ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ

Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity

Efdpu@aol.com www.Finote.org

ፕሮግራም፡ ረቡዕ እሁድ ከምሽቱ ሁለት ሰአት እስከ ሶስት ሰአት በ 25 ሜትር ባንድ

Programm. Wednesday and Sunday 8.00 PM – 9.00PM on 25 meter band

የፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሀተታ

የሞራል ጥያቄ

መጋቢት 2 ቀን 2007 .. የተላለፈ የሰውን ልጅ፤ ህይወት ካላቸው ከሌሎች ተንቀሳቃሽ ፍጡራን የተለየ ከሚያደርገው አንዱ፤የሞራል ጥያቄ ነው። ይህ የሞራል ጥያቄ ፤ የሰውን ልጅ በመሠረቱ ከእንስሳት ይለየዋል መባሉ፤ እንስሳቱና አራዊቱ እንደሚኖርቱ የዘፈቀደ ህይወት ለመምራት አለመፈለጉ ነው። ሰውን ሰው ሊያደርጉት ከሚችሉት ዋና ዋና ባኅርያት ውስጥ፤ የሞራሉ ተገዥ መሆኑን በገቢር ሊገልፅ መቻሉ ነው። ይህንንም ሀቅ ፤ለሞራል ክብር የሚሰጥ ሰው ሁሉ ይስማማበታል ።

የሞራል ጥያቄ ሲነሳ፤ መስተዋል የሚገባው፤ የዕምነትና የፍልስፍና ጠበብት ከሚሰጡት ግንዛቤ በላይ፤ በሰፊ ማዕቀፍ ከመስተናገዱም አኳያም ጭምር ነው። በዚህ ዕይታ ሲመለከቱት፤ ሰፊ ትርጉም ይኖረዋል ሊባል ይቻላል ። የሰው ልጅ በታሪኩ፤ በኅብረት መኖር ከቻለበት ወቅት ጀምሮ፤ ከማኅበረሰቡ ጋር ሊያገናኛው የሚችል የባኅሉና የዕምነቱ ነፀብራቅ ሊሆን የሚችል የሞራል ዕሴት ይኖረዋል ። ዕምነቱንና ኑሮውን ኣጣጥሞ፤ አብሮ ተከባብሮና ተማምኖ ለመኖር የሚያስቸለው የሞራል መስተጋብር ሲኖረው ነው ። በሞራል ዕሴት የሚያምን ሰው፤ የህግ የበላይነትን ስለሚያከብር፤ የህገወጦችን ትግባር በፅናት የቃወማል ። ለአምባገነን አገዛዝምም አይመችም ።

ሞራል ሲባል፤ ክፉውንና ደጉን፤ በመለየት ብቻ የሚወሰን አይሆንም ። በርኅራሄና በጭካኔ፤ በውሸትና በሀቀኝነት፤ በድብቅነትና በግልፅነት፤ በሀሜታና በአሉባልታ፤ ወዘተ በሚነፃጸሩ የሰው ልጅ ባኅርያት ዙሪያ የሚሽከረከሩ መግለጫዎች አይደለም ። የሞራል ልዕልና ( integrity ) አለኝ የሚል ሰው ፤ መጀመሪያ ራሱን ከሞራል ሽልታ ነፃ ማውጣት አለበት ። በዚህ አኳያ እራሱን ነፃ ካላወጣ፤ ስለ ሌላው ለመተቸት ብቃት አይኖረውም ። የሞራል ጥያቄ መታየት የሚገባው፤ ሁለንተናዊ መስተጋብርን ባካተተ ማኅበራዊ ክስተትንና ሂደትን ሁሉ ከሚያዳስስ፤ ከሚገመግምና ከሚለካ ሚዛን አኳያም ጭምር ነው።

አስነዋሪና አስከባሪ፤ አስማስጋኝ፤ አስነቃፊና አስወዳጅ የሆኑትን የማኅበረስብ ዕምነቶች ለይቶ በማወቅ ፤ ለሞራል ዕሴቶች የሚሆኑትን አክብሮ መያዝ፤ ሞራላዊ ግዴታ እንደሆነ፤ ስለ ሞራል ልዕልና የሚጨነቅ ሁሉ ይገነዘበዋል ። የሥነ አዕምሮ ሊቃውንት ለሞራል ሥልጣን ታላቅ ቦታ ይሰጡታል።

ይህንን በሚገባ የተረዳ የድርጅት አባል፤ በትግል ሂደት ሊያጋጥመው የሚችለውን ችግር ሁሉ ፤ በቀላሉ ሊቋቋም ይችላል ቢባል ማጋነን አይሆንም ። አባላትን ከድርጅት፤ ድርጅትን ከትግል፤ ብሎም ከሕዝብና ከሀገር ጋር ለያስተሳስር የሚቻለው፤ የሞራልን ጥያቄ ጠንቅቆ በመረዳት ነው። ይህ ደግሞ፤ በዘለቄታ መልኩና ባስተማማኝ ደረጃ የተጀመረውን ትግል ከፍፃሜ ለማድረስ የሚያስችል ዕምነትና ጥንካሬ ይሰጣል ።

ከዕምነት አኳያ ሲታይ፤ እስከ መጨርሻው በዕምነቱ ፀንቶ የቆየ ብፅዑ ነውይባላል። ይህ ማለት፤ እስከ ፍፃሜው ፀንቶ የታገለ የአቸናፊነትን አክሊል ይቀዳጃል ማለት ነው ። ሁሉንም ሰብስቦ የሚይዝ ሀብል ዕምነት ነው ።የሞራል ዕሴቶችን ያላቀፈ ዕምነት ግን ብቻውን ብቃት የለውም ። በሀገሮች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች፤ በባልና ሚስት መካከል የሚፈፀሙ የጋብቻ ውሎችና ፤ ሌሎች የውል ሰነዶች ፤ በመሠረታዊ መልኩ ዘላቂ ሊሆኑ የሚችሉት የዕምነት ፅናት ሲኖራቸው ነው ። ዕምነት፤ ሞራልን አጅበው የሚመጡ ሌሎች የሰው ልጅ ባኅርያትን ያስራቸዋል ። የሽ ልጥ ማሰሪያው ልጥ እንደሚባለው ሁሉ፤ በዕምነት ላይ የተመሰረተ መተማመን ፤ እስከ ዘለቄታው የሚያቆይ የትግል ዋስትናን ይሰጣል ። የሰውን ልጆች የሞራል ልዕልናም ሆነ የባኅርይ ታላቅነት መዝኖ ለማወቅ፤ ሁሉም የኅብረትሰብ አባል ሞራሉን ጠብቆና አክብሮ ሲገኝ ነው ።

በወታደራዊ ሳይንስ መዝገበቃላት፤ ሞራል ሲተርጎም፤ የሠራዊቱን የውጊያ ብቃትና ችሎታ በከፍተኛ ደረጃ መድረሱን አረጋጋጭ እንደሆነ ይገልጻል። በከፍተኛ ሞራል ይዋጋል የሚባል ሠረዊት፤አይበገሬነትን ፤የማጥቃትን እንጅ የመቸነፍን ጠባይና ምልክት የማያሳይ የሀገር መከላካያ ሠራዊት ማለት ነው ። ከዚህ በላይ፤ የመንፈስ አንድነት ( esprit de corps ) ሲጨመርበት፤ ከከፍተኛው የሞራል እርከን መድረሱ አስተማማኝ ይሆናል ። የሠራዊቱ የሞራል ብቃቱ ከፍተኛ ነው የሚባለው ይህንን ሁሉ በማከተቱ ነው።

በሀገር ወዳድነቱና በጀግንነቱ በአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልነበረው ያ የኢትዮጵያ መከላካያ ሠራዊት፤ በማይታመን ፍጥነት እንዲንኮታኮት የተድረገው፤ ወያኔዎች እንደሚውሸክቱት ሳይሆን ፤ አስቀድሞ በተደረገው አሳዥኝ ሁኔታ፤ደርግ፤ የሀገሪቱን የጦር ጀኔራል መኮንኖች ስለረሸናቸው ነበር። ብቃትን ከጀግንነት፤የሀገር ፍቅርን፤ ከወታደራዊ ዕውቀት ጋር አጣምረው የያዙት የሀገሪቱ የጦር መኮንኖች ተግድለው/ ተረሽነው፤ ተዋጊው ሠራዊት፤ በፖለቲካ ካድሬ አምሣ አለቃዎች በመመራቱ፤ ወታደሩ ሞራሉ በመውደቁ ነበር እንጅ ፤ የወያኔዎቹ ችሎታ እንዳልነበረ፤ ዛሬ የሚወጡት የታሪክ ሰነዶችና መጻሕፍት በማስረጃ የተደገፈ ምስክርነት እያቀረቡ ናቸው።

ከዚያ በኋላ የሆነው ምንድን ነው ? ኢትዮጵያ መሪ የሌላት ሀገር ስትሆን፤ መከላካያ ሠራዊቷም አዛዥ በማጣቱ ተበትኖ ቀረ። ይህ ደግሞ አዛኙ የሀገራችን ታሪክ ሆኖ ቀርቷል። ታሪኩ የሚታደስበት ቀን ግን ይመጣል ። የሀገሪቱም ትንሣዔ ሩቅ አይሆንም።

መጣሁ መጣሁ ሲለው የወያኔ ውሪ፤

ዘቅዝቆ ሮጠ ወደ ሀራሪ

የተባለውም፤ የመሪዎችን ድካማነት ለማግለጽ እንጅ፤ የሠራዊቱ ጀግንነትማ እንደተከበረ ይኖራል ። ሞራል ያለው ትውልድም እየተፈጠረ መምጣቱ አይቀሬ ነው !

የቸገረው ዱቄት ከነፋስ ይጠጋል እንደሚባለው፤ ሕዝብ በድለውና ሀገር አጥፍተው የሚሸሹ፤ የሞራል ልዕልና የሌላቸው ሰዎች፤ እንደ ነፋስ ባክነውና ተቅበዝብዘው ይጠፋሉ። ያስጠጓቸው መናፍስትም እንደዚህ በአውሎነፋስ ይወድማሉ። የወያኔውቹም ዕድል ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም ።

የሞራል ብቃትና ጥንካሬ ጉዳይ ከተነሳ፤ ለኢሕአፓ፤ ወዳጅ ቀርቶ፤ ባላንጣም ቢሆን ፤ የሚመሰክረው አንድ ሃቅ አለ ። በድርጅቱ ውስጥ ሆኖ ትግሉን የቀጠለውም ይሁን የተሰናበተው ሁሉ፤ ከሚካፈላቸው የጋርዮሽ ማንነት መለያ ባኅርይ፤ ፓርቲው ከሰጣቸው አስተምህሮዎች መካከል፤ የሞራል ልዕናና የመርኅ (ፕርንስፕል) አጠባበቅ ጎዳይ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዙ ናቸው። ለመርኅ ተገዥነት የሚያበቁትን ምሶሶዎችን የተከለው በሦስት መሠረቶች ላይ ነው ማለት ይቻላል። እነርሱም፦

1. የፓርቲውን ህግ፤ ደንብና ሥነሥርዓት ማክበር፤

2. በሀገራዊ ጥቅምና በሕዝብ ሉዓላዊነት አለመደራደር፤

3. ትግሉ የሚጠይቀውን ማነኛውንም መሥዋዕት መክፈል ናቸው።

እነኝህን መስፈርቶች አሟልቶ መገኘት፤ የጠነከረ መልኅቅ ( anchor ) መያዝ ማለት ነው። ጠንካራ መልኅቅ ይዞ መታገል ደግሞ፤ በሂደት የሚያጋጥሙትን መስናክሎች ሁሉ ድፍጥጦ ለመጓዝ ያስችላል። ለማንና ለምን መታግልን ማውቅ ፤ ጠላትንና ወዳጅን ለይቶ መፈረጅ፤ ሞራልየለሹን ከመንፈሰጠንካራው አበጥሮ አብጠርጥሮ ማየት ፤ የትግሉ አካል መሆኑን መረዳት ተገቢ ይሆናል ።

ከትጥቅአስፈችዎች ጉዳት የመከላከሉ ጉዳይ ፤ በአርምሞ የሚታይ አይሆንም። ። በታጋይ ድርጅቶች ውስጥ ፤ ለጥቅም ተገዥ የሚሆኑትን ሞራለ ቢስ ሰላዮችን ሰርስሮ ማስገባት፤ የአምባገኖች ቋሚ ተግባር ነው። ስለ እነኝህ መንፈሰድካማ ሰወች ምንነት፤ የቅድሚያ ዕውቀት ማግኘት፤ የመርጃ ተግባር መሆኑ ባይካድም፤ ኅብረተሰቡ ነቅቶ እንዲጠብቅ ግን አስፈላጊቱ ወሳኝ ነው።

ትግሉን በፅናት ይዞ የሚቅጥለው ኃይል፤ ዓርዐያነቱ አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን፤ ለሚቀጥለውም ትውልድ ጭምር ስለሚሆን፤ ዕፁብድንቅ ነው ሊባል ባይቻልም እንኳን፤ እንከንየለሽ ታሪክ አስመዝግቦ ማለፍ ይጠበቅበታል ። የፓርቲው አባላትአካላት፤ ይህንን ታላቅ እሳቤ በአዕምሯቸው ዋስጥ አስገብተው እንደሚታገሉ የረዱታል።። ይህም በበኩሉ፤ ፤ የሞራል ልዕልና፤ በትግላቸው ውስጥ ዓይነተኛ ስፍራ እንዳለው ይገነዘቡታል ።

እነኝህን ሁሉ ታላላቅ ግንዛቤወች አንግቦ መታጋል ቀላል ተግባር አይደለም ። ለተቃማጭ ሰማዩ ቅርብ ነው እንዲሉ፤ ይህንን ኃላፊነት ለመሸከም የማይፈልግ ሁሉ ግን ሊረዳው አይችልም ። አይፈልግምም ። የሞራል ትርጉም የማይጋባቸው ሰዎች፤ የሀገር መምራት ኃላፊነት ሊያገኙ ቀርቶ፤ በሥላጣን አካባቢ ሊቀርቡ እንኳን አይጋባቸውም የሚባለው፤ ከዚህ ሀቅ በመነሳት ነው።

ለሞራል ተጠያቂነት ደንታ የሌላቸው ግለስቦች ፤ ዛሬ በሀገራችን መንበረ ሥልጣን ላይ ይገኛሉ ። እነኝህ ሰወች ፤ ለአለፉት ሩብ ( 1/4ተኛ ) ምዕተ ዓመት በሀገራችን ላይ የፈጸሙትን ሁለንተናዊ ወንጀል በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የተመዘገበ በመሆኑ፤ ወደዚያ አናመራም ። ሞራለ ብልሹዎች፤ ኩራትየለሾችና ሀገራዊወኔ ቢሶች መሆናቸውን ያረጋገጡበትን ሁለት ማስረጃዎች ግን ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይሆኑም ። እነርሱም፤

1ኛው ሀገመንግሥት ብለው ያመጡት ሰንድ ያረቀቁላቸው የሀገራችን ቀንደኛ ጠላቶች የሆኑት ባዕዳን መሆናቸውና

2ኛው ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ጥፋት የመጨረሻው ስብስባ የቴካሄደው እንደዚሁ በባዕድ ሀገር መሆኑ ነው። በሞራል ስባሪ የሚመራ ሥርዓት፤ የመራል ልዕልና ያለውን ሕዝብ ሊገዛ ቀርቶ፤ ባጠገቡ እንዲያልፍ ሊፋቀድለት አይገባም ።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ያክል ታላቅ ሕዝብ ዕድሉ፤ በባዕዳን እጅ ተዋስኖ ሲመጣለትና የሀገሩም መገነጣጥል በባዕድ ከተማ ( ሎንዶን ) ሲወስን ከመየት የበለጠ ምን ውርደትና ጥቃት ይመጣል ?

በበኩላችን፤ ትግሉን በጽናት ጠብቆ የቀጠለው ኃይል፤ የሞራል ምልዑነቱን አስከብሮ ይቀጥላል የሚል ፅኑ ዕምነት ስለአለን ፤ የኅብረተሰብ ሙሉ ትብብራና ደጋፍ እንደማይለየን አንጠራጠርም ።

ሁሉንም ነገር ጊዜ የፈተዋል የሚባለው አነጋገር ከዕውነት የራቀ ነው ባይባልም፤ ማነኛውንም ሁኔታ ጊዜ ይፈተዋል ብሎ ጊዜን ከመጠበቅ ይልቅ፤ የተሻለ ሁኔታን ለማምጣት የሚያስችለውን ጊዜ ለማግኘት፤የሞራልን ከፍተኝነት አንግቦ መታጋል አማራጭ አይይኖረውም ። የጊዜ ተለዋዋጭነት መኖሩ የተፈጥሮ ሂደት ስለሆነ፤ ተለዋዋጩን የጊዜ አጋጣሚ እየተጠቀሙ ለድል መብቃት፤ የሞራል ብቃትን የየዘ ሁሉ ከልብ ይረደዋል።

ዓለም ወረተኛ እንደ ግንቦ ጥጅ ፤

ያገኘሽ ሲጠጣሽ ያጣሽ ሲጎመጅ ! ”

እያሉ በጊዜ አመንዝራነት ከመገርም ይልቅ፤ ከዚያ በላይ በማሰብ፤ የጊዜን አጋጣሚ እየተጠቀሙ ፤ ሁኔታውን መለውጥ መቻል አለበት። ይህ ፤ጊዜ ሊሰጠው የሚግባ አይደለም ። ለአለፉት ግማሽ መዕተዓመት የኢትዮጵያ፤ ሕዝብ ፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያበቁ ሁለት ማልካም ዕድሎችን አጥቷል ። በሞራለቢሶች ተነጥቋል ። ሦስተኛው ዕድል እየመጣለት ነው። ይህንን ሣልሳዊው ዕድል ለያጣ አይገባውም ። ሣልሳኛውን ዕድል በሚገባ ከተጠቀመበት፤ ሀገሩን አድኖ፤ እራሱንም ማዳን ይችላል ።

እኛ፤ ብስራትን እንጅ መርዶን አንፈልግም ። ብሥራቱን ለማወጅ ግን በዓላማችን ፀንተን እንታገላለን ። ኢትዮጵያም ለዘለዓለም ትኖራለች !

ሀገራችን በነፃነቷ ለዘለዓለም ትኖራለች !!!!

ምንጭ ደብተራው