June 17, 2017 – 

በሐዋሳ ሐይቅ ላይ ትልቅ ስጋት መደቀኑን ነዋሪዎች ገለጹ

BBN news June 16, 2017

የሐዋሳ ሐይቅ ትልቅ ስጋት እንደተደቀነበት የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ከስምንቱ ስምጥ ሸለቆ ሐይቆች አንዱ የሆነው የሐዋሳ ሐይቅ የከተማዋ ውበት ከመሆኑም በላይ፣ በርካታ የከተማ ነዋሪዎች ዓሳ በማጥመድ እና ሰዎችን በማስጎብኘት ኑሯቸውን የመሰረቱበት የዕለት ገቢ ምንጭ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ሐይቁ ትልቅ ስጋት እንደተደቀነበት በመግለጽ የሚመለከተው አካል እርምት እንዲወስድ የከተማዋ ነዋሪዎ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
በሐዋሳ እየተገነባ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከተጠናቀቀ በኋላ ከውስጡ የሚወገደው ቆሻሻ የከተማዋን ሐይቅ ይበክለዋል የሚል ስጋት ያደረባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ፓርኩ ተገንብቶ ሳይጠናቀቅ በፊት መንግስት ማስተካከያ እንዲያደርግበት ጠይቀዋል፡፡ የሃዋሳ ኢንድስትሪ ፓርክ ከሃዋሳ ሃይቅ በግምት 3 .ሜ ላይ በ 150 ሄክታር ገደማ መሬት ላይ እየተገነባ ያለ የትናንሽ ኢንዲስትሪዎች ስብስብ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ የፍሳሽ ማስወገጃዉ ጉዳይም የከተማዋን ነዋሪዎች አስጨንቋል ተብሏል፡፡ በዚህም የተነሳ የከተማዋ ነዋሪዎች ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› እስከማለት ደርሰው ድርጊቱን የሚቃወም የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ እያደረጉ እንደሚገኙ አስተያየት ሰጪዎች ለቢቢኤን ገልጸዋል፡፡ መንግስት፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚወጣው ፍሳሽ ወደ ሐይቁ ከመግባቱ በፊት ኬሚካላዊ ህክምና እንደሚደረግለት ቢገልጽም፣ ጉዳዩ ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነ አለመታወቁ ነገሩን በእጅጉ አክብዶታል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተም የተደረገ በቂ እና ተጨባጭ ሁኔታ ስለመኖሩ ከመንግስት በኩል በሰፊው የተገለጸ ነገር የለም፡፡ የከተማዋ ነዋሪም ጉዳዩን አስመልክቶ መንግስት ሰፊ እና አሳማኝ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ሲሆኑ፣ መንግስትም ለህብረተሱ ጥያቄ ተገቢውን መልስ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ከዚህ ቀደም ከሃዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የሚወጣው እና ወደ ሐይቁ የሚገባው ፍሳሽ ትልቅ ጭቅጭቅ አስነስቶ የነበረ ሲሆን፣ ሆስፒታሉ ሲገነባ ጀምሮ የከተማው ነዋሪ ተቃውሞን ሲገልጽ ነበር፡፡ ከሆስፒታሉ የሚወጣው በካይ ፈሳሽ ሐይቁ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገልጾ፣ ከሐይቁ ውስጥ የሚጠመደውን ዓሳ ላለመብላት የተደረገ ዘመቻ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የህዝብ ጫና የበረታበት መንግስት ሆስፒታሉን ወደ ሌላ አካባቢ ለማዞር ሳያስብ እንዳልቀረ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ አሁን ደግሞ በከተማዋ እየተገነባ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ሌላ ስጋ ደቅኗል፡፡