Wednesday, 21 June 2017 14:19

ጋዜጣው ሪፖርተር 

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሥራም ሆነ በተለያዩ ምክንያት በሳዑዲ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች በ90 ቀናት ሀገሩን ለቀው እንዲወጡ፣ ይህ ካልሆነ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የሰጠው የማስጠንቀቂያ ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ሰባት ቀናት የቀሩት ቢሆንም አብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ለመመለስ አለመመዝገቡ ተሰማ። የሳዑዲ መንግሥት ከመጋቢት 21 ቀን 2009 .ም ጀምሮ ባሉት 90 ቀናት በሕገወጥ መንገድ በሀገሩ የሚኖሩ የማናቸውም ሀገር ዜጎች ሀገሩን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ የሚታወስ  ሲሆን የፊታችን ሰኔ 21 ቀን ቀነ ገደቡ ይጠናቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንኑ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹ በሠላም ሳዑዲን ለቀው እንዲወጡ የሚያግዝና የሚከታተል በምክትል ጠ/ሚኒስትር የሚመራ ግብረሃይል በማቋቋም፣ አስፈላጊ የጉዞ ሰነዶች እንዲመቻቹላቸው በማድረግ፣ በመቀስቀስ፣ ለተመላሾች ከቀረጥ ነጻ ንብረቶቻቸውን እንዲያስገቡ በመፍቀድ፣ የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ ላይ ቅናሽ በማድረግ በፍጥነት የተንቀሳቀሰ ሲሆን በአንጻሩ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ አለመሆኑ አሳሳቢ ሆኗል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው እስካለፈው ሳምንት መጠናቀቂያ  ድረስ ወደሀገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው እየተመለሱ ያሉ ወገኖች ቁጥራቸው ከ83 ሺ ገደማ ነው። ይህ ቁጥር በሳዑዲ ዓረቢያ ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመቱ ከ200 ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ተብሏል።

አንዱና ዋናው ችግር በውጭ ያሉት ወገኖች በተለያየ መንገድ ወጥተው በመስራት በሀገር ቤት ያሉ ወገኖችን በፋይናንስ የሚደግፉበት ሁኔታ መኖሩ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከሳዑዲ ለቅቆ መውጣት ገቢን ያስቀራል በሚል ፍርሃት ዝም ብሎ የሚሆነውን መጠበቅ የመረጡ ወገኖች የበዙ መስሏል ብሏል። ኢትዮጽያዊያኑ የማስጠንቀቂያው ቀነ ገደብ አልፎ ለእስርና እንግልት ከመዳረጋቸው በፊት ወይንም ቀነ ገደቡ ከደረሰ በሃላ ከመሯሯጥ አስቀድመው ለመውጣት ቢጥሩ መልካም መሆኑን መክሮ በሳዑዲ የሚኖሩ ወገኖች ቤተሰቦችና ወዳጆች ከምንም በላይ ጉዳዩ እንደሚመለከታቸው በመገንዘብ ችግሮች ከመሰከሰታቸው በፊት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት አሳስቧል።