በክልሎች መካከል አስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ችግርና የኦሮሚያ ክልል አዲሱ ተሞክሮ

14 Jun, 2017

By ዘመኑ ተናኘ

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ ክልሎች መካከል ያለው  አስተዳደራዊ ወሰን በቅጡ የተካለለ ባለመሆኑ፣ የተለያዩ ግጭቶች የተከሰቱ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አንዱ ክልል ከሌላው ክልል የሚለይበት አስተዳደራዊ ወሰን በግልጽ የተካለለና የተወሰነ ስላልሆነ፣ በክልሎች መካከል ባሉ አጎራባች ነዋሪዎች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቶ ያለፈበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መካከል ተፈጥሮ በነበረው አስተዳደራዊ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የብዙ ሰዎች ሕይወትና ንብረት መጥፋቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ግጭት የተነሳ ዜጎች ከቀያቸው ተሰደዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ይህ ችግር ከክልሎች አልፎ አገራዊ በመሆን በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል የፖለቲካ አለመረጋጋት ፈጥሮ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

በ1997 ዓ.ም. በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ተካሂዶ የነበረው ሪፈርንደም የተሟላ ባለመሆኑ፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚኖሩ ዜጎች ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብተው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የነበረው የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር አሁንም ድረስ የራስ ምታት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በአንድ ወቅት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኘው ጠገዴና በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው ፀገዴ መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን  ያልተካለለ በመሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች በሚኖሩ ወገኖችና በሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች መካከል ቅሬታ እንዳለ ገልጸው ነበር፡፡ ይህ ችግር የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ እያለፉ በመሆኑ በቅርብ እንደሚፈታ ቢናገሩም፣ እስከ ዛሬ  ድረስ መፍትሔ አላገኘም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት ተከስቶ ለነበረው ሁከትና ብጥብጥ እንደ መነሻ ምክንያት ከተወሰዱ ጉዳዮች አንዱ በክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን ያልተካለለ በመሆኑና ከዚህ ጋር ተያይዘው በመጡ ሌሎች ጉዳዮች እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ የነበረው ብጥብጥ ለወራት የቀጠለና በኋላ ላይም መሠረቱን አስፍቶ አገራዊ ቀውስ አስከትሎ እንዳለፈ አይዘነጋም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ለማስፋፋት በተደረገው እንቅስቃሴ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር ያላት አስተዳደራዊ ወሰን እንደተካለለ መረጃዎች ቢጠቁሙም፣ ከተማዋን ወደ ጎን ለማስፋፋት በተደረገው ሙከራ በሕዝቡ ዘንድ ተቃውሞ በማስነሳቱ ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱ ይታወቃል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ በአብዛኛው ከኦሮሚያ ክልል ጋር የምትዋሰን በመሆኑ፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልታገኝ የሚገባው ጥቅም መረጋገጥ እንዳለበት ለብዙ ጊዜ በክልሉ ተወላጆች ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡ ጥያቄው ከቀረበ ብዙ ዓመት ቢያስቆጥርም ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ባካሄዱት ውይይት፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልታገኝ ስለሚገባት ጥቅም በሚመለከት በሚቀጥለው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ተናግረዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል ከትግራይ ክልል በስተቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ክልሎችና የከተማ መስተዳደሮች ጋር ይዋሰናል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ክልሎች መካከል በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት አብላጫ ያለው የኦሮሚያ ክልል፣ በአስተዳደራዊ ወሰን ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ክልሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም ከጋምቤላ ክልል ጋር በነበረው የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር ምክንያት በሁለቱ ክልሎች መካከል በሚኖሩ ዜጎች በተቀሰቀሰ ግጭት ንብረት መውደሙ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን በቅጡ ያልተካለለና ያልተወሰነ በመሆኑ፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ቅራኔ እንደነበር ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራር ተናግረዋል፡፡

ከአፋር ክልል ጋር ባለው ሰፊ አስተዳደራዊ ወሰን ምክንያትም ችግሮች ሲፈጠሩ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱን ክልሎች በሚያዋስኑዋው የአርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽና ለእርሻ ሲሉ በአጎራባች ክልሎች መካከል በተደጋጋሚ ጊዜ  ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰንም በግልጽ የተካለለ ባለመሆኑ፣ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ነዋሪዎች መካከል ተደጋጋሚ የሆነ ግጭትና ሁከት ሲከሰትና የሰው ሕወት ሲጠፋ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳ  የሁለቱ ክልል ነዋሪዎች አርብቶ አደሮች ቢሆኑም፣ ለፍየሎቻቸውና ለግመሎቻቸው ግጦሽ እርስ በእርሳቸው ሲጠፋፉና ሲገዳደሉ እንደቆዩ ይነገራል፡፡

አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በበኩላቸው ሰፊ የሆነ መሬት የሚጋሩ ሲሆን፣ በእነሱም መካከል የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር በመኖሩ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ግጭቶች ሲፈጠሩ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ሁለቱን ክልሎች በሚያዋስነው ምንጃር አካባቢ በተደጋጋሚ ጊዜ በነዋሪዎች መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ክልሎችና የከተማ መስተዳደሮች መካከል ግልጽ የሆነ አስተዳደራዊ ወሰን ባለመካለሉ የተነሳ፣ በዜጎች መካከል በተደጋጋሚ ጊዜ ግጭትና ንትርክ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ይህ ግጭትና ንትርክ አሁንም ድረስ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያ በዘጠኝ ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረች ፌዴራላዊ አገር ነች፡፡ እነዚህ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የራሳቸው የሆነ አስተዳደራዊ ወሰንና  የአስተዳደር ሥርዓት ተበጅቶላቸው መተዳደር ከጀመሩ ከ20 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ክልሎች የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በሰጣቸው መብት ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር አልፈው እስከ መገንጠል የሚደርስ መብት አላቸው፡፡

ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌድሪ) አስተዳደር ጥላ ሥር ሆነውና ራሳቸውን በማስተዳደርና በመምራት ከሌሎች ክልሎች ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን በመፍጠር እንደሚኖሩ በሕገ መንግሥቱ ላይ ተደንግጓል፡፡ ክልሎች በሚያመሳስላቸው ጉዳዮች ላይ አብረው በመሥራትና አብረው በማደግ ራሳቸውን የመለወጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አንዳንድ ክልሎች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተባብረውና ተጋግዘው ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ ክልሎች እርስ በራሳቸው አብረው ከመሥራታቸው ባሻገር፣ በመካከላቸው ልዩነቶች ሲፈጠሩና ግፋ ሲልም ለፀብና ለተለያዩ ጉዳዮች ሲዳረጉ ይታያል፡፡ በመካከላቸው ያለው አስተዳደራዊ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ደግሞ በክልሎች መካከል ቅራኔ በመፍጠር ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በክልሎች መካከል ያለው የወሰን  ይገባኛል ጥያቄ በተደጋጋሚ ጊዜ በተለያዩ ክልሎች መካከል ሲፈጠር የቆየና በሕዝቦች መካከል ቅሬታን ፈጥሯል የሚሉ ወገኖች  አሉ፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች ደግሞ አድገውና ከፍ ብለው በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ብጥብጥና ሁከት አስከትለው እንዳለፉ በማስታወስ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ክልሎች በቆዳ ስፋትም ሆነ  በሕዝብ ቁጥር አብላጫ ያለው የኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ በአብዛኛው ከክልሎች ጋር ወሰን በመጋራትም ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ የመልካም አስተዳደር ችግር መፈጠሩን የክልሉ መንግሥት በማመኑ በክልሉ አመራሮች ላይ ሹም ሽር አድርጓል፡፡ በአገሪቱ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለውን ክልል ማስተዳደር ከባድና አቅም የሚጠይቅ ጉዳይ እንደሆነ ባለሙያዎች ሲገልጹ ቢሰማም፣ ይህን ጥያቄ ለመመለስ በክልሉ በወጣት ኃይል የሚመራ ከፍተኛ አመራር ተቋቁሟል፡፡ ይህ አብዛኛው ወጣት የሆነው የክልሉ ከፍተኛ አመራር፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት ላይ ታች ሲል ታይቷል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ ችግር ሆኖ የነበረውን የወጣቱን የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንስቶ ከክልሎችና ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን የወሰን ጥያቄ፣ እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ግጭቶችንና ብጥብጦችን ለመፍታት በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ወደ ሥልጣን ከመጣ ከዓመት ያልበለጠው የአቶ ለማ መገርሳ አዲሱ ካቢኔ የክልሉን ሁለንተናዊ ችግር ለመፍታት እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ሲሞካሽ እየተሰማ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል የኢኮኖሚ አብዮትን ከማቀጣጠል ጀምሮ ከተለያዩ ክልሎች ጋር ያለውን የወሰን ችግር ለመፍታት ሌት ከቀን እየሠራ መሆኑን፣ በቅርብ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ አዲሱ የክልሉ ካቢኔ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በአብዛኛው የክልሉ ወጣቶች ዘንድ አድናቆትን እየተቸረው እንደሆነም  የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ ኦሮሚያን የኢንዱስትሪ ማዕከል ከማድረግ ባለፈ ሰላም የሰፈነበት ክልል ለማድረግ አሁንም  እንቅልፍ ሳይወስደው እየሠራ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር ተፈጥሮ የነበረውን የወሰን ችግር የፈታ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ጋር ያለውን የወሰንና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በእንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ጊዜያት ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና በክልሎች መካከል ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር የስምምነትና የሰላም ኮንፈረንስ አካሂዷል፡፡ በዚህም ለዓመታት ያህል በድንበር አካባቢ ይኖሩ በነበሩ ነዋሪዎች መካከል ይፈጠር የነበረውን ውዝግብና ብጥብጥ በመፍታት ረገድ የተጓዘው ጉዞ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ነዋሪዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡
በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አደራዳሪነት የተካሄደው ይህ አስተዳዳራዊ ወሰንን የማካለል ሥራ፣ ኦሮሚያ ክልልን ከሚያዋስኑ ክልሎች ጋር ከዚህ በፊት የነበሩትን ችግሮች እንደሚፈታ ታምኖበታል፡፡

አስተዳደራዊ የወሰን ችግሮች መኖራቸውን አምኖ ይህንን ችግር ለመፍታት ወደ ሥራ የገባው የኦሮሚያ ክልል አዲሱ ካቢኔ፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን አስተዳዳራዊ ወሰን ለመፍታት ዛሬም ድረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የክልሉ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር የነበረውን የረጅም ጊዜ ችግር በሰላም ከተፈታ ወዲህ፣ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በሚኖሩ ወገኖች መካከል ምንም ዓይነት ግጭት አለመፈጠሩን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡

በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል አዲሱ ካቢኔ በአሁኑ ወቅት ከጎረቤት  ክልሎች ጋር ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን በማካለልና በክልሉ ፀጥታ እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ እየሠራ ያለው ሥራ፣ በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን እያገኘ መምጣቱን የሚናገሩ አሉ፡፡

የክልሉ ባለሥልጣን እንደሚሉት፣ አዲሱ የክልሉ ካቢኔ የ2009 ዋነኛ ዕቅዱ ኦሮሚያን በሚያዋስኑ ክልሎች መካከል ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን በግልጽ መለየት ነው፡፡ በክልሉ ብሎም በአዋሳኝ ድንበሮች መካከል የሚኖሩ ዜጎች ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንደሆነም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከወራት በፊት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና የአፋር ክልል አስተዳደራዊ ወሰኖችን ጨምሮ፣ ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር የወሰን ማካለል መደረጉን ባለሥልጣኑ አስረድተዋል፡፡

ግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር የተደረገው  የአስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ስምምነትም በይዘቱ ከጋምቤላ ክልል ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሥልጣኑ፣ በሁለቱ ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚኖሩ ወገኖችን ያካተተ አጠቃላይ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ አጠቃላይ አስተዳዳራዊ ወሰኑን የማካለል ሥራም በቅርብ ቀን  እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡

ከአስተዳደራዊ ወሰን ጋር በተያያዘ ኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ብሎም በአገር ደረጃ ግጭትን ለማስቀረት የሚያችል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡ ከዓመታትና ከወራት በፊት በወሰን ምክንያት የጠፋው የሰው ሕይወትና ንብረት ሁለተኛ እንዳይደገም፣ የኦሮሚያ ክልል አዲሱ ካቢኔ የቤት ሥራው አድርጎ እየሠራ እንደሆነ አክለዋል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ደግሞ፣ በክልሎች መካከል ያለው ግጭት ሊወገድ የሚችለው ሁሉም ክልሎች እንደ ኦሮሚያ ክልል የቤት ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ ሲሠሩ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

መምህሩ እንደሚሉት በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ግጭትና ሁከት መነሻ ምክንያት ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ በክልሎች፣ በተለይም ኦሮሚያ ክልል በሚያዋስናቸው ሌሎች ክልሎች ጋር የነበረው የወሰን ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ተገንዝቦ ወደ ሥራ የገባው አዲሱ የኦሮሚያ አስተዳደር ካቢኔም ምሳሌ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የግጭትና የሁከት መነሻ የነበረውን የኦሮሚያ ክልል ሰላም የሰፈነበትና ወጣቶች የሥራ ዕድል ባለቤቶች እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር እየተጫወተ ያለውን ሚና ያደነቁት መምህሩ፣ ሌሎች ክልሎችም በመካከላቸው ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን መፍታት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች  ሚኒስቴር  ይህንን ጉዳይ አጠናክሮ በመያዝ፣ በሌሎች ክልሎች መካከል ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን መፍታት እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡

ግሎባላይዜሽን እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለና ዓለም አንድ መንደር ሆና ሳይንስና ቴክኖሎጂ እየረቀቀ በመጣበት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ገና በአስተዳደራዊ ወሰን ማካለል ችግር ውስጥ ገብታ ደፋ ቀና ማለት እንደሌለባት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሥልጣኔ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ሴኮንድ ባልሞላ ጊዜ እየተቀጣጠለ ባለበት በዚህ ዘመን፣ የዓለም አገሮች ከሌላው ኃያል የሚሆኑበትን ዘዴ ለመቀየስ ደፋ ቀና በሚሉበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ገና ዳዴ ማለት እንደሌለባት ያስረዳሉ፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያለው የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር ከኦሮሚያ ክልል ተሞክሮ በመውሰድ ሊፈታ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በ2009 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል አዲሱ ካቢኔ ዓላማ የሆነውን የወሰን ማካል ችግሮችን በመፍታት የክልሉን ፀጥታ ማስፈን እንደሆነና በ2010 ዓ.ም. ደግሞ ፊቱን ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንደሚያዞር የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡ ከአማራ ክልል ጋር ያለውን አስተዳደራዊ የወሰን ችግር ለመፍታት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ኃላፊነቱን ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ የሚናገሩት ባለሥልጣኑ፣ በቀሪዎቹ ሦስት ወራትም ችግሮችን ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ ካሉ የአንዱ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ይህ ግለሰብ የኦሮሚያ ክልል ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር ያደረገውን የአስተዳደራዊ ወሰን ይዘትና ሌሎች ዝርዝር ስምምነቶችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ክልልና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ደርሰውበት የነበረውን አስተዳደራዊ የወሰን ማካለል ስምምነት ይዘትና ዝርዝር ጉዳዮች ለሚዲያዎች ይፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ ይህንን ግን ባለሥልጣኑ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ወደፊት ከሁሉም ክልሎች ጋር ስምምነት ከተደረገ በኋላ ዝርዝር  የስምምነት ይዘቶችን ይፋ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል፡፡