የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች! “ክፋት” – በሁሉም መስክ!!
June 8, 2017 08:06 am By Editor
መርዛማ ፍሬ 11፡ የታሪክ መቃብር!
በስሜት በሚነዳ የዘውግ ፖለቲካ ውስጥ ታሪክ ትልቅ ማገዶ ሆኖ ቀርቧል። የኢትዮጵያ ታሪክ አካታችነት ባለው መልኩ በአጎልባች ሚና (ብሔራዊ ተዋፅዖ) መፃፍ እየተገባው ምክንያታዊነትን አስመንኖ የልዩነት ሃረጎችን ብቻ በመምዘዝ በየአቅጣጫው የሚፃፍ መሆኑ ከተካረረ ሙግት ሊፀዳ አልቻለም። መዋቅራዊ ድጋፍ ባለው መልኩ የታሪክ ሙግቱ እየተካረረ በመምጣቱ ብሔራዊ ርዕይ ርቆን የመንደር አጥር እስከመስራት ደርሰናል።
ደርግ በየትኛውም ያህል መጠን አምባገነንና ጨፍጫፊ ሆኖ ቢገኝም የኢትዮጵያን ታሪክ ሲንቅና ሲያንቋሽሽ አልተገኘም። ከቶውንም ለብሔራዊ ርዕይ መፍጠሪያነት እንደግብዓት ተጠቅሞበታል። ከመነሻው ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ስሜትን (የጋራ ማንነትን) በመካድ ራሱን ብቸኛ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር አድርጎ የሰየመው ህወሓት፣ የአገሪቱን የረዥም ጊዜ ታሪክ ባለቤትነት አውርዶ በ100 ዓመት የታሪክ ሁነት ውስጥ ለመቀንበብ የሞከረበት መንገድ የታሪክ መቃብር ቆፋሪ ያደርገዋል። እነ መለስ ከበረሃ አዲስ አበባ እንደገቡ በጊዮን ሆቴል በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ዕድሜ 100ዓመት እንደማያልፍና ይህንኑ ጋዜጠኞች “እንደ አዝማሪ” ሲደጋግሙት እንደነበር ሞት እንደ ቡሽ ያስፈነጠረው መለስ ዜናዊ በዕብሪት ተናግሮ ነበር፡፡
በዘውጎች መካከል ደማቅ የልዩነት መስመር ለማስመር የቀደሙ የታሪክ ቁርሾዎችን በማስፋትና በመለጠጥ በኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ ትከሻ ላይ የፖለቲካ ቁማር መጫወት የህወሓት የተለመደ ተግባር ሆኗል። እጅግ የበዛ የመርማሪነት ልቦና እና ልዩ የሙያ ሥነ-ምግባር የሚጠይቀው የታሪክ ትምህርት የህወሓት ካድሬዎች የዘውግ ፖለቲካ ማስፈፀሚያ አጀንዳ ሆኗል። የህወሓትን የታሪክ መቃብር ቆፋሪነት ሚና ታከው የወጡ ሌሎች የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች የኢትዮጵያን ታሪክ እስከ ጥገኛ ቅኝ ግዛት ሃተት ድረስ በመለጠጥ ኢትዮጵያ እንደ አገር የቆመችበትን የታሪክ መንገድ ሲኮንኑ ውለው ያድራሉ።
የኢትዮጵያን ነገሥታት መዝለፍና መሳደብ፣ ባልዋሉበት ማዋል ለዘውጌ ብሔርተኞች የማይናቅ “የፖለቲካ ትርፍ” አለው። ይህን መሰሉን ተግባር ህወሓት ከፊት ለፊትም ሆነ ከጀርባ ሆኖ በማራገብ ስራው ተጠምዶ ይገኛል። ፀጋና መከራ ሞልቶ ከፈሰሰበት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጋራ ማንነቶችን በማሳደግ ብሔራዊ ርዕዮችን መቅረፅ የሚቻልበትንና የአብሮነት ዋልታችን ማፅናት የሚቻልበትን ዕድል እያመከነ ያለው ህወሓት ስለ ሥልጣን የበላይነት የታሪክ መቃብር ቆፋሪነቱን ቀጥሎበታል።
የኢትዮጵያ አገራዊነት ታሪክ ተፃራሪ ትርጓሜዎች ከዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባ ሂደት የተመዘዙ መንታ ሰበዞች ናቸው። ታሪክ የፖለቲካ ፍላጎት ማሟያ ሆኖ እየቀረበ ያለውም ተፃራሪ ትርጓሜዎችን አብዝቶ በመለጠጥ ነው። መደባዊ ይዘት የነበረውን ዘውዳዊውን የጭቆና ዘመን ወደ ዘውጋዊ ጭቆና በመጠቅለል የ“ጨቋኝ” “ተጨቋኝ” ታሪክ ማቀጣጠል የህወሓት የተጠና የፖለቲካ መስመር ነው። በቀደመው ጊዜ እትዮጵያዊያን ለታሪክ ማንነት ፍፁማዊ ወጥ ይዘት በመስጠት የሚነሳ ግንዛቤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ገዥ ሥርዓታዊ መርህ ነበር። ታሪክ እንደሚባለው ዳቦ ባይብስልም እንኳን በትላንት እና በነገ መሀከል ያለ ድልድይ ነው። ህወሓት በታሪክ ጥላቻ የሰከረ ድርጅት በመሆኑ የትላንትና እና የነገ አገናኝ ድልድይ የሆነውን ታሪክ ዛሬ ላይ ወደ መቃብር እያወረደው ይገኛል።
በክህደት የታጀበው የታሪክ ምርኩዝ የህዝባዊ ታሪክ ፀሃፊያንን እውቀት በዘውግ ተኮር “ፍርዳቸው” የተነሳ ብኩን ሲሆን አስተውለናል። ስለ ዘውገና ታሪክ ለመፃፍ የተነሱ የታሪክ ፀሐፍት ከዘውግ አጥር መሻገር አቅቷቸው በአደባባይ ዘዉጌ ወገንታኝነታቸውን ሲያውጁ ታዝበናል። ዝግና የተመረጠ የታሪክ ግንዛቤ ይዘው የሚነሱ የታሪክ ፀሐፍት ታሪክን የዘውግ ፖለቲካ ገበያ አድርገውታል። የህወሓትን የታሪክ መቃብር ቁፋሮ ተከትሎ በአደባባይ እየታየ ያለው የታሪክ ስካር “ደፋሩን” ወደ እብሪት፣ ስሜታዊውን ደግሞ ወደ ጭፍን የዘውግ አክራሪነት እንዲሳብ አድርጎታል።
የኢትዮጵያን የነገ ተስፋዎች የናደው ህወሓት የአገሪቱን (ጥንታዊ) የህዝብ መስተጋብር፣ ግዛታዊ አንድነት እና ቀጣይ ታሪክ አደጋ ላይ ጥሎታል። ተጨባጭ የታሪካችን ፍሰት ኢትዮጵያ እንደ አገር ለመቆም የበዛ የህይወት መስዋትነት ተከፍሏል። እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ጠመዝማዛ የታሪክ መንገድም አልፈናል። በብዙ መስዋዕትነት የተገኙ በጎ ፍሬዎችን (ጉንደት፣ ዶጋሌ፣ አምባላጌ፣ አድዋ ድሎችን) በጋራ ማክበርና ማወደስ ተስኖን፣ የማህበራዊ ትስስሮሻችን በአያሌው ላልቶ፣ አገራዊ አንድነታችን አደጋ ላይ የጣሉና ከሥርዓታዊ መልሶ ማዋቀር (የህወሓትን ጭቆና በጋራ ከመሻገር) ይልቅ መበተን (መገንጠል) ላይ ያጠነጠኑ ተፃራሪ የዘውግ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እንደ አሸን በመፍላታቸዉ አገሪቱን የመበተን ጫፍ ላይ አድርሷታል።
የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ መስመር ዜጎችን በዕድሜ፣ በፆታ፣ በሙያና መሰል ዘርፎች በማደራጀት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር የሰርክ ተግባሩ ነው። በከተሞች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማህበራት ሥም በማደራጀት የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያው ሲያደርግ ቢስተዋልም የታሪክ ባለሙያዎችን በማህበር ለማደራጀት አልደፈረም። ህወሓት የቀደመውን የኢትዮጵያን ታሪክ በበጎ ጎኑ መስማት የማይሻ የታሪክ መቃብር ቆፋሪ ድርጅት ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ መስመር (ቀኖና) መሰረት ሊስትሮዎች እና አነስተኛ የሙያ ዘርፍ ላይ የተሰማሩትን፣ የጉልበት ሰራተኞችን ሳይቀር በማህበራት ባደራጀበት ሁኔታ የታሪክ ባለሙያዎች በማህበር እንዲደራጁ እና የታሪክ ጥናት ሙያ መስክን እንዲያስፋፉ ለማድረግ የሚያስችል ፈቃድ ነፍጓል። የታሪክ ባለሙያዎችም ራሳቸውን በየቤተ መፅሐፍቱ ከመቅበርና የውጭ አገር ፌሎውሺፕ ከማሳደድ በተሻገረ ይህ ነው የሚባል ተግባር ሲፈፅሙ አልታየም።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አገሪቱ አንድም የታሪክ ጥናት ላይ የሚያተኩር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር መፅሔት (journal) የላትም። የታሪክ ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደረጃ እንደ መርሐ – ግብር መስጠት ያቆመባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ናቸው። በአንጋፋነቱ የሚታወቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎችን በመቀበል ካቆመ ሁለት የትምህርት ዘመናት አልፈዋል። ህወሓት እንደ አቅጣጫ ይዞት ያለው ነገር የታሪክ ትምህርትን በመደምሰስ በልዩነት ውስጥ ብቻ የሚባክን አልቦ-ታሪክ ትውልድ መፍጠር ነው። ለታሪክ ጥናት የተሰባሰቡ ባለሙያዎች በሌሉባት ኢትዮጵያ፣ ታሪክ የፖለቲካ ፍላጎት ማሟያ ሆኖ ሲቀርብ እየታዘብን ነዉ። ከዚህም አልፎ ታሪክን እና ተረትን በመቀላቀል የታሪክን ሰብዓዊና ቁሳዊ ሃብት ሲያራክሲ ይታያል። የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ታሪክ ላይ ያለን የተዛባ ምልከታ ውጤት ነው። የአገር ምስረታ ሂደቶችን አብዝቶ መኮነን እልፍ ሲል ደግሞ ጉዳዩን እስከ ጥገኛ ቅኝ ግዛት ድረስ በመለጠጥ ከአብሮነት ይልቅ የመበተን (መገንጠል) ደወሎችን በየጊዜው መስማት የዛሬዋን ኢትዮጵያ ይበልጥ የሚገልፃት ሁነት ሆኗል።
የህወሓት የታሪክ ጥላቻ መንስኤ ከኢትዮጵያ ጥላቻ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የታሪክ መቃብር ቁፋሮው መንፈሳዊና ቁሳዊ የታሪክ ሃብቶችን ከማራከሱ በላይ አብሮነታችን የሚሸረሽር የስጋት ምንጭ ሆኖ ቀርቧል። በታሪክ ጥላቻ የሰከረው ህወሓት የኢትዮጵያን እንደአገር የመቀጠል ህልውና ቅርቃሮ ውስጥ ከቶታል።
የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውና ከአደጋ ማውጣት የሚቻለው ከጥልቅ ትቅቅፍም ሆነ ከተካረረ የታሪክ ውግዘት በፀዳ መልኩ የአገሪቱ ታሪክ ሙያው በሚጠይቀው ሥነ-ምግባር መሰረት ከፖለቲካዊ ውገና በራቀ መልኩ ለሙያው መርሆዎች መታመን ሲቻል ነው። ለዚህ ደግሞ ታሪክን ለታሪክ ሙያተኞች ብቻ መተው ግድ ይላል። ከዚያ በፊት ግን በአገራዊና በታሪክ ጥላቻ የሰከረው ህወሓት ለታሪክ በቆፈረው ጉድጓድ መቀበር ይኖርበታል።
መርዛማ ፍሬ 12፡ የማህበራዊ ዕሴቶች መውደም!
ኢትዮጵያ እንደአገር ፀንታ የቆየችው በነገሥታቱና በገዥዎች ኃይል (ብቻ) ሳይሆን ህዝቡ በማህበረ-ኢኮኖሚ ትስስሮሹ የፈጠረው ድርና ማግ የማይበጠስ በመሆኑ ነው። ዘውግና ኃይማኖትን የተሻገረው ማህበራዊ ትስስሮሽ ኢትዮጵያን እንደ አገር አፅንቶ ያቆያት ቢሆንም በበታችነት ህመም የሚሰቃየው ህወሓት በጥላቻ ፖለቲካ እየተመራ የህዝቡን አብሮነት እና ማህበራዊ መስተጋብር ለመበጣጠስ ብዙ ርቀት ተጉዟል – በተለይም በከተሞች!
ምንም እንኳ መደባዊ ልዩነት የነበረ ቢሆንም በከተሞች የነበረው የህዝብ አሰፋፈር ዘውግና ኃይማኖትን ያላማከለ ጥብቅ ትስስር የሚታይበት ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ከተማን እንደማሳያ ብንወስድ በየሰፈሩ የነበረው ማህበራዊ ትስስሮሽ ራሱን የቻለ ማህበራዊ ወጌሻ ነበር። ኃይማኖታዊና ዘውጋዊ የልዩነት መስመሮች ሳይገድቡት ማህበራዊ ትስስሮሹን ከፍ አድርጎት የነበረው አዲስ አበቤ ከምርጫ 97 በኋላ “የልማት ተነሽ” በሚል የህዝቡን የቀደመ ማህበራዊ ትስስሮሽ ብጥስጥሱን አውጥቶታል።
ህወሓት ይህን ያከናወነው የቀደሙ የከተማ ነዋሪዎች የፈጠሩት ማህበራዊ ትስስሮሽ ለህዝባዊ እምቢተኝነቶች ጉልበት መሆናቸውን ምርጫ 97 ላይ በመረዳቱ ነው። እዚህ ላይ ሟቹ መለስ ዜናዊ “ደሃ ከአዲስ አበባ ይወጣል” ያለበትን ደሃ-ጠል ንግግሩን ሳንዘነጋ መሆኑ ልብ ይላል።
የአዲስ አበባ የቀደሙ ሰፈሮች በልማት ሥም መፍረሳቸው ቀጥሏል። ለተነሽዎቹ ተገቢ ካሳ ካለመስጠቱም በላይ በአዲስ አበባ ዳርቻ ቦታዎች ላይ እየተገነቡ ባሉ ኮንደሚኒየም መንደሮች እርስ በእርሳቸው የማይተዋወቁ እንዲሁም በጥርጣሬ የሚተያዩ “ጎረቤቶች” ተፈጥረዋል።
ለብዙዎቻችን እንደዋዛ የሚታየው “የቡና ጠጡ” ሥነ-ሥርዓታችን ላይ በእናቶቻችን ይነሱ የነበሩ ማህበራዊ ጉዳዮች የህብረተሰቡ ማህበራዊ ወጌሻ (Social Therapy) ሆነው ያገለግሉ ነበር። ይህ ማህበራዊ ወረት በተጠኑ የፖለቲካ ሴራዎች “ነበር” ወደ መባል ደረጃ ላይ ደርሷል። “ቡና ጠጡ” የሚለዉ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓታችንም የአገዛዙ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ በማድረግ የወል ባህላችን ሲያራክሰዉ እያየን ነዉ።
በ“ልማት ሥም” ተነሽ የሆኑ ነባር ነዋሪዎችን ብትንትን አድርጎ በማስፈር፣ ኃይማኖታዊ ልዩነቶችን በማክረር በተለይም በክርስትና እና በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች መካከል “አክራሪ ሙስሊም”፣ “አክራሪ ክርስቲያን” በሚል ፍርጃ እና በዘውጎች መካከል የጥርጣሬ መንፈስ በመፍጠር የአብሮነት እሴቶችን በማውደም ላይ ተነጥሎ የቆመ የከተማ ነዋሪ ለመፍጠር ህወሓት የሴራ ፖለቲካው ላይ ተጠምዷል። ዛሬ ላይ የጉርብትና እርሾ በሌለው መልኩ በርን ዘግቶ መቀመጥ በበዛበት አዲስ አበባ ዘውጋዊ ማንነትን ከተንተራሱ ማህበራዊ ግንኙነቶች በተሻገረ መልኩ ሰዋዊ ጉርብትና ነጥፏል። በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዘውጋዊ ማንነት ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖ ቀርቧል።
ደስታና መከራን እንደሰው በጉርብትና ትስስር ከመካፈል ይልቅ አካባቢያዊ ማንነትን ማጠንጠኛ ያደረገ “ማህበራዊ” ግንኙነት ገንግኗል። የንግድ ትስስሩ ዘውጋዊ መረብ የተዘረጋለት ሆኗል። በክርስትና እናትና አባትነት፣ በአይን አባትነት፣ በዕድር መረዳጃ ማህበራትና መሰል ማህበራዊ ሁነቶች ጥብቅ ትስስር የነበረው የከተማ ነዋሪ የአንድነት መስመሮች እየሰለሉ የልዩነት ሃዲዶች ተበራክተዋል። አዲስ አበባ አለም አቀፍ ከተማ ብትሆንም እንደ ዜጋ የከተሜ ባህሪ የሚንፀባረቅባቸው ሰዎች ውስን ናቸው።
የመረዳጃ ማህበራት ሳይቀር በዘውጋዊ ማንነት ስር የተቀነበቡ ድኩማን ማህበራት ሆነዋል። ለእርስ በእርስ መረዳዳትና መተጋገዝ መትጋት ቀርቶ ቋንቋ ተናጋሪነትን መመዘኛ ያደረገ የማህበረ-ኢኮኖሚ ትስስር ተዘርግቷል። በጊዜ ሂደትም እንደ አገር የነበሩን ማህበራዊ ዕሴቶች እየጠፉ ሄደዋል። ይህን የታዘበው የዘመናችን ባለቅኔ በዕውቀቱ ሥዩም፡-
“ሕዝብ እየጠበበ ዕድር እየሰፋ
የሚያቀባብር እንጅ የሚያኗኑር ጠፋ”
ሲል የማህበራዊ ዕሴቶቻችንን መውደም በግጥም መልኩ አመሳጥሮ ነግሮናል።
በከተሞች የሚስተዋለው ሰብዓዊ ንጥፈት የማህበራዊ ዕሴቶቻችን መውደም ምልክት ነው። እንደ አገር ያቆሙን ማህበራዊ ትስስሮሻችን እየተሸረሸሩ ዘውጋዊ ሃዲዶች እየሰፉ መሄዳቸው እንደ ዜጋ ሊያሳስበን ይገባል። የአገዛዙ ጌጥ የሆኑት ምግባር የጎደላቸው ነጋዴዎች፣ ህሊናቸውን የሸጡ ሙያተኞች የሚፈፅሙት ድርጊት፣ ለጆሮ ሰቅጣጭ የሆኑ ወንጀሎች፣ … ሁሉ የማህበራዊ ዕሴቶቻችን መውደም ምልክቶች ናቸው። በዚህ ሁሉ ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ ውስጥ ለፀፀትም ሆነ ለእርምት ዝግ የሆነው ህወሓት ለሥልጣን የበላይነቱ ማህበራዊ ቀውሱን ማፋፋሙን ተያይዞታል።
ጥልቅ የሆነ የትላንት ድምሰሳ እና የተቻከለ የዘውግ ፖለቲካ ምልከታ ያለው ህወሓት፣ ማህበራዊ ዕሴቶቻችንን አፍራሽ በሆነው የሴራ ፖለቲካው የውድቀት ጉዞውን ተያይዞታል። ውድቀቱም የብቻው አለመሆኑ እንደአገር ያሳስበናል። የግንቦት ሃያን መርዛማ ፍሬዎች ለማርከስ በኢትዮጵያዊ ስሜት እንደዜጋ ትውልዳዊ ኃላፊነትን መውጣት ግድ ይላል።
መርዛማ ፍሬ 13፡ የተቋም መኻንነት!
ኢትዮጵያ የአገረ-መንግሥት (ግዛት) ምስረታዋን በዳግማዊ ምኒልክ የንግሥና ዘመን ከሞላ ጎደል አጠናቅቃ ነበር። አገሪቱን እንደ አገር የሚያስቀጥሏትን እና ዓለም አቀፋዊ ሞገስ የሚፈጥሩላት ተቋማትን መፍጠር ግን ተስኗታል። ከዳግማዊ ምኒልክ ጅምር የተቋማት ምሥረታ ጀምሮ ከአንድ ክፍል ዘመን (100 ዓመት) በላይ ተጉዘን ይህ ነው የሚባል አርያነት ያለው ተቋም መመስረት አልተቻለም። አገዛዙ በቀደመው ግዜ ለመቆመ ዳዴ ይሉ የነበሩ ተቋማትን ከቶውንም ከወታደራዊ ደርግ በላይ አብዝቶ መደቆሱን ተያይዞታል። “ዴሞክራሲን በጎ ትሩፋት ለአገሪቱ አስተዋውቄአለው” እያለ የሚመፃደቀው ህወሓት፣ የአገሪቱን ተቋማት ጭራሽኑ በማምከን የሚስተካከለው ገዥ ኃይል ያለ አይመስልም።
ወረቀት ላይ የሰፈሩ ህግጋትና በተጨባጭ ያለው አሰራር ፍፁም ለየቅል በሆነባት ኢትዮጵያ ተቋማቱ በቁጥር በርከት ያሉ ቢመስሉም ወጥ በሆነ የህወሓት የፖለቲካ ፍላጎት የታፈኑ መኻን ተቋማት ተፈጥረዋል። ለአገራዊ ችግሮቻተን የጋራ መፍትሄ ማመንጨት አለመቻላችን ከተቋም እጦት ጋር ይያያዛል። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የግብርና መስክ ምርምርና ሌሎች ማህበራዊ ግልጋሎቶች አቅርቦት በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፣ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የፍትህ ተቋማት የግፍ ማዕከል፣ የፖለቲካ ድራማ መድረክ መሆናቸው ከዚህም አልፎ ተቋማቱ በካድሬዎች መሞላታቸው፣ በአገራዊ፣ አካባቢያዊ ብሎም በአህጉራዊ ጉዳዬች ላይ ጥናትና ምርምሮችን የሚያድርግ የሙያተኞች ስብስብ (think-tank) አለመኖሩ፣ በየዩኒቨርሲቲዉ ተሰሩ የሚባሉ ጥናትና ምርምሮችም የመምህራኑ ኑሮ መደጎሚያ መሆናቸዉ፣…አገሪቱ በተቋም መኻን የተጠቃች ለመሆኗ አስረጅ ምሳሌዎች ናቸው።
በሕግ አውጭና የፍትህ ተቋማት፣ ሚዲያ፣ ፖለቲካ ፖርቲ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ቢሮክራሲ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ አገራዊ የሽምግልና እና የዕርቅ ተቋማት በዘላቂነት ኖረውን አያውቅም ። አሉ የሚባሉት ተቋማትም ከህወኃት የፖለቲካ መስመር ጋር የተጣበቁ፣ የጥቅመኘነት ፖለቲካ አራጋቢዎች ናቸው። ከቀደም ጀምሮ ወታደራዊው መንግስት የንጉሳዊ ሥርዓቱን፣ ህወሓት ደግሞ የደርግን ተቋማት ሙሉ በሙሉ በማፈራረሱ የተከማች ዕውቀት እና የዳበረ ተቋማዊ አሰራር ርቆናል። በማህበራዊ ጉዳዮች፣ በኢኮኖሚ አማራጭ ፖሊሲዎች፣ በወታደራዊና በደህንነት ጉዳዩች ወ.ዘ.ተ ላይ የሚያተኩሩ (ሙያ ተኮር) ገለልተኛ ተቋማት ባለመኖራቸው አማራጭ ዕይታዎችን ርቀውን በአንድ ጠቅላይ አምባገነን የወንበዴ ቡድን የፖለቲካ ፍላጎት መነዳት የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ሆኗል። ነፃ ተቋማት ተፈጥረው ማየት የማይሻው አገዛዝ ፣ የአገሪቱን ተቋማት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ላይ የተገደበ ነው። የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ይህን መስሉን ሁነት (ተቋማትን መኻን ማድረጉን) ለማገዝ የወጣ “ህግ” መሆኑን ልብ ይሏል።
በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የትኛውም ተቋማት ላይ ረዣዥም የቁጥጥር እጆቹን የዘረጋው ህወሓት፤ መንግሥታዊ ተቋማቱን የሚመሩ አካላትን መመልመያ መስፈርቱ በሙያዊ ብቃት/ችሎታ ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነት ነው። በተቋማቱ ውጥስ የተዘረጋው የ1፡5 የጥርነፋ አደረጃጀት ተቁማቱ ከህዝባዊና አገራዊ አገልግሎት የተነጠሉ እና የሃሳብ ድርቀት የሚስተዋልባቸው ረብ የለሽ ተቋማት ሆነዋል። በአሰራር ደረጃ ህዝባዊ ዝንባሌ የሌላቸው የአንድ ፖለቲካ ፖርቲ ፍላጎት ማስፈፀምሚያ ከመሆን በተሻገረ የአዲስ አስተሳሰብና አሰራር አዋላጅ መሆን ያልቻሉ መኻን ተቋማት ናቸው።
በተቋማቱ ላይ ምሁራዊ ድባብን አፍዝዞ ካድሬዊ አሰራርን ያነገሰው አገዛዝ፣ ተቋማቱን ወጥ በሆነ ተዋረዳዊ የዕዝ ሰንሰለት ጠርንፎ ይዟቸዋል። ሩብ ክፍለ ዘመንን የተሻገረ የሥልጣን ላይ ቆይታ ያለው ህወሓት በአገሪቱ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተቋም መገንባት አልቻለም። ህወሓት ሥልጣን ላይ እስከ ቆየ ድረስ የተቋማቱ መኻንነት ቀጣይነት ይኖረዋል።
መርዛማ ፍሬ 14፡ “ሕግ” የጠሉትን መምቻ የፖለቲካ መዶሻ!
ህወሓት “የሰመረለት” አምባገነን ድርጅት ቢሆንም ከአቻው ደርግ ለየት የሚልበት ሕግን ለአገዛዙ ፍላጎት ማርኪያ እንዳሻው የሚጠቀምበት አዲስ ሁኔታ መፍጠሩ ነው። አምባገነኖች በራሳቸው “ሕግ ነን” የሚሉ ቢሆንም ህወሓት ከዚህ የተለየ መንገድ መርጧል። ባልተጻፈ ሕግ ዜጎችን ከማስር ጀምሮ ካሰሩ በኋላ “ሕግ” ማውጣት፤ በተጠርጣሪ ዜጎች ላይ የሃሰት ክስ ከመመስረት እስከ ሃሳዊ መረጃና ማስረጃ (የሰው፣ የሰነድ) ማሰባሰብ ድረስ ያሉ ሂደቶችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ህግን መጫወቻ አድርጎታል።
ህወሓት ሩብ ክፍለ ዘመን በተሻገረ አገዛዙ በርካታ ሕግጋትን አውጥቷል። እንደ ሌሎች አምባገነን አገዛዞች ሕግ አልባ አይደለም። ይህ ልዩ ያደርገዋል። አይዞህ ባይ እና ድርጎ ሰፋሪዎቹ ምዕራባዊያኑ በፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ሞጋች የህብረተሰብ ክፍሎች፣ … ላይ የሚያካሄደውን ወከባና የእስር ዘመቻ በተመለከተ ሲጠይቁት “ሕግ ስለተላለፉ ነው” የሚል ምላሽ በተደጋጋሚ ሲሰጥ ታይቷል። “ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት የአገሪቱ ሰላምን የማረጋጋት መንግሥታዊ ኃላፊነት አለብኝ” የሚለው ህወሓት፣ ለዘፈቀደ የጅምላ እስሩ እና የአደባባይ መንግሥታዊ ፍጅቱ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ “ሕጋዊ” ሽፋን ሲሰጠው ይስተዋላል። እልፍ ሲልም “ችግራችን የአፈፃፀም ነው” በማለት የአደባባይ ወንጅሉን ለማንፃት የሃሰት ካባ ይደርባል። የፖለቲካ ነክ ተከሳሾች ሕጉ የትም እንደሚያደርሳቸው እየታወቀ ህወሓት እደፈለገ በሚያሸከረክረዉ “ሕግ” ዙሪያ እንዲከራከሩ ያደርጋል።
በ“ሸብርተኘነት ወንጀል” የተከሰሱትን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ሞጋች የህብረተሰብ ክፍሎች፣… ወዘተ የክስ ጉዳይ ሳንዘነጋ ከዚህ ወጣ ያሉ ጉዳዩችን መመልከት ይቻላል። ለአብነት ከመሬት ነጠቃው ጋር በተያያዘ የወጡትን ሕጎች ስንመለከት በሕግ ደረጃ በጣም የሚገርሙ ናቸው። ያልወጣ የሕግ አይነት የለም፤ የአዋጭነት (feasibility study)፣ የኬሚካል አጠቃቀም፣ የአፈር ብክነት መከላከል፣ የአየር ንብረት መከላከል፣ … በተመለከተ የተቀመጡ ሕግጋት አስደናቂ ናቸው። ሕግጋቱን ከውጭ ለሚያያቸው ግሩም ናቸው። ግን አንዳቸውም አይተገበሩም።
የፀረ-ሽብር ህጉ እና የተሻሻለው የፕሬስ አዋጅ በዋናነት ግልጽ የመብት ጥሰት የሚፈጽሙ ሸውራራ ህግጋት ናቸው። ህወኃት በየዘርፉ ማውጣቱና ለእያንዳንዱ አረመኔያዊ ድርጊቱ “ህግን” መከታ/ሽፋን ማድረጉ የተለየ የወንበዴ ስብስብ ያደርገዋል።
ምንግዜም ቢሆን “ሕግ” የሚለው ኃይለ-ሃሳብ ለህወሓት የጠሉትን መምቻ የፖለቲካ መዶሻ ነው። ህወሓት ሁሌም ቢሆን አፋኝና የሰመረለት ህግጋቱን እንዴት እንደሚያራክሳቸው በደንብ ያውቅበታል። በፍርድ ቤቶች በኩል የተጨፈለቀው የዳኞች ነፃነት ለህወሓት የረከሰ የፍትህ ሥርዓት ዋነኛ አስረጅ ምሳሌ ነው።
ኢ-ፍትሃዊነትን በፍትህ ካባ የከለለው ህወሓት ሕግን የጥላቻ ፖለቲካ ማራመጃው አድርጎታል። በዚህም ለህወሓት “ሕግ” የጠሉትን መምቻ የፖለቲካ መዶሻ ነው። ነገሩ ግሪካዊው ፈላስፋ ፕሌቶ “ፍትህ ኃይለኞችን ለመጠበቅ የተቋቋመች መገልገያ መሳሪያ ነች” እንዳለው ነው። የህወሓትን አፋኝና የይስሙላ ህግጋትን በመጣስ ሕግና ፍርድን በእጅ መጨበጥ አማራጭ የሌለው የመፍትሄ መንገድ ሆኖ ቀርቧል።
መርዛማ ፍሬ 15፡ “ኪራይ ሰብሳቢነት”!
ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል ያልተገባ የኢኮኖሚ ጥቅም በማጋበዝ ብቻ የሚተረጎም ሳይሆን ከዚህም ባለፈ የፖለቲካ ጥቅም ትስስር (ኔት ወርክ) እና አካባቢያዊ ማንነትን መሰረት ያደረገ የሥልጣን መደጋገፍንም የሚጨምር የትርጉም ይዘት አለው። የአገዛዙ የፖለቲካ መሃንዲሶች ለማመን በሚከብዱ የሙስና መረቦች በመተብተባቸው በህዝቡ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጥልቅ ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ የተፈጠሩ ህዝባዊ አመፆች የአደጋው አንዱ ገጽታ ነው። ሁለተኛው የአደጋው መልክ ደግሞ ባለሥልጣናቱ እንደ ቡድን በሚዘረጉት የሙስና መረብ ከጥቅም ትስስራቸው ጋር በተያያዘ እንደመንግስታዊ መዋቅርም ሆነ እንደ ድርጅት የሚመጡ ግምገማዎችን በጋራ የሚመክቱበት (እየመከቱ ያለበት) እንዲሁም ባለሥልጣናቱ የራሳቸውን የቡድን አባል ወደ ተሻለ የሥልጣን ከፍታ ለማውጣት የሚያደርጉት ርብርብ የቡድን ፍላጎት የሚታይበት በመሆኑ ፍላጎቱ ከሌላው ቡድን ጋር የሚጋጭ ከሆነ በዚህ መሀከል የሚፈጠረው ልዩነት ከሥርዓቱ አልፎ ለአገርም አደጋ የሚሆንበት ዕድል ይኖራል።
በዚህ አግባብ የህወሓት የበላይነት እንደተጠበቀ ሆኖ ለኢሕአዴግ እንደ “ግንባር” ኪራይ ሰብሳቢነት የድርጅቱ አደጋ ሆኗል። ‹የግንባሩን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢነት ነው› የመባሉ እውነታም ከዚህ የመነጨ ነው። በተለይም የፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ ዘውግን መሰረት ያደረገ ቡድንተኝነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ አደጋው ጠባብነትን መታያው አድርጎ እዚህም እዚያም እየታየ ነው። በቀጣይ ይህን ተከትሎ የሚፈጠረው ችግር ከአገዛዙ ስብስብ አልፎ ለአገርም (የእርስ በእርስ ጦርነት) የከፋ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይደለም። በተለይም በመከላከያና በፖሊስ (የፌዴራልና የክልል) ሰራዊቱ ያለው አድሏዊ የሹመት ሁኔታና የከፋ ሙስና ከዘውግ ፖለቲካዉ ጡዘት አኳያ ራሱን የቻለ የጊዜ – ቦምብ ማለት ነው።
አገዛዙ “ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመታገል ጥረት እያደረኩ ነው” እያለ ዲስኩሩን ቢያሰማም፣ ችግሩ ከመባባሱ ውጪ ጠብ ያለ ለውጥ በአደባባይ ሊታይ አልቻለም። እጅግ አስደንጋጭ የሙስና ሪከርዶች በ“ተወካዮች ምክር ቤት” በኩል በሪፖርት መልኩ ሲታለፍ ማየት የሚደንቅ አይደለም። አቅም አልባነት መታያው የሆነው የአገሪቱ “ጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ በአደባባይ “ሙስና አለ! ነገር ግን ማስረጃ የለንም!” ሲል የተናገረው ጉራማይሌ ንግግር ሙስናና አገዛዙ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም መንታ ገጽታ ለመሆናቸው አስረጅ ምሳሌ ይሆናል። በተለይም በመሬትና በፍትህ አስተዳደር እንዲሁም በመንግሥት ንብረት ግዢና ሽያጭ፣ ታክስ ተኮር ጉዳዮች ላይ እየታዩ ያሉ ግልፅ የሥልጣን መባለጎችን ስናስተውል አገሪቷን እንደ “መንግስት” እያስተዳደራት ባለው አገዛዝ ላይ እምነት እንድናጣ ያደርገናል።
በ2008ዓ.ም የሥራ ዘመን የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ለ”ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት ሃያ አምስት የሚሆኑ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ህጋዊነት የሌለው የንብረት ግዢና ሽያጭ ማካሄዳቸውን፣ ሥራቸውን የለቀቁ ሰራተኞች በሌሉበት እስከ ስድስት ወር የሚደርስ ደመወዝ እንደተከፈላቸው፣ ያለ ጨረታ የኮንስትራክሽን ግንባታ ሥራዎች ለተለያዩ ተቋራጮች እንደተሰጠ፣ ህጋዊ የደመወዝ ጭማሪ ላልተደረገላቸው ሰራተኞች በህገ – ወጥ መንገድ ተጨማሪ ክፍያ የከፈሉ መስሪያ ቤቶች መኖራቸውን፣… ሪፖርቱ ያመለክታል። በዚህም እንደ አገር ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተመሳከረ ሒሳብ መኖሩን ይጠቁማል። ሪፖርቱ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን (ዩኒቨርሲቲዎችን) ብቻ የሚመለከት ነው። በመንግስት የልማት ድርጅቶችና በየክልሉ ያለውን ምዝበራ ከዚህ ሪፖርት አኳያ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የንብረት ግዢና ሽያጭ ችግር አለባቸው፣ ህጋዊ የፋይናንስ አሰራር አልተከተሉም በሚል በሪፖርቱ የጠቆማቸው መንግስታዊ ተቋማት አመራሮች በህግ ሲጠየቁ አላየንም።
በርግጥ በአገዛዙ ቤት ፖለቲካን እንጅ የህዝብን ገንዘብ መስረቅ የአገዛዙ አንዱ ገጽታ ነውና የተለየ እርምጃ አይጠበቅም። ይሁንና እነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ከገንዘብ ባለፈ የፖለቲካ ፍንገጣ ያሳዩ ቀን ‹ፋይላቸው› ከመሳቢያ መውጣቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ረገድ የዛሬውን “ፓስተር” የትላንቱን “ማርክሲስት” ታምራት ላይኔን፣ የፈርዖናዊ ዕብሪት ባለቤት የነበረውን ስየ አብርሃን፣ ሴት አውሉን መላኩ ፈንታን እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል።
በህወሓት/ኢህአዴግ ቤት፣ ከሁሉም የሙስና አይነቶች ከባዱ ሙስና የመሬት ወረራን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለው ምዝበራ ዋናው ተጠቃሽ ነው። በዚህ ዘርፍ እየታየ ያለው ሙስና “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ የከፍተኛ አመራሮችን ፈለግ በመከተል ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች “ከድርሻቸው” በላይ በወዳጅ ቤተ ዘመድና በሙታን ስም ሳይቀር የመሬት ወረራውን ተያይዘውታል። የታችኛው አመራር ምዝበራ አይን እያወጣ በመምጣቱ “ኪራይ ሰብሳቢነትን እየተዋጋሁ ነው” የሚለው አገዛዙ፣ ለአስመሳይ ፖለቲካው ማሳያ ይሆን ዘንድ አልፎ አልፎ የታችኛውን አመራር ጭዳ ሲያደርገው ይታያል። ነገሩ ‹የኪራይ ሰብሳቢዎች መተካካት› አይነት ነገር ነው። የበላ ይሻራል። ያልበላ ይሾማል። ሹዋሚውና ሻሪው ህዝብ ሳይሆን የላይኞቹ የህወሓት ቁንጮ አመራሮች ናቸው። የሩብ ክፍለ ዘመኑ የአገዛዝ ተሞክሮም ኡደቱ በዚህ መልኩ እየቀጠለ እንደመጣ አመላካች ነው።
ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በተለይም ሃሰተኛ የመሬት ባለይዞታነት መረጃ በማዘጋጀትና ህጋዊ ቅድመ ሁኔታ ላላሟሉ ሰዎች በጥቅም ትስስር መሬት የመስጠቱ ሁኔታና የአመራሩ የመሬት ቅርምት ከአዲስ አበባ ከተማ በከፋ መልኩ በሌሎች የክልል ከተሞች እንዳለ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነው። በፍትህ አስተዳደር በኩልም አስደንጋጭ የሙስና ተግባር እየተፈፀመ ይገኛል። ከ50 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ በመቀበል በሃሰተኛ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፍርደኞችን የለቀቁ የፌዴራሉና የክልል ማረሚያ ቤቶች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችን እንዲሁም ከሙስና ጋር በተያያዘ የዳኞችን ክስ/ስንብት መስማት ከዓመት ዓመት እየተለመደ መጥቷል።
እንግዲህ በ“ሕግ በምትመራ” አገር ላይ ከዓመት ዓመት አስደንጋጭ የሙስና ዜናዎችን በሪፖርትም፣ በክስም መልክ እያየንና እየሰማን በመሆኑ “መንግስት” የሚባለው አካል ምን እየሰራ እንዳለ መጠይቅ ግድ ይለናል። የመሬትና የፍትህ አስተዳደርን እንደማሳያ አንስተን እጅግ በጥቂቱ ተመለከትን እንጂ ገቢዎችና ጉምሩክ ላይ እና በመንግስት የልማት ድርጅቶችና ተቋማት ምን አይነት ጉድ ሊፈፀም እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም።
በየዓመቱ ተዝቆ ከማያልቁ መንግስታዊ ጉዶች መካከል እጅግ ጥቂቱን ቆንጥሮ በሪፖርት መልኩ ለ“ተወካዮች ምክር ቤት” የሚያቀርበው የፌዴራሉ ኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርት ከአንድ ሰሞን ወሬ የተሻገረ ረብ ያለው ለውጥ አልታየበትም። ከአሳ ነባሪዎች ይልቅ ትንንሽ አሳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ “መረቡን” መጣል የሚያዘወትረው “የፌዴራል የሥነ – ምግባርና የፀረ – ሙስና ኮሚሽን” በአዋጅ የተሰጠው “ሥልጣን” መልሶ በአዋጅ ተገፏል። ኃላፊነትና ተግባሩም ሙስናን በተመለከተ ባነርና በራሪ ወረቀት በማዘጋጀት ተገድቧል።
የፍትህ ሚኒስተር በአዋጅ ፈርሶ “የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ” በሚል በአዲስ መልኩ ተደራጅቷል። አዲሱ አደረጃጀት የሥራ አስፈፃሚውን ገደብ የለሽ የንዋይና የሥልጣን ብልፅግና እየተከታተለ በህግ እንዲዳኝ ከማድረግ ይልቅ፤ ልቅ የፖለቲካ ይሁንታ የሚሰጥ ሆኖ ተገኝቷል።
አገሪቱ በአስከፊ የህዝብ አመፅ አልፋ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተው፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አካላቸው ጎድሎ፣ ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደም ደርሶ በጉይዩ ላይ ተጠያቂ የተደረገ መንግሥታዊ አካል አለመኖሩና አገዛዙ ከጊዜ ወደ ጊዜ በምልዓት እየተገበረ ያለው የህዝብ ሃብት ምዝበራ በመቀጠሉ በቀጣይ አገዛዙን የሚያፈራርሰው ህዝባዊ አመጽ ካለ ክቡር መስዋዕትነት ስለመገባደዱ መታመን የሚቻል አይደለም!!
የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች — የአንድ ጎጥ የበላይነትና የመበታተን አደጋ!
June 2, 2017 08:06 pm By Editor
ራሳቸውን “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር” ብሎ በመሰየም የትግራይን ሕዝብ ሽፋን በማድረግ፤ “የምታገለው ለአንተ ነጻነት ነው” በማለት፤ መልሶ እታገልለታለሁ ያለውን ሕዝብ ያስጨፈጨፈው፣ ያስራበው፣ የግፈ ሰለባ ያስደረገው፣ … ራሱን ህወሓት እያለ የሚጠራው የወንበዴዎች ቡድን የኢትዮጵያን የሥልጣን መንበር ከተቆናጠጠ በኋላ የትግራይ ሰዎችን በሌላው ኢትዮጵያዊ ለማስጠላትና “ስም ለማሰጠት” እንዲሁም ለማጠልሸት ባለፉት 26ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል። እነዚህ በኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ አነጋገር “የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ …” የኢትዮጵያን ሃብት እየዘረፉ በትግራይ ኢንቨስት በማድረግ፣ የትግራይ ተወላጆችን የተለያዩ ስልቶችን – ከግድያ እስከ ማስገደድ – እየተጠቀሙ የወንጀላቸው ተባባሪ እንዲሆኑ በማድረግ፤ ትግራዮችን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በማስጠላት ጉዳዩን ከራሳቸው በማውረድ በሕዝብ መካከል የሚደረግ በማስመሰል እኩይ ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። ለሆዳቸው ያደሩን በፕ/ር መስፍን አነጋገር “አእምሯቸው የሻገተባቸው” ይህንን ማታለያና ማባበያ እየወሰዱ ከሌላው የኢትዮጵያ ወገናቸው ጋር ሆድና ጀርባ በመሆን “ነጻ አውጣኝ” ብለው በስምምነት ያልሰየሙት ቡድን ባዶ ተስፋ እየሰጠ የውንብድና ተግባር ሲፈጽምባቸው የተግባሩ ተባባሪዎች ሆነዋል።
ባለፉት 26ዓመታት ከግንቦት 20 “ካተረፍናቸው” “መርዛማ ፍሬዎች” አንዱ የዘውግ ወይም የጎጥ (የጎሣ) ፖለቲካ ነው። ከዚህ የከበረው ደግሞ ላለፉት 26ዓመታት አገር “በነጻ አውጪ” ስም በግፍ እየገዛ ያለው ህወሓት ብቻ ነው!
መርዛማ ፍሬ 9. የከረረ የዘውግ ፖለቲካ!
የኢትዮጵያን አገራዊ የማንነት እሴቶች ለአዲሱ የፖለቲካ ሥርዓት ማዋቀሪያነት መጠቀም ለኢትዮጵያ የተቃውሞ ኃይሎች የተሻለ መንገድ መሆኑን የሚወተውቱት የፍልስፍና ምሁሩ ፕ/ር መሳይ ከበደ ናቸው። ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚስተዋሉት ችግሮች ሁሉ ቀዳሚና እጅግ አስቸጋሪ የሆነው ዘውጋዊ ፖለቲካ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ህወሓት/ኢህአዴግን ለመጣልና አዲስ ሥርዓት ለመመስረት ስለ ዘውግና ዘውጋዊ ፖለቲካ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት (መያዝ) አስፈላጊ እንደሆነም ይመክራሉ። “ህወሓት/ኢህአዴግ ከተሸነፈ የዘውግ ፖለቲካ በራሱ ይጠፋል” ብሎ ማሰብ ከንቱ ምኞት መሆኑን ያሰምሩበታል።
የፕሮፌሰር መሳይ ስጋት ተገቢ መሆኑን እናምናለን። ለዚህም በኢትዮጵያ የዘውግ ብሔረተኝነት ጅማሮ ከማህበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥልቅ ቅሬታ ጋር በተያያዘ የሚነሳ በመሆኑ ነው። የዘውግ ፖለቲካ ከ26 ዓመት ወዲህ የተጀመረ ሳይሆን ከዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ነገሥታት ጋር የነበረው ግንኙነትና የማዕከላዊ መንግስቱ አመሰራረት፣ አወቃቀር፣ አሰያየም፣ … ጉዞ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጭብጦችን መነሻ በማድረግ የታሪክ ጡዘት በመፍጠር በ“ጨቋኝ” Vs “ተጨቋኝ” ትርከት ዘውጋዊ ንቃት መፍጠር አገር ገንጣዩ የህወሓትም ሆነ በኢትዮጵያ “አንድነት እናምናለን” የሚሉ የዋለልኝ መኮንን “ደቀመዛሙርት”ና የእስካሁን አድናቂዎች የሆኑት የ“ያ-ትውልድ” ዘውጌ ብሄርተኞች ውርስ ምልከታ ነው። የዘውግ ብሄርተኝነት መከራከሪያውም በደልና ጭቆናው መደባዊ ይዘት ያለው አለመሆኑን በ“ማመን” የተነሳ ነው። በዚህ መሰል ትርክት በየራሳቸው የታሪክ ክህደት መስመር “አገራዊ አጀንዳ” ይዘናል ያሉትን ለጊዜው ተወት ተደርገው ህወሓት እና ኦነግ የመጨረሻ አቅማቸውን በመጠቀም በዘውጎች መካከል ደማቅ የልዩነት መስመር ለማስመር ሞክረዋል። የኢትዮጵያን ማህበረ-ባህል ኑባሬ በመፋቅ መደባዊ ጭቆናውን ወደ ዘውጋዊነት በመለጠጥ ፈጠርን የሚሉት ዘውጋዊ ንቃትም አገር አፍራሽ ሚና ከመጫወት የዘለለ አልሆነም።
የሩብ ክፍለ ዘመኑ መዋቅራዊ የዘውግ ፖለቲካ አካሄድ ፍፁም አገር አፍራሽ የሆነ የከረረ ስሜት ያለበት እንደሆነ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምስቅልቅል ገጽታ ህያው ምሳሌ ናት። አገሪቱ ውስጥ ብዙ ትንንሽ “አገሮች” እየተፈለፈሉ በመሆናቸው ዜግነትን የሚንተራሰው የጋራ ማንነት ተጨፍልቆ የ“እኛ” እና የ“እነርሱ” ባዩ በዝቷል። “ከክልላችን ውጡ” የሚለው ኃይል አከል እርምጃም የዚህ የከረረ የዘውግ ፖለቲካ ወላጅ ነው። ለብዙ ዘመናት ያለ ድንበር ከለላ አብረው ሲኖሩ የነበሩ ጎሣዎችና ዘውጎች፣ የዘውግ ፖለቲካ በከረረ መንገድ መዋቅራዊ ይሁንታ ማግኘቱን ተከትሎ በተሰሩ ሰው ሰራሽ ወሰኖች የተነሳ የማንነት ጥያቄ ለልዩነት መስፋት ሰበብ ሆኗቸዋል። እነዚህ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ባልተካለለው ድንበርና ወሰን ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በጋራ ከመጠቀም አልፈው ወደ ርስበርስ ግጭት መግባት የጀመሩት ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ነው።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ እየታዩ ያሉ የድንበር ግጭቶች በአፍሪካ በመጀመሪያዎቹ የድህረ-ቅኝ ግዛት ዘመናት ሲስተዋሉ ቆይተዋል። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የፈጠሯቸው ሰው-ሰራሽ ድንበሮች ለአፍሪካዊያን የእርስ በእርስ ግጭት መነሻ ምክንያት እንደነበሩ ታሪክ የሚያስታውሰው ነው። በአባቶቻችን ተጋድሎ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ቅኝ-ገዥ በመያዟ የድንበር ግጭቶችና ዘውግ ተኮር ትንቅንቶች መገለጫዋ ሆኗል።
ለአንድም ኅልዮታዊ ትንታኔ የማይመቸው የዘውግ ፖለቲካ በከረረ መልኩ እየተለጠጠ መሄዱ ኢትዮጵያ ይህን ክፉ ጊዜ እንዳትሻገር አንቆ ይዟታል። በአንድ ዘውግ (ለአብነት፡- ኦሮሞ) ስር ከአምስትና ስድስት በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች በተቋቋሙባት ኢትዮጵያ የዘውግ ፖለቲካ የሊሂቃኑ አቋራጭ የሥልጣን መንገድ ሲሆን ይታያል። “መገንጠልን መደገፍ በራሱ የመገንጠል እንቅስቃሴዎችን ያረግባል” የሚለው የቀደመ ምልከታ ዛሬ ላይ የበዛ ፍንገጣ የሚስተዋልበት የብተና ደወል ሆኗል። በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ሂደት ውስጥ አካባቢያዊ ማንነት ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ ዘውጋዊ መፈክሮችን ከማነብነብ ባለፈ አገሪቱ የመጣችበትን ረዥም የታሪክ ውጣ ውረድ፣ የነፃነትና የድል መንገድ እንዲሁም ማህበራዊ ስሪት በቅጡ ያላወቁ “ኢትዮጵያ” በሚለው ሥም ጥላቻ የተነደፉ ጨለምተኛ (NIHILIST) ትውልድ እዚህም እዚያም እየታየ ነው።
በተካረረው የዘውግ ፖለቲካ መስመር መሃል፣ ህወሓት ዘውጎችን የጎንዮሽ እያፋጠጠና እያጋጨ ትግራይን እንደአገር መገንባቱን ቀጥሏል። የከፋ የርስ በርስ ጦርነት ጋባዡ ህወሓት ኢትዮጵያን ወደ ብተና እየገፋት ይገኛል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዘውጋዊ ፖለቲካን ማጥፋትም ሆነ የብቻ መሰረታዊ መንገድ ማድረግ የሚታሰብ አይደለም። ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ እንደሚሉት ግን በመካከላዊ አሰራር የአገሪቱን አንድነትና ዘውጋዊ ፖለቲካ እንዲተባበሩ ማድረግ ይቻላል።
ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ርዕይና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ቅዱስ ዴሞክራሲ ያስፈልጋል። በዘመነ-ህወሓት ይህን መተግበር ቀርቶ ማሰብ በራሱ በ“ሽብርተኝነት” እንደሚያስወነጅል የ“ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬ ውጤት የሆነችው ኢትዮጵያ ህያው ምሳሌ ነች።
መርዛማ ፍሬ 10. ዘውጋዊ ኢኮኖሚክስ
የዛሬዋ ኢትዮጵያ የገዥ ኃይል አስኳል ህወሓት መሆኑን ማወቅ እንደማይከብደው ሁሉ በአገሪቱ ውስጥ ቁጥራቸው የበዛ የኢኮኖሚ ሊሂቃኖችም ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪ የተገኙ መሆናቸውን ለመጠራጠር የማይቻል ያፈጠጠ እውነት ላይ እንገኛለን። “ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረ ፖለቲካዊ የበላይነቱን ያረጋግጣል” በሚለው ድርጅታዊ “ፍልስፍና” የሚመራው ህወሓት የአገርና የህዝብ ኃብትን ለትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ማደሉን ከተያያዘው ሩብ ክፍለ ዘመን ተቆጥሯል።
ዛሬ ላይ በአደባባይ አፍጥጦ የሚታየው የትግራይ ተወላጆች የኢኮኖሚ የበላይነት እዚህ ደረጃ ለመድረስ ሦስት የሽግግር ጊዜ ማዕቀፎችን አልፏል። ሦስቱም የሽግግር ጊዜያቶች የራሳቸው የሆኑ ታሪካዊ አመጣጦች ቢኖሯቸውም የኢኮኖሚ የበላይነቱን በማፍጠኑ ረገድ ተያያዥነታቸውና ተደጋጋፊነታቸው ከፍ ያለ ነው።
ለትግራዮች የኢኮኖሚ የበላይነት መፈጠር በር ከፋች የሆነው የመጀመሪያው የሽግግር ጊዜ ድህረ-ደርግን ተከትሎ ከ1983 – 1991 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ህወሓት በአገሪቱ ላይ በዘረጋው ዘውጋዊ የፖለቲካ መዋቅር ላይ የበላይነቱን ለማስረገጥ በማዕከላዊ “መንግስቱ” እና በክልሎች በየዘርፉ በግልጽና በስውር ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚሰጡ ትግሬዎችን መመደብ የጀመረበትና የኢትዮጵያን የፖለቲካል-ኢኮኖሚ መዋቅር በራሱ ፍላጎት መቅረጽ የቻለበት ጊዜ ነበር። በመከላከያና ደህንነት፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ትግራይ ተወላጆ ቁልፍ ቁልፍ ቦታ እንዲይዙ የተደረገበት፣ የቀበሌና የኪቢያድ ቤቶች እንዲሁም የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ምሪት እነሱው በብዛት ያገኙበት፣ በተለየ መልኩ በደቡብና በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል የብቻ ኮንትሮባንድ ንግድ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገበት፣ በከተሞች የአነስተኛና መካከለኛ የንግድ እንቅስቃሴዎችን (ሸቀጣሸቀጥ፣ የልብስ ንግድ፣ ጋራዥ፣ የወርቅና ብር ቤቶች፣ …) ከኤርትራዊያን ጋር ጎን ለጎን መስራት የጀመሩበት፣ በየክፍል ሃገሩ የነበሩ የአገሪቱ ሃብቶች (እንደ ጎንደሩ ግዙፍ ጄኔሬተር፣ የጋምቤላ ጄኔረተር፣ የአዲስ አበባ ትልልቅ የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖች፣ … ወዘተ) ወደ ትግራይ ክልል በመጓጓዝ፣ የክልሉ ህዝብ አዲስ የሥነ-ህዝብ አሰፋፈር እንዲከተል በማድረግ በተለይም በምዕራብ ትግራይ ተከዜን ተሻግሮ ሁመራ፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ በጥቅሉ ወልቃይትንና አካባቢውን በመጠቅለል ነባር ህዝቡን በመግፋትና በመዋጥ ለም መሬቱን የብቻ ተጠቃሚ ለመሆን የተሰራውን ግፍ ታሪክ የሚያስታውሰው ነው። ከዚህም ባለፈ የጦርነት ፍፃሜ የብቻ ተቋዳሽ የሆነው ህወሓት ከመንግስታዊ መዋቅሩ በተጨማሪ የዘውግ ኢኮኖሚ ኢምፓየር መፍጠሪያ መሳሪያ የሆነውን ግዙፉን ኢፈርት የህዝብ ንብረቶችን በመጠቅለል እና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ ንግድና ልማት ባንክ ብድር በመውሰድ ራሱን በማግዘፍ ትግራይን እንደአገር ማደራጀት የጀመረበት የመጀመሪያው የጊዜ ማዕቀፍ ነው።
ለትግራዮች ዘውጋዊ የኢኮኖሚ የበላይነት ሁለተኛ የጊዜ ማዕቀፍ የሆነው ከኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ከተነሳ በኋላ ከ1991 – 1997 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ ነው። በድህረ-ደርግ የመጀመሪያ ጊዜያት በከተማ አፍላ ፍቅር ውድቀው የነበሩት ሻቢያና ህወሓት በድንበር ግጭት የተነሳ ሁኔታዎች መስመር ሲስቱ የኤርትራ ተወላጆ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ተደረገ። በዚህም የአገሪቱ የኢኮኖሚ ኃይል አሰላለፍ ከቀደመው የጊዜ ማዕቀፍ መጠነኛ ለውጥ የታየበት ሆነ።
ከኤርትራዊያን ስንብት በኋላ የትግሬዎች በዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እጃቸው እየረዘመ መጣ። መዋቅራዊ ድጋፍ ባለው መልኩ ኮንትሮባንድ እና ግብር አልባ ንግድን በዋና ዋና ከተሞች በበላይነት መከወን ቀጠሉ። ከንግድ እንቅስቃሴው ባሻገር በፖለቲካ መዋቅሩ ከህወሓት ዳግማዊ “ህንፍሽፍሽ” በኋላ በመለስ ዜናዊ መሪነት በጥገኞች የኢህአዴግ አልባና አጋር ድርጅቶች ታዛዥነት የትግራዮች የኢኮኖሚ ሊሂቃን ግስጋሴን የሚያቆመው ጠፋ። ከትግራይ ክልል ውጪ ያለው እንቅስቃሴ ይህን ሲመል በክልሉ ውስጥ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና ልዩ ፖሊሲዎች አፈፃፀም ከኤፈርት፣ ማረትና ትልማ ፕሮጀክቶች ጋር እየተመጋገበ ትግራይን ከድቀት ወደ ከፍታ አሻገራት።
በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባገኘው ጦርነት የደቀቀ ኢኮኖሚ ከመታቀፏ በተጨማሪ የጦርነቱ ማህበራዊ ቀውስ የከፋ ደረጀ የደረሰበት ጊዜ ነበር። ይህም ሆኖ ትግራዋያን ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ፣ ከአድዋ እስከ ቦረና፣ ከአክሱም እስከ ጅጅጋ፣ ከሽሬ እስከ ጎጃም፣ ከአዲግራት እስከ ጋምቤላ፣ … ድረስ የኢኮኖሚ የበላይነቱን ከማስቀጠል ወደኋላ አላሉም።
አዲስ አበባ ላይ በልዩ ሁኔታ በቦሌ፣ ሃያት ሁለት፣ ሳሪስ፣ ተክለሀይማኖት፣ ቄራ፣ ሲ.ኤም. ሲ.፣ ፒያሳ ባሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የትግራዮች ድርሻ ከፍ ሊል ታይቷል። መርካቶ ላይም እንዲህ እንዳሁኑ ጉልህ ባይሆንም አንፃራዊ እንቅስቃሴዎች ነበሩት። እስከዚህ ጊዜ ድረስ የትግራይ ተወላጆችን የኢኮኖሚ የበላይነት በተመለከተ በኢ-መደበኛ ወጎች ከማውራትና በነፃ-ኘሬስ ላይ ደፋር ፀሐፍት “ትግራይ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ (ሌላው አገር ይድማ)” በሚል ያሰሙ ከነበረው ነቀፌታዎች ባሻገር ጉዳዩን በፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ወደ አደባባይ የወጣ አንድም ኃይል አልነበረም። ግና፤ የዘውግ ኢኮኖሚክሱ እየባሰበት ተጠያቂነትና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የዜጎች ኢ-ፍታሃዊ የገቢ መጠን ቋንቋ ተናጋሪነትን መነሻው አድርጎ እየሰፋ በመሄዱ በቅድመ-ምርጫ 97 ወቅት ጉዳዩ የአደባባይ ሙግት ለመሆን በቃ። ዓይን አውጣነትን የተካኑበት የህወሓት ሰዎች “ትግራይ ዛሬም በጦርነት የደቀቀች ክልል ነች” በማለት ተከራከሩ። በወቅቱ የነበረው የአገር ሀብት ምዝበራ በይፋ ከካዝና ማራገፍ ወደ ምርጫ ኮሮጆ ግልበጣ አድጎ ህወሓት፣ የትግራይ ኢኮኖሚ ሊሂቃን እና ከዘውጉ ውጪ ያሉ ጥቂት ታማኝ ባለሃብቶች በንጹሃን ደም እየተረማመዱ የዘውግ ኢኮኖሚክሱን አድማስ አስፉት፤ የገቢ ኢ-እኩልነቱን ከቶም የማይደረስበት አደረጉት።
ድህረ-ምርጫ 97 ላይ ጀምሮ እስከአሁን የዘለቀው የትግራዮች የኢካኖሚ የበላይነት ጉዞ ሦስተኛው የጊዜ ማዕቀፍ ላይ የሚያርፍ ነው። ይህ ጊዜ ህወሓት በሙሉ ጉልበቱ ሆን ብሎ ትግራይንና ተወላጆቹን መጥቀም የጀመረበት ጊዜ ነው። አገሪቱ በተከታታይ አስር ትውልዶች ውስጥ ከፍላ የማትዘልቀው የብድር ዕዳ ውስጥ እየዘፈቀ በ“ልማታዊ መንግስት” ሥም የዘውግ ኢኮኖሚክሱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ቢሮክራሲው ላይ ያለው ዘረኛ ቁጥጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረና እየተጠናከረ መጥቷል። በተለይም ኢሚግሬሽን፣ ውጪ ጉዳይ፣ መከላከያና ደህንነት፣ የማዕከላዊና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ አየር መንገድ፣ ጉምሩክና የቀረጥ ጣቢያዎች፣ ባንኮች … ወዘተ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች በትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተወረሩ ናቸው። ከዚህም አልፎ በፖለቲካ ጋብቻ ትስስርና በኗሪነት ቆይታ በየክልሉ ክልላዊ “ዉክልና” የያዙ የፖለቲካ ታማኞች መፍጠር ችለዋል።
በቢልዬን ዶላሮች የሚቆጠር ካፒታል ባለቤት የሆነው ኢፈርት፣ ማረት፣ ትልማ ትግራይን እንደ አገር የመገንባቱን ዘመቻ ተያይዘውታል። ታክስ ተኮር ድጋፍ፣ የባንክ ብድር፣ የመሬት አቅርቦት፣ የተመቻቸላቸው የትግራይ ባለሃብቶች በአገሪቱ የሆቴል፣ የእርሻ፣ የኮንስትራክሽን፣ የባንክ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርት፣ በመዝናኛ፣ ማዕድን ምርት፣ የውጭ ንግድና መሰል ግዙፍ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዋል።
አብሮነታቸውንን የሚያጠናክሩ ማህበራዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ የልዩነት ግንብ እየከለልን ከመሄዳችን ባሻገር ቋንቋ ተናጋሪነትን የተንተራሰው የገቢ ኢ-እኩልነት የኢትዮጵያን ነገ እጅግ አሰፈሪ አድርጎታል። ትግራዋያን ዛሬ ላይ ያለውን እጅግ የተዛባ የሃብት የክፍፍል ከመቃወም ይልቅ ሁነቱን እንደ “ትልቅ ማህበራዊ ዕድል” በመቁጠር የዘረፋው ተሳታፊ ሲሆኑ እየታየ ነው። የነገ የብቻ ዋይታቸውን በሚያብስ መልኩ የብቻ የኢኮኖሚ ጥቅመኘነት አካሄዱ የበዛ ዋጋ እንደሚያስከፍልና ይህም በህወሓት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሤራ መሆኑ የገባቸው አይመስልም። ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲቃቃሩ ብቸኛ መጠለያቸው ህወሓትን እንዲያደርጉ የታለመ መሆኑን “እንዲጠሉ” የተደረጉት ትግራዮችም ሆነ “እንዲጠሉ” የተደረገው ሌላው ሕዝብ ቆም ብሎ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ለአንድ ዘውግ የሚደረግ የኢኮኖሚ አድልዎ በሌላኛው ዘውግ የከረረ ስሜት ከመፍጠሩ ባሻገር የፖለቲካው ታማኝ የሆኑ አካላት እኔም “የድርሻዬን” ላገኝ እንጅ “ኢትዮጵያ” ምንተዳየ የሚል ከንቱ የጥቅመኝነት ፖለቲካ አሰላለፍ ፈጥሯል። ሞራል የሌለው ትውልድም በገፍ አምርቷል። ይህ የተደረገው ደግሞ ህዝቡን ወደ ጥቅል ድህነት በመክተት ነው። ዘውጋዊ አካሄድ ባለው መልኩ ህዝቡን ሆን ብሎ ደሃ በማድረግ በኑሮ ሃሳብ እንዲጨነቅ ካደረጉ በኃላ መላወሻ ሲያጣ ሆድ አደር ተገዥ ማድረግ የህወኃት የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነው። ገንዘብ አምላኪ ህዝብ በመፍጠር ሰዎች ወንድም እህታቸውን ለጥቂት ገንዘብ ሲሉ አሳልፈው እንዲሰጡ የሚያደርግ ሰብአዊ ንጥፈት እና አልቦ-ሞራል የሆነ ትውልድ መፍጠር የህወሓት ግብ ነው።
በተለይ ይህ ሁኔታ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ የሚታይ ሆኗል። በየጊዜው ለመፍረሳቸው ዋነኛ ምክንያቶች ሞራል የሌላቸው ለጥቅም የተገዙ ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ “ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚለው የቀደመ ቃለ-ግቡነት በርቀትም እንኳ የማያውቁ የክህደት ህመምተኞች በጥቅም መደለላቸው ነው። በዘውጎች መሀከል የተፈጠረው የገቢ ኢ-እኩልነት አገሪቱን ወደ ርስ በርስ ጦርነት እየገፋት ነው። የአገሪቱ የቀደሙ ማህበራዊ ዕሴቶች መውደም እና የወንጀል መበራከት ግጭት አባባሽ ሆነው ቀርበዋል። ይህም ወደ ትግራዋያን ያዘነበለው የዘውግ ኢኮኖሚክስ ውጤት ነው። ድርጊቱም የቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ ነው። መርጠው አንዱን ዘውግ የበላይ ያደርጋሉ ከዚያ እንግሊዞች አፍሪካ ላይ በተለያዩ አገራት እንዳደረጉት አገሩን ለቀው ሲወጡ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ጥለው ይወጣሉ። የኢትዮጵያን ለየት የሚያደርገው “ቅኝ-ገዥው” ኃይል የአገር ውስጥ መሆኑና የወጣበትን ዘውግ ለይቶ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ የበላይነት መምረጡ ነው። ትግራይ በየትኛውም መጠን እንደአገር ብትሰራ እንኳ ኢትዮጵያን ለብተና ዳርጎ “ታላቋን ትግራይ” መመስረት ሊሳካ የማይችል ከንቱ ቅዠት ነው። ቅድሚያ የኢትዮጵያን ህዝብ አንጡራ ሃብት መመለስ ለድርድር የማይቀርብ ተግባር ነው። ከዚህ ባለፈ ተይዞ ያለው የነጠቃና የተገንጣይነት መንገድ በ“ጠላት” የተከበበች ትግራይ፣ መፈናፈኛ ያጣች ኩርማን አገር ከመመስረት ያለፈ አይሆንም።
ይህ መንገድ ለትግራዋያን ብቻ ሳይሆን ለራሷ ለትግራይም የሚያዋጣ አይደለም። አገሪቱን በደም ካሳ (ጉማ) መያዥያነት ሰንጎ የያዘው ህወሓት እና የትግራይ ተወላጆች ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ቆም ብለው ሊያጤኑት ይገባል። እየመጣ ያለው መዓት እንኳንስ ለትግራይ ለምስራቅ አፍሪካም ያሰጋል!!
የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች – የመንግሥት ውሸት፣ የሃይማኖት ተቋማት ውድቀት፣ … (ክፍል ሦስት)
May 30, 2017 11:00 pm By Editor
የትግራይ ሕዝብ “ነጻ አውጡኝ” ብሎ ሳይሰይማቸው፣ ሳይመርጣቸው፣ ሳይጠይቃቸው፣ ራሳቸውን “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር” ብለው የሰየሙ ወንበዴዎችና ሽፍቶች የምኒልክ ቤተመንግሥት ከገቡ 26 ዓመታት ተቆጥረዋል። በቂም፣ በበቀል፣ በክፋትና በኢሞራላዊ ተግባራት የተሞሉ፤ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ፈጽሞ የሚያጠራጥር፤ ማንነታቸው ይህ ነው ተብሎ የማይታወቅ፤ በሐሰት ስም ከበረሃ እስከ ቤተመንግሥትና ዓለምአቀፍ መድረክ ላይ የታዩ፤ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የትግራይን ሕዝብ ያስጨፈጨፉ (ሐውዜንን ይጠቅሷል)፤ ሲነሱ አንዳች ገንዘብ ያልነበራቸው መናጢዎች በበረሃ የድሃ ረሃብተኛ እህል ዘርፈው በመሸጥ፤ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያን ሐብት ሙልጭ አድርገው ዘርፈው ሲያበቁ “የራሳችን ንብረት ነው” በማለት ኤፈርት የሚባል የወንበዴዎች ሃብት ማከማቻ ቋት የፈጠሩ፤ ከበረሃ እስከ መንግሥታዊ ሥልጣን ድረስ ውሸት መለያቸው የሆነ፤ የሃይማኖት ተቋማትን ያረከሱ፤ ተዘርዝሮ የማያልቅ መርዛማነት በኢትዮጵያ የተከሉ … ህወሓት እና ህወሓታውን እነዚህ ናቸው። ዕፍረት ዓልባ ድንቁርናቸው በለገሳቸው አንደበትም እስካሁን “በነጻ አውጪ ስም” አገር ለምን እንደሚገዙ ሊያስረዱን ይሞክራሉ።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኮ/ሎ ጎሹ ከ26 ዓመት በፊት በትክክለኛ ሁኔታ ገልጸዋቸው ነበር፤ እንዲህ ሲሉ “… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” እጅግ መሳጭ የሆነውን ሙሉ ንግግራቸውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል።
የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች ክፍል ሦስት ይቀጥላል፤
መርዛማ ፍሬ 5. የ“መንግሥት” ውሸት!
በፖለቲካል ሳይንስ መዝገበ ቃላት “መንግስት” (state) የሚለው ቃል ከባህሪያት አቀራረብ አኳያ አከራካሪ እንደሆነ ይነገርለታል። “መንግስት” እንደ መንግስት ሊያሟላቸውና ሊኖሩት የሚገቡ ባህሪያት እስከሌሉት ድረስ “መንግስት” የሚለውን ቃል የሚመጥን አይሆንም። በትንሹም ቢሆን አንድ መንግስት የህዝብ ውክልና ያለው፣ በህዝብ የተመረጠ፣ ይፋዊ መዋቅሮችን በየዘርፉ ዘርግቶ ያለ አንዳች ልዩነት ለአገር ዕድገት የሚተጋ፣ ስለዜጎቹና ሉዓላዊነቱ ግድ የሚሰጠው፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች (ባለሥልጣናት) ያሉበት ስብስብ “መንግሥት” የሚለውን ቃል ከሚተረጉሙልን ጭብጦች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
ህወሓት/ኢህአዴግ ከመነሻው ጀምሮ ከአቅሙ በላይ በፕሮፓጋንዳ የተወጠረ በሃሳዊነት የቆመ እውነት ጠል ድርጅት መሆኑን የመጣበት የታሪክ መንገድ የሚነግረን እውነት አለ። በተዛቡ የታሪክ ትርክቶች እና በክህደት የታጀበውን የድርጅቱን “ሚኒፌስቶ” እያሰመርንበት ከዚህ የጥላቻ መሳሪያው የሚጨለፉ ውሸቶች ሁልቆ መሳፍርት የሌላቸው መሆናቸውን እናስታውሳለን። በበበረሃ የውንብድና ትግል ወቅት “በድምፀ ወያኔ” ራዲዮ፣ በ“ወይን”፣ “ታጠቅ”፣ … በተሰኙ የህትመት ውጤቶቹ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው አካል የነበሩ ጉዳዮች ዛሬም ድረስ ይዘታቸውን እያሰፉ በ”መንግስታዊ” መዋቅሩ በስፋት ይንፀባረቃሉ። “ለሽምቅ ውጊያ ፕሮፓጋንዳ ትልቅ ኃይል ነው” የሚለው መከራከሪያ የግራ ኃይሎች ሃሳብ ነው። ፕሮፓጋንዳ ሲባልም አንድን ጉዳይ ለጥጦና አስፋፍቶ ማውራት በሚል አግባብ ሊተረጎም ይችላል።
የህወሓት/ኢህአዴግ የበረሃ ፕሮፓጋንዳ ከዚህም የወጣ ፍፁም ምናብ ወለድ ነበር። “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የተሰኘው ተከታታይ የፈጠራ ቅፆች ለዚህ አብይ ማስረጃ ናቸው። የዚህ አይን ያፈጠጠ ውሸት ልማድ ዛሬ ላይ የምርጫ ኮሮጆን በመገልበጥ፣ የአደባባይ መንግስታዊ ፍጅትን በ“ህጋዊነት” ሽፋን ሥም በማፅደቅ፣ የአንድ ዘውግ የፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት የአገሪቱ “ዕድገት” ማሳያ አድርጎ በማቅረብ፣ ጎተራ ላይ የሌለ የገበሬ ምርት በቁጥር ፈጠራ (ድርደራ) ብቻ ያለ አስመስሎ በማቅረብ፣ የመንገድ፣ ድልድይ፣ ህንፃ እና ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማስፈፀሚያ ብር ዘርፎ የግንባታውን ሂደት በበሬ ወለደ የቁጥር (ፐርሰንት) ዘገባ አሰልቺ ዜና ደጋግሞ ከመስራት እስከ ተራራ መስረቅ ድረስ የደረሰ “መንግስታዊ” ውሸት መስማት ከተላመድን ሩብ ክፍለ ዘመን ተሻገርን።
አገዛዙ እንደአገር እያስፋፋው ያለው የውሸት ባህል በጊዜ ሂደት አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል እየለመደው በመሄዱ ህዝቡ የውሸት ባህል ነፀብራቅ ውጤት እንዲሆን አድርጎታል። ተዘቅዝቆ የተተከለን ችግኝ በሪፖርት የሚያፀድቁት የአገዛዙ ካድሬዎች በ1፡5 የጥርነፋ አካሄድ ያልታቀደው ታቅዷል፣ ያልተሰራው ተሰርቷል፣ … በሚል የሚያስተላልፉት ሪፖርት በተጠና የፕሮፓጋንዳ ስልት የ“ዜና” ግብዓት ሲሆን እየታየ ነው።
“መንግስት” ነኝ ባዩ የሽፍቶች ስብስብ የአገዛዙን ዕድሜ ለማስቀጠል ይዋሻል፣ የመንግስት ሰራተኛው ስለሚሰራው ስራ ይዋሻል፣ ነጋዴው ግብር ለማስቀነስ ይዋሻል፣ ትልልቆቹ ሙያና ሙያተኞችም ከውሸት አዙሪቱ ሲወጡ አልታዩም። የኃይማኖት መሪዎች ሃሳዊነት ባለው መልኩ የ“መንግስት” ውሸት አባሪ ተባባሪ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ አሁን አሁን “ቁጥር” የተባለ ነገር በእጅጉ የረከሰባት አገር ሆናለች። የአገሪቱ የኢኮኖሚ “ዕድገት” ላለፉት አስር ዓመታት በሁለት አሃዝ ተመነደገ ሲሉ ሕዝቡ ግን ዕድገቱን ሌማቱ ላይ አጣው፤ የጤና ሽፋኑ “100%” ደረሰ የሚለው ፕሮፓጋንዳ በኮሌራና መሰል ውሃ ወለድ በሽታዎች አስደንጋጭ ዜና የጤና ሽፋኑን አይረቤነት እያየ ነው። የአገሪቱ የትምህርት ሽፋን “96% በላይ” ደረሰ የሚለው ዜና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው የማያቋርጥ ፍልሰት፣ በከተሞች በየጎዳናው ከተበተኑ ታዳጊ ህፃናት የጎዳና ህይወት፣ ትምህርት በዞረበት ያልዞሩ ሴተኛ አዳሪዎች፣ … የትምህርት ሽፋኑ ደረሰ የተባለበት ቁጥር ላይ ለመድረሱ ብርቱ ጥርጣሬ ያድርብናል።
ከሁሉ በላይ አስፈሪው ነገር እውነት እየሰለለች ውሸት እየፋፋ መሄዱ እንደ አገር ያሉብንን ችግሮች አወሳስቧቸዋል። ከችግሮቻችን በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛታቸው የእውነትን ቀጭን መስመር ይበልጥ ገዝግዞታል። እነርሱም ያለቅጥ ይዋሻሉ፤ የማይፈጽሙትን ተስፋ እንደ ጣቃ ጨርቅ በየቀኑ ይቀዳሉ፤ ነጻነት የናፈቀውን ሕዝብ ገንዘቡን፣ ጊዜውን አንዳንዴም ህይወቱ ይዘርፉታል፤ በመጨረሻ ከህወሓት ጋር አንሶላ ሲጋፈፉ ይገኛሉ። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት እንደአገር የተጫነብን “መንግስታዊ” ውሸት ሁለንተናችን በክሎታል፤ አቆሽሾታል፤ አሳድፎታል። ከብክለቱ ለመፅዳት ማህበራዊ ወጌሻ ማግኘት ግድ ይለናል። ከዚያ በፊት ግን የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ይቀድማል። የአደበባይ “መንግሥታዊ” ውሸት ያነገሰብን አገዛዝ እስካልተነቀለ ድረስ ኢትዮጵያ ነፃ አትወጣም።
መርዛማ ፍሬ 6. የኃይማኖት ተቋማት ውድቀት!
በአስራ ሰባት ዓመቱ ወታደራዊ የደርግ አገዛዝ ጊዜ የኃይማኖት ተቋማት እመቃ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነበር። ከ“ህግ” ሽፋን ጀርባ ከደርግ ግራ ዘመም እይታ የበዛ አክራሪ የሆነው ህወሓት “መንገዴ” ከሚለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መነፅር አኳያ የኃይማኖት ተቋማቱን እንደሚመለከት ይታወቃል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ በባህሪው የየትኛውንም ተቋማት ነፃነት ከቶውንም ማየት የማይሻ፣ የተቋማቱ ነፃ ሆኖ የመንቀሳቀስ መብት ላይ ረዣዥም እጆቹን ደጋግሞ እየጫነ ሲጨፈለቅና ሲያስጨፈልቅ እንደኖረ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። በዚህ ረገድ የኃይማኖት ተቋማቱን ነፃነት በመንፈግ ፈርጣማ የፖለቲካ ክንዱን አሳርፎባቸዋል። በዚህ የተነሳ የኃይማኖት ተቋማቱ ተቋማዊና ሞራላዊ ውድቀት ላይ ናቸው።
ህወሓት ወደ በረሃ ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ “ማህበራዊ ጠላት” አድርጎ የፈረጀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ነው። በበረሃ ቆይታውም ዋልድባን ጨምሮ ትልልቅ ገዳማትን በመሰለልና በማሰለል የቤተክርስቲያናቱን ምስጢራት ሲያራክስና ቅርሷን ሲያወድም፤ ለባዕዳን ሲቸበችብ ቆይቷል። ወደ አገዛዝ መንበሩ ሲመጣም በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁለቱን (ክርስትናን እና እስልምናን) ግዙፍ ኃይማኖታዊ ተቋማት ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ዕቅዱን ዳር ለማድረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በኩል በህይወት ያሉትን ብፁዕ አቡነ መርቆሪዮስን በማባረር ኃይማኖታዊ ቀኖናውን በፍፁም በሚጋፋ መልኩ የህወሓት ጉዳይ ፈፃሚ የነበሩትን የአድዋውን ተወላጅ፣ ከመለስ ጋር አብረው የተሸኙትን አቡነ ጳውሎስን በምትካቸው የተኩበት ሁኔታ፤ በድህረ ደርግ ጊዜያት ለህወሓቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የአፈና መንገድ እና ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖታዊ ተቋም ውድቀት ጅማሬ ሆኖ ሊታይ ይችላል።
በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ማህበራዊ ቦታ ተነፍጎ የቆየውን እስልምናን በ“ኃይማኖት ነፃነት” ሥም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲያውል የቆየው ህወሓት/ኢህአዴግ በጊዜ ሂደት ከኃይማኖቱ ሊሂቃን ጋር በቀጥታ ተላትሟል። የ“አወሊያ ንቅናቄ”ን መነሻው ያደረገው ትግል የአገዛዙ ራስ ምታት ሆኖ ከርሟል። ክፉ ጠባሳው ዛሬም ድረስ አልሻረም። በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ፊት አውራሪነት “እስልምናን በቁጥጥር ስር የማዋል” እና “አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተላበሰ እስልምና የመፍጠር ዓላማ” ያነገበው ዘመቻ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ብርቱ ተቃውሞ የገጠመው በመሆኑ ለበርካታ ወጣቶች ህይወት ማለፍ፣የአካል መጉደልና የሙስሊሙ ወኪሎች “ኮሚቴዎች” በሃሳዊ ወንጀል በካንጋሮው ፍርድ ቤት በኩል ወደ እስር ሲወረወሩ አይተናል።
ህወሓት/ኢህአዴግ በግልጽ የሚታዩትን የሁለቱን ኃይማኖት “ሲኖዶስ” እና “መጅሊስ” በማይታይ ስውር መዳፉ ጨብጦ እየጋለበ ኃይማኖታዊ ተቋማቱን የፖለቲካ ክንፍ እንዲሆኑ አርክሷቸዋል። በሁሉም ኃይማኖቶች በተቋም ደረጃ በተሰገሰጉ የአገዛዙ ቅጥረኛ የኃይማኖት “መሪዎች” አገርንና ትውልድን ከጥፋት ከመታደግ ይልቅ የአገዛዙን ፖለቲካዊ የበላይነት ለማስቀጠል የሚተጉ፣ የፈጣሪን ቃል ከመስበክ ይልቅ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ “የልማት መሪ ሃሳብ” ማንነታቸውን የተቆጣጠራቸው፤ ህወሓት/ኢህአዴግን መቃወም ፖለቲካ፣ መደገፍ ግን ኢትዮጵያዊነት የሚመስላቸው፤ ከአባታዊ ተግባር በተቃራኒው ፖለቲካዊና “”ልማታዊ ሚና ያላቸው መሆኑ ለኃይማኖት ተቋማቱ ውድቀት በር ከፋች ሆኗል።
የኃይማኖት ተቋማቱ የአገዛዙን የፖለቲካ መስመር ጠብቀው እስከተጓዙ፣ የፖለቲካ ታዛዥነታቸውን በአሜን ባይነት ስሜት እስከተቀበሉ ድረስ በተቋማቱ ውስጥ ያሉትን ብልሹ አሰራሮችንም ሆነ አይን ያወጡ የዘረፋ ተግባራትን በተመለከተ ጠያቂ የለባቸውም። የቤተ-እምነቶች አፀደ በንግድ ተቋማት ተወርሮ፣ ሰማያዊ ተልዕኳቸው ቀርቶ ንግድ ተኮር የሆነ ተግባር ላይ ተዘፍቀዋል። የኃይማኖት “መሪዎች” አገዛዙ በምልዐት እያስቀጠለ ያለውን አገራዊ የዘረፋ ተግባር በየተቋማቶቸቸው አጠናክረው ቀጥለዋል። “ምላጭ ካበጠ በምን ይበጡ? ውሃ ካነቀ በምን ይውጡ?” እንዲሉ የኃይማኖት ተቋማቱ በዚህ መሰል የሞራል ልሽቀት እየተጓዙ ባሉበት ሁኔታ አገሪቱንና ትውልዱን የሚያስቡ የኃይማኖት “አባቶች” አደባባዩ ላይ ተመናምነዋል። በአገዛዙ የፖለቲካ አካሄድ እየደረሱ ያሉትን ማህበራዊ ቀውሶች ሊጠግንና ሊያሻሽል የሚችል ማህበራዊ ኃይል ከቶም በጠፋባት ኢትዮጵያ፣ የኃይማኖት ተቋማት እንደ ተቋም መውደቃቸው ሰብዓዊና መንፈሣዊ ንጥፈት የተበራከተበት ዘመን ላይ አድርሶናል።
የኃይማኖት ተቋማትን ከሰማያዊ ተልዕኮ ወደ ዓለማዊ (ፖለቲካዊ) ግብ ያወረደው አገዛዝ ራዕይ አልባ የሚባክን ትውልድ፣ የታቦታት ነጋዴ ካህን፣ ንግድና ኡላማነት የተምታታበት ሼኽ፣ ባለትዳር አማጋጭ ፓስተር፣ ፈሪሃ-ፈጣሪ የሌለባቸው ስግብግብ ነጋዴዎች (ጀሶን ከጤፍ ጋር ቀላቅለው እንጀራ ብለው የሚሸጡ አውሬዎችን)፣ … በማፍራት ረገድ ተሳክቶለታል። የዚህ ሁሉ ማህበራዊ ቁልቁለት ሥረ-ምክንያት የ“ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬ የወለደው የኃይማኖታዊ ተቋማት ውድቀት መሆኑ ችግሮቻችንን ከፖለቲካው በላይ አወሳስቦታል።
መርዛማ ፍሬ 7፡ የኢትዮጵያዊነት ፈተና!
ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ከአካባቢያዊ ማንነትና ከጎሣ በተሻገረ ለኢትዮጵያዊነት መታመን ህይወትን እስከማጣት የሚደርስ ዋጋ የሚያስከፍል አደጋ ሆኗል። እስር፣ እንግልት፣ ስቅየት፣ ስደት፣ እልፍ ሲል ደግሞ ሞት በኢትዮጵያዊነት የመታመን አደጋዎች ናቸው። በዜግነት ማዕቀፍ የሚተረጎም የጋራ ማንነት በቀጨጨባት ኢትዮጵያ ዘውጋዊ ማንነት የፖለቲካ ሜዳው መገለጫ ሆኗል። ዘመናዊት ኢትዮጵያ እንደ አገር እውን ከሆነች ወዲህ ኢትዮጵያዊ መሆን (ዜጋ) እና ኢትዮጵያዊነት እንዲህ እንደ ህወሓት የአገዛዝ ዘመን የፖለቲካ ልዩነት ምንጭ እና አከራካሪ የሆነበት ዘመን አልነበረም ማለት ይቻላል። ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ የዘውግ ፖለቲካ የሁሉም ነገር መስፈርት በመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ፈተና ላይ ወድቋል። በዚህም የአንድነት ሳይሆን የመለያየትና የቅራኔ ምንጭ መሆን በህዝቡ ዘንድ ስጋትና ውጥረት ሲፈጥር ይታያል። ዘውጋዊ ግጭቶችም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ ስፖርት ሜዳዎች ድረስ እየታዩ ነው።
በአካባቢያዊ ማንነት የታጠረ የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኙ ህወሓት የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመቅበር ረዥም ርቀት ተጉዟል። በአደባባይ “የጋራ ማንነት የለንም” የሚለውን የታሪክ ኑፋቄ ከማስማት እስከ ታሪክ ክለሳ ድረስ፣ የቀደሙ የታሪክ ቁርሾዎችን በማንሳት ትውልድ ከፋፋይ ሃውልቶችን ከማቆም እስከ የወል የማህበራዊ እሴቶችን የማጥፋት እኩይ ድርጊት፣… የደረሱ አውዳሚ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል።
ቂምን ለትውልድ በማውረስ ኢትዮጵያዊነትን እያከሰመ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ለመሹለኪያ ይሆነዉ ዘንድ ትግራይን እንደ አገር የመገንባት ሂደቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። የቅኝ ገዥ ባህሪ የሚንፀባረቅበት ይሄው ድርጅት ኢትዮጵያን እንደ አገር ያቆሟትን አገራዊ አዕማዶች በማፍረስ ተጠምዷል። በርግጥ በዚህ እኩይ ተግባር የተጠመደው ህወኃት ብቻ ሳይሆን በተቃውሞ ጎራው ያሉት የዲያስፖራ አክራሪ ዘውጌ ብሄርተኞችም የድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው። የሳይበር ልፈፋው መዋቅራዊ ድጋፋ ካለው የህወሓት አፍራሽ ድርጊት ጋር የሚነፃፀር እንዳልሆነ ግን እንረዳለን። የግራ ቀኙ አዉዳሚ ተግባር አገሪቱን ወደብተና እየገፋት ይገኛል።
የትላንቷ ኢትዮጵያ ፍጹም ልክ ነበረች ማለት ተገቢ ባይሆንም የጊዜውን አስገዳጅነት የተከለች ነፃ አገር ኢትዮጵያ መመስረቷ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይመስለንም። በዚህ አግባብ ኢትዮጵያዊነት በጭፍን የሚቀበሉት ውርስ ቀኖና አይደለም። ይልቁንም እንደዘመኑ ማህበረ-ፖለቲካ የለውጥ ሂደት እየተገለጸ የሚሄድና የሚሻሻል አካታች አገራዊ ምልከታ ውጤት ነው።
የትላንት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዛሬው የኢትዮጵያዊነት እርሾው የሚዘነጋ አይደለም።ይህም ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ባለበት መርገጥ ግድ የሚለው አጀንዳ ሳይሆን ተራማጅነቱን የማያቋርጥ የጋራ ቤት ምስረታ (አገረ-መንግስት) ሂደት ባካተተ መልኩ የዛሬዋን ኢትዮጵያ የሚመጥን የኢትዮጰያዊነት ስሜት ለመፍጠር የተሻለ መንገድ እንደሆነ ይስማናል። ኢትዮጵያዊነት ከአካባቢያዊ ማንነት በተሻገረ ዜግነትን የተንተራሰ የአገራዊ ምልከታ ውጤት ነው። በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ያሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቅርሶች መገለጫቸውና ሃብትነታቸው አገር አቀፍ እንዲሆን የሚያስችል መዳረሻውን (ግቡን) የጋራ ማንነት በማጠናከር ላይ የሚያተኩር አገራዊ ስሜት ነው።
እውነታው ከዚህ በተቃራኒው እየሆነ መሆኑ ግን ኢትዮጵያዊነትን ፈተና ላይ ጥሎታል። የኢትዮጵያዊነት ፈተና በማወሳሰቡ ረገድ ደግሞ ህወሓት መዋቅራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ ሌት ተቀን ተግቶ እየሰራበት ይገኛል። በርግጥ ኢትዮጵያዊነት ከተጋረጠበት ፈተናም ሆነ ከቀደመ ውርስ ቀኖናዊ ባህሪው ተሻግሮ አካቶነት ያለው የጋራ ማንነት ማሳደግ የሚችል የአገራዊ ስሜት መገለጫ እንዲሆን ከተፈለገ የ“ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬ ባለቤት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ላይ መቅበር ግድ ይላል።
መርዛማ ፍሬ 8. የሰላማዊ ትግል መጨፍለቅ!
በ1987 ዓ.ም በብዙ ንትርኮች ግን ደግሞ በህወሓት/ኢህአዴግ ርዕዮት ዓለም የተቀነበበው “ሕገ-መንግስት” ሲፀድቅ፤ ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ ለቀጠሉ የህዝባዊ ተቃውሞ ጥያቄዎች መስረታዊ መነሻ የሆኑ ጭብጦችን ቢያካትትም የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲመጣ ሊጠቀም ይችላል የሚያስብሉ አንቀፆችን አካትቶ ነበር። ለዚህ መሰሉ ተስፈኝነት አስተዋፆኦ ያደረጉት ደግሞ፣ በሰነዱ ላይ የተካተቱት በነፃ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት፣ እንዲሁም በምርጫ ፖለቲካ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ የሚያስችሉ አንቀፆች መኖራቸው ነበር።
ይሁንና ከነእንከኑ “ሕገ-መንግስቱ” ከፀደቀ ማግስት ጀምሮ በተደረጉት ተከታታይ ፌዴራላዊና የአካባቢ “ምርጫዎች” የመድብለ ፖርቲ ሥርዓት ህልው የሚሆንበትን ዕድል በመጥበብ ጀምሮ ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ ተዘርግቷል። በአገሪቱ የፖለቲካ ተቋማት መቃብር ላይ የቆመው አገዛዝ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት”ን ወደ “ህወሓት/ኢህአዴግ ምክር ቤት” ቀይሮታል። የፖለቲካ ምህዳሩን በመዘጋጋት የተጠመደው አገዛዝ መንግስታዊና ህዝባዊ ሃብትን በመጠቀም እስከ እያንዳንዱ ቤተሰብ በወረደ የ1፡5 ጥርነፋ አወቃቀር ጠቅላይ አምባ ገነንነቱን አደንድኖታል።
አገዛዙ የተቃወሞ ፖለቲካ አመራሮችን በማስር፤ በማሳደድ እና በማዳከም የብቻ የረዥም ጊዜ ገዠነቱን ለማፅናት ብዙ ርቀት ሄዷል። ይህም የአፈና መንገድ፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን ከጅምሩ ከመቀልበሱ ባሻገር በ“ሕገ-መንግስቱ” የተቀመጠውን የመድብለ-ፓርቲ ፖለቲካን የመመስረት ህዝባዊ ዕድልን አጨልሞታል።
በውጤቱም አገሪቱን ወደብተና የሚገፉ ህዝባዊ አመፆች እዚህም እዚያም ገንፍለው ወጥተዋል። ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የኃይል አማራጭን የሙጥን ያለው አገዛዝ መንግስታዊ ፍጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። አገዛዙ የመጣበትን መንገድ ምርጫቸው ያደረጉ የነፃነት ኃይሎች በሚያደርሱት ጥቃት አገሪቱን “መንግስት” አልባ አስመስሏታል። በጎንደርና ባህርዳር አካባቢ በየጊዜው እየፈነዱ ያሉ ቦምቦች የጋዛ ሰርጥን ውጥረት የሚያስታዉስ ሆኗል። የፖለቲካ ነፃነት እጦት እና የሰላማዊ ትግል መጨፍለቅ ወደ ህዝባዊ አመጽ እና የህብዑ ጥቃት እንደሚገፋ የህወሓቷ ኢትዮጵያ ከበቂ በላይ ምሳሌ ነች።
ህወሓት/ኢህአዴግ “እታመንለታለሁ” የሚለውን “ሕገ መንግስት” በመጨፍለቅ የሚስተካከለው የፖለቲካ ኃይል የለም። “ሕገ-መንግስት” መኖሩ ትዝ የሚለውም ሆነ የሚያስታውሰው በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎችንና የፓርቲ-ፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦችን ከነፓርቲያቸው ለመምታት “ህገ – መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ …” የሚል ሃሳዊ የውንጀላ “ክስ” ለመመስረት ሲፈልግ ብቻ ለመሆኑ በተደጋጋሚ የታየ እውነታ ነው።
የኢትዮጵያን ማህበራዊ ስሪት በቅጡ መረዳት ባልቻሉት የትግራይ ሽፍቶች የሚመራው ህወሓት በበረሃ በኩል በምዕራባውን አንጋሾቹ ተረድቶ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የሰላማዊ ትግል ጀምበር ለአፍታ ፈንጥቃ ተመልሳ በማዘቅዘቋ ብረት ማንሳት ብቸኛ የነፃነት መንገድ ሆኖ ቀርቧል። አሁን ባለው ዘውጋዊ መካረር ኢትዮጵያን ለርስ በርስ ጦርነት የቀረበች አገር አድርጓታል።
የችግሩ መውጫ ጫፍ ከነፖለቲካዊ ልዩነቶቻችንም ቢሆን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ ላይ ሙሉ ኃይልን ማሳረፍ ያልተፈተሸው የትግል መንገድ ነው በማለት በርካታዎች ይከራከራሉ። ነውጥ አልባ ትግልን በፍጹም ልባቸው የሚደግፉና የሚያምኑበት ደግሞ በትክክለኛው አልተሞከረም እንጂ ነውጥ አልባው መንገድ ለኢትዮጵያ ችግር ፍቱን ነው ይላሉ፡፡ እስካሁን በኢትዮጵ የተካሄደውን ትግል ሰላማዊ የፓርቲ ምርጫ ትግል እንጂ እውነተኛ ነውጥ አልባ ትግል አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
የግንቦት ሃያን መርዛማ ፍሬዎች በተከታታይ ዕትም መዳሰሳችን ይቀጥላል።
የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች – የመሬት ነጠቃና ስደት (ክፍል ሁለት)
May 28, 2017 03:03 pm By Editor
የዛሬ 26 ዓመት ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ብሎ የሰየመ የወንበዴዎችና የሽፍታዎች ስብስብ በምዕራባውያን አንጋሾቹ ታግዞ የምኒልክን ቤተመንግሥት ከተቆጣጠረ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቃላት እንደ እሣት እየተፉ ታሪክ ፈጽሞ ሊረሳው የማይችለውን ንግግር ያደረጉት ድንቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ – ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ!! ስለ ኤርትራ መገንጠል እና ስለ ህወሃት የአስፈጻሚነት ተግባር የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የትንቢት ያህል፤ ሳግ እየተናነቃቸው ይህንን ነበር የተናገሩት፤
“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” እጅግ መሳጭ የሆነውን ሙሉ ንግግራቸውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ በአስተዳደሩ ተመስግኖ በክብር የተሸኘ ገዥ ስለመኖሩ የሚያወሳ ታሪከ-ድርሳን ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስልም። ሁሉም አገዛዞች የተወገዱት በአመፅ አልያም በተፈጥሮ ሞት ነው። ልክ የዛሬ 26 ዓመት 1983 ዓ.ም. ወርሃ ግንቦት በምዕራቡ አለም ረዳትነት በጠመንጃ ወደ ሥልጣን የመጣው አፓርታይዳዊው የህወሓት ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በቀደሙት ገዥዎች የብረት ጫማ ውስጥ ተከልሎ አፈናና ግድያውን “ግፋ በለው!” ማለቱን አላቆመም። በዚህ መንግሥታዊ ፍጅቱ ከትውልዱ ጋር ክፉኛ ተላትሟል። አሁን በተጨባጭ እየታየ ካለው ህዝባዊ ብሶት አኳያ የአገዛዙ ግብአተ መሬት ሩቅ አይመስልም።
በቀደመው ዕትማችን የ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች በሚል ስለከሸፈው የፌዴራል ሥርዓት እና የትምህርት ፖሊሲው ክስረት ማስነበባችን ይታወሳል። እነሆ በክፍል ሁለት ዕትማችን የአፓርታይዳዊ አገዛዝ አራማጁ ህወሓት ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የዘራቸውን በርካታ መርዛማ ፍሬዎች መካከል ሁለቱን ብቻ ከማሳያዎች ጋር ማስነበባችን እንቀጥላለን።
መርዛማ ፍሬ 3. የመሬት ነጠቃ
የኢትዮጵያ የቀደሙ ነገሥታት መደባዊ ይዘት ባለው መልኩ ከሚነሳባቸው የህዝብ አስተዳደር በደል ውጪ የግዛት ማስፋፋት እና አንድነት ጥበቃ ረገድ እጅጉን አኩሪ ታሪክ አላቸው። ከመሬት ጋር የተያያዘው ግዛት የማስፋት ሁነት ጋር በተያያዘ እትዮጵያዊ ሁሉ ሞቱን ሲያስብ “የአገሬ አፈር ይብላኝ” በማለት ለመሬቱ ያለውን ፍቅር ይገልፃል። እትብቱንም ከመሬት ጋር በማስተሳሰር “እትብቴ የተቀበረበት” ሲል ፍቅሩን ይገልፃል። ይህ የተለየ ተዛምዶ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረ ቢሆነም ዛሬ ላይ በተቃራኒው የእፍረት ምንጭ እየሆነ ነው። ህወሓት መሀሉን አገር ዳር እያደረገው ህዝቡ ችግር ላይ ወድቋል። በየቀየው የህዝቡን መሬት የሚቀራመቱ ባዕዳን በገዥው ኃይል አመቻማችነት ይጠራሉ። ገዥዎቻችንም በዘር ማንዝራቸዉ ሥም መሬትን ባሻቸው መጠን መቀራመታቸውንም ተያይዘውታል።
ስለመሬት ጉዳይ ስናነሳ ቀዳሚው ጥያቄያችን የየዋህ ዜጋ ጥያቄ መሆን አለበት፣ “እኔ አገሬ የምላት ኢትዮጵያ፣ ጎኔን የማሳርፍበት የቤት መስሪያ ቦታ በሊዝ ግዛ የምትለኝን ነው?!” “ያ – አድማስ ይታያችኋል? … እስከዚያ ድረስ የሰፈሩትን አባወራዎች አንሷቸውና መሬቱን አልሙበት” በሚል ለባዕዳን ቀያችን የሚሸጥ ሰው በላ አገዛዝ በምን አግባብ “መንግሥት” ብለን ልንጠራው እንችላለን? እዚህ ላይ በተለይ በውጪ የሚገኙ የሚዲያ ውጤቶች ይህንን አፋኝ ቡድን “የህወሓት መንግሥት” እያሉ ሲጠሩ ስንሰማ እርስበርሱ የሚጋጭ ነገር እየተናገሩ መሆናቸውን አለማስተዋላቸው ብዙዎች የታዘቡት ነው። “አገዛዝ” መባልም ሲበዛበት ነው።
ዜግነት፣ የመሬት ባለቤትነት መገለጫ ነው። ዜግነት በዚህ መሬት ላይ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የባለመብት ድርሻን ህጋዊ አድርጎ የሚደለድል የፍትህ ምርኩዝ ነው። በኢትዮጵያ መሬት ላይ መኖር፣ መክበርና መከበር፤ ለመሬቱ ከመሞት ጋር የተያያዘ መብትና ግዴታ ነው። መብቱ ከሌለ ግዴታው የለም፤ ግዴታ ከሌለ መብትም የለም።
ለህወሓት/ኢህአዴግ የመሬት ጉዳይ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ የደም ስሩ ነው። “መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” በሚል “የገጠሩም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው” በሚል ያወዛግባል። “ህዝብ” ማነው? “ብሔሮች” እነማን ናቸው? “ብሔረሰቦች” የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? … 26ዓመታት አልፈዋል መልስ ግን የለም!!!
በ“ህዝብ፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች” ብያኔ ላይ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወተው ህወሓት “መሬት አይሸጥም አይለወጥም” ባለበት አንደበቱ የ“ሊዝ ህግ” በማውጣት የመሬት ሽያጭ ንግዱን አጧጡፎታል። በከተሞችም ሆነ በገጠር የሚታየው የመሬት ነጠቃ የዜግነት መብትን የጨፈለቀ “በላኤሰባዊ” አካሄድ ነው። በከተሞች ያለው የመሬት ቅርምት ህወሓት ከሚከተለው “ዘውጋዊ ኢኮኖሚ” ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው። በተለይም የሊዝ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምር መዋቅራዊ ድጋፍ ያላቸው የትግራይ የኢኮኖሚ ሊሂቃን እና የገዥው ኃይል ተለጣፊ ባለሃብቶች በዋናነት አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ዋና ዋና ከተሞች ያሻቸውን ያህል የቦታ ስፋት ነባር ነዋሪውን በማፈናቀል ቅርምቱን አጠናክረው ቀጥለዋል፡ የሊዝ ክፍያው የሚፈፀመው በረዥም ጊዜ ሂደት መሆኑና ከባንክ ብድር መመቻቸቱ ደግሞ ባለሃብቶቹ ሰብዓዊነት በጎደለው አልቦ ርህራሄ ያሻቸውን ድሆዎች አፈናቅለው የህንፃ ባለቤት ይሆናሉ። አልያም መሬቱን ያለከልካይ አጥረው ይይዛሉ። ድሆቹን ዘወር ብሎ የሚያያቸው አንድም አካል የለም። “የልማት ተነሽ” ከሚለው መጠሪያ ስማቸው በስተቀር የሚተርፋቸው አንድም ጥሪት የለም። በዚህ መሰል የሚገፉ ዜጎች መውደቂያቸው እንደ “ቆሼ” ባሉ ቦታዎች ይሆናል።
ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያዊያንን የመሬት ባለቤትነት መብት በመካድ ትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪነትንና ፖለቲካዊ ታማኝነትን መለኪያ ባደረገ መልኩ ለመሬት ቅርምቱ አገዛዙ ይሁንታ ሲሰጥ እየታየ ነው። በ“ልማት” ሥም ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ በገዛ መሬታቸው ላይ ጥበቃና የቤት ሰራተኛ ሆነው ሲቀጠሩ እየታየ ነው። እንዲህ ላለው በደል አዲስ አበባ ከበቂ በላይ ማሳያ ነች። በጆሞ፣ ሲ.ኤም.ሲ.፣ ገላን፣ የካ አባዶ፣ መሪ፣ ለገጣፎ፣ … ወዘተ ባሉ ኮንዶሚኒየምና ሪል ስቴት መንደሮች የጥበቃ፣ የልብስ አጣቢነት፣ የአትክልት ሰራተኝነት፣ … መሰል ስራዎችን ከሚሰሩት ሰራተኞች ውስጥ ከዓመታት በፊት የመሬቱ ባለቤት የነበሩትን ዜጎች ፈልጎ ማግኘት የሚከብድ አይደለም። “መንግስተ ሰማያት የእግዚአብሔር፣ ቤት (ኮንዶሚኒየም) የገብረ እግዚአብሄር ነው” የሚለውን የአዲስ አበቤዎች መራር ቀልድ በመስመር መሃል ማስታወሱ የመሬት ተቀራማቹን ማንነት ይበልጥ የሚያሳብቅ ይመስላል።
በክልል ከተሞች እና በገጠር አካባቢዎች የ“ኢንቨስትመንት” አማራጭ በሚል የዜጎች ከመሬት መፈናቀል፣ ከግጦሽ መሬት መባረርና በግዴታ የሚፈፀም የመንደር ምስረታ በተጨማሪም የደን መጨፍጨፍና የብርቅዬ የዱር እንሰሳት መሰደድ ከመሬት ቅርምቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተጨባጭ ጉዳቶች ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል እና አፋር ክልል ወደር የለሽ የመሬት ቅርምት ሰለባዎች ናቸው።
ርካሽ መሬት፣ በአነስተኛ ወጪ የሚገኝ የሰው ኃይል፣ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ ታክስ ተኮር የሆነ መንግስታዊ ድጋፎችን የሚያገኙት፣ የቻይና፣ የህንድ፣ የሳውዲ አረቢያ፣ የቱርክ፣ … ባለሃብቶች መሬትን በተመለከተ ከህወሓት ጋር በአፍላ ፍቅር ወድቀዋል። የሰፋፊ መሬት ስጦታው በቅርምት የሚተረጎም ቢሆንም ህወሓትና ኩባንያዎቹ (የውጪ ባለሃብቶች የሚመሯቸው) በተድበሰበሰ እና እጅግ ምስጢራዊ በሆነ የንግድ ስምምነት መሬቱን እየተቀባበሉት ይገኛል። በተለይም በጋምቤላና በምስራቅ ኦሮሚያ በብሔራዊ ፓርክነት ተወስነው የተከለሉት ድንበሮች ሳይቀር ተጥሰው ለህንዱ ካሩቱሪና ሳዑዲ ስታር ባለሃብቶች መሬቱ ተቸብችቧል። የመሬት ቅርምቱ አስከፊነት ደግሞ እነዚህ ሰፋፊ መሬቶች ለኢንቨስተሮቹ ሲተላለፉ በስምምነቱ ቀዳሚ ተጠቂ የሚሆኑትን የአርብቶ አደሮችን እና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ፍፁም የዘነጋ መሆኑ ነው።
ለምርት ግብዓት የሚሆኑ ቁሶችን በመጠቀም ምርታማነትን መጨመር፣ ከግብርና ጋር በተያያዘ ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ሴክተሮች መሻገር እንዲሁም ያልታረሱ መሬቶችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚሉት አማራጮች የኢትዮጵያ ገበሬዎች የዕድገት አማራጮች ቢሆኑም መሬትን እንደ ዓይኑ ብሌን የሚያየው ህወሓት በአማራጭ ኢንቪስትመንት ሥም ለውጭ ባለሃብቶች፣ ለትግራይ የኢኮኖሚ ሊሂቃን እና ለተለጣፊ (ሎሌዎች) የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ለም መሬት ማደሉን ተያይዞታል። በዚህም ባሉበት ከመርገጥ ወርደው የበይ ተመልካችነት እና ምፅዋት ጠባቂነት ደረጃ ላይ የደረሱት አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በአስር ሚሊዮን ይቆጠራሉ። 26ኛው የ“ግንቦት 20 በዓል” እየተከበረ ባለበት በዚህ ዓመት እንኳ አገዛዙ በይፋ ባመነው አህዛዊ መረጃ መሰረት 7.8 ሚሊዮን ህዝብ (በአብዛኛው ገጠር) የዕለት ምግብ ደራሽ ተረጂ ነው። ህወሓት ከቁጥር ጋር ያለበትን ችግር ስናስተውል የረሃብ አደጋ ያንዣበበባቸው የዕለት ምግብ ተረጅ ዜጎች ከተጠቀሰው ቁጥር በእጥፍ እንደሚልቅ መረዳት ይቻላል።
ህወሓት/ኢህአዴግ በኢንቨስትመንት ሥም ለመሬት ነጠቃው ይሁንታ ሲሰጥ፤ መሬቱን ነዋሪዎችን ከቀያቸው በማፈናቀል ከማቅረብ በተጨማሪ ከቀያቸዉ በመፈናቀላቸዉ የተቆጡ ዜጎች አንዳችም ጥቃት እንዳያደርሱ መከላከልና የአፈና እርምጃ ለመውሰድ ለባለሃብቶች የገባው ግዴታ አለ። በዚህ ረገድ በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልል የታየው ተከታታይ አፈና እና ግድያ ህወሓት ለባለሃብቶቹ ለገባው ግዴታ መገለጫ ይሆናል።
በውጪ ኩባንያዎች ስር ያለ የመሬት መጠን (በተለይ ካልተጠቀሰ ቦታዎቹ ጋምቤላ ናቸው)
ተ.ቁ የድርጅቱ ስም አገር የተረከበው የመሬት መጠን (በሔክታር) ምርመራ
1 ካሩቱሪ ህንድ 300,000 ሊዝ
2 ቢ ኤች ኦ ህንድ 27,000 “
3 ቨርዳንታ ሀርቨስት ህንድ 3,012 “
4 ሁናን አግሪ ካልቸር ቻይና 25,000 “
5 ቻድሃ አግሮ (በኦሮሚያ) ህንድ 122,000 “
6 ኢማሚ ባዮቴክ (በኦሮሚያ) ህንድ 80,000 “
7 ሻምፓርጂ (ቤንሻንጉል) ህንድ 50,000 “
8 ሳኡዲ ስታር ሳኡዲ አረቢያ 139,000 “
9 ሳናቲ አግሮ ህንድ 10,000 “
10 ሩቺ ሶያ አግሪ ህንድ 25,000 “
11 ላኪ ኤክስፖርት ህንድ 5,000 “
ምንጭ “Dessalegn Rahmato, Land to investors: Large-Scale Land Transfers in Ethiopia, 2011″
ከዚህ በላይ የተመለከተው ሰንጠረዥ በኢንቨስትመንት ሥም በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለውን የመሬት ቅርምት ይበልጥ የሚያሳይ መረጃ ነው። እነዚህ የውጭ ድርጅቶች ታክስ ነክ መንግስታዊ ድጋፍና የባንክ ብድር አገልግሎት ተመቻችቶላቸው በርካሽ የሰው ኃይል እና በተስማሚ አየር ንብረት በመታገዝ፤ በለም መሬታችን ላይ እንዳሻቸው ሲያዙ የነበሩ/የሚያዙ መሆናቸውን እያስመርንበት ከዚህ ከልካይ አልባ ፍቃድ ጀርባ የህወሓት ባለሥልጣናት የያዙትን ዘረፋ መረዳት አይከብድም። የጋምቤላ መሬት ቅርምት ጉዳይ በዚህ የሚያልቅ ሳይሆን ከውጪ ባለሃብቶች በላይ የትግራይ ተወላጆችን ገደብ የለሽ የንዋይ ፍቅርን በሚያንፀባርቅ መልኩ መሬቱን ወርረው የያዙበትን ሁኔታ አያይዘን ማስታወስ እንወዳለን። የጋምቤላ አርብቶ አደሮችንና አርሶ አደሮችን ዜግነታዊ መብት በሚጨፈልቅ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ነጠቃ የአፓርታይዱን አገዛዝ የሚያስታውስ ነው።
ከመሬት ነጠቃው ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ለጅቡቲ መንግስት 3 ሺህ ሄክታር ለጥራጥሬ ምርት፣ የህንድ ኩባንያዎች ለሆኑት ለኢማሚ ባዮቴክ 80 ሺህ ሄክታር ለጃትሮፋና ለምግብ ዘይት ዘር፣ ለአልሚደሃ ኩባንያ 28 ሺህ ሄክታር ለሸንኮራ አገዳ፣ ለሮምቶን አግሪ ኩባንያ 10 ሺህ ሄክታር ለቲማቲም ምርት በሚል መሬቱ በሊዝ ተቸብችቧል። በደቡብ ክልል ከ2001 ዓ.ም. ጀምር 200ሺህ ሄክታር የሚያካልል 16 የኢንቨስትመንት ስምምነት ተደርጓል። እያንዳንዱ ኢንቨስትመንት ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ ሲሆን ሁሉም የተሰጠው ለውጭ ባለሃብቶች ነው። በአፋር ክልል 409,678 ሄክታር መሬት በማዕከላዊ መንግስቱ መሬት ባንክ አማካኝነት ለባለሃብቶች ተመድቧል። በአማራ ክልል በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እንደተዘገበው ከ175 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለውጪ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት ተመድቧል (በአጠቃላይ የመረጃ ምንጭ፡ “the Oakland Institute’’)
ከዚህ በላይ የተመለከቱ መረጃዎች በኢትዮጵያ ያለውን
የመሬት ነጠቃ ከብዙ እጅግ በጥቂቱ አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ።
የመሬት ቅርምቱ በለስ የቀናቸው የውጪ ኩባንያዎች በኢንቨስትመንታቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማስረፃቸው ቀርቶ በጉልበትና በአነስተኛ የሙያ ተግባራት ለሚቀጥሯቸው ኢትዮጵያዊያን ክብር ሲሰጡ አይታይም። ዝቅተኛ ወርሃዊ ደመወዝ ከመክፈል ጀምሮ የጤና ኢንሹራንስ በመንፈግ፣ በቂ የመኖሪያ አካባቢ እና ደህንነት መጠበቂያ መንገዶችን ባለመፍጠር፣ የሰራተኞችን የጡረታ ሽፋን አለመክፈል፣… የመሳሰሉ ችግሮች ኩባንያዎቹ ዘወትር የሚወቅሱባቸው በጎ ያልሆኑ ተግባሮቻቸው ናቸው።
ገጠር ከተማ ድረስ ባደረሰው የመሬት ነጠቃ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በዋናነት ትግሬዎች መሆናቸውን ስናስብ ከመጋረጃው ጀርባ በአገር ላይ ተይዞ ያለውን ህወሓታዊ ቁማር አብዝተን እንድንኮንነው እንገደዳለን። “ግንቦት 20” ካበቀለብን መርዛማ ፍሬዎች አንዱ የመሬት ነጠቃ ነው። አገዛዙ መሬትን በተመለከተ በያዘው ቀኖናዊ ምልከታው ላይ የሽፍታ ባህሪው ታክሎበት የዘረፋ ምንጩ አድርጎታል። ከመሬት ነጠቃው ጋር በተያያዘ የህዝብ ብሶት ጫፍ እየረገጠ በመምጣቱ ህወሓት/ኢህአዴግ ከፈኑን በሚሰፋ፣ መቀበሪያውን እየቆፈረ ባለ ቅርብ ወራጅ (ሟች) ይመስላል።
መርዛማ ፍሬ 4፡ ስደት
የኢትዮጵያዊያን የስደት ታሪክ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያስቆጠረ፣ እንደየጊዜ ማዕቀፉ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መነሻ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም ካለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ ያለው የስደት ታሪካችን በአመዛኙ ከፖለቲካ ነፃነት እጦቱ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። በዘመነ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለው የስደት ጭብጥ መነሻው ዘረኝነት ባጠላበት አፓርታይዳዊ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ የተፈጠሩ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለስደቱ አባባሽ ምክንያት ሁነዋል።
ምሁር ጠል በሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ሸፍጥ የተነሳ አገር ጥለው በተሰደዱ ምሁራን ቁጥር ኢትዮጵያን ከዓለም አገራት ቀዳሚ ተጠቂ ከሆኑት ውስጥ የሚያሰልፋት የOnlineuniversities.com ዘገባ፤ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያብራራል። እንደ ሪፖርቱ መደምደሚያ ባለፉት አስር አመታት ብቻ ኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚሆኑትን የላቁ ምሁራን በስደት ምክንያት አጥታለች። የህክምና ባለሙያዎች የሚበዙበት ይኽው ስደት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ሳይሆን በህዝቡ ጤና መጓደል ላይ ጭምር ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።
በቦሌ በኩል ያለው አስፈሪ የስደት መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ በሞት ሸለቆ ውስጥ የመጓዝ ያህል በሚከብደው የሰሃራ በረሃ የስደት ጉዞ ውስጥ በአሸዋው ተውጠው ፣ በቀይ ባህር ሰጥመው ፣ በአክራሪ እስላማዊ ቡድኖች ታፍነውና ታርደው፣ … የቀሩት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከግምት በላይ ነው። ብዙ ህልም ይዘው ቢወጡም ገንዘባቸው ባክኖ ህልማቸው ከመብነኑ ባሻገር ህይወታቸውን ያጡት፣ የመንፈስ ስብራት የደረሰባቸው ዜጎች የ“ግንቦት ሃያ” መርዛማ ፍሬ ሰለባ ናቸው።
በህገ-ወጥ መንገድ ከሚሰደዱ ዜጎች ውስጥ 60% የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ UNHCR (2013፣ 2014፣ 2015፣ 2016) ሪፖርት የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ሄዷል። ስደተኞቹ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የዘለቀ የትምህርት ደረጃ ያላቸው፣ አነስኛ የሙያ ክሂል ባለቤት የሆኑ፣ የሚሰደዱበትን አገር መዳረሻ በቅጡ ያልለዩ፣ ከውጪ አገር ዜጎች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ ችግር ያለባቸው መሆኑ የስደተኞቹን መከራ አብዝቶታል።
በሲጋራ ፍም ሰውነታቸው የተለበለበ፣ አሲድ ሰውነታቸው ላይ የተደፋባቸው ፣ ለወራት ተገደው የሚደፈሩ፣ የሰውነት አካላቸውን (ኩላሊት) የተቀሙ (Organ Traffic) ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ታሪክ መስማት የተለመደ ሆኗል። እንደ የመንና ሊቢያ ባሉ መንግስት አልባ አገራት በኩል የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን በሽብርተኛ ቡድኖች በመታገት አስከፊ እንግልት፣ ስቅየትና ግድያ ይደርስባቸዋል። በእገታ የሚያዙ ስደተኞች በአሸባሪ ቡድኖች አስገዳጅነት አገር ቤት ያሉ የቤተሰብ አባላት ገንዘብ እንዲልኩ እንደሚገደዱም በየጊዜው የምንሰማው የመከራ ዜና ነው።
በደቡብ አፍሪካ፣ በሊባኖስ፣ በኩዌት፣ በቤሩት፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ … ወዘተ በመሳሰሉ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በግፍ ተገድለው በአደባባይ መጣላቸውን፣ በመኪና አደጋ ህይወታቸው ማለፉን፣ ከፎቅ ላይ ራሳቸውን በመፈጥፈጥ ህይወትቸውን ማጥፋታቸውን … መሰል አሰቃቂ የዜና ዘገባዎች እንደ ሜትሮሎጂ ዘገባ በየዕለቱ መስማት ከጀመርን ውለን አድረናል። የዜጎቹ የመከራ ዜና ግድ የማይሰጠው ህወሓት/ኢህአዴግ በብዙ ጭንቀትና መከራ ስደተኞቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ለቤተሰብ መደጎሚያ ወደ አገር ውስጥ መላካቸው የምንዛሬ እጥረቱን የሚሸፍንለት በመሆኑ ህገ ወጥ ስደቱንም ቢሆን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል። የአገዛዙ ጭንቀት የምንዛሬ እጥረት እንጅ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የመከራ ህይወት ግድ አይሰጠውም።
ምዕራባዊያኑም ቢሆን ለራሷ ዜጎች መሆን አቅቷት በወደቀ አገዛዝ ስር የምትከላወስ አገር መሆኗን እያወቁ “ኢትዮጵያ የስደተኞች ቤት” ሲሉ ከደቡብ ሱዳን የምንሻል መሆናችንን በምፀት ይነግሩናል። ራሱን ከሱማሌያ እና ከኤርትራ ፈራሽ “መንግሥታት” ጋር የሚያወዳድረው ህወሓት/ኢህአዴግ የራሱን ዜጎች አሰቃቂ የስደት ገመና ደብቆ ስለጎረቤቶቹ ያወራል።
የኢትዮጵያን ድንበሮች ተሻግሮ የሚደረግ ስደት እጅግ የከፋ አደጋ ያለው ተግባር መሆኑ እየታወቀ ኢትዮጵያዊያኑ ወጣቶች ወደ ኋላ አላሉም። በየጊዜው ከሚመጡ መረጃዎች አኳያ የስደቱ ቀዳሚ ተሳታፊ ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ (አዲስ አበባን በውስጠ ታዋቂነት ይዘን) ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ክልሎች ህወሓት/ኢህአዴግ ምን ያህል የበረታ በደል እንደሚፈጽም አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነው። ከዚህ እውነታ አኳያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ስደትን ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ብቻ በመነሳት በፍቃዳቸው የሚያደርጉት አለመሆኑን መረዳት እንችላለን። ይልቁንስ ከፖለቲካ መዋቅሩ ዘረኛ አካሄድ የተነሳ የኢኮኖሚ የኃይል ምንጮች (የገቢ ሁኔታ) ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመንፀባረቁ ውጤት ነው። በጥቅሉ ስደት ከ”ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬዎች ውስጥ አንዱ ነው ስንል የኢኮኖሚ ውድቀቱ ከፈጠረው ጥልቅ ድህነት ባሻገር በፖለቲካ ጉዳይ በገፍ የተሰደዱ/ የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር የበዛ በመሆኑ ጭምር ነው።
“ጠላት” ካላበዛ ህልውናውን የሚያስረግጥ የማይመስለው ህወሓት/ኢህአዴግ በግፍ ጭቆና አስመርሮ ከአገር የሚያስወጣቸው ኢትዮጵያዊያን የአገዛዙ ራስ ምታት ሲሆኑ እየታየ ነው። የዲያስፖራው ፖለቲካዊ መከፋፈልና የውስጥ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአገዛዙን ውድቀት በማፋጠኑ ረገድ ዲያስፖራው ደጋፊ ኃይል ነው። ላወቀበትም የመርዛማ ፍሬው ማርከሻ (ማምከኛ) ከምንጩ ዳር ይገኛል።
ኢትዮጵያን ላለፉት 26 ዓመታት በግፍ ሲገዙ የቆዩት የህወሓት/ኢህአዴግ ፖሊሲዎች ያፈሩት እነዚህን መርዛማ ፍሬዎች ብቻ አይደሉም። የእነዚህ ፖሊሲዎች ባለቤቶች ግን ማን እንደሆኑ ከላይ በመግቢያው ላይ ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ በሚገባ ተናግረውታል። እንዲህ ነበር ያሉት፤
“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …”።