ድረስ ለግጭት ሽፋን መሰጠቱ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ነገር ግን ግጭት ለመኖሩ ዕውቅና ከሰጠን በኋላ እሱን የምንሸፍንበት የተለያየ መንገድ ይኖራል፡፡ ግጭቱ ምን ያህል የተወሳሰበ እንደሆነ ለማብራራት የተለያዩ አካላትን ድምፅ ማካተት ይቻላል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን በፈጠረው ዕድል በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚንፀባረቁ የግለሰብ አስተያየቶችን በሚዲያ ዘገባዎች ማካተት ይቻላል፡፡ ይህ ግን በአብዛኛው ተግባር ላይ ሲውል አይታይም፡፡

ሪፖርተር፡ጋዜጠኞች የናይል ጉዳይ ላይ ሚዛናዊ ዘገባ መሥራትና በተመሳሳይ ብሔራዊ ጥቅማቸውን እንደ ዜጋ እንዴት ማስከበር ይችላሉ?

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/)– ይኼ ብሔራዊ ጥቅም የሚባል ጽንሰ ሐሳብ በግሌ ያበሳጨኛል፡፡ በአጠቃላይ በአፍሪካና በመላው ዓለም ከተንሰራፋው የብሔርና ብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ ጋር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተጋጨሁ ነው፡፡ ቀደም ብሎ የጠራ ርዕዮተ ዓለም በመቅረፅና እሱንም በመግለጽ፣ እንዲሁም የፓን አፍሪካኒዝም ስሜትን በማቀንቀን የሚታወቁት የመለስ ዜናዊ አንዳንድ ሐሳቦችን አደንቅ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ማንም ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዚዳንት እንደሚያደርገው የኢትዮጵያን ያስቀደመ እንቅስቃሴ ነበር የሚያደርጉት፡፡ እ... 1950ዎቹ፣ በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ ለአፍሪካ አርዓያ የሚሆኑ የሚዲያ ውጤቶች ነበሩ፡፡ በወቅቱም የቀድሞ ጋዜጠኞች የነበሩት ክዋሜ ንክሩማህንና ጆሞ ኬንያታን የመሳሰሉ ሰዎች ከአገር የዘለለ ርዕይ አስፈላጊነትን ይሰብኩ የነበረ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ንቅናቄዎችን በሚያገለግል መንገድ የተቃኘ መሆኑ ግን አልቀረም፡፡ የተለያዩ አገሮችን ለሚያካልለው ናይል የፓን አፍሪካኒዝም ስሜት ሊጠቅም ይችላል፡፡ በብሔርተኝነት ዘመን የፓን አፍሪካኒዝም ስሜት ጥቅም ላይ የማይውል ከሆነ ምናልባትም ጋዜጠኞች መልሰው ሊያመጡት ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች አንዱ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄ ከአፍሪካ አኅጉር በቀላሉ መውጣት የማይችለው ውኃ ይህን ሁሉ ግጭት ሲፈጥር፣ ከአፍሪካ እየወጡ ሌሎች አገሮችን የሚጠቅሙ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ለምን ተመሳሳይ ችግር እንደማይፈጥሩ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡ሥልጠናው አንዱ ትኩረት ያደረገበት ጉዳይ ጋዜጠኞች በናይል ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት ተቀናጅተው እንደሚሠሩ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ሚዛናዊ ሆነው ሙያቸውን አክብረው መሥራትና በተመሳሳይ የራሳቸው አጀንዳ ሊኖራቸው ከሚችለው እነዚህ አካላት ጋር በትብብር ሊሠሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/)– በዚህ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች ሐዘን ይሰማኛል፡፡ በተለይ የኅትመት ጋዜጠኞች በኢንተርኔት በነፃ ከተለያዩ ምንጮች ከሚገኝ መረጃ በሚገጥማቸው ውድድር የተነሳ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ናቸው፡፡ በዚህ ጫና ላይ ጋዜጠኞች በናይልና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ኤክስፐርት እንዲሆኑ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ ጋዜጠኞች አንዳንድ ጉዳዮች አከራካሪ መሆናቸውን ለመረዳት የግድ ዝርዝር ዕውቀት አያስፈልጋቸውም፡፡ በብሔራዊና በዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ በሚሰጡ አስተያየቶች ሐሰተኛ የሳይንስ መረጃ እንደሚሰጥም አስተውለናል፡፡ እነዚህ ሐሰተኛ ቁጥሮች እንዲታረሙና ውይይት እንዲደረግባቸው ጋዜጠኞች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡  

ሪፖርተር፡እንደ ሚዲያ ባለሙያነትዎ በናይል ጉዳይ ላይ ሚዲያው የትብብርንም ሆነ የግጭት አቅጣጫን ተከትሎ ሽፋን ሲሰጥ እንዳዩ አምናለሁ፡፡ ይህን የተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማስተዳደርና ለመጠቀም እንዲቻል፣ ከዚህ አንፃር ሊቀየሩ የሚገባቸው ተጋዳሮቶች ምንድን ናቸው?  

ኢጂኒዮ ጋግሊያርዶኔ (/)– እንደዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች ላይ ጋዜጠኞች እርስ በርስ ሲከባበሩና ለሌሎች ሰዎች ሐሳብም አክብሮታቸው የሚታይ ቢሆንም፣ ጋዜጠኞች ወደ አገራቸው ሲመለሱ በሥራዎቻቸው ይህ ስሜት አይታይም፡፡ ለዚህ ከላይም ሆነ ከታች የሚመጣው ጫና አስተዋጽኦ እንዳለው እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኞቹ ለብሔራዊ ታዳሚዎቻቸው ሲጽፉ ከዚህ ስሜት ውስጥ ጥቂቱን እንኳን ይዘው ቢቆዩ ትልቅ መሻሻል ያመጣ ነበር፡፡ አንዳንዴ ጋዜጠኞች ሚዛናዊና ገለልተኛ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ሲንፀባረቅ አያለሁ፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ጋዜጠኛው የራሱን ስሜት ሲያካፍል ብቻ ነው ሁሉንም መረጃ በዓውድ በዓውዱ ማሳየት የሚችለው፡፡ ከናይል ጉዳይ አንፃር ይኼ አስፈላጊ ነው፡፡ ግጭቶች በአግባቡ ከተያዙ ብዙ ልንማርባቸው እንችላለን፡፡ ከግጭት በኋላ ሰዎች ቅድሚያ የሚሰጧቸው ዋጋዎች ላይ ዳግም ግምገማ ሊያደርጉና የተፈጠሩትን ስህተቶች ሊያዩ ይችላሉ፡፡

ሰለሞን ጐሹ‘s blog

Author

anon