June 24, 2017

አበው እንዲህ ያለ ግራ የሚያጋባ ነገር ሲገጥማቸው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ በማለት የተፈጠረው ግራ አጋቢ ሁኔታ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ በሚያስገነዝብ መልኩ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፣ ለካ ወደው አይደለም የዚህ አይነቱን አባባል የሆነ አሳሳቢ ጉዳይ ሲገጥማቸው እንደ ዋዛ ጣል የሚያደርጉት፡፡

 

 

 

 

 

 

 

በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የራያ ህዝብ ላይ የሚደርሰው አስተዳደራዊ በደል፣ ከልማት የመገለል ሁኔታ፣ ባህላዊ ወረራ፣ ስነልቦናዊ ጫና እንዲሁም ሆን ተሎ እየተፈጠረ ያለው የማንነት እና ማህበራዊ ቀውስ አልበቃ ብሎ አሁን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ነገር ደግሞ ፍጹም ሰብአዊ የሆነውን መብቱን የማፈን ሒደት ሲታሰብ ይኸ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ የት ድርስ ይጓዝ ይሆን? የሚቆመውስ መቼ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ እያደረገን ይገኛል፡፡
በተለይም በቅርቡ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በራያ አላማጣ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ቀበሌዎችን ጎብኝተውና ነዋሪዎችንም አነጋግረው ከተመለሱ በኋላ ሁኔታዎች ሊሻሻሉ ይችላሉ የሚል ተስፋ አሳድረው የነበሩ ወገኖች ጭምር ከድጡ ወደ ማጡ እንደሆነባቸው ሀሳባቸውን በደፍረት መግለጽ መጀመራቸው እየተደመጠ ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፣ አቶ አባይ ወልዱ ወደ ራያ አካባቢ በተለይም ወደ ዋጃና አካባበው ዘልቀው የገጠር ነዋሪዎችን ሰብስበው ጭምር ለማነጋገር ሲሞክሩ ነዋሪዎቹም ይቅርታ ያድርጉልንና ክቡርነተዎ እኛ የትግርኛን ቋንቋ መስማትም ሆነ መናገር ስለማንችል ውይይቱን በአማርኛ ቋንቋ ቢያደርጉት የተሻለ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡላቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ ምን ሲደረግ በማለት ሀሳባቸውን ውድቅ ያደርጉባቻዋል፡፡
ነዋሪዎቹም እንግዲያውስ ንግግረዎ የቁራ ጩኸት ሆኖ እንደይቀር ከፈለጉ በሚያግባባን ቋንቋ ቢያወያዩን መልካም ነበር አይ ካሉ ግን ያሻዎትን ሊሉ ይችላሉ እኛ ግን ምኑም አይገባን በማለት በጨዋ ደንብ ለማስገንዘብ ቢሞክሩም ሰሚ ጆሮ ሊያገኙ አልቻሉም፣ ይባስ ብለው እንዴት እስከዛሬ ደረስ የትግርኛን ቋንቋ መስማትም ሆነ መናገር ሳትችሉ ቀራችሁ በማለት ያፋጥጧቸዋል፣ አይ ጌታው እኛ እኮ ድሮም ትግሬዎች አልነበርንም፣ አሁንም የእናት ቋንቋችንን ትተን የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ንሆን አንችልም፣ የእናንተ ቋንቋ እንዲስፋፋ የምትፈልጉትን ያህል እኛም በቋንቋችን መጠቀም እንፈልጋለን እና የእኛንም ሰብአዊ መብት ልታከብሩልን ይገባል ሲሉ ይሞግቷቸዋል፡፡
ይኸ ሁኔታ በእጅጉ ያበሳጫቸው ርዕሰ መስተዳድሩም የወረዳ አመራሩን ሰብስበው እስካሁን ድረስ የማነን ጎፈሬ ስታበጥሩ ቆይታችሁ ነው የአካባቢው ህዝብ የትግርኛን ቋንቋ መስማትም ሆነ መናገር ሳይችል የቀረው በማለት የሰላ ትችትና ጠንከር ያለ ሂስ ሰንዝረውባቸው ወደ መቀሌ ያቀናሉ፡፡
እንኳንስ ዘንቦብሽ ድሮውንም ጤዛ ነሽ ነበርና ነገሩ እነ ገሬ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በአካባቢው ከትግርኛ ቋንቋ በስተቀር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር፣ በንግድ ድርጅቶች ታፔላ ላይ በአማርኛ ቋንቋ ተጽፎ የነበረውም በአፋጣኝ ተፍቆ በትግርኛ እንዲተካ፣ ይህ ትዕዛዝ የማይፈጸም ከሆነ ደግሞ የመቀጣጫ እርምጃ እንደሚወሰድ የሚያሰገነዝብ ውሳኔ ያስተላልፉና የማስጠንቀቂያ መዓታቸውን ያዥጎደጉዱባቸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለማሳደር ከመፈጠሩም በላይ የንግዱ ማህበረሰብ ለአላስፈላጊ ወጭ እንዲዳረግ በማደረግ ላይ ናቸው፡፡ ከዛም አልፈው እረ እንዴት ነው ነገሩ እኛ እኮ ከጥንት ጀምሮ አማርኛ ተናጋሪዎች ነን እንዴት አሁን ላይ ደርሰን ትግርኛ ተናጋሪዎችና ትግሬ እንድንሆን ትጠብቃላችሁ ብለው ለሚጠይቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ታዲያ አማራ ከሆናችሁ ለምን ወደ አማራ ክልል አትሄዱም በማለት የአያት ቅድመ አያት ባደማቸውን (ቀያቸውን) እና ለዘመናት ሲጠቀሙበት የኖሩትን የእርሻ መሬታቸውን ለእነ ገሬና መሰሎቻቸው አስረክበው ወደ አማራ ክልል አንዲሄዱ ያለሀፍረት በአደባባይ መናገር ጀምረዋል፡፡
ይህም ሁኔታ ቀደም ሲል ጀምሮ በተለያዩ ጽሁፎቼና ንግግሮቼ ደጋግሜ ለማስገንዘብ እንደሞከርሁት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአጠቃላይና የአካባቢውን አስተዳደራዊ መዋቅር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥረውት የሚገኙት የራያ ተወላጅ ያልሆኑት የህወሀት ካድሬዎች ለምና የውሀ ሀብት ባለጸጋ የሆነውን የራያን መሬት እንጂ ህዝቡን እንደማይፈልጉት ያረጋግጣል፡፡
በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ እነዚህ ሰዎች በፌዴራሉ ህገ መንግስት አንቀጽ አምስት ላይ የተቀመጠውን ሁሉም ቋንቋዎች እኩል እውቅና የማግኘት መሰረታዊ መብትንና በማንኛውም ሁኔታ ለገደብ የማይችለውን በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጠቀም መብትን እንኳ የሚያገናዝብ ህሊና ያልፈጠረባቸው መሆኑ ነው፡፡ እርግጥ ነው የክልሉ የስራ ቋንቋ ትግርኛ እስከሆነ ድረስ በክልሉ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነዋሪ የክልሉ መንግስት በሚሰጣቸው የህዝብ አገልግሎቶች ላይ ከቻለ በቀጥታ ካልቻለ ደግሞ በአስተርጓሚ አማካኝነት እንዲጠቀም ሊገደድ ይችል ይሆናል፡፡
ከዚህ አልፎ ግን ተፈጥሯዊ በሆነው የእለት ተዕለት ማህበረሰባዊም ይሁን ግለሰባዊ ግንኙነት ሳይቀር ጣልቃ እየገቡ ይህን ቋንቋ ካልተናገርህና በዚህ ቋንቋ ካልጻፍህ የዚህ ክልል ነዋሪና አካል ነህ ልትባል አትችልምና የግድ አንዱን መምረጥ ይኖርብሀል አይነት አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠር በምንም ስሌት በህግ ያልተደገፈና ምክንያታዊ ያልሆነ ትዕዛዝ እጅግ አደገኛ የሆነ ድርጊት ከመሆኑም በላይ የዜጎችን ሰብአዊ መብት የሚደፈጥጥ፣ የፌዴራሉን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ብቻ ሳይሆን እንገዛበታለን የሚሉትን የክልሉን ህገ-መንግስት መርሆዎች ጭምር ዋጋ የሚያሳጣ መሆኑ አሌ ሊባል የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡
የዚህ አይነቱ የማንአለብኝነት እንንስቃሴና የህግ የበላይነትን በአደባባይ የሚንድ ድርጊት ውሎ አድሮ በመንግስትና በሰላማዊው ህብረተሰብ መካከል ያልተፈለገ ግጭት እንዲፈጠር በር የሚከፍት፣ ነዋሪው ህዝብም በመንገስት ላይ ያተገባ ጥርጣሬ እንዲይዝ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ማገናዘብ አለመቻል በራሱ ከሁሉም የከፋው ችግር በመሆኑ በጊዜ ሊታረም ይገባል፡፡
ከንግድ ድርጅቶች የታፔላ ጽሁፍ ጋር ተያይዞ መደረግ የሚኖርበት ታፔላው ላይ የሚጻፈው ጽሁፍ መጀመሪያ የክልሉ የስራ ቋንቋ የሆነው የትግርኛ ቋንቋ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ ቀጥሎ በሚኖረው ቦታ ላይ ደግሞ ባለድርጅቱ የሚፈልገው ቋንቋ (አማርኛ ወይም እንግሊዘኛ አሊያም አገውኛ ወይም አፋርኛ ሊሆን ይችላል) እንዲሰፍር ማድረግ ነው፣ ይህም ሁኔታ ህግና ስርአትን ተከትሎና የንግዱን ማህበረሰብ በማወያየት ጭምር ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል እንጂ የሆነ አጋጣሚ ሰፈጠር በስሜትና በእልህ ተነሳስቶ መሆን የለበትም፡፡
የዚህ አይነቱ አሰራር ደግሞ ሩቅ አገር ሳንሄድ ከበርካታ አመታት በፊት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ውስጥ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ላይ ተግባራዊ የሆነ አገር በቀል አሰራርና ህግ መኖሩ ይታወቃል፣ ከዚህ ውጭ ከትግርኛ ቋንቋ ውጭ በአማርኛ ቋንቋ መጻፍም ሆነ ማጻፍ አሊያም መናገር አትችሉም የሚል አይነት ጭፍን የሆነ አቀራረብ ካለ ግን በፍጹም ተቀባይነት የማይኖረው ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በእርግጥም በማንአለብኝነት ላይ የጠመሰረተ ጭፍን ትዕዛዝ ሊሆን እንደሚችል በቀላሉ መገመት ይቻል ካልሆነ በስተቀር የፌዴራል ስረአትን በግንባር ቀደምነት አራማዳለሁ ከሚል ወገን በፍጹም የሚጠበቅ ድርጊት አይደለምና በውል ሊታሰብበት እንደሚገባ በድጋሜ ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
በአጠቃላይም ባለፉት ሀያ አምስት አመታት በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ የሚገኘው የአስተዳደር በደልም ሆነ ከልማት የመገለል ሁኔታ እንዲሁም ግልጽ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚመነጨው በዋነኛነት የራያን አካባቢ ለም መሬት እንጂ ህዝቡን እንደ ራስ አካል አድርጎ ካለመውሰድ ጋር የሚያያዝ ሲሆን ይኸ ህዝብ አንድ ቀን በቃኝ ከእናንተ ጋር እንድኖር የሚያደርገኝ ማህበራዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ትስስር የለም ሊለን ስለሚችል አንድም በቅድሚያ ማንነቱን ለማስቀየር መረባረብ አሊያም አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ለማድረግ ያላሳለሰ ስራ መስራት ከሚል የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን እጅግ ሰብአዊነት የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም ከመፈለግ እንደሆነ መገመት አይከበድም፡፡