June 13, 2017

ከጥቅት ወራት በፊት በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ከፍተኛ አመራር አባል፣ ኦቦ ቃሲም ሁሴን አባናሻ፣ ላስ ቬጋስ በሚገኝ የሕሊና ራዲዮ ጣቢያ ላይ ቀረቡ። “ኦሮሞው የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። ይሄ እኮ ዴሞክራሲያዉ የሆነ አለም አቀፍ መርህ ነው። ለምንድን ነው ሰዎች ህዝብ ድምጽ ይስጥ ሲባል የሚቃወሙት ?” አሉ። እርሳቸው ድምጽ ይስጥ የሚሉት ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ህዝብ ነው። ያለ ህዝብ ፍቃድ፣ በሃይል የተመሰረተች አንዲት ክልል ዉስጥ የሚኖሩ የአንድ ብሄረሰብ ተወላጆች ብቻ የሚሰጡትን ድምጽ፣ በየትኛው የህግ መስፈርትና ሚዛን ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚችል ግልጽ ባይሆንም፣ የኦነጉ አመራር ኦሮሞው ድምጽ ሰጥቶ መገንጠል ፍላጎቱ ከሆነ ኦሮሚያን የመገንጠል መብቱ መረጋገጥ እንዳለበት ተከራክረዋል። (ያው የተለመደዉና የከሸፈበት የአርባ አመታት የኦነግ አቋም)

ኦቦ ቃሲም ተያያዥ ጥያቄ ቀረበላቸው። “እሺ የኦሮም ህዝብ ድምጽ የመስጠትና የፈለገውን የመምረጥ መብት አለው ካልን፣ ለምሳሌ በብዛት አማርኛ ተናጋሪና ከተለያዩ ብሄረሰቦች የሆነው የአዳማና የምስራቅ ሸዋ ህዝብ፣ በኦሮሚያ ዉስጥ መቀጠል አንፈለግም ቢል የህዝቡ ራስን በራስ የመወሰን መብት ተከብሮለት፣ ከኦሮሚያ መውጣት ይችላል ወይ ? “ ብለው ተጠየቁ። የኦቦ ቃሲም ትክክለኛ መልስ መለሱ።”በሚገባ፤ ይችላሉ” ነበር ያሉት።

አዲስ አበባ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ሊኖርባት እንደሚችል ይገመታል። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና ከመሆኗም በተጨማሪ የአገሪቷ የኢኮኖሚክ ማእከልም ናት። አዲስ አበባ የሁሉም ናት። ለስራ፣ ለመሻሻል ከሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ሰው ወደ አዲስ አበባ ይጎርፋል። የተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት በዘር በመከፋፈሉ ዜጎች በሁሉም የአገሪቷ ግዛት በነጻነት የመኖር፣ የመመላለስ እድላቸው በጣም የጠበበ ሆኗል። “ይሄ የናንተ መሬት አይደለም» ተብለው በሚናገሩት ቋንቋ ምክንያት፣ በተለይም አማራ ተብለው ዜጎች እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። የሥራ እድል የሚነፈጉበት ሁኔታም ነው ያለው። ስለዚህ ሰላም ፣ ደህንነት የሚፈልግ ፣ ለሕልዉናው ሲል አቅጣጫዉን ወደ አዲስ አበባ ያዞራል። አዲስ አበባ መሸሸጊያና መጠለያ ስለሆነች። በናቴ በኩል እጅግ በጣም ብዙ ዘመዶች ነበሩኝ። ሃረር አካባቢ። አሁን ብዙዎቹ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።

አዲስ አበባ ከመስፋቷ የተነሳ፣ አዲስ አበባ አቅራቢያ ያሉ ከተሞችም፣ በጣም አድገዋል። አዳማ/ናዝሬት በአንድ ሰዓት ይገባል። ቢሾፍቱ፣ ሰበታና ቡራዮ የአዲስ አበባ አካል ናቸው ማለት ይቻላል። ቡራዩ በሕዝብ ብዛት ከአምቦ በልጣለች። ሰበታ ከወሊሶ በልጣለች። ቢሾፍቱ ከነቀምቴ በልጣለች። አዳማን ጨምሮ በዚያ የሚኖሩ ዜጎች የስነ-ልቦና አመለካከታቸው አዲስ አበባ ካሉት ጋር የተመሳሰለ ነው። የናዝሬት ልጅ ሲባል የአዲስ አበባ ልጅ እንደማለት ነው። በአጭሩ አዲስ አበባና አካባቢዋ (አዳማን ጨመሮ) በኢኮኖሚና በማህበረሰባዊው ረገድ ተሳስረዋል። አሁን ያለው ሕወሃትና ኦህዴድ በሃይል የዘረጉት የፖለቲካ አርቴፊሻል መስመሮችና ግንቦች ናቸው። አዲስ አበባ ማንም ዜጋ፣ ዘር. ሃይማኖት ሳይጠየቅ በነጻነት ይኖራል። አርቴፊሻሉን የፖለቲካ መስመር አልፎ ኦሮሚያ ሲገባ ግን የተለየ ታሪክ ነው። የፈጠጠ ዘረኝነትን እናያለን። በባለስልጣናቱ።

እንግዲህ እኛ እየጠየቅን ያለነው በአዲስ አበባና አካባቢዋ ያለው ህዝብ (አዳማን ጨመሮ) የራሱን እድል በራሱ ይወስን የሚል ነው። ሳይፈለግ አፋን ኦሮሞ ብቻ የሥራ ቋንቋ በሆነባት፣ የአፓርታይድ አይነት አንድን ዘር ብቻ የመጥቀም መንግስታዊ አሰራር በሰፈነባትና ከ25 አመት በፊት በተፈጠረችዋ ኦሮሚያ መቀጥል ካልፈለገ ሕዝቡ ከኦሮሚያ ክልል የመውጣት መብቱ ሊክበርለት ይገባል።

አንዳንድ ወገኖች ይሄ ከሆነ ደም መፋሰስ ነው ይላሉ። ሊያስፈርሩን ይሞክራሉ። ይሄን አይነት ማስፈራራትን በማየት አንዳን ደካማ ድርጅቶች ለነዚህ ወገኖች ማስፈራሪያ የተንበረከኩም አሉ። “እነርሱን ማቀፍ አለብን” እያሉ ሊለማመጧቸው ይሞክራሉ። እንዴት ነው ከአሁን ለአሁን ወለጋና አርሲ ያሉ ወጣቶች ያምጻሉና ተብሎ አዲስ አበባን ጨመሮ የሸዋ ህዝብ ባልፈለገው አስተዳደር፣ ባልፈለገው ክልል መቀጠል አለበት የሚባለው? እንዴት ነው ከሁን ለአሁን አርሲ የተወለዱት እነ ጃዋር፣ ወለጋ የተወለዱት እነ ሌንጮ ለታ ይቃወማሉና እኛ አዲስ አበባና ናዝሬት የተወለድን ያለፍላጎታችን፣ በአገራችን እንደ እንግዳና መጤ የምንቆጠረው ? ይህ በሕግም ፣ በሞራልም፣ በዴሞክራሲም አንጻር አያስኬድም።

ለዚህ ነው አማርኛና አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ የሆነበት፣ ሁሉም በ እኩልንት የሚተዳደሩበት፣ አዲስ አበባን ጨመሮ ሸዋ የሚባል ክልል ይኖር ብለን የምንከራከረው። ይሄን በማለታችን አንዳንድ ወገኖች በኦሮሞው ላይ እንደመነሳት፣ የኦሮሞዉን ገበሬ እንደመበደል፣ፌዴራሊዝምን እንዳለመቀበልና የድሮው ስር፤ዓት እንደመናፈቅ አድርገው ዉይይቱን አቅጣጫ ሊያስቀይሩ ይሞክራሉ።

1. አፋን ኦሮሞ ከዓምርኛጋር የሥራ ቋንቋ ይሆናል። ያ ማለት ሁለት ወይም ሶስት የአፋን ኦሮሞ ትምህት ቤቶች ማቋቋም ስይህን 9አሁን ኦሮሞው አክቲቪስቶች እንደሚጠይቁት) በሁሉም የአዲስ አበባ፣ በአማራው ክልል የሰሜን ሽዋ ዞን ሳይቀር አፋን ኦሮሞ እንደ ትምህርት ይሰጣል። አፋን ኦሮሞ አድማሱን ያሰፋል። ታዲያ ይሄ እንዴት ጸረ-ኦሮሞ ሊሆን ይችላል”

2. በድሮው ስርዓት የሥራ ቋንቋው አማርኛ ብቻ ነበር። አሁን አፋን ኦሮሞም የሥራ ቋንቋ ይሆናል። ያ ማለት በኢሕአዴግ መንግስት ተገኘ የተባለው በቋንቋ የመገልገል፣ የመማር መብት አይወሰድም። የሚሆነው አንዱ ወይ ሌላው ከማለት አማርኛም አፋን ኦሮሞም ሁለቱም የሥራ ቋንቋ ይሆናሉ። በድሮው ስርዓት አሃድዊ ስርአት ነው የነበረው። አሁን የፌዴራል ስርዓት ነው የሚሆነው። ልዩነቱ ግን አዲስ አበባና አካባቢ ወይም ሸዋ የራሱ አንድ ፌዴራል ክልል ይሆናል።
በአዲስ አበባና በአካባቢዋ በተለይም በከተሞች ብዙ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወለዱ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት እንዳሉት፣ በገጠራማ አካባቢዎች የሞሉት የኦሮሞ ገበሬዎች ናቸው። ይህ የኦሮሞ ማህብረሰብ በአፋን ኦሮሞ የሚገባውን አገልግሎት ያገኛል። ልጆቹ አፋን ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን አማርኛም ይማሩለታል። ይናገሩለታል። በቀላሉ ኢኮኖሚው ውስጥ ይገቡለታል። በነጻነት ገበሬው ያመረተውን አዲስ አበባ ቢሾፍቱ፣ አዳማ…. ሄዶ መሸጥ ይችላል። አዲስ አበባ ያለው የልማት፣ የጤና፣ የትምህርት እንቅስቃሴ ተካፋይ ይሆናል።

3. የኦሮሞ ገበሬዎች ከመሬታቸው በልማት ስም እየተፈናቀሉ የግፍና የሰቆቃ ሰለባ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ግን ሸዋ የሚባል ክልል መኖሩ የገበሬውን ችግር አያባብስም። ኦሮሚያ የሚባል ክልል መኖሩ የገበሬውን ችግር እንዳልቀነሰ። ላለፉት 25 አመታት የኦሮሞ ገበሬ የተፈናቀለው ኦሮሚያ በምትባል ክልል ውስጥ እየኖረ ነው። ( የኦሮሞ ገበሬ ችግር መሰረቱና ምንጩ የመሬት ፖሊሲው ነው። አዲስ አበባ አካባቢ ያሉ መሬቶች ዋጋቸው ትልቅ ስለሆነ መሬቱን ሸጦ ብዙ ትርፍ ሊያገኝበት ሲችል ያ ሊሆን አልቻለም። ሊያገኝ ከሚገባው ትርፍ ከአዲስ አበባ ራቅ ብሎ በፊት ነበረው መሬት ሶስት፣ ራት እጥፍ የሚሆን መሬት ሊገዛበት ይችል ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን መሬት የመንግስት ስለሚባል፣ ገዢዎች ለገበሬው እንበል 10 ሺህ ብር ሰጥተው፣ በልማት ስም ያፈናቅሉትና ለኢንቨስተሮች መቶ እጥፍ ያከራዩታል። ዘጠኝ ሚሊዮን ዘጠኛ ሺህ ኪሳቸው ያስገባሉ ማለት ነው። መሬት የገበሬው ከሆነ ግን ፣ ገበሬው ምን አልባት አሥር በመቶ ግብር ቢከፍል እንጂ አብዛኝው ግንዘብ ኪሱ ነው የሚገባው። )

የገበሬው መሰረታዊ ጥያቄ የሰላም፣ የመብት፣ የፍትህና የልማት ጥያቄ ነው። አፋን ኦሮሞና አማርኛ የሥራ ቋንቋ የሆነበት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ ሸዋ የሚባል ክልል ከኖረ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ እያሉ መከፋፈሉ ቀርቶ፣ ሁሉም በስራዉና በዜግነቱ ተከብሮ ፣ የአንዱ ቅርስ የሌላው፣ የአንዱ ቋንቋ የሌላው ሆን፣ አገራችንን በፍቅርና በአንድነት የምናሳድግበት አጋጣሚ ይፈጥርልናል።

አንዳንዶች ስለሸዋ የጻፍከው ለሁሉም አገሪቷ የሚሰራ ነው ይላሉ። በከፊል ትክክል ናቸው። እንድ ጂማ፣ አሰላ አካባቢ ያሉ ከአዲስ አበባ አካባቢ ግር ተመሳሳይነት አላቸው። ግን ደግሞ ወደ ምእራብ ወለጋ ዞኖች ብትሄዱ በዚያ 97% አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ባሉበት ቦታ አማርኛም የሥራ ቋንቋ ይሁን ማለት ብዙ አያስኬድም። ሸዋ ግን የተለየ ነው። አዲስ አበብባ ጨመሮ ከግማሽ በላይ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ አይደለም።