Wednesday, 21 June 2017 14:32

ፋኑኤል ክንፉ 

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በዘረጋችው መጠነ ሰፊ የስኳር ልማት ዙሪያ መንግስታቸው ትምህርት ማግኘቱን ከመግለጽ ውጪ፣ አንድም ተጠያቂ አካል ማቅረብ አልቻሉም። ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው፣ አንድ ቀን በዚህ ስኳር ልማት ዙሪያ ኃላፊነት የሚወስዱ በሕግ የሚጠየቁ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መኖራቸው አይቀሬ እንደሆነ የአደባባይ እውነት ነው።

በዚህ ጽሁፍ ካለፈው ሳምንት የከሰም ጉብኝታችን የቀረውን ክፍል ይዘን ቀርበናል። በተለይ የከስም ስኳር ፋብሪካ እና የእርሻው ዘርፍ ምን እንደሚመስል የሚያካፍሉን፣ ሁለት በስኳር ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ኃላፊዎችን አነጋግረናል።

ከእነዚህም መካከል የከሰም የፋብሪካ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ዋበላ አንዱ ናቸው። አቶ ታደሰ ከሃያ ስድስት ዓመት በላይ በስኳር ኢንዱስትሪው ውስጥ አገልግለዋል። በወንጂ እና በአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካዎች ሰርተዋል። ሌላው በከሰም የእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምሩጽ ወልዳይ ናቸው። አቶ ምሩጽ በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሰላሳ አራት አመት አገልግለዋል። ቀደም ብለው በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ አሁን ደግሞ በከሰም ስኳር ፋብሪካ እያገለገሉ ይገኛሉ። 


እነዚህ ከፍተኛ የስኳር ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች መንግስት በዘረጋው የስኳር ልማት ስትራቴጂ ላይ ከልምዳቸው በመነሳት ያካፈሉን ቁምነገር አለ፤ ሰሚ ካለ ይስማ። በተጨማሪም በወቅታዊ የከሰም ስኳር ፋብሪካ የሥራ ክንውን ዙሪያ አነጋግረናቸዋል። መልካም ንባብ።

የስኳር ልማቱ ላይ ስትራቴጂክ የሆነ

የአስተሳሰብ ክፍተት አለበት”

አቶ ታደሰ ዋበላ

የፋብሪካ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ

ሰንደቅ ፋብሪካው እስካሁን በፕሮጀክት ደረጃ ነው ያለው ወይንስ ፋብሪካውን ሙሉ ለሙሉ ተርክባችሁታል?

አቶ ታደሰ ዋበላ– አዎ በፕሮጀክት ደረጃ ነው። በቅርቡ በአፕሪል 28 እስከ 30 ባሉት ቀናት “performance guaranty” test አድርገናል። ይህ ማለት ፋብሪካው 6ሺ ቶን አገዳ ቢቀርብለት በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ ያለማቋረጥ ይፈጫል? የሚለውን ለመፈተሽ ነው። አገዳ አከማችተን ባደረግነው ፍተሻ ፋብሪካው በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ 6ሺ አንድ መቶ አገዳ ፈጭቷል። ፋብሪካው በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው።

የፋብሪካው የአዋጭነት ጥናት እንደሚያሳየው፣ በአገዳው ውስጥ መገኘት ያለባቸው የንጥረ ነገሮች መጠን በመቶኛ ሲያስቀምጥ፤ ፋይበር 13 ነጥብ 5፣ ሱክሮስ ከ13 በላይ እና ባዕድ ነገሮች 3 በመቶ የሆነ የሚል ነው። ከአሚባራ የሚመጣው አገዳ ግን በመቶኛ ሲገለፅ፤ ፋይበር 19፣ ሱክሮስ ከ10 በታች፣ ባዕድ ነገሮች ከ3 እስከ 7 በመቶኛ ናቸው። ባዕድ ነገሮች በበዙ ቁጥር ስኳር እንዳይወጣ ከማድረጋቸውም በላይ ስኳሩን ይዘው ወደ ሞላስስ ይዘልቃሉ። ከባዕድ ነገሮች የፀዳ አገዳ ሲሆን ብቻ ነው ጥሩ ስኳር ማግኘት የሚቻለው። ስለዚህም በእርሻው ላይ መስራት ይጠበቅብናል።

ሰንደቅ የፋብሪካው ብቃት (Efficiency) እንዴት ነው?

አቶ ታደሰ ዋበላአጠቃላይ የፋብሪካው የሰዓት ኤፊሸንሲ 80 በመቶ ይሆናል ተብሎ ተቀምጧል። ይህ ማለት በቀን 4800 ቶን አገዳ ፋብሪካው መፍጨት ይጠበቅበታል። ዳሩ ግን ከአሚባራ በቀን 4800 አገዳ ማምጣት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። አሁን ባለው ደረጃ በአብዛኛው የሚመጣው 3700 ቶን አገዳ ነው። ለዚህ ምክንያቶቹ የመንገዱ ርቀትና መንገዱ ያልተስተካከለ መሆን፣ የአሚባራ ማሳ ለጥጥ የተዘጋጀ በመሆኑ አገዳውን ከማሳ ማንሳት አመቺ አይደለም። አገዳው በዶዘር እየተገፋ ለመጫን ስለሚሰናዳ ዶዘሩ በርካታ ባዕድ የሆኑ ነገሮች አብሮ ከአገዳው ጋር ገፍቶ ያመጣል። ይህም በመሆኑ ብዙ ባዕድ ነገሮች ፋብሪካው እያጣራ ያራግፋቸዋል። በፋብሪካ የገባው የሱክሮስ መጠን እና የሚወጣው የስኳር መጠን በጣም የሚገርም ነው።  ፋብሪካው ዘመናዊ (Distributed control system) በመሆኑ 7 ነጥብ 8 ሱክሮስ እየገባ 7 አካባቢ ስኳር እየወጣ ነው።

ባለፈው አመት የፋብሪካው እቅድ ሲያዝ ለፋብሪካው የሚቀርበው የሱክሮስ መጠኑ የተገመተው 10 ነጥብ 38 በመቶ ሲሆን እየቀረበ ያለው የአገዳው የሱኩሮስ መጠን ይዘት 7 እና ከዚያ በታች በመቶኛ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት፤ ከአሚባራ የሚመጣው አገዳ ዕድሜው ከ32 ወር በላይ በመሆኑ እርጅና ተጭኖታል። አገዳ ለምርት መድረስ ያለበት ግን ከ14 እስከ 16 ወር ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ ማለት ከአሚባራ የሚመጣው አገዳ ስኳሩን ጨርሶ ወይም ለራሱ ስኳሩን ተጠቅሞት ነው። እንደዚህ እድሜው ከፍ ያለ አገዳ ለቀድሞዎቹ ለወንጂ እና ሸዋ ፋብሪካዎች ቀርቦ ቢሆን፣ አንድም ስኳር ማግኘት አይቻልም። በዕቅድ ደረጃ ከአረጀ አገዳ የተጠበቀውም የስኳር መጠን ስህተት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ስለዚህም ይህ መደገም የለበትም። መሬት ላይ ባለው ነገር ማቀድ እንደሚገባን አሳይቶን ያለፈ የምርት ዘመን ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ የፋብሪካው አቅም እና የአገዳውን አቅርቦት እንዴት ይገልፁታል?

አቶ ታደሰ ዋበላ በመጀመሪያው ምዕራፍ ማለትም አሁን ባለበት ደረጃ በቀን 6ሺ ቶን አገዳ ፈጭቶ ስድስት ሺ ኩንታል ያመርታል ተብሎ የተመሰረተ ፋብሪካ ነው። ሆኖም በተደረገው ማስፋፊያ እና በተገጠሙለት የፋብሪካው ክፍሎች ወደ አስር ሺ ኩንታል የማምረት አቅም ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም ሲባል የፋብሪካው cane handling, preparation, milling, evaporation and clarification ክፍሎቹ በቀን አስር ሺ ኩንታል ስኳር ፋብሪካው እንዲያመርት ተደርገው የተገመጠሙ ናቸው። ትንሽ መጨመር ከሚያስፈልጋቸው የፋብሪካው ክፍሎች መካከል pumps, pipe, vacuum pan, center fugal ናቸው።

ፋብሪካው በዚህ ደረጃ የተዘጋጀ ቢሆንም አስር ሺ ቶን አገዳ በቀን ለመፍጨት በሚያስችል ደረጃ የተዘጋጀ የአገዳ ምርት የለም። የፋብሪካው የአዋጭነት ጥናት እንደሚያሳየው ፋብሪካው አስር ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም እንዲኖረው የተደረገው ሃያ ሺ ሔክታር መሬት በከሰም ዙሪያ እናለማለን ከሚል ታሳቢ ነበር። አሁን ላይ በፋብሪካው ዙሪያ የለማው አገዳ 3ሺ ሔክታር ነው። እንዲሁም፤ በአሚባራ 6ሺ ሔክታር የለማ መሬት አለ። በድምር 9 ሺ ሔክታር አገዳ ነው ያለው።

በቀን 6ሺ ቶን ለሚፈጭ ፋብሪካ በ9ሺ ሔክታር ላይ የለማ አገዳ በቂ ምርት አይደለም። ምክንያቱም በስሌቱ መሰረት ከሁለት ሔክታር የአገዳ ማሳ የሚገኘው አንድ ቶን አገዳ በመሆኑ ነው። 6ሺ ቶን አገዳ ለሚፈጭ ፋብሪካ በትንሹ 12 ሺ ሔክታር የአገዳ ማሳ ያስፈልገዋል። ይህም የሚሆነው ሞቃታማ ቦታ ለሚተከሉ ፋብሪካዎች ብቻ ሲሆን፤ ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ባለባቸው ቦታዎች የሚተከሉት ፋብሪካዎች 6ሺ ቶን አገዳ ለመፍጨት 15ሺ ሔክታር የለማ አገዳ ያስፈልጋቸዋል።

ሰንደቅ በቀጣይ ዓመት የአገዳው አቅርቦት እንዴት ነው የሚሆነው? የአገዳ ዝርያዎች ቢለያዩም ከ13 እስከ 18 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በአማካኝ እንደሚደርሱ ማጣቀሻዎች ያሳያሉ። 

አቶ ታደሰ ዋበላ– በዚህ አካባቢ ከ14 እስከ 16 ወራት ባለው ጊዜያት አገዳ እንደሚደርስ ሰምቻለሁ። የኬን ሳይክሉን መመልከት አስፈላጊ ነው። ለምሳል ዛሬ የተቆረጠ አገዳ ዳግም የሚቆረጠው ከ12 ወር በኋላ ነው፤ በዚሁ መሰረት የቆረጣውን ሁኔታ መከለስ ይገባል። ዋናው አማራጭ ግን በከሰም ዙሪያ አገዳ መትከል ነው። ፕሮጀክቱም አዋጪ የሚሆነው በከሰም ዙሪያ አገዳ ከተተከለ ብቻ ነው።

ሰንደቅ የአንድ ኪሎ ግራም ስኳር የማምረቻ ወጪያችሁ ስንት ነው?

አቶ ታደሰ ዋበላ– አዲስ ፋብሪካ ነው። ትክክለኛው ወጪ መሰራት አለበት። performance guaranty test እስከምናካሂድ ድረስ ፋብሪካው በቻይናዎች ይዞታ ውስጥ ነበር። አሁን ኦፕሬሽኑ ወደ እኛ ይዞታ የገባ በመሆኑ ወጪን መስራት እንችላለን። የቀሩ ሥራዎችን ደግሞ በኮንትራት ውል ቻይናዎቹ እንዲጨርሱ እየተደረገ ነው። ያልተሞከሩ የፋብሪካው ክፍሎች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። ከእነሱ መካከል የቆሻሻ ማጣሪያ ፕላንት፣ የውሃ ማጣሪያው ሲስተም፣ ኃይል ከሚያመነጩ ተርባይኖች መካከል አንዱ አልተሞከረም። እነዚህን ቻይኖቹ በኮንትራት ውል እየሰሩ ይገኛሉ።

ሌላው ሃያ ስድስት ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንችላለን። ከዚህ ውስጥ 6ሺ ቶን አገዳ ለመፍጨት አስራ አንድ ሜጋ ዋት ብቻ ነው የምንጠቀመው። ትርፍ ከ10 ሜጋ ዋት በላይ አለን። ይህንን ትርፍ ኃይል ከብሔራዊ ኃይል ማሰራጫ መስመር ጋር ለማያያዝ ሰብስቴሽን መትከል ይቀራል።    

ሰንደቅ ስኳር ማምረት እድሜ ጠገብ ሳይንስ ቢሆንም፣ ስኳር ኮርፖሬሽን አስር ፋብሪካ በአንድ ጊዜ ለመስራት አቅዶ አንዱን እንኳን በቅጡ ማጠናቀቅ አልቻለም። እርስዎ ከሃያ አመት በላይ በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ ካካበቱት ልምድ አንፃር፣ ለስኳር ልማቱ ውድቀት መሰረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ምን ታዝበዋል? ምንስ ይመክራሉ?

አቶ ታደሰ ዋበላ– እንዳልከው ለረጅም ዓመታት በስኳር ፋብሪካ ሰርቻለሁ። የተፈጠሩት ችግሮችን ለመለየት ከደቾች (ኔዘርላንድ) ጀምሮ እንዴት የስኳር ልማት እያደገ እንደመጣ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል። በ1953 በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሲመሰረት በአነስተኛ መጠን ነው የተጀመረው። የአገዳ እርሻ በአክሲዮን ደረጃ በዚያ ዘመን ይሸጡ ነበር። ምክንያቱም ሰው እንደራሱ ቆጥሮ እንዲያለማው በማሰብ ነው። በሒደትም የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ውጤታማ ሆነ። ትርፋማም እየሆነ ሄደ። በተገኘው ትርፍ ግን ወዲያው ፋብሪካ አልተተከለም። ውጤታማነቱ በደንብ ሲረጋገጥ ከስምንት አመታት በኋላ በሸዋ ሌላ ተጨማሪ የስኳር ፋብሪካ ተከፈተ። ስያሜውም ወንጂ ሸዋ ፋብሪካ የሚል መጠሪያም ተሰጣቸው።

ሁለቱ ፋብሪካዎች በቀን በድምር 3ሺ ቶን አገዳ እየፈጩ በዓመት 700ሺ ኩንታል ስኳር ያመርቱ ነበር። ድርጅቱም አትራፊ ሆነ፣ ሠራተኞችም ተጠቃሚ ነበሩ። ሕብረተሰቡንም ተጠቃሚ አደረጉ። ከወንጂ ሸዋ ፋብሪካ ባገኙት ትርፍ ደግሞ መተሐራ ስኳር ፋብሪካን መሰረቱ። መተሐራም የተከፈተው ከስምንት አመት በኋላ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በሠራተኞች ዘንድ ልምድ ክህሎት እየዳበረ መጥቷል። ወጪያቸውም ኢኮኖሚካል ነበር። ደረጃ በደረጃ በስኳር ልማት ከፍተኛ ልምድና እውቀት በሀገራችን ተገኝቷል። ከሃያ ሰባት አመታት በኋላም ቢሆን በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ለመትከል ተችሏል።

አሁን በያዝነው አካሄድ ግን የስኳር ፕሮጀክቶች በዝተው፣ አምራች መሆን የቻሉት በጣም ትንሽ ናቸው። አስር የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በአንድ ጊዜ ውጤታማ ለማድረግ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ነው። በፕሮጀክቱ ላይ ለተሰማራው የሰው ኃይል በራሱ የደሞዝ ክፍያ በአንድ ጊዜ መፈጸም ከባድ ወጪ ነው። በስኳር ልማቱ ላይ ስትራቴጂክ የሆነው አስተሳሰብ ክፍተት ያለበት ነው። ምክንያቱም አስር ስኳር ፋብሪካ ለመትከል በአንድ ጊዜ ከማቀድ፣ ሁለት ስኳር ፋብሪካዎችን ለመትከል ቅድሚያ ቢሰጥ ኖሮ ዛሬ ላይ የተደረሰበት ሁኔታ ላይ አንገኝም ነበር። ሁለት ፋብሪካዎችን ከተከልን በኋላ ከእነሱ የሚገኙ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በመነሳት እንዲሁም ወደ ምርት ገብተው አትራፊ መሆናቸውን አረጋግጠን፤ ወደ ተጨማሪ ሁለት ፋብሪካዎች ተከላ ተሰማርተን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ያጋጠሙን ችግሮች ባልተከሰቱ ነበር። በተጠና ሁኔታ ወደሥራ ገብተን ቢሆን፤ የማምረቻ ወጪያችን ይቀንሳል። እንደሀገር ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆን በቻልን ነበር። አሁንም የረፈደ ነገር የለም። በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለመስጠት መስራት ይጠበቅብናል።¾

 

 

 

ከግድቡ በተያያዘ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያሳውቁ መሳሪዎች በሲስተም ደረጃ ተጠናቀው ወደ መስመር አልገቡም”

አቶ ምሩጽ ወልዳይ

የእርሻ ዘርፍ ሥራአስኪያጅ

 

ሰንደቅ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዘር አገዳ ተከላ የተጀመረው መቼ ነው? የአገዳ አቅርቦቱ ክፍተት እንዴት ሊከሰት ቻለ?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ– ከሰም አካባቢ ያለውን መሬት በማልማት፣ ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ተጨማሪ የአገዳ አቅርቦት ለማዘጋጀት ነበር የመጀመሪያው ዕቅድ። የከሰም ግድብ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እየተገነባም ነበር። የዘር አገዳም ተከላም በወቅቱ በከሰም ጀምረን እያለ መንግስት የአቧራ መልካ እርሻ ልማትን ተረክበን አገዳ እንድናለማ ፈቃድ ሰጠ። ብዙም ሳይቆይ አዲስ መመሪያ ከመንግስት ተላለፈ። ይኸውም፣ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍል የስኳር ልማት እንዲዘረጋ በመወሰኑ፣ ከሰም ራሱን ችሎ የስኳር ፋብሪካ እንዲሆን መወሰኑ ተገለፀልን። በተያዘው ዕቅድ መሠረት 6ሺ ቶን በቀን ለመፍጨት 12ሺ ሔክታር ውሃ ገብ መሬት ለማልማት ነበር።

ወደስራ ለመግባት ሁሉ ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በከሰም ግድብ ፍልውሃ በመገኘቱ ፕሮጀክቱ ለረጅም ጊዜ ተጓተተ። በወቅቱ ፍል ውሃውን ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ አልነበረም። አንድ የቻይና ኩባንያ ተቀጥሮ ሥራው ረጅም ጊዜ ወስዷል። ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላም የፋብሪካው የአዋጪነት ጥናት እንደገና ተከለሰ። የተሰጠው ምክንያት የፋብሪካውን አቅም ከፍ ካልተደረገ በስተቀር አሁን በተቀመጠው የፋብሪካው አቅም አዋጪ ሊሆን አይችልም ተባለ። በቀን የሚመረተው የስኳር መጠንም ወደ 10ሺ ከፍ እንዲል እና የአገዳ ማሳው ልማትም ወደ 20ሺ ሔክታር እንዲያድግ ተወሰነ።

ሥራው በተጀመረ መሐከል ላይ ሜቴክ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደረገ። የፋብሪካ ተከላውን በተመለከተ መሰረት ቆፍረው ነበር። ለረጅም ጊዜ በሜቴክ እጅ ከቆየ በኋላ መጀመሪያ ውል አስረነው ከነበረው የቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ ጋር፣ አዲስ ውል አስረን ወደ ሥራ ተገባ። ሜቴክም ከሥራው ወጣ። ኮፕላንት ኩባንያ በአጭር ጊዜ አፋጥነው ፋብሪካውን ጨርሰዋል። ስለዚህ ለአጠቃላይ ፕሮጀክቱ መዘግየት በዋናነት ከግድቡ ጋር በተያያዘ ነው። ከውሃ ኮንስትራክሽ እና ከዲዛይንና ቁጥጥር የመንግስት መስሪያቤቶች ጋር ነበር አብረን ሥንሰራ የነበረው።

ሰንደቅ ለምንድን ነው ይህን ያህል ጊዜ ፕሮጀክቱ ሳይጠናቀቅ የቀረው? አፈፃጸሙ በጣም አናሳ በመሆኑ የለማው መሬት 3ሺ ሔክታር ብቻ የሚጠጋ ነው።

አቶ ምሩጽ ወልዳይ– ፋብሪካው ቢዘገይም ደርሷል። የፋብሪካው አቅም እና የአገዳ አቅርቦት በጣም ሰፊ ክፍተት ነው ያለው። ያለውን ክፍተት ለመሸፈን የተደረጉ ጥረቶች አሉ። ከአሚባራ እርሻ አገዳ ባለሃብቶች አልምተው እንዲያቀርቡ ተደርጓል። አሁንም ግን ክፍተት አለ። ዋናው ችግር ግን ከመሬት አቅርቦት እና ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው። አሁንም መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በዚህ ዓመት 1500 ሔክታር መሬት ለማልማት አቅደን የነበረ ቢሆንም፣ የመሬት አቅርቦት ግን የለም። የውሃና መስኖ ኢነርጂ መስሪያቤትም ጥሎ ወጥቷል።

ሰንደቅ ውሃ ገብ መሬት የማቅረብ ኃላፊነቱ አሁን ለማን ተሰጥቶ ነው ያለው

አቶ ምሩጽ ወልዳይ– አሁን ያለው ሁኔታ ስኳር ኮርፖሬሽን ተረክቦ በራሱ ኃላፊነት እንዲሰራ ነው ያለው አቅጣጫ።

ሰንደቅ በግድቡ በመዘግየቱ ፕሮጀክቱ እንደዘገየ ገልጸውልኛል። አሁንም ግን ግድቡ ከፍተኛ መጠን ውሃ እያፈሰሰ ነው። ቀጣይ የሚገጥማችሁ ችግር አይኖርም?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ– ግድቡን በተመለከተ ዲዛይኑ ኳሊቲው እንዲሁም ቀሪ ሥራዎቹ ያልተጠናቀቁ አሉ። ኤልክትሮ ሜካኒካል ሲስተሙም ወደሥራ አልገባም። ውሃ መጨመር መቀነስ ብትፈልግ መቆጣጠር አትችልም። አካባቢው የእሳተ ጎሞራ ሲነሳበት የነበረ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የቀበርናቸው ፊዚዮሜትሪክ መቆጣጠሪያዎች አሉ። እነዚህ ወደ መሬት ውስጥ ሰላሳ ሜትር ተቆፍሮ የተቀበሩና ከግድቡ ጋር የተያያዙ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚለኩ የሚያሳውቁ መሳሪዎች በሲስተም ደረጃ ተጠናቀው ወደ መስመር አልገቡም።

ሶስት ትናንሽ ግድቦችም አሉ። ማስተንፈሻው ተጠናቋል ማለት ይቻላል። ውሃው ሊሄድባቸው የሚችሉ ቦታዎችም ተለይተው ተሰርተው አልተጠናቀቁም። ግድቡ ‘Earth Dam’ በመሆኑ በጠጠር የተሞላ ነው። ውሃውን በመገደቢያነት የተጠቀሙበት የተራራው አጠቃላይ ጂዖሎጂካል ነገሩን ስትመለከተው፣ አንድ ወጥ ድንጋይ አይደለም። በተራራዎቹ መሃል መሃል ላይ ቀይ አፈር የያዘ ክፍት ቦታዎች አሉ። እነዚህ ቦታዎች ፍሳሽ ለማሾለክ የተጋለጡ ናቸው። ከስር በኩል ላለው ክፍት ቦታ በግራውቲንግ ቴክሎጂ ተሰርቷል። የቀረው ግን ተሰርቶ አልተጠናቀቀም። አጠቃላይ በሆነ መልኩ አሁንም ፍሳሽ አለ። በተለይ ውሃው ሲሞላ ከፍተኛ መጠን ይኖረዋል። ፍሳሹ ወደፊት አደጋ ከመሆኑ በፊት በጣም ክትትል ይፈልጋል። ፍሳሽ በርግጥ ሊያጋጥም ይችላል። ከጎን እና ጎን የሚወጣ ፍሳሽ ግን አደገኛ ነው።

ሰንደቅ በእርሻው ውስጥ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። እንስሳዎችም አሉ። በአገዳ ጋሪ ማመላለሻ መንገዶችም ላይ በርካታ ፍየሎችና በጎች ሲተላለፉ ነው የሚታየው። ድርጅቱ ነፃ የእርሻ ዞን መመስረት እንዴት አልቻለም?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ– ሰዎችን ከአካባቢው አናስለቅቅም። የሚደረገው በተበታተነ ቦታዎች ያሉትን የአካባቢው ነዋሪዎችን በአንድ መንደር ውስጥ እንዲሰፍሩ ቦታዎችን በማስተካከል ማንቀሳቀስ ነው። መንደር ሰርተን ቤቶች ገንብተን፣ ት/ቤት ገንብተን ለማሕበራዊ አገልግሎት የሚሆኑ ቤቶችም ሰርተን በሳቡሬ አካባቢ ያሰፈርናቸው አሉ። ቀደም ብሎ የገነባናቸው ቤቶች የአካባቢው ሕብረተሰብ በሚኖረው መልክና መጠን የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ አልተቀበለውም። በእንጨት የተሰሩ በቀላሉ ንፋስ የሚወስዳቸው በጣም ጠባብ ቤቶች ናቸው የሚል ቅሬታ በመቅረቡ ቅሬታቸውን ተቀብለን ዘመናዊ ቤቶች ገነባን። ለቤቶቹ ግንባታ የወጣው ወጪ ከፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪዎች አንፃር በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኘ ስለተባለ መንግስት ውሳኔ ይስጥበት ተብሎ፣ የመንግስት ውሳኔ አገኘ።

የተሰጠው ውሳኔ ማሕበራዊ ተቋሞችን በመገንባት ሕብረተሰቡ እንዲሰባሰብ ማድረግ ነው። እንዲሁም አንድ ሔክታር ለአንድ አባወራ አልምቶ መስጠት። በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉብኝት በመጡ ወቅት የደቡብ ክልል ልምድ ነው ተብሎ አንድ ሔክታር አልምቶ እንደዚሁ ከመስጠት፤ አንድ አራተኛውን አትክልቶች እንዲያለሙበት እና ሶስት አራተኛውን በማሕበር ተደራጅተው አገዳ አልምተው ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ ተወሰነ። ከስምምነትም ተደረሰ። አሁን በዚህ የስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው ያለነው። አዲስ የመሬት አቅርቦት ሲገኝ ጎን ለጎን የአካባቢውን ሕብረተሰብ ጥቅም እየጠበቅን እየሰራን ነው። ይህም ማለት የመንግስት ይዞታ ይኖራል፤ የህዝቡም ይዞታ ይኖራል። ሌሎችንም ጉዳዮች ተመካክረን ነው የምናደርገው። ለምሳሌ የከሰም ቀበሌ የቱጋ ይሁን የሚለውን ከሕብረተሰቡ ጋር ተወያይተን ነው የምንወስነው። ስለዚህ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር ያለን የሥራ አቅጣጫ ከላይ እንዳስቀመጥኩት ነው። ከአካባቢው የሚለቁበት ሁኔታ አይፈጠርም።

ሰንደቅ ለእርሻ የምትጠቀሟቸው መሣሪያዎች የመለዋወጫ አቅርቦት ምን ይመስላል?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ– የማሽነሪ መለዋወጫዎች ውሉ ላይ የፋብሪካው ኮንትራክተር የቻይና ኮምፕላንት ነው የሚያቀርበው። ከግዢው ጋር በተገናኘ መጀመሪያ ማቅረብ የነበረበትን መለዋወጫ ኩባንያው አቅርቧል። የቀረበበት ጊዜ በራሱ ክፍተት አለው፤ የዘገየ ነበር። ግዢ ከተከናወነ በኋላ ያቀረበውም ማሽነሪዎች ላይ ክፍተት ነበረው። ኩባንያው ያቀረብኩት በውሉ መሰረት ነው የሚል መከራከሪያ ቢያነሳም፣ አንዳንዶቹ ማሽነሪዎች ከእኛ ሥራ ጋር የማይሄዱ ናቸው። ከኮርፖሬሽን ጋር በተደረገ ውይይት ቬክሎቹን እንዲለወጡ ተደርገዋል። ኩባንያው በዘመናዊ መሣሪያዎች ከስሮ እንዲተካ ተደርጓል።

ሌሎቹ ግን ለምሳሌ ገልባጮቹ ያቀረብኩት በተሰጠኝ ስፔሲፊኬሽን መሰረት ነው አለ። ወደ ሃያ ስድስት የሚሆኑት ገልባጮች እየሰሩ አይደለም። እስካሁንም መግባባት አልተቻለም። ከጥራት አንፃር የሚታዩ ችግሮች አሉ። ትራክተሮቹ የተወሰኑት ይሰራሉ፤ ሞዲፊኬሽንም የሚፈልጉ አሉ። ዋናው ችግር ግን መለዋወጫ ማግኘት አልቻልንም። ሀገር ውስጥ አቅራቢ የሌላቸው ማሽነሪዎች አሉ። ከአመረቷቸው ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራን እንገኛለን።

 

ሰንደቅ ከሰላሳ አመት በላይ በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደሰሩ ነግረውናል። ከሰም ፋብሪካን ከመሰረቱ እስከ አሁን ደረጃ የደረሰበትን ያውቃሉ። ከዚህ አንፃር መንግስት በያዘው የስኳር ልማት ስትራቴጂ ላይ ምን አስተያየት አልዎት? ከሰምን ጨምሮ እንዳይደገሙ የሚሏቸው የአሰራር ግድፈቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ– ይህንን ፕሮጀክት የመተሐራ ማስፋፊያ ተብሎ የተረከብነው በ1999 .. ነው። ከዚያ ቀጥሎ በ2004 .. ስኳር ኮርፖሬሽን ተብሎ በአዲስ መልክ ሲቋቋም በከሰም ፋብሪካ ሥር ፕሮጀክቱ ተጠቃለለ። የከሰም ግድብ ግን ቀደም ብሎ በ1996 .. ነው የተጀመረው።

ባይደገም የምንለው፤ ፕሮጀክት በባሕሪው ገደብ አለው። መነሻ አለው፤ መድረሻ አለው፤ የጊዜ ገደብ አለው። ለፕሮጀክት የሚመደብ በጀት መታወቅ አለበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ፕሮጀክት ለማስፈፀም ስትገባ አደገኛ ነው። ለምሳሌ አሁን ያለው ፕሮጀክት ገደብ አልነበረውም። ፕሮጀክቱ ወረቀታችን ላይ የጊዜ ገደብ ነበረው፤ በተግባር ግን የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አልነበረውም፤ በጣም የተለጠጠ ፕሮጀክት ሆኗል። ለዚህ ፕሮጀክት የተመደበው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? የወጣው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? ብሩስ ከወዴት ነው የሚገኘው? አሁን ለፕሮጀክቱ ገንዘብ ያስፈልጋል ገና ሃያ ሺ ሔክታር መሬት አቅርቦት ላይ መድረስ ይጠበቅብናል። የፕሮጀክት ምዕራፍ ላይ ሆኖ፣ ብድር መመለስ በጣም ከባድ ነው። እንደዚህ አይነት አሰራር በስኳር ፋብሪካ ልማቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎች የፕሮጀክት ሥራዎች ላይ መደገም የለበትም።

በእቅድ አለመመራት የሚያመጣው ክፍተት በፍጥነት መስተካከል አለበት። የኮንትራት አድሚኒስትሬሽን አቅም በጣም ከፍ ባለ ደረጃ ማደግ አለበት። አለበለዚያ የሚመጣው ገንዘብ በብድር የሚገኝ በመሆኑ፣ በእቅድ ስለማይሰራ የብድር ገንዘቡ ያልቃል፤ ሥራዎች ግን አያልቁም። ስለዚህ የብድር አዙሪት ውስጥ መዞር መቆም አለበት። ልማት እንደዚህ አይሰራም። ልማት ምላሹ ተሰልቶ ነው የሚሰራው፤ ለሌሎችም እንዲተርፍ ይደረጋል። በወረቀት ላይ የሰፈረ እቅድ እንደሌለ ተደርጎ በሕብረተሰቡ ሲነገር እንሰማለን። እውነቱ ግን በወረቀት ላይ ታሳቢ የሚደረጉ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉም ሰፍረው ነው ያሉት፤ ችግሩ በእቅዱ መሰረት ማስፈጸም ነው። ለምሳሌ የከሰም ግድብ በእቅዱ መሠረት ባለማለቁ ስንት ከፍተኛ ሚኒስትሮችን ያፈራረቀ ግድብ ነው። በሚደረጉ ለውጦች የሚፈጠሩ ክፍተቶች መኖራቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው። አሁንም የሔድንባቸውን መንገዶች ለማስተካከል ብዙ ሥራዎች ያስፈልጋሉ።

ስንደቅ