June 16, 2017

ዕበጉራጌ ዞን የዐማሮች ንብረት ወደመ፤ በሕግ ጥበቃ ስር ያለ ዐማራ በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፎ ተገድሏል

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ግምቱ ከአምስት ሚሊዮን ብር የሆነ የዐማራ ተወላጆች ንብረት ከሰኔ ፬ እስከ ሰኔ ፮ ቀን ፪፻፱ ዓ።ም በቀቤና ብሔረሰብ አባላት መውደሙን ከቦታው ዛሬ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል ዕ የሚል ዜና እራሳቸውን የአማራ አክቲቪስት ነን በሚሉ ሰውች ተለቆ በመራገብ ላይ ነው። እንደ ዜናው አገላለጥ ሰውየው ይህ ሁሉ የደርስበት አማራ ስለሆነ ብቻ ነው የሚል ሲሆን አቀራረቡም የአማራዎችን ትኩረት በመሳብ ወደ ሌላ ዙር አቅጣጫ የመሳብ ሂደት ነው። እውነቱ ግን ይኽ አይደለም።

እሁድ እለት ሁለት ጎረቤታሞች ይጣላሉ። አንዱ ቀቤና ሲሆን ሌላው አማራ ነው። የጠቡ መነሻ በአንደኛው ግቢ ውስጥ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ወሰድክብኝ የሚል ነው። ተሰዳደቡ፤ ተዛዛቱ። ምሽት ላይ የ፰ ወ እርጉዝ የቀቤና ሴት ተመታች፤ ሴትየዋ ያረገዘችው መንታ ህፃናትን ነበር። ሆስፒታል ተወሰደች፤ እናትና አንዱ ህፃን ሞቱ። አንደኛው ህፃን በህይወት ተወለደ። ዜናው ሰፈሩን ረበሸ። አማራው በጥርጣሬ ታሰረ። የሰፈሩ ሰው እሱ ነው የመታት የሚል እምነት አለው። የተወሰኑ የቀቤና ወጣቶች ወደ እስር ቤት ሄደው ፓሊሶቹን ደብድበው ሰውየውን ገደሉት፤ ቤቱንም በእሳት አቃጠሉት። አሁን በጉዳዩ የአገር ሽማግሌዎች ገብተውበት በርዷል።

ይህን መረጃ የሰጠ ሰው በሴትየዋና ህፃኑ በቀብር ላይ የተገኘ ሲሆን የተፈጠረው ነገር ሰውን ሁሉ ያሣዘነ እንደመሆኑ አማራ ቀቤና ጉራጌ ሳይባል ሰብዓዊነት ያለው ሁሉ በተገኘበት የቀብር ስነ ስርዓቱ ተፈጽሟል።

ለማስታወስ ያህል ቀቤና ጉራጌ ዞን ውስጥ ወልቂጤ ከተማ አካባቢ የሚገኝ እራሱን የቻለ ብሄረሰብ ቢሆንም ከመካከላቸው በጉራጌ ዞን ውስጥ መካለላቸውን የማይወዱ አሉ። በ ፩፱፱፫፨፱፬ አካባቢ በወያኔ በተቀነባበረ አሻጥር ቀቤኖች ወልቂጤ የእኛ ስለሆነ ጉራጌ ለቆ ይውጣልን ብለው ከፍተኛ የሆነ ደም መፋሰስ ከመድረሱ በፊት በብልህ ሰዎች ጥረት ነገሩ ተረጋጋ። ወልቂጤ ውስጥ ችግር አለ ከተባለ እንኩዋን ችግሩ ያለው በቀቤና በጉራጌ እንጂ በቀቤና በአማራ ወይም በጉራጌና በአማራ መካከል አይደለም። ቀቤናዎች ወልቂጤ የኛ ነን ይላሉ፤ ወልቂጤ ደግሞ በቀቤና መንደሮች የተከበበች ከተማ ናት።

ከዚህ ውጭ ተጨማሪ የወደመ ንብረት በሌለበት ሁናቴ ነገሩን ጎሳዊ ቅርጽ መስጠቱ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ትርፍና ኪሳራውን አስልቶ የማይራመድ፤ ለግላዊ ፍላጎት ሲባል ብቻ በአገር ላይ ቁማር መጫወት አክቲቪስትነት አይደለም። ይልቁንም በጸረ ወያኔ ትግሉ ላይ ወሃ በመቸለስ እንቅፋት መሆን እንጅ።

የወያኔ ማኔፌስቶ ጠላቴ አማራ የሚል ነው። አራት ነጥብ። ይኽ ነገር ወያኔ ገሃነም እስኪገባ ከሰማይ በታች ባለ ትንትኔ አይቀየርም። ለዚህ ተፈጻሚነት ደግሞ ይኽን ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብሄረሰቦች አልፎ ከሱዳን እስከ ሱማሌ ያልገዛለት ጠላት የለም። አላማውም ግልጽ ነው፤ የቁርጡ ቀን ሲመጣ እንደ ገና ዳቦ በሁሉም ማእዘን እሳት አንድዶበት ለመሄድ ነው። የእድሜ ልክ የቤት ስራ ሊሰጠው ነው። ዛሬ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአማራነታቸው ተቆርቁረው የተነሱ አክቲዚስቶችለዚህ አይነቱ የወያኔ ሴራ ግብአት ላለመሆናቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ ሊያመጡ አይችሉም። እነሱም ባቅማቸው ለአማራ ያልገዙለት ጠላት የለምና። ዛሬም የሚራገበው የወልቂጤ ዜና ሌላ ትርጉም የለውም፤የቀረው አንድ ጉራጌ ነበርና እርሱንም ጠላት አድርጋችሁ ፈርጁልኝ ነው።

 ሰው ሆኖ መፈጠር የድንቅ አእምሮ ባለቤት መሆን ነው። ሰማየ ሰማያትን ቀዶ ማሰብ መቻል ነው። ይህችን አለም ድንበር አልቦ ማድረግ ነው። እንደ መላእክት በመንፈስ መነጠቅ ነው። እኛ ደግሞ በአባቶቻችን የደም ዋጋ የተገዛን የሰማእታት ልጆች ነን። መጫሚያ የሌላቸው የቀደሙት አባቶቻችን ከአራቱም ማእዘን እየፈሰሱ በከፈሉት ዋጋ ነው እዚህ ያደረሱን ስንል ዛሬ የቆምንበት አፈር በነሱ አጥንትና ደም ጭምር ተለውሶ የተሰራ ነው ለማለትም ጭምር ነው። እኛ ደግሞ ከዚህ አፈር ጋር በእትብታችን ጭምር የተገመድን እንደመሆናችን ከዚህች መሬት ብቻ ሳይሆን ከዚህ ማንነት ወደየትም አንሄድም ወደየትም አንወርድም። ይኽ ውበታችን ብቻ ሳሆን እንደ አንድ ሉአላዊ ህዝብ የሚያኖረን ዋስትናችንም ነው። ሰንኮፋው ወያኔና ኩባንያው ነው። መፍትሄው እሱን ነቅሎ መሄድ ነው። ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን ብለን የተስፋ ስንቅ የምንሰንቅና ተስፋችንም ስጋና ደም ገዝቶ እውን እንዲሆን እስከ ሲዖል ዳርቻም ቢሆን ለመጓዝ ቁርጠኛ መሆን እንጅ ከዚህ ራእይ መጉደል ጉዞውን የኋሊት ያደገዋል።

በአባቶቹ የወገብ ልክ መሙላት ያቃተውና ወያኔ ሰፍሮ በሰጠው ማንነት እንዲያስብ የተሰራ ብቻ ሳይሆን በዚህም የሚኮራ ትውልድ ከዚህ አካሄድ ጀርባ የተጠመደለትን አደጋ ማየት የተሳነው ብቻ ነው። ሰው ከአመክንዮ ወርዶ ሁሉን ነገር በስጋና በደም ብቻ መመንዘር ሲጀምር ምን ያህል ከእውነት ጋር እንደሚጣላና ሜዳና ገደሉን መለየት እንደሚሳነው ዳር ቆሞ ለሚያየው ሁሉ ፍንትው ያለ እውነት ነው። ችግሩ እርሱ በጎሳ ተስቦ መለከፉ ብቻ አይደለም። መለከፉን አለማወቁ ነው፤ ሌላውም እንደሱ እንዲሆንለት እንቅልፍ ማጣቱ ነው። በሌላ አነጋገር ታምሜያለሁና እናንተም፣ ታመሙ ማለቱ ነው። ሁሉም ታሞ ታሞ አስተማሚ በሚጠፋበት ቤት ማን ጥርኝ ውሃ እንደሚያቀብል እግዚአብሔር ይወቅ።በጎረቤታሞች መካከል በተነሳ ግጭት ግለሰቦች በደረሰባቸው ልብ ሰባሪ ሀዘን ተግፍተው የፈጸሙትን የሃይል እርምጃ እንደ ሰው ሆኖ ከተቻለም እንደራስ ሆኖ መፍረድ ሲገባ ዝም ብሎ እርምጃ የተወሰደበት ሰው ምንም ይስራ ምንም ነገር ግን አማራ ብቻ ስለሆነ የሌላውን ጉዳት ባለማየት ብቻ ሳይሆን የተፈጸመውን ወንጀል ወደ ጎሳ ፖለቲካ በማውረድ እነሱ ለሚፈልጉት አላማ ማዋልና ህብረተሰቡንም በዚያው በኩል እንዲፈስ ማራገብ ወይ የጤና ጉዳይ ካልሆነ አለማነስ ነው።

ከምእራባዉያን የዜና ማሰራጫ ቋቶች በሚወጣ ፕሮፓጋንዳ የተፈለገውን ያህል ተጽእኖ ማሳደር አልተቻለም ተብሎ ቢቢሲና ሲኤን ኤን የአረብኛ ጭምብል ለብሰው በኩዋታር ከተሙና አልጀዚራ ሆነው መጡ። ከሱኒዎች እምብርት ኩዋታር በሚፈልገው የራሱ ቋንቋ የሚረጨውን ሁሉ ገና ለገና አረብኛ ነው በሚል ጆሮውን የሰጠው አረብ ሁሉ አልጀዚራን ተከትሎ ወደ ሰናኦር ዘመን ማዝገም ከጀመረ ሁለት አስርተ አመታት ሊሞላው ነው። ኢራቅ፣ ሊቢያ ሶሪያ የመን አፍጋኒስታን ካርታ ላይ አሉ ማለት አይቻልም። ቱርክ ግብጽ ባህሬን ኩዋታርና ሳውዲ አረቢያ ደግሞ ከፊት መስመር ተሰልፈው ቀናቸውን እየጠበቁ መሆኑን ለማየት አራት አይን አያስፈልግም። ከዚህ የማይማር ካለ ጤናውን ይፈትሽ።