June 14, 2017

የግልገል ጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብና በኦሞ ሸለቆ የሚካሄዱ የመስኖ ፕሮጀክቶች በቱርካና ሐይቅ ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ እንዲጠናላት ኬንያ በይፋ ለኢትዮጵያ ጥያቄ አቀረበች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥያቄውን መቀበላቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ኬንያ ጥያቄውን ያቀረበችው በቱርካና ሐይቅ የውኃ መጠን መቀነስና ከሐይቁ በሚገኝ የዓሳ ሀብት ሕይወታቸውን የመሠረቱ ኬንያውያን በውኃው መቀነስ ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመዝለቅ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት መሰንዘር፣ እንዲሁም ከብቶችን መዝረፍ ከጀመሩ በኋላ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኬንያ ፓርላማ አባላት በአገሪቱ መንግሥት ላይም ጫና ማሳደራቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋዊ ጥያቄ ለኢትዮጵያ አቻው ያቀረበ ሲሆን፣ ጥያቄውም ኢትዮጵያ በኦሞ ወንዝ ላይ የጀመረቻቸው ፕሮጀክቶች በኬንያ ቱርካና ሐይቅና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚያደርሱት አካባቢያዊና ማኅበራዊ ጉዳቶች በሁለቱ አገሮች ባለሙያዎች እንዲጠኑ የሚል ነው፡፡

የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የተውጣጡ ባለሙያዎች በቱርካና ሐይቅ ጉብኝት ማድረጋቸውንና የኬንያ ባለሥልጣናትን ሥጋት መገንዘባቸውን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በቱርካና ሐይቅ ላይ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊና የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ከኬንያ መንግሥት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚቻልበት ውይይት እየተካሄደ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከአሥር ዓመት በፊት ሲጀመር ተመሳሳይ ጉዳት በቱርካና ሐይቅ ላይ ያደርሳል በሚል መነሻ፣ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ ተቃውሞ ሳቢያም ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከሚያስፈልገው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን ለማበደር የመግባቢያ ስምምነት የሰጡት የአፍሪካ ልማት ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ በጫናው ምክንያት ራሳቸውን ከፕሮጀክቱ ማግለላቸው አይዘነጋም፡፡

በኃይል ማመንጨት አቅሙ ከአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው ግልገል ጊቤ ሦስት 1,800 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ የገጠመው የፋይናንስ እጥረት ከቻይና በተገኘ 495 ሚሊዮን ዶላር ተሸፍኖ፣ ከአሥር ዓመታት በኋላ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ከጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተጨማሪ ኢትዮጵያ በኦሞ ወንዝ ላይ የዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የመስኖ ፕሮጀክቶችን መጀመሯን በቅርቡ ይፋ ማድረጓን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንም በቅርቡ ከአንድ የቻይና ኩባንያና ከሌሎች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ጋር ለመስኖ ግንባታው ውል ማሰሩን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ኬንያ ያነሳችው ጥያቄ ድንበር ተሻጋሪ በሆነው የዓባይ ወንዝ ላይ ከተጀመረው የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዙሪያ በግብፅ ከቀረበው ተቃውሞ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ቢኖረውም፣ የኬንያ ዋነኛ ሥጋት የተነሳው የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶቹ ላይ ሳይሆን በመስኖ ፕሮጀክቶቹ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዓባይ ጉዳይ ኬንያ የኢትዮጵያ አጋር በመሆኗ፣ እንዲሁም የቀረበው ጥያቄ በወዳጅነትና በዓለም አቀፍ መርህ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የኢትዮጵያን ይሁንታ እንዳገኘ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ – ዮሐንስ አምበርብር