June 20, 2017
ከአንድ ማስፈንጠሪያ ተነስቼ አንድ የትግርኛ ዘፈን ኢካድፍ ድረገፅ ላይ ቪዲዮውን ተመለከትኩና ከልብ አዘንኩ፡፡ እነዚህ ወያኔዎች በፈጣሪም ላይ እንዳመፁ ተረዳሁ፡፡ ለነገሩ መረዳቴን አደስኩት እንጂ እንደአዲስ አልሆነብኝም፡፡ ምክንያቱም ከመነሻቸው ጀምሮ ፍጡራኑን ሲያጭዱና ሲረመርሙ አሁን ድረስ በመዝለቃቸው ከእግዚአብሔር መንገድ ማፈንገጣቸውን እኔ ብቻ ሳልሆን ማንም የሚገነዘበው ነው፡፡ ዘመናችን እንዳለ የቅሌት ዘመን ሆነ አይደል እንዴ! የመነኩሴ ዘፋኝ?

ይህ ዘፈን አንዲት መነኩሴ ከነሙሉ የምንኩስና አልባሳቷ ሆና የዘፈነቺው ነው፡፡ በተግባሯ የቀለለችን መነኩሲት አንቱ ማለት አንቱታን ማባከን ነውና አንቱ አልልም፡፡ ግን ይህች መነኩሴ በወያኔ የተቀነባበረች የትያትር መነኩሴ ትሆን ወይንስ እውነተኛ መነኩሴ? ለጊዜው አላወቅሁም፡፡ እውነተኛ መነኩሲት ሆና አስኬማዋንና ቆቧን ለሕወሓት ድውይ ዓላማ አውላ ከሆነ ጥፋቱ የራሷ ብቻ ነው፤ የሞተ ሰው ተነስቶ መግደል አይችልምና፡፡ “መንኮሰ” ማለት “ሞተ” ማለት ነው እያሉ ቀሳውስቱ ያስተምሩናልና መነኩሴ ለፈጣሪው ሲል በቁሙ እንደሞተ ተቆጥሮ የቁም ተዝካርም አውጥቶ በምናኔና ቃለ እግዚአብሔርን በማስተማር ይኖራል፡፡ በአካል እስኪሞት ድረስ እንጂ በመንፈስ የሞተው ቆብ ሲጭን ነው፡፡ ነገር ግን ዘፈኑ የተሠራው በወያኔው የተለመደ ድራማ የተቀነባበረ አለባበስ ከሆነ ተጠያቂው ወያኔ ነው፤ ይህን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የሆኖ ሆኖ እንደዚህ ዓይነት ሥራ ብልግና ብቻ ሳይሆን ትልቅ ኃጢኣትም ነውና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ፈርዶበት በወያኔ የሚሠራ ምድራዊ ወንጀልም ይሁን ሃይማኖታዊ ህፀፅ ሁሉ ወደርሱ ማነጣጠሩ አልቀረም፡፡ እስኪያልፍ ያለፋልና በማተባቸው የፀኑ ተጋሩ ለተወሰነች ጥቂት ጊዜ ቻል ማድረግ ሊኖርባቸው ነው፡፡ እንጂ ወያኔ ጓዟን እየሸከፈች ትመስላለች፡፡ ከውስጥ ዐዋቂ እንደሚሰማው ከሆነ  “መሄዴ ነው መሰናበቴ ነው ችላው ምንድን ነው” እያለች መዝፈን ጀምራለች አሉ፡፡ ያጠራቀሙትን ያን ሁሉ ቢሊዮን ዶላር ግን የት ሆነውና በየትኛውስ ዕድሜያው በልተው ይጨርሱት ይሆን? ወይ ሰው የመሆን ዕዳ!

ይህ ዘፈን የእግዚአብሔርን ክብር በተጋሩ አካባቢ የሚያጎድፍ ይመስለኛል፡፡ “ቀኝህን ሲጠፉህ ግራህን ድገምለት” “ጠላትህን ውደድ”፣ “አትግደል”(ከአሠርቱ ትዕዛዛት አምስተኛዋ)፣  “የጓደኛህን ሚስትና ሀብትና ንብረት አትመኝ” (ከአሠርቱ ትዕዛዛት ዘጠንኛዋ) የሚልን አምላክ “ቆቤ ቦምብ ቢሆን ጠላቴን አደባየው ነበር”፣ “ምርኩዜ ክላሽን ቢሆን ጠላቴ ላይ አርከፈክፍበት ነበር” የሚል ዘፈን በሃይማኖት ስም ለዚያውም በበቁ መነኩሴ ስም ማዘፈን ወጥን መርገጥ ብቻ ሳይሆን የፈጣሪን ዐይን በወስፌ መደንቆል ነው፤ ክርስስን በመሳም አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከዚህ በላይ ኃጢኣት አልሠራም፤ የርሱ በአንድ ፊቱ ይሻላል፡፡ ስለሰው ልጅ ፍቅር በሞተው ክርስቶስ ስም ይህን ሰይጣናዊ ዘፈን ማዘፈን በዓለም የመጀመሪያው ትልቁ ኃጢኣት መሆን አለበት – በእውነቱ ስለዝቅጠታቸው አፈርኩ – መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠን በወደድኩ ያን ቅሌት ከማይ፡፡ አንድም ሃይ ባይ አለመኖሩና “ኧረ ይሄስ ነገር ይቅርብን” አለማለቱ እጅግ ያሳዝናል፡፡ በሰው እንደለመዱት ይቀልዱ፡፡ በእግዚአብሔር እንዴት ይቀለዳል? በፈጣሪ መኖር ወያኔዎች እንደማያምኑ እረዳለሁ፡፡ ቢሆንም በሌሎች ሃይማኖት መቀለድም የነውር ነውር ነው፡፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሰው ልጅ ከንቱነትም በጣም ተከዝኩ፡፡ “ስንት ሺህ ዓመት ለመኖር ነው ይህን ያህል መቅለልና መዋረድ ያስፈለገው?”  ብዬም አምርሬ አዘንኩ፡፡

ክርስትና ቀድሞ የገባበትና የተስፋፋበት የትግራይ መሬትና ሕዝብ በዚህ ዘፈን ምን እንደሚሉ ባውቅ ደስ ባለኝ፡፡ ለማንኛውም ይህ ዘፈን ስንቱን የእግዚአብሔር ትዕዛዛት እንደደፈጠጠ ታውቁት ዘንድ አሠርቱ ትዕዛዛትን ከዚህ በታች እንመልከት፡፡ ደግሞም እባካችሁን ወደኅሊናችን እንመለስ፡፡ “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም” ብሎ ክርስቶስ በወንጌሉ የተናገረው እንዲህ የሚያፋጀን ምግብና መጠጥ ቀርቶ ይህ ሁሉ የሚያማምር ህንፃና መንገድ ሁሉ ያልፋል፤ ሰማይና ምድርም ይለወጣሉ፤ ያልፋሉ ለማለት ነው፡፡ በትንሽ ነገር ዘላለማዊ ትዝብት ውስጥ አንግባ፡፡ እናም ወያኔዎች እባካችሁን አሁንም ቢሆን ልብ ግዙና ቢያንስ በዚህ ዘፈን ይቅርታ ጠይቁ፡፡ የሃይማኖት ንቀት ነው፡፡ እውነተኛ ፓትርያርክና የሃይማኖት አባት ከሃቀኛ የሃይማኖት ተቋም ጋር ቢኖረን ኖሮ ትወገዙ ነበር፡፡ በስማም! ምን ዓይነት ጊዜ ላይ አደረስከኝ በል! ጉድ ነው፡፡

  1. እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡ ዘጸ 202-3፡፡

  2. የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፡፡ ዘጸ 207፡፡

  3. የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ አክብረውም፡፡ ዘጸ 2010፡፡

  4. አባትህንና እናትህን አክብር፡፡ ዘጸ 2012፡፡

  5. አትግደል፡፡ ዘጸ 2013፡፡

  6. አታመንዝር፡፡ ዘጸ 2014፡፡

  7. አትስረቅ፡፡ ዘጸ 2015፡፡

  8. በሐሰት አትመስክር፡፡ ዘጸ 2016፡፡

  9. አትመኝ፡፡ ዘጸ 2017፡፡

  10. ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፡፡ ዘሌ 1918፡፡