June 22, 2017

ስዩም ተሾመ

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በጀርመንና ኦስትሪያ የቀኝ-አክራሪ ብሔርተኞች ከእነሱ በስተቀር ሌላ ማንም ትክክል ሊሆን አይችልም በሚል ፅንፍ ረገጡ። ራሳቸውን ከሰው ዘር ሁሉ “ምርጥ” መሆናቸውን ለራሳቸው መሰከሩ። በመጀመሪያ ከሁሉም የተሻሉ ምርጦች መሆናቸውን ደጋግመው ለፈፉ። ቀጠሉና እነሱ ከሌሎች ሁሉ የተሻሉ ምርጦች ስለሆኑ ሌሎች ደግሞ ከእነሱ እኩል ምርጦች ሊሆኑ እንደማይችሉ ማሰብ ጀመሩ። እንዲህ እያለ ሄዶ በመጨረሻ ከምርጦች መሃል ተመራጮችን ለይተው አወጡ። በመጨረሻ ሰብዓዊ ክብራቸውን ከፍፈው በዓለም ታሪክ አሰቃቂ የሆነውን የዘር-ማጥፋት ፈፀሙ።

አክራሪ ብሔርተኞች ከመጨረሻው የሞራል ዝቅጠት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያደረጉት ነገር ቢኖር ከእነሱ እስተሳሰብ ጋር አብሮ የማይሄድ፣ ፅንፍ አክራሪነትን የሚቃወም ፅንሰ-ሃሳብ ያላቸው መጽሃፍትን ሰብስቦ ማቃጠል ነው። በወቅቱ ሁኔታውን የታዘበው የስነ-ልቦና ልሂቁ ሲግመንድ ፍሮይድ፤ “በጣም ተሻሽለናል…ኧረ በጣም ተሻሽለናል! ድሮ ድሮ ፀኃፊዎችን ነበር የምናቃጥለው! ዛሬ ግን መፅሃፍቶቻቸውን እያቃጠልን ነው” ብሎ ነበር። በእርግጥ ይሄ መሻሻል ከሆነ እኛም በጣም ተሻሽለናል። ደርግ ፊደል የቆጠረን ሁሉ መንገድ ላይ በጥይት ዘርሮ ይፎክር ነበር። ኢህአዴግ ደግሞ ፊደል የፃፈን እስር ቤት አስገብቶ ሰብዓዊ ክብሩን ይገፈዋል። ከዚህ አንፃር በጣም ተሻሽለናል!

ሲግመንድ ፍሮይድ የስነ-ልብና ተመራማሪ (psychoanalyst) ነበር። ከዚህ ጋር የተያያዘ ደግሞ የታሪክ ስነ-ልቦና “Psychohistory” የሚባል የጥናት ዘርፍ አለ። የዚህ ዘርፍ ግንባር ቀደም ተመራማሪ የሆኑት እንደ “Hans Meyerhoff” and “H. Stuart Hughes” ያሉ ምሁራን እንደሚሉት ታሪክ (history) እና የስነ-ልቦና ምርምር (psychoanalysis) በአስገራሚ ሁኔታ ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ ግብ ነው ያላቸው። ለምሳሌ፣ David E. Stannard” የተባለው ፀኃፊ “Shrinking History” በተሰኘ መፅሃፉ ገፅ 45 ላይ የታሪክና የስነ-ልቦና ምርምር ግብን “to liberate man from the burden of the past by helping him to understand that past” በማለት ይገልፀዋል።

ከላይ እንደተጠቀሰው የታሪክ እና የስነ-ልቦና ምርምር ግብ መሆን ያለበት ሰውን ስላለፈው ግዜ እንዲያውቅ በማድረግ በአመለካከቱ ውስጥ የተቀረፀውን ጠባሳ ማስወገድ ነው። በቀድሞ ታሪክ በተፈፀመ በደልና ጭቆና በግልና በማህበራዊ ስነ-ልቦናችን ላይ ያሳረፈውን ጠባሳ መፋቅና ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተሳነን ጤናማ የሆነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም። የታሪክ ጠባሳን ዘወትር እያወሳን፤ መጥፎ-መጥፎውን በሌሎች ላይ እየለጠፍን፥ ስለራሳችን በጎ-በጎውን እያሰብን፣ የሌሎችን ጥፋት እየዘከርን የራሳችንን ጥፋት ከዘነጋን፣ ሌሎችን ለሁሉም ነገር ተጠያቂ፥ እኛ ደግሞ በሁሉም ነገር ተጠቂ አድርገን የምናስብ ከሆነ፣ እውነታን ማየት፥ ማስተዋል ይሳነናል፣ የሌሎችን መከራና ስቃይ መገንዘብ ይከብደናል። በቀድሞ ታሪክ በእኛ ላይ የተፈጸመውን በደልና ጭቆና ዳግም በሌሎች ላይ እየፈፀምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ቀርቶ በትንሹ እንኳን መገመት ይሳነናል።

ያለፈ ታሪክ የወደፊት ተስፋችንን ማጨለም የለበትም። የታሪክ ጠባሳን እያሰብን ዛሬ ሌሎችን ማቁሰል የለብንም። የዛሬ ቁስል ነገ ላይ ሌላ ጠባሳ ይፈጥራል። የትላንት ቁስል እያከክን ዛሬ ላይ ያቆሰልነው ሰው ነገ በተራው ቁስሉን እያከከ ሊያቆሰለን ይመጣል። ያኔ ዛሬ ላይ እኛ ያላደረግነውን ነገ ላይ ሌሎች እንዲያረጉት መጠበቅ የዋህነት ነው። ዛሬ ላይ በጥፋቱ ሳይሆን ያለፈ ታሪክ እየቆጠርክ የዘራህው ቂም ነገ ላይ በቀል ሆኖ ይጠብቅሃል። የትላንቱን ቂም ይዘህ ዛሬ ላይ ስትበቀለው እሱም ነገ እንዲበቀልህ ቂም እየጠነሰስክ ነው።

ይሁን እንጂ፣ አሁን በኢትዮጲያ ያለው ሁኔታ ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ ነው። በጥላቻ ክፉኛ የታመመው ማህበራዊ ስነ-ልቦናችን የታሪክ ጠባሳችንን ከማከም ይልቅ ቂም-በቀል እየደገሰልን ይገኛል። የጥላቻ ፖለቲካን ለማስወገድ በቅድሚያ ስለ ቀድሞ ታሪካችን፣ ስለ ወቅታዊ ፖለቲካችን፣ ስለ የወደፊት ተስፋችን በግልፅ መነጋገር አለብን። በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተደብቆ ያለውን ቂምና ጥላቻ ፍቆ ለማስወገድ ሁላችንም ሃሳብና ስሜታችንን ያለገደብ መግለጽ መቻል አለብን።

እንደኛው ወገን ለብቻው የታሪክ ጠባሳን እያከከ የተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል ግን እንኳን ስላለፈው ታሪክ፣ ዛሬ በእውን ያየውን፣ ስለ ወደፊቱ ያሰበውን እንዳይናገር የሚታፈን ከሆነ ነገ ላይ ሌላ ትልቅ ጠባሳ ይኖረናል። እንደ ሀገርና ሕዝብ፣ የቀድሞ ታሪካችን የነገ ተስፋችንን እያጨለመ ነው። ስለ ቀድሞ ታሪክ መፃፍና መናገር ዘረኝነትና ጥላቻ ከሆነ፣ ስለ ዛሬው ፖለቲካ መፃፍና መናገር ወንጀል ከሆነ፣ ነገ ላይ ምን አለን? ስለ ትላንትና ዛሬ መነጋገር ከተሳነን ለነገ ቂም-በቀል አሳደርን፡፡