ሰኔ 6 ቀን፤ 2009 ዓ፤ም

በዚያች የመከራዋ ጽዋ ሞልቶ አላልቅ ባለባት ምድር ላይ፤ ላይን የሚዘገንኑ ለጆሮ የሚቀፉ ወንጀሎች በምንወደው ህዝባችን ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ ሲደርስ አይተናል፤ እኛም የዚህ ግፍ ሰለባዎች አይደለንም ማለት ከቶውንም አይቻልም፡፡ ሞት፣ እስራት፣ እንግልት፣ አይን ያወጣ ዘረፋ እና ሌሎችም ኢሰብአዊ ጥሰቶች በየደቂቃው የምንሰማቸውና የምናያቸው የኢትዮጵያዊያን የእለት ተእለት ተግባሮች ከሆኑ ቆይተዋል፡፡

በተለይ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ተብዬ፤ ገና መንበረ-ስልጣኑን ከመቆናጠጡ አስቀድሞ በማኒፌስቶው ላይ በግልጽ ያንድን ብሔር ተወላጆች እና አንድን የሃይማኖት ተቋም ለይቶ ለማጥቃት ከተቻለም ለማጥፋት የሚል ከቶውንም እትዮጵያዊ በሆነ ጭንቅላት ሊታሰቡ የማይችሉ መርሃ-ግብሮችን ነድፎ መነሳቱ ለማንኛችንም የተደበቀ ምስጢር አይደለም፡፡ ይልቁንስ እነሱ ራሳቸው በሚቆጣጠሯቸው የዜና አውታሮቻቸው እስኪሰለቸን ድረስ ነግረውናል፤ በማንአለብኝነት ያሻቸውን እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ በተለይ በሰፊው የጎጃም ህዝብ ላይ የደረሰው እና እየደረሰ ያለው ፍጹም መረን የለቀቀ ኢሰብአዊ ወንጀል ከቀን ወደ ቀን እየሰፋና እየተባባሰ ይገኛል፡፡ በገጠራማው ክፍል በሚገኙ ሴት እህቶቻችንና እናቶቻችን ላይ ዘራቸውን እንዳይተኩ፣ ወልደው እንዳይስሙ፣ በተፈጥሮ የተቸራቸውን የፈጣሪ ጸጋ በክትባት መልክ ልጅ አልባ ከማድረግ ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለዘመናት ታፍሮና ተከብሮ የሚኖረውን የጎጃም ህዝብ ተውልዶ ባደገበት፣ ዘርቶ ባጨደበት፣ እናት ሃገሩ ላይ እንደ ባእድ ጓዜን ማቄን ሳይል እንዲፈናቀል እና እንዲሰደድ ተፈርዶበት አይተናል፡፡ እንዲሁም እጅግ በርካታ የተማረ ሃይል ለሃገሪቷ ሲያበረክት የነበረን ማህበረሰብ በተጠና መንገድ በማዳከም ተጽኖ ፈጣሪነቱን ለመቀነስ በርካታ ትምህርት ነክ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ ባጭሩ አስተውሎ ላጤነ ሰው፤ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ እና አሁን አስተዳድራለሁ በሚለው መንግስት ተብየ፤ ከማንም በላይ እንደ አማራ ህዝብ ይፋዊም ሆነ ሰልታዊ ጥቃት የተፈጸመበት ማህበረሰብ የለም፡፡ በተጨማሪም በለምለምነቱና በሰፊ የተፈጥሮ ማእድን ክምችቱ የሚታወቀው ትልቁ የመተከል አውራጃ ዛሬ ለፖለቲካዊ ቁማር ሲባል ተሸንሽኖ ከጎጃም ተነጥሏል። ይህ የተከበረ እና ምስጉን ህዝብ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ሉዓላዊ ሆና እንድትመሰረት፤ ተከብራና ተፈርታ ለዘመናት እንድትኖር፣ ሉአላዊነትዋን እንድትጠብቅ፤ በማንኛውም እና በየትኛውም ግዜ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በማበር ደሙን ሳይሰስት አፍስሶላታል፤ አጥንቱን ከስክሶላታል፡፡ ይህ ታሪክ ያማይሽረው ሃቅ ነው፡፡

በደል ሲበዛ፣ ፍትህ ሲጓደል እና የአንድ ብሄር የበላይነት ከመጠን በላይ ሲሰፍን ህዝብ በቃኝ ማለቱ አይቀሬ የሆነ የመኖር ሀቅ ነው፡፡ በየዘመናቱ ህዝብ ጭቆናን መሸከም ከሚችለው አቅም በላይ ሲሆንበት በተናጥልም ይሁን በቡድን እምቢኝ ብሎ መብቱን ለማስከበር ተነስቷል፤ ይነሳልም፡፡ ከነዚህ ህዝብ ባንድነት ከተነሳባቸው የመብት ጥያቄ አመጾች ውስጥ በቅርቡ ያየናቸው፤ እጅግ በርካታ ወገኖችን ያጣንባቸውን የጎንደር እና የጎጃም እንዲሁም በኦሮሚያ የተቀጣጠለውን የህዝብ አመጽ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በዚህ ከዳር እስከ ዳር እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ በነበረው የህዝብ አልገዛም ባይነት፡ እጅግ በርካታ ማህበረሰቦች የተሳተፉበት፣ ለቁጥር የሚያዳግቱ ወገኖቻችንን በጠራራ ጸሃይ በጥይት አረር የተነጠቅንበት ጊዜ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ካለምንም መከላከያ ባዶ እጃቸውን ነጻነታቸውን ለመጠየቅ በየጎዳናው መውጣታቸውን አስከትሎ በአልሞ ተኳሽ የስርአቱ ቀኝ እጆች ተረሸነዋል፡፡ ደማቸው በየአስፓልቱ እንደ ውሃ ሲፈስ ባይናችን አይተናል፤ ያየነውን የከፋ አረመኔአዊነትም እያንገሸገሸን ውጠነዋል፡፡ በተለይ ባህርዳር ላይ በአንድ ቀን ብቻ የተገደሉት ወንድምና እህቶቻችን ብዛት፣ የተገደሉበት አረመኔአዊ መንገድ መቼውንም ቢሆን ልንረሳው የማንችለው ጥቁር ቀናችን ነው።

በወቅቱ ይህንን የወገን ጩኸት አቅም በፈቀደ መጠን ለመታደግ ብሎም አለኝታነታችንን ለማሳየት በጥቂት በሚተዋወቁ ሰዎች አማካኝነት፡ ከወዲያ ወዲህ ተሯሩጠው የጎጃም አለምአቀፍ ትብብር የሚል ማህበር እንዲጸነስ ሆነ፡፡ የጎጃም አለምአቀፍ ትብብር መነሻው በህዝባዊ አመጹ የተጎዱ ወገኖቻችንን በተለያዩ ነገሮች አቅሙ የፈቀደውን ማድረግ ቢሆንም ይህ በወገናችን ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል እስከመጨረሻው ድረስ የሚያከትምበትን መንገድም ያፈላልጋል፡፡ ይሄን አላማ ለማሳካትም ይህ ህብረት ዘለቄታዊና አመርቂ ውጤት ለማምጣት እንዲሁም በቶሎ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ በመተዋወቅ ላይ የተመሰረተ አካባቢያዊ ህብረት መፍጠር አስፈላጊ ነው ብሎ በጽኑ ያምናል፡፡ ይህ ማለት ግን አስፈላጊ ሆኖ በታሰበበት ጊዜ እና ቦታ ሁሉ የሚጠበቅበትን ድርሻ ከማንኛውም ተመሳሳይ አላማ ካላቸው ድርጅቶች ጋር አብሮ አይሰራም ማለት አደለም፡፡

ላለፉት ዘጠኝ ወሮች በህዝብ በተመረጡ ጊዚያዊ አመራሮች አማካኝነት ሰለቸኝ እና ደከመኝ በማያውቁ ትንታግ መሪዎች ማህበሩ ሲመራ ቆይቷዋል፤ ከተቋቋመበት እጅግ አጭር ጊዜ አንጻርም አመርቂ በሚባል መልኩ የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ነሓሴ 29 ቀን፤ 2008 (September 4, 2016) የመመስረቻ ጉባኤውን በዋሽንግተን ዲሲ (Washington DC) ሲያደርግ በወቅቱም በባህርዳር፤ በዳንግላ፤ በቻግኒ፤ በእንጅባራ፤ በፍኖተሰላም፤ በደብረማርቆስ እና በሌሎችም የጎጃም አካባቢዎች የተቀጣጠለውን የለውጥ ጥያቄ ለማገዝ፤ የተጎዱ ወገኖችን አቅም በፈቀደ መንገድ ለመርዳት የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አስከትሎም በሜኔሶታ ግዛት ከጎንደር ህብረት ጋር በመተባበር የተሳካ የገቢ ማሰባሰብ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የ ጎ ፈንድ ሚ (gofundme) አካውንት በወቅቱ ተከፍቶ አመርቂ በሚባል መልኩ ገንዘብ ተሰብስቧል፡፡ ጊዚያዊ ኮሚቴው ይህንን ገቢ ወዲያው እንዳገኘ እጅግ አስቸጋሪ ውጣ ወረዶችን ተቋቁሞ ለተጎዱ ሰዎች አለኝታነቱን በሚገባ አስመስክሯል፡፡

ምንም እንኳ ግዚያዊ ኮሚቴው ሲቋቋም ከሁለት ወር ባላነሰ ጊዜ ውስጥ ቋሚ አስተዳዳሪ ለመምረጥ ታሳቢ አድርጎ ቢሆንም በጊዜው የነበረው የወቅቱ አስቸጋሪነት እና የመተዳደሪያ ደንቡን ለማውጣት የወሰደው እልህ አስጨራሽ ረዘም ያለ ጊዜ እስካሁን እንዲዘገይ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም ጠንካራ መሰረት ያለው ድርጅት ለቀጣዩ ተረካቢ ለማስረከብ በማሰብ የጊዜያዊ ኮሚቴው በዚህ እጅግ አጭር ጊዜ ውስጥ በገንዘብ የማይተመን ስራ ሰርቷል፡፡ ይህ ቁርጠኝነታቸው በርግጥም ሊመሰገን የሚገባ መሆኑን የጎጃም አለምአቀፍ ትብብር በጽኑ ያምናል፡፡

በመጨረሻም በግንቦት 19 እና 20 2009 (May 27 & 28 2017) ጠቅላላ ጉባኤው ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ተጉዘው በዳላስ ቴክሳስ ተሰባስቦ፣ ከፍተኛ የሆነ ምክክር እና ክርክር ለሁለት ሙሉ ቀናቶች አድርጎ የመተዳደሪያ ደንቡን አጽድቋል፡፡ እንዲሁም ቀጣይ የጎጃም አለምአቀፍ ትብብር ቋሚ የአመራሮች ቦርድ አባላትን (Board of Directors) በመምረጥ የስራ ክፍፍል አድርጎ ውጤታማ ስራ ሰርቷል፡፡ እጅግ ጠንካራ እና ጽኑ አላማ ያላቸው፣ የመተዳደሪያ ደንቡን መሰረት አድርገው ለመስራት ቃል የገቡ አስራ አንድ (11) አባላት ያሉት አመራሮች ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች፣ አምስት ቦርድ ኦፍ ትረስቲ ( 5 Board of Trustee) እና ኦዲት ኮሚቴ በጠቅላላ ጉባኤው በደንቡ መሰረት ቀርበው በአብላጫ ድምጽ ተመርጠው ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

አዲሱ አመራርም በቀጣይ በአባላቱ እና በአመራሮቹ መካከል አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በመለዋወጥ ተቀራርቦና ተወያይቶ የሚሰራበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ አላስፈላጊ የሆኑ የሃሰት ውዥንብሮችንም ለማጥፋት አባላቱ ከማህበሩ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ሌላው የጎጃም አለምአቀፍ ትብብርን ጥንካሬ የሚያሳየው እና ሊያስመሰግነው የሚገባው ነገር የገንዘብ አወጣጡ ግልጽነት (financial recording system) ሲሆን በወቅቱ የተሰበሰቡትን የጠቅላላ ጉባኤ አባላትን አስደስቷል፡፡ ይህ አሰራርም ጠንክሮ ይቀጥላል፡፡ ይህ ማህበር ምንም እንኳ የተፈጠረበት ወቅት ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ችግር ውስጥ ቢሆንም አላማው ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን የሁላችንንም ያላሰለሰ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ባካባቢያችን ላይ ዘለቄታዊ ለውጥ እንዲመጣ፣ የጎንዮሽ እና የጥርጥር መንፈሰን ሰብረን፣ ሁላችንም በህብረት እንነሳ፡፡ የጎጃም አለምአቀፍ ትብብርን እንዲቀላቀሉ በዚህ አጋጣሚ የጥሪ ደወል እናሰማለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ! !

ጎጃም አለምአቀፍ ትብብር

Gojjam Global Alliance