21 Jun, 2017

ዘመኑ ተናኘ

ኤርትራና ጂቡቲ በመካከላቸው ባለውና ዱሜራ እየተባለ በሚጠራው ተራራማ ደሴት ላይ ለዘመናት ሲወዛገቡ ቆይተዋል፡፡ ይህ በቀይ ባህር ጠረፍ ዳርቻ የሚገኘው ተራራማ አካባቢ ለወታደራዊ ዓላማ ካለው ፋይዳ የተነሳ፣ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ጊዜያት ሲነታረኩበት ቆይተዋል፡፡ ዱሜራ ወይም ራስ ዱሜራ እየተባለ የሚጠራው ሥፍራ ከቀይ ባህር የሚነሳና ዙሪያውን በውኃ የተሸፈነ ደሴት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኤርትራና ጁቡቲ በዚህ የድንበር አካባቢ አማካይነት ከሁለት ጊዜ በላይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ማሳለፋቸውን የሁለቱ አገሮች የታሪክ ማኅደር ያስረዳል፡፡

እጅግ አነስተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ሁለቱ አገሮች የወደብ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ኤርትራ የምፅዋና የአሰብ ወደቦች ባለቤት ነች፡፡ ጂቡቲ ደግሞ የዶራሌ፣ የጂቡቲና የታጁራ ወደብ ባለቤት ነች፡፡ ሁለቱ አገሮች ተፈጥሮ ከሰጣቸው አቀማመጥ የተነሳ ለወታደራዊ ዓላማና ለንግድ ሥራ ተፈላጊ ናቸው፡፡ የሁለቱ አገሮች ከቀይ ባህር ጋር በቀጥታ መገናኘት ደግሞ የተፈላጊነታቸውን መጠን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ አካባቢ የዓለም ሕዝብ በተለይም የዓረብና የአውሮፓ አገሮች ዓይን ማረፊያ ነው፡፡

አውሮፓውያን አፍሪካን በቀኝ ግዛት ለመከፋፈል ዕቅድ ሲወጥኑ በጂቡቲና በኤርትራ በኩል ያለውን አካባቢ ለመቆጣጠር የነበራቸው ፍላጎትና የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ የሁለቱ አገሮች ተፈላጊነት ከፍ ያለ መሆኑን ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ጣሊያን ቀይ ባህር የሚያዋስነውን አካባቢ ለመያዝ ያደረገችው እሽቅድምድም ከፍተኛ እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ አውሮፓዊቷ አገር ፈረንሣይ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በጂቡቲ በኩል ያለውን አካባቢ ለመቆጣጠር ወታደራዊ ቤዟን በዚህ አካባቢ በማሥፈርና መሠረት በመያዝ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ግዛቷን ለማስፋፋት ያደረገችው ሙከራ፣ ለዚህ ቦታ ተፈላጊነት ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ እነዚህ አውሮፓዊ አገሮች በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የሚያዋስነውን ግዛት በተመለከተ እ... 1935 ስምምነት አድርገዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረትም ይህንን አካባቢ ከወታደራዊ ቀጣና ነፃ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

... 1996 ኤርትራ ዱሜራ አካባቢ ጦሯን በማሠለፍ ከጂቡቲ ጋር ወደ ጦርነት ገብታለች፡፡ ጉዳዩን ጂቡቲ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ብታቀርብም ዘላቂ መፍትሔ ሳይሰጥ እንደቀረ ይነገራል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ጉዳዩ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ከፍተኛ ሥጋት እንደሆነ አመልክተው በአስቸኳይ መፈታት እንዳለበት አሳስበው ነበር፡፡ እ... 2004 በሁለቱ አገሮች መካከል በነበረው ግጭት 44 ያህል የጂቡቲ ወታደሮች ሲገደሉ ከ55 በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንደቆሰሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በኤርትራ በኩል ደግሞ 100 ያህል ወታደሮች ተገድለዋል፣ 100 ወታደሮች ተማርከዋል፣ 21 ያህሉ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ በወቅቱም የጂቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ፣ ‹‹ሁሌም ወዳጆች ነበርን፡፡ አሁን የራሳችንን መሬት በጉልበታቸው ለመውረር መጡ፡፡ እኛ ደግሞ ተገቢውን ዕርምጃ ወስደናል፤›› ብለው ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱ የአሜሪካ የመከላከያ ኃይል ደኅንነት ኤጀንሲ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ጂቡቲ 18,000 ያህል ወታደሮቿን ለጦርነቱ ዝግጁ ስታደርግ፣ ኤርትራ በበኩሏ ከ200,000 በላይ አዘጋጅታ ነበር፡፡

ለብዙ ዓመታት ያህል በፈረንሣይ እጅ የቆየችው ጂቡቲ በኤርትራ ጦርነት ሲታወጅባት ቅድሚያ ከጎኗ ከተሠለፉ አገሮች መካከል ፈረንሣይ አንዷ እንደነበረች ተጠቁሟል፡፡ የፈረንሣይ መንግሥት ለጂቡቲ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡

የኤርትራ መንግሥትን የጂቡቲ ወረራ ለማስቆም ጣልቃ ከገቡ የዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ቀዳሚው የዓረብ ሊግ ነው፡፡ ኤርትራ ከአውሮፓ አገሮች ጋር ባላት የቆየ ጥላቻ በሁለቱ አገሮች መካከል ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን የድንበር ግልግል አውሮፓውያን እንዳያዩት ኤርትራ ያደረገችው ጥረት ከፍተኛ እንደነበር የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡

በመርህና በፖሊሲ ደረጃ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የተለየ አቋም ይዞ ብቅ ያለው የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ኤርትራንና ሕዝቦቿን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጧል፡፡ በዚህም የተነሳ ፊቱን ወደ ዓረብ አገሮች በማዞር ሳዑዲ ዓረቢያ በምትዘውረው የገልፍ አገሮች ስብስብ ታዛቢ አባል ከመሆን ባሻገር፣ በአገሪቱ የዓረብኛ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡

ኢሳያስ አፈወርቂ መራሹ የኤርትራ መንግሥት፣ በአገሪቱ አንድም ቀን ምርጫ ሳያካሂድ ከሃያ ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ ቆይቷል፡፡ የቀይ ባህርን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ፊታቸውን ወደ ኤርትራ ካዞሩ የዓረብ አገሮች መካከል ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅና ኳታር ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የዓረብ አገሮች በቀጣናው ለመስፋፋትና ወታደራዊ ይዞታ ለማግኘት ሲሉ ኤርትራን በአንድም ሆነ በሌላ ሲረዷትና ሲደግፏት እንደቆዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዓባይ ወንዝ ጋር ለብዙ ዘመናት እሰጥ አገባ ውስጥ የቆየችው ኢትዮጵያም ጉዳዩን በአንክሮ ስትከታተለው እንደቆየችና አሁንም ድረስ እየከታተለችው ለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ ራሳቸውን የቻሉ ሉዓላዊ አገሮች ቢሆኑም፣ በወዳጅነት መዝለቅ የቻሉት ግን ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ኤርትራ በዱሜራ ግዛት ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ወረራ እንደምታካሂደው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ግዛት በሆኑት በባድሜና ሽራሮ ላይም ወረራ በማካሄድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር ሞክራለች፡፡

1990 .. የተጀመረው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በሁለቱ አገሮች መካከል በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የሰው ሕይወትና በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል፡፡ የኤርትራ ጠብ አጫሪነትን በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ሁከትና ብጥብጥ እንዲኖር እየሠራች ነው ሲል፣ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሳይቀር ወንጅሏታል፡፡ ድርጅቱ ከውንጀላም አልፎ ማዕቀብ ጥሎባታል፡፡ ማዕቀቡ እስከዛሬ ድረስ ያልተነሳለት በመሆኑ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰባት ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ባለበት ጊዜ፣ ከጂቡቲ ጋር ወደ ሌላ ጦርነት ለመግባት እየተዘጋጀች እንደሆነ ሰሞኑን ተነግሯል፡፡  

በጂቡቲና በኤርትራ መካከል የነበረውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት በቦታው ተሰይመው የነበሩ የኳታር ወታደሮች ከሳምንት በፊት አካባቢውን ለቀው ሲወጡ፣ ኤርትራ ወታደሮቿን በአካባቢው እንዳሠለፈች የጂቡቲ መንግሥት አስታውቋል፡፡

የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ከኳታር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ካቋረጡ በኋላ፣ ኳታር ወታደሮቿን ከጂቡቲና ኤርትራ ድንበር አስወጥታለች፡፡ የኳታር መንግሥት አሸባሪዎችን ይረዳል ተብሎ ሲወነጀልና ሲከሰስ ቆይቶ ኢራን ከገልፍ አገሮች ስብስብ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ የኳታር መንግሥት በመገለሉ ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል ዋነኛው ጉዳይ ወታደሮቹን ከሁለቱ አገሮች ድንበር ማስወጣቱ እንደሆነ በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ወታደሮቹን ለማስወጣት የወሰነው ደግሞ የኤርትራ መንግሥት ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጎን መሠለፉን ባስታወቀ ማግሥት እንደሆነ አስረድቷል፡፡

ኢትዮጵያን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለመጉዳትና የተለመደ የጠብ አጫሪነት አባዜውን ለመወጣት ሁሌም ሳዑዲ ዓረቢያንና ግብፅን ተከትሎ እንደሚሄድ የሚነገርለት የኤርትራ መንግሥት፣ በቀጣናው የበላይ ሆኖ ለመታየትና የተለመደ የማተራመስ አጀንዳውን ለማራመድ ሲል የአሰብ ወደብን ለሳዑዲ መራሹ ኃይል ከማከራየት ጀምሮ የግብፅ መንግሥት በወደቡ አካባቢ ወታደራዊ ቀጣና እንዲኖረው እያደረገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

... ሰኔ 24 ቀን 2008 የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኒውዮርክ የጂቡቲው ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ዳይሌታና የኤርትራው አምባሳደር በተገኙበት ሁለቱን አገሮች በሚያወዛግባቸው ዱሜራ ጉዳይ ላይ ስብሰባ አካሂዶ ነበር፡፡ ከወራት በፊት ጉዳዩን እንዲያጠራ ተልኮ የነበረው የፀጥታው ምክር ቤት አጣሪ ኮሚቴም በዱሜራ አካባቢ ለጦርነት ዝግጁ የሆነው የኤርትራ ጦር ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ከፍተኛ ሥጋት እንደሆነ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ጅቡቲ ወታደሮቿን ከአካባቢው ብታስወጣም፣ የኤርትራ መንግሥት እንቢ እንዳለ ለምክር ቤቱ ቀረበ፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት እ... ጥር 14 ቀን 2009 ባካሄደው ስብሰባ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ይህ ውሳኔ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ‹‹ቁጥር 1862›› እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፣ የኤርትራ መንግሥት በአምስት ሳምንታት ውስጥ ጦሩን ከአካባቢው እንዲያስወጣ ውሳኔ የሰጠ ነው፡፡

ከፀጥታው ምክር ቤት ጋር ብዙም የማትጣጣመው ኤርትራ ውሳኔውን ወደኋላ በመግፋት ለጦርነት ዝግጁ ሆና እንደነበርም በወቅቱ ተገልጿል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች ዘዋሪነት ይንቀሳቀሳል በማለት የምትወነጅለው የፀጥታውን ምክር ቤት ውሳኔ ኤርትራ ሳትቀበለው ቀርታለች፡፡ ገና ወደ ሥልጣን ሲመጣ ጀምሮ ለአሜሪካና አውሮፓ አገሮች ብዙም ፊት ያልሰጠው የኤርትራ መንግሥት፣ ራሱን ለተሻለ ጦርነት ዝግጁ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የጂቡቲ መንግሥት በወቅቱ አስታውቋል፡፡

የኋላ ኋላ የአፍሪካ ኅብረትን ይሁኝታ አግኝቶ ወደ አደራዳሪነት የመጣው የኳታር መንግሥት በኤርትራ በኩል ተቀባይነት ለማግኘት ችሏል፡፡ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ ከስምንት ዓመት በላይ በኤርትራ ታስረው የነበሩ የጂቡቲ ወታደሮችን በማስለቀቅ እርቀ ሰላም ማምጣት የቻለው የኳታር መንግሥት፣ እ..አ ከ2010 ጀምሮ በሁለቱ አገሮች ድንበር መካከል 400 ያህል ወታደሮቹን አሰማርቶ ቆይቷል፡፡

ለዓረብ አገሮች ጆሮው እንደሚከፈት የሚነገረው የኤርትራ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ በመስማማት ጦሩን ከአካባቢው ለማስወጣት ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር፡፡ እ... ከሰኔ 10 ቀን 2010 ጀምሮ በሥፍራው የነበረው የኳታር ጦር ግን ባለፈው ሳምንት አካባቢውን ለቆ ወጥቷል፡፡

አልሸባብንና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችን እንደሚረዳ ተደርሶበት ማዕቀብ የተጣለበት የኤርትራ መንግሥት፣ ከኳታር ጋር የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኑነት እንዳቋረጠ ሰሞኑን የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከግብፅ መንግሥታት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያገኝ የሚነገርለት የኤርትራ መንግሥት፣ ከኳታር ጋር ገንብቶት የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት መቋረጡን ኳታር ይፋ አድርጋለች፡፡

በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ሥጋት እየሆነ የመጣውን አልሸባብ በመደገፍና በማስታጠቅ ቀጣናውን በተለይም ኢትዮጵያንና ጎረቤት አገሮችን ለማተራመስ ሌት ከቀን እንደሚሠራ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በተደጋጋሚ ጊዜ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ አሁንም ድረስ ከድርጊቱ መቆጠብ እንዳልቻለ የሚነገርለት የኤርትራ መንግሥት፣ ከጂቡቲ ጋር ተፋልሞ የግዛት ማስፋፋት ምኞቱን ለማሳካት እየሠራ እንደሆነ ሚስተር ፓወፒ ራውኒ የተባሉ በኡጋንዳ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ለፍራንስ 24 የእንግሊዝኛው ጣቢያ ተናግረዋል፡፡ ፓወፒ እንደሚሉት የኤርትራ መንግሥት የማተራመስ ተግባሩን የጀመረው ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህ ድርጊቱን በማስፋፋት አልሻባብን እየረዳና እየደገፈ ለአቅም አዳም እንዳደረሰው ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ደግሞ ለሌላ ጦርነት ከጂቡቲ ጋር እንደተጫጨ ገልጸዋል፡፡

ከስድስት ሚሊዮን የማይበልጥ የሕዝብ ቁጥር ይዞ የግዛት ማስፋፋት ምኞት ያለው የኤርትራ መንግሥት መከታ የሚያደርገው የባህረ ሰላጤው አገሮችን እንደሆነ በቅርቡ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከወታደራዊ ሎጂስቲክስ ጀምሮ ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮችን ከዓረብ አገሮች እንደሚያገኝ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያን ከፊቱ፣ ግብፅን ደግሞ ከጎኑ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ እየተነገረ ያለው የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት፣ እነሱ በጉንፋን ከተያዙ እሱም ተይዞ ያድራል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡    

ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነትም ሆነ ሰላም በሌለበት ቀጣና ውስጥ መኖር ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አፍኖ በመውሰድ የጉልበት ሥራ ከማሠራት ባሻገር፣ በእስር እያንገላታ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ተገልጿል፡፡ ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል በማዕድን ቁፋሮ ተሰማርተው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን አፍኖ በመውሰድ ከፍተኛ የሆነ ብዝበዛ አድርሶባቸው እንደነበር ታፍነው ተወስደው የተመለሱ ዜጎች ተናግረዋል፡፡

2009 .. ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ክልል ገብቶ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን አፍኖ ለመያዝና ጥቃት ለማድረስ ያደረገው ሙከራ ይታወሳል፡፡ በዚህም የተነሳ ለአንድ ሳምንት ያክል በሁለቱ አገሮች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ይህን የመሰለ ግንኙነት ያላት ኤርትራ ሰሞኑን ደግሞ ፊቷን ወደ ጂቡቲ አዙራለች፡፡ የጂቡቲን ሉዓላዊነት በመድፈር በቀይ ባህር አካባቢ ወሳኝ የሆነውን የባቤል መንደብ ለመቆጣጠር ሙከራ እያደረገች እንደሆነ የጂቡቲ መንግሥት አስታውቋል፡፡

በዚህ አካባቢ ተፅዕኖ ፈጣሪ መስሎ መታየት የኤርትራ ባህሪ ነው የሚሉት የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣ በአገሩ ሕዝብ ላይ ድንበሩ እንደተወረረ ወሬ በመንዛት ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ መቆየት የሚፈልግ መንግሥት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የኤርትራ በጂቡቲ ግዛት ላይ አዲስ ወረራ ማካሄድ ለኢትዮጵያ ቀጥተኛ የሆነ ተፅዕኖ እንደሌለው የሚናገሩት ይልቃል፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት የሚለው በአልጀርሱ ይግባኝ የለሽ ውሳኔ ያገኘሁትን መሬትን ኢትዮጵያ ቀምታኛለች፡፡ ይህንን ደግሞ ያደረገችው ምዕራባውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመሆናቸው ነው የሚል እምነት አለው፤›› ብለዋል፡፡

የዲስኮርስ መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ዳደ ደስታ ግን የኤርትራ በጂቡቲ ግዛት ወረራ ማካሄድ ለኢትዮጵያ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ አቶ ዳደ ሲያብራሩ የኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከቆመ ወዲህ ኢትዮጵያ የጂቡቲን ወደብ እንደምትጠቀም፣ ይህ ወደብ በተለይም ፖታሽ ይመረትበታል ከተባለው የታጁራ ወደብ ጋር በቅርብ ርቀት ያለ በመሆኑ በኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ላይ ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ ሰሞኑን ኤርትራ እንደያዘችው የሚጠቀሰው የባቤል መንደብ ደግሞ ለእነዚህ ወደቦች ቅርብ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ያለውን ቀጥተኛ ተፅዕኖ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ አካባቢ በጣም ከፍተኛ ቦታ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ቀይ ባህር አካባቢ አሻግረን ስናይ በዙሪያው ያሉ ብዙ ቦታዎችን ለማየት የሚያስችል ስፍራ ነው፤›› ያሉት አቶ ዳደ፣ ይህንን አካባቢ መያዝ ማለት ክፉ ዓላማ ላለው ኃይል በጣም ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አካባቢው በጣም ብዙ የንግድ መርከቦች የሚተላለፉበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ባይኖራትም የቀይ ባህር ኃይል እየተባለች የምትጠራ አገር ነች፡፡ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ያላት ተሰሚነትና ኃያልነት ዘላቂ ሊሆንና ሊረጋገጥ የሚችለው በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን መዳረሻ ለሌሎች አገሮች መናኸሪያ እንዳይሆን ስትጠብቅና ስትከላከል እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ስትራቴጂካዊ አካባቢ ወደ እንደዚህ ዓይነት የሥጋት ቀጣና መሸጋገሩ ለኢትዮጵያ እንቅልፍ የሚነሳና የሚያናድድ ጉዳይ እንደሆነ አቶ ዳደ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳዮች ስትራቴጂ ጥናት ተቋም ውስጥ የጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ አበበ ዓይነቴ በበኩላቸው፣ ጉዳዩን የአፍሪካ ኅብረት የያዘው ከመሆኑ ባሻገር የኤርትራ መንግሥት እንደከዚህ ቀደሙ በማናለብኝነት ስሜት የሄደበት ባለመሆኑና ጉዳዩን ለማጥናት ፈቃደኝነቱን በማሳየቱ፣ የዚያን ያህል የከፋ ጉዳት በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ሊያስከትል እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡

የተለያዩ ባለሙያዎችና አስተያየት ሰጪዎች የኤርትራ በጂቡቲ ግዛት ወረራ ማካሄድ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ለብዙ ዓመታት ለኢትዮጵያ ጋሬጣ ሆና ስታስቸግር የነበረውን የኤርትራ መንግሥት ከጂቡቲ ጋር በመተባበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሥልጣን ማስወገድ ተገቢነት ላይ ሲከራከሩ ተደምጧል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ይህንን ይበሉ እንጂ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት አገር ብትሆንም በአገር ውስጥ ያልተረጋጋ ነገር ያላት በመሆኑ ወደዚህ ጉዳይ የምትገባ ከሆነ ብዙ ጣጣ ይዞባት ሊመጣ እንደሚችል ኢንጂነር ይልቃል ያስረዳሉ፡፡ አቶ ዳደ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር አብራ ኤርትራን ወደ መውጋት ከመግባቷ በፊት የተለያዩ ጥናቶች መሥራት እንደሚገባት ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ወደዚህ ብትገባ ልታገኘውና ልታጣው የምትችለው ጉዳይ፣ ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ በቀጣናው ያለው አሠላለፍና ሌሎች ዝርዝር ነገሮች መታየት እንደሚገባቸው ይገልጻሉ፡፡ አቶ አበበ ደግሞ ጉዳዩ ወደዚህ የሚያስገባ እንደማይሆን ያምናሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረትና የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን የያዙት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የኤርትራ የተለሳለሰ አቋም መኖር ችግሩ በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚችል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ መሠረት ሁለቱ አገሮች ተቀራርበው ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት እንዳለባቸው ይፋ አድርጓል፡፡ ችግሩንም ኢትዮጵያ በቅርብ እየተከታተለች እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህንን ጉዳይ በቅርበት ለመከታተልና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሲባል ኮማንድ ፖስት እንደተቋቋመ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተገለጸ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ መግለጫም ሆነ አስተያየት እስካሁን የለም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት የልዑካን ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሥፍራው እንደሚልክ አስታውቋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ተቀራርበው በመነጋገር መፍታት እንደሚባቸው ተናግሯል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ የፀጥታው ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2009 .. በዝግ ስብሰባ እንደሚመክርበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኳታር ከቀጣናው መውጣት ማግሥት ጀምሮ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ደፋ ቀና ሲል እንደታየ የሚነገርለት የኤርትራ መንግሥት ፀረ ምዕራባዊያን አቋሙን አሁንም እንዳላቆመ እየተነገረ ነው፡፡ የሰሜን ኮሪያ ፀረ ምዕራባዊ አመለካከት ከኤርትራ ጋር ወዳጅ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚረዳው ተነግሯል፡፡

ኳታር ጦሯን ከቀጣናው ማስወጣትና ጂቡቲ በኤርትራ ተወርሬያለሁ የማለቷን ውንጀላ በተመለከተ የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ እስካሁን ድረስ ኳታር ከቀጣናው ለምን እንደወጣች ለማወቅ እንዳልቻለና የጂቡቲን ወቀሳም ረጋ ብሎ በማጥናት ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በሌሎች ጉዳዮች ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ የሁለቱን አገሮች ችግር ለመፍታት ከባድ እንደማይሆን ኢንጂነር ይልቃል ይገልጻሉ፡፡ በሁለቱ አገሮች ላይ ሕዝቡ የመወሰን መብት ኖሮት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በሁለቱም አገሮች ከተመሠረተ ያለውን ችግር መፍታት እንደሚቻል ቢገልጹም፣ አቶ ዳደ ግን በኤርትራ በኩል ያለው የሰላም አማራጭ ዝግ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥት ከአሁን በኋላ ወደ ሰላማዊ መንገድ መጥቶ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም ይላሉ፡፡ መፍትሔው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ እጅ እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት በመሆኗ፣ ጂቡቲ ደግሞ በሕዝብ ቁጥርም ሆነ በቆዳ ስፋት ትንሽ በመሆኗ ሁለቱን አገሮች የመነካካት፣ የማጨናነቅና አሸንፋለሁ የሚል ስሜት በኤርትራ በኩል እንዳለ አቶ ዳደ ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ዓይነት የኤርትራ ሐሳብ ግን ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መዝጋት እንዳለባት ያሳስባሉ፡፡

ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ኳታር የለቀቀችውን ሥፍራ የግብፅ ወታደሮች ሊይዙት ይችላሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ጂቡቲ ልትቀበለውም ላትቀበለውም እንደምትችል የገለጹት አቶ ዳደ፣ ግብፅ በጣም ጠባብ የሆነውንና ከሜድትራኒያን ወደ ቀይ ባህር የሚሻገረውን የስዊዝ ካናል የምታስተዳድር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ይህንን አካባቢ የማስተዳደር ዕድል ካገኘች ልትፈጥረው የምትችለው ወታደራዊ ኃይልና ሊኖራት የሚችለው ስትራቴጂካዊ ቦታ ኃያል ሊያደርጋት እንደሚችል አቶ ዳደ ይናገራሉ፡፡ ግብፅ ይህንን ማድረግ ቻለች ማለት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሥጋት ከማስወገድ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ኃያልነቷን ልታጣ እንደምትችል አቶ ዳደ ይስማማሉ፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅ በነበሩበት ጊዜ ኤርትራ ከሁለቱ ወደቦች በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከኢትዮጵያ ገቢ ታገኝ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን ያህል ፀጋ አጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ጦርነት የገባችው ኤርትራ፣ ከአሁን በኋላ ግማሽ መንገድ መጥታ ልትደራደር እንደማትችል እየተገለጸ ነው፡፡

በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ የማተራመስ ተልዕኮ እንዳለው የሚነገርለት የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት፣ የአገሬውን ሕዝብ ከጎረቤት አገሮች ጋር በማቆራረጥና በማለያየት እየሠራ ካለው ባሻገር እጁን ለሰላም የማይዘረጋ በመሆኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በኃይል መነሳት እንዳለበት የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ ሊከተለው የሚችል አዲሱ ፖሊሲ እየተጠበቀ ነው፡፡

የኳታር ጦር ከአካባቢው መውጣት ተከትሎ በጂቡቲ ግዛት ጦሩን እንዳሰፈረ የሚነገረው የኤርትራ መንግሥት፣ በአንድም በሌላም የኢትዮጵያን መንግሥት ለማዳከም ብሎ የወሰደው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በጂቡቲና በታጁራ በወደብ የሚጠቀመው የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ዕድል እንዲያጣ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ለማዳከም ዕርምጃውን እንደወሰደ ግምታቸውን የሚናገሩ አሉ፡፡

ግንኙነታቸውን ያቋረጡት የባህረ ሰላጤውን አገሮች በማደራደር ኩዌት እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ሰኔ 12 ቀን 2009 .. ወደ ኩዌት ያቀኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (/) አድንቀዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የበኩሏን ማበርከት እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡ የኩዌት አሚር በበኩላቸው የባህረ ሰላጤው አገሮች ልዩነት ከአገሮቹ አልፎ በሌሎች አገሮች ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ፣ በቶሎ ሊፈታ እንደሚገባውና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ቀዳሚ ሆና እየተንቀሳቀሰች መሆኗን አድንቀዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለኩዌት አሚር የላኩትን መልዕክት አስረክበዋል፡፡

ሰሞነኛው የኤርትራና የጂቡቲ ጉዳይ ተፅዕኖው ከሁለቱ አገሮች ባለፈ በሌሎች ጎረቤት አገሮች በተለይም ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በብዙዎች እየተነገረ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ሰሞነኛ እሰጥ አገባ በአንክሮ በመከታተልና አሠላለፏን በማሳመር፣ ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚገባት አስተያየት ሰጪዎች ይስማማሉ፡፡

Author

anon