ከዚህ ቀደም “የአማራ-ብሔርተኝነት ከየት ወደየት?” የሚል ፅኁፍ ፅፌ ከጨረስኩ በኋላ በስህተት ከኮምፒውተሬ ውስጥ ስላጠፋሁት ሳይታተም ቀረ። ፅኁፉ በዋናነት “ቤተ-አማራ” የሚባለው ቡድን በሚያቀነቅነው የአማራ-ብሔርተኝነት ላይ ያጠነጠነ ነበር። በእርግጥ እንደ ኢህአዴግ ያለ ጨቋኝ ስርዓት ዜጎች የሚያነሱትን የእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን በኃይል ማፈን ባህሪው ነው። የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ሲታፈን ደግሞ የማህብረሰቡ የፖለቲካ ልሂቃን የብሔርተኝነት ስሜት ማቀንቀን ይጀምራሉ።

ስዩም ተሾመ

“የአማራ ብሔርተኝነት” መነሻ ምክንያት የአማራ ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል መታፈኑ ነው። በመሰረቱ “ብሔርተኝነት” የሕዝብ ንቅናቄ ለመቀስቀስ (mobilization) እና ለማዳፈን (demobilization) ዋና መሳሪያ ነው። የመከፋፈል መርሆችን (Principles of division) በማስቀመጥ የሚታወቀው ፈረንሳዊው ተመራማሪ “Bourdieu” የአንድ ሀገር ሕዝብን የመከፋፈል መሰረታዊ ዓላማና ግብን እንዲህ ይገልፀዋል፡-

“Principles of division function within and for the purposes of the struggle between social groups…What is at stake in the struggle is power over the classificatory schemes and systems which are the basis of the representations of the groups and therefore of their mobilization and demobilization: the evocative power of an utterance which puts things in a different light” Distinction. A social critique of the judgement of taste, 1984.

ከዚህ አንፃር፣ ለምሳሌ የቀድሞ የሕውሃት መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ አና በደርግ መንግስት በኃይል ሲዳፈን የትግራይ ልሂቃን የብሔርተኝነት ስሜትን ማቀንቀን እንደጀመሩ ይገልፃል። በመጨረሻም፣ በብሔርተኝነት ስሜት በመቀስቀስ (mobilization) እና በራስ-የመወሰን መብትን (rights of self-determination) ተስፋ በመስጠት የሕወሃት የትጥቅ ትግል ተጀመረ። በሕወሃት መሪነት የተመሰረተው ኢህአዴግ የደርግ ስርዓት ከስልጣን ካስወገደ በኋላ በብሔር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ የአፓርታይድ ስርዓት ዘረጋ።

የብሔር-አፓርታይድ ስርዓት ዓላማና ግብ ደግሞ በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ (majority) ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ሕዝብ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዳፈን (demobilization) ነው። ለዚህ ደግሞ ባለፉት አስር አመታት የኢህአዴግ መንግስት የግምገማ ሪፖርቶች ውስጥ “ትምህክተኝነት” እና “ጠባብነት” የመንግስታዊ ስርዓቱ አደጋዎች በሚል ያልተገለፁበት ግዜ የለም። ብሔርተኝነትን እያቀነቀነ ወደ ስልጣን የመጣው ሕወሃት መራሹ የፖለቲካ ቡድን የአማራና ኦሮሞ ሕዝብን የመብትና ነፃነት ጥያቄ “ትምክህተኛ” እና “ጠባብ-ብሔርተኛ” እያለ ያሸማቅቃል። “ትምክህተኛ” እና “ጠባብ-ብሔርተኛ” የሚሉት “Bourdieu” – “the evocative power of an utterance which puts things in a different light” የሚለው ዓይነት ፋይዳ ያላቸው ቃላት ናቸው።

በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ንቅናቄ የሚወስደው ወደ እርስ-በእርስ ጦርነት ሲሆን መጨረሻው ደግሞ ጨቋኝ ስርዓት መፍጠር ነው። በምንም ዓይነት ተዓምር ቢሆን የብሔርተኝነት ንቅናቄ ወደ ዴሞክራሲ አያደርስም። በመሆኑም፣ ብሔርተኝነት ለሚታገሉለት ሕዝብ መብትና ነፃነት ሆነ ለጎረቤት ሀገር ሰላምና ደህንነት አይበጅም። ለምሳሌ፣ ብሔርተኝነትና በራስ-የመወሰን መብትን ዓላማ አድርገው የተነሱት ሕወሃትና ሻዕቢያን እንመልከት።

በራስ-የመወሰን መብት በክልል ደረጃ ራስን-በራስ ከማስተዳደር እስከ መገንጠል ሊደርስ ይችላል። ሕወሃት ብሔርተኝነት እያቀነቀነ በጀመረው የትጥቅ ትግል አሸንፎ የትግራይ ሕዝብን ራስን-በራሱ እንዲያተዳድር አደረገ። ነገር ግን፣ መብትና ነፃነትን ከማረጋገጥ አንፃር ግን የኢህአዴግ የብሔር ፖለቲካ ለትግራይ ሕዝብ ሆነ ለተቀረው የኢትዮጲያ ህዝብ ከአምባገነንነት ሌላ ያመጣው ትርፍ የለም። በተመሳሳይ፣ የኤርትራ ብሔርተኝነት እያቀነቀነ የትጥቅ የጀመሩት የኤርትራ አማፂያን ከኢትዮጲያ በመገንጠል የራሳቸው ሉዓላዊ ሀገር መሰረቱ። ነገር ግን፣ አሁንም ድረስ የታሪክ ቁስል ከማከክ በዘለለ የኤርትራዊያንን መብትና ነፃነት አልተከበረም። የትጥቅ ትግል ከጀመሩበት የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ መንግስት ቀርቶ ከወታደራዊ ደርግ የባሰ ጨቋኝና ጦረኛ የሆነውን የሻዕቢያ መንግስት ከመፍጠር ባለፈ በኤርትራዊያን መብትና ነፃነት ሆነ በጎረቤት ሀገሮች ሰላምና ደህንነት ላይ ያመጡት ለውጥ የለም።

በአጠቃላየ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቼም ቢሆን የብዙሃንን መብት፣ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አያስችልም። የብሔርተኝነት መጨረሻ ጦርነትና ጨቋኝ ስርዓት ነው። ምክንያቱም፣ የብሔርተኝነት ፅንሰ-ሃሳብ በራሱ ከነፃነት ይልቅ በጠላትነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ብሔርተኝነት የሰው-ልጅን ሰብዓዊነት ገፍፎ ከተራ እንስሳት በታች ያደርገዋል። በእርግጥ አገላለፁ ኃይለ-ቃል የተቀላቀለበት ወይም ግነት የበዛበት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ እውነታው ይሄ ነው። ብሔርተኝነት ሰውን ከተራ እንስሳት ለምሳሌ፣ ከቀበሮ፥ ጅብ፥ ውሻ፥… በታች ያደርገዋል። በኢ-ሰብዓዊነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ንቅናቄ መጨረሻው የሰዎችን ሰብዓዊ መብትና ፖለቲካዊ ነፃነት የሚገፍፍ ጨቋኝና ጦረኛ መንግስታዊ ስርዓት መመስረት ይሆናል። በቀጣዩ ክፍል “ለምንና እንዴት?” የሚለውን በዝርዝር እንመለከታለን።

ብሔርተኝነት የሰው-ልጅን ወደ አውሬነት ይቀይራል (ክፍል-2)

ታላቁ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዜያብሄር አሁን ርዕሱን በረሳሁት ድርሰት ውስጥ በውሻና ሰው መካከል የተደረገ ቃለ-ምልልስ አለ። ሰውዬው ከሚጠጣው አረቄ ትንሽ የቀመሰው ውሻ ሲሰክር በሰውኛ ዘይቤ መሳደብ ይጀምራል፤ “እኛ ውሾች እንደ ሰው “እኛ” እና “እናንተ” ብሎ አናውቅም” ይላል። ባለቤቱ “እንዴት ባክህ?” ሲለው “በቃ…ሁላችንም “እኛ” ነን” ይለዋል። ደራሲው ጋሽ ስብሃት በዚህ ቃለ-ምልልስ ያስተላለፈው መልዕክት በደንብ የገባኝ ከአራት አመታት በኋላ ነው፡፡

የጋሽ ስብሃት ሃሳብ የገባኝ “Edmond Leach” የተባለውን ምሁር ትንታኔ ካነበብኩ በኋላ ነው። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ከሰው ልጅ በስተቀር በሁሉም እንስሳት ዘንድ አንድ ዝርያ እስከሆኑ ድረስ ሁሉም “እኛ” ናቸው። ለምሳሌ፣ ውሻ ጥቁር ሆነ ነጭ፣ የፈረንጅ ሆነ የሀበሻ፣ የጀርመን ሆነ የአሜሪካ፣…ወዘዘተተ ሁሉም ደመ-ነፍሳዊ በሆነ የምልክት ቋንቋ ይግባባሉ። ስለዚህ፣ ውሾች ሲጣሉ ሆነ ሲፋቀሩ የሚግባቡበት፥ ስሜታቸውን የሚገልፁበት የጋራ መግባቢያ አላቸው።

የሰው ልጅን ጨምሮ ሁሉም እንስሳት አንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ባህሪ አላቸው። እሱም “ፀብና ጥቃት” (aggression) ውጫዊ እና ውስጣዊ አይደለም። ማለትም፣ የውሻ ፀብና ጥቃት ለምሳሌ በጅብ፥ ቀበሮ፥…ላይ እንጂ የራሱ ዝርያ በሆነ ሌላ ውሻ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። በእርግጥ በውሾች መካከል የእርስ-በእርስ ፀብና ጥቃት ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን፣ በጣም በተለየ አጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር አንድ ውሻ በሌላ ውሻ ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት አይፈፅምም። ብዙ ግዜ ታዝባችሁ እንደሆነ፣ አንድ ጉልበተኛ ውሻ ለፀብ ወይም ለመናከስ እየሮጠ ሲሄድ ሌላኛው ውሻ ጭራውን እያወዛወዘ ከተለማመጠው ወይም መሬት ላይ ከተኛ አይነክሰውም። እዚህ ጋር ሊሰመርባቸው የሚገቡ ሁለት ነጥቦች አሉ። አንደኛ፡- ጉልበተኛው ውሻ የሚፈልገው የሌላውን ውሻ ተገዢነት ወይም ተሸናፊነት ነው፣ ሁለተኛ፡- ውሾች በፀብና ግጭት ውስጥ የሆነው እንኳን እርስ-በእርስ በምልክት ይነጋገራሉ፥ ይግባባሉ።

ከሁሉም እንስሳቶች በተለየ የራሱን ዝርያ የሚገድል ፍጡር የሰው-ልጅ ብቻ ነው። “Edmond Leach” ይሄን ኢ-ተፈጥሯዊ የሆነ የሰው ልጅ ባህሪ በዋናነት ከሰው ልጅ የቋንቋ አጠቃቀምና አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይገልፃል። በእርግጥ የሰው ልጅ ሁሉም ነገር ከራሱ አንፃር የማየት ባህሪ አለው። ቋንቋችንም ከዚሁ አንፃር የተቃኘ ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ሰው ለራሱ ቅርብ የሆኑትን ሰዎች፤ እናት፥ አባት፥ ልጆች፥ እህት፥ ወንድም፥ ልጆች፥…ወዘተ ያሉትን “እኛ” ሲል ከዚህ ቀረቤታ ውጪ ያሉትን ደግሞ “እነሱ” ይላል።

“የእኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። “እኛ” የስዩም ቤተሰቦች ከሆንን የጋሽ ስብሃት ቤተሰቦች “እነሱ” ናቸው፣ “እኛ” አሰላዎች ከሆንን “እነሱ” አደዋዎች፥ አሳይታዎች፥…ናቸው። “እኛ” ኦሮሞች ከሆንን እነሱ አማራዎች፥ ትግሬዎች፥ ወላይታዎች፣ “እኛ” ኢትዮጲያዊያን ከሆንን “እነሱ” ግብፃዊያን፥ ኤርትራዊያን፥ ጀርመናዊያን፣ “እኛ” በምድር ላይ የምንኖር ሰዎች ከሆንን “እነሱ” በሌላኛው ዓለም የሚኖሩ “መናፍስት”…ወዘተ ናቸው።

በጣም ቅርብ የሆኑትን “እኛ” ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት ይቻላል። በጣም ሩቅ የሆኑትን “እነሱ” ደግሞ ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት አይቻልም። ለእኛ በጣም ቅርብ የሆኑትን ስራና ተግባር በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም በንግግር መግባባት ስለሚቻል የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም። ለእኛ በጣም ሩቅ የሆኑት ደግሞ በእለት-ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ስለሌላቸው ምንም ስጋትና ፍርሃት ሊፈጥሩ አይችሉም።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። በዚህ መሰረት፣ ሩቅ ባሉት “እነሱዎች” እና ቅርብ ባሉት “እኛዎች” መካከል ሌላ ሦስተኛ “እነሱዎች” አሉ። እነዚህ ሦስተኞቹ “እነሱዎች” ከቦታና ግዜ አንፃር ለእኛ ቅርብ ቢሆኑም ሥራና ተግባራቸውን ግን በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም ተነጋግሮ መግባባት አይቻልም። “በእኛዎች” እና በሦስተኛ “እነሱዎች” መካከል ላለው ልዩነት መነሻ ምክንያቱ ተነጋግሮ መግባባት አለመቻል ነው። “እኛ” እና “እነሱ” በሚለው እሳቤ መሰረት፣ ሰዎች የተለየ ቋንቋ ሲናገሩ፣ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ሲሳናቸው፣ በዚህም አንዱ የሌላውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅና መገመት ሲሳነው፣ “እኛ” ሰዎች፥ ሌሎቹን ደግሞ ከሌላ የእንስሳት ዝርያ የመጡ ለምሳሌ “ውሾች” አድርገው ይስላሉ።

የሰው ልጅ በቅርቡ ካለ ሰው ጋር መነጋገርና መግባባት ከተሳነው፣ በዚህም የሰውዬውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅ ሆነ መገመት ከተሳነው፣ አንዱ በሌላው ላይ ስጋትና ፍርሃት ይጭራል። በቅርብ የሚኖሩ ሰዎች የማይነጋገሩ፥ የማይግባቡ፥ የማይተዋወቁና የማይተማመኑ እርስ-በእርስ እንደ ሌላ ፍጡር መተያየት ይጀምራሉ። አንዱ ራሱን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያየ ሌላውን ግን እንደ አውሬ ማየት ይጀምራል። እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ይህን ግዜ የሰው ልጅ ከሰብዓዊነት ወደ አውሬነት ይቀየራል፡-

“…our propensity to murder is a back-handed consequence of our dependence on verbal communication: we use words in such a way that we come to think that men who behave in different ways are members of different species. In the non-human world whole species function as a unity. …If anything in my immediate vicinity is out of my control, that thing becomes a source of fear. This is true of persons as well as objects. If Mr X is someone with whom I cannot communicate, then he is out of my control, and I begin to treat him as a wild animal rather than a fellow human being. He becomes a brute. His presence then generates anxiety, but his Jack of humanity releases me from all moral restraint: the triggered responses which might deter me from violence against my own kind no longer apply.” A Runaway World: Lec. 3: Ourselves and Others, 1967   

ከሰው ልጅ በስተቀር ሌሎች እንስሳት ምንም ያህል ቢራራቁ ወይም ቢቀራረቡ፣ አንድ ዓይነት ዝርያ እስከሆኑ ድረስ በምልክት ቋንቋ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ስለዚህ፣ በመካከላቸው ምንም ያህል ልዩነት ቢፈጠር አንዱ ሌላውን እንደ ሌላ ዝርያ ፍጡር አይመለከተውም። እዚህ ጋር ጋሽ ስብሃት በሰውኛ ዘይቤ “በውሾች ዘንድ “እኛ” እና “እነሱ” የሚባል ነገር የለም” ያለው ማስታወስ ተገቢ ነው። በእርግጥ ውሾች አንድ ዓይነት መግባቢያ ቋንቋ አላቸው። ስለዚህ፣ ከጎንደር ሆነ አሳይታ፣ ከአክሱም ሆነ ወላይታ፣ …ከየትኛውም አከባቢ የመጡ ውሾች እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ነገር ግን፣ ከተጠቀሱት አከባቢዎች የመጡ ሰዎች በአንድ ቦታ ቢገናኙ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት አይችሉም።

እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ሁለት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች በጋራ ጉዳይ ላይ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ከተሳናቸው አንዱ ራሱን እንደ ሰው ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) ማየት ይጀምራል። ይሄ ነገር ግን በውሾች መካከል አይከሰትም። በመሆኑም፣ ሰዎች በብሔርና በዘር ቡድን መስርተው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እርስ-በእርስ ሲጨፋጨፉ ውሾች ግን ሁሉም “እኛ” ስለሆኑ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም። በአጠቃላይ፣ በ”እኛ” እና “እነሱ” እሳቤ ከሚመራው የሰው ልጅ በስተቀር የአንድ ዝርያ እንስሳት እንዲህ በጭካኔ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እርስ-በእርስ መገዳደል እንደ ማንኛውም እንስሳ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ አይደለም። የሰው ልጅ ግን በዘር/ብሔር/ሀገር ተቧድኖ እርስ-በእርስ ይገዳደላል። ለዚህ ዋናው ምክንያት አንዱ ወገን ራሱን እንደ ሰው፣ ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) መመልከቱ ነው። የሰው ልጅ ራሱን “እኛ” እና “እነሱ” ብሎ ለመመደብ የሚጠቀምበት ዋና መለያ መስፈርት “ቋንቋ” ነው። በተመሣሣይ፣ አንድን ብሔር ከሌላው ለመለየት አንዱና ዋንኛው መስፈርት ቋንቋ ነው። በሀገራችን በስፋት የሚስተዋለው የብሔርተኝነት ስሜት በዋናነት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው።

ስለዚህ፣ “ብሔርተኝነት” ሁለት ጎን-ለጎን የሚኖሩ የተለያየ ብሔር ተወላጆችን እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) እንዲተያዩና እንዲጨካከኑ፣ በዚህም እርስ-በእርስ እንዲገዳደሉ በሚያደርግ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅን የአውሬነት ባህሪ እንዲላበስ በማድረግ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። እንዲህ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቼም፥ የትም ቢሆን ሕዝብን ወደ ጦርነትና እልቂት የሚወስድ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ብሔርተኝነት በራሱ የጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት ውጤት ነው። በአማርኛ መዝገበ ቃላት “ጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት” የሚለውን፤ “ጥልቀት የሌለው፣ በስፋት የማይገነዘብ፥ አርቆ ማየት የጎደለው” የሚል ፍቺ አለው። በተመሳሳይ፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው ደግሞ “ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፣ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። ስለዚህ፣ ከብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ከእኛ ያነሰ ክብርና ዋጋ መስጠት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህ አንፃር፣ ብሔርተኝነት የአንድን ብሔር መብትና ነፃነት ከማረጋገጥ ባለፈ ራስን ከሌሎች የተሻለ አድርጎ በማሰብ ወይም ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ዝቅተኛ ግምትና ክብር በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ራሱ ጎሳ ብቻ የሚያስብና በሌላው ላይ ጥላቻ ያለው የፖለቲካ ቡድን ከራስ-ክብር (Self-respect) ይልቅ በራስ-ወዳድነት (Egoism) የሚመራ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ለራስ ክብር (Self-respect) የሚደረግ የነፃነትና እኩልነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም የሰብዓዊነት (humanity) እና የጋራ እሰቶችን (common values) በማስረፅ የሚካሄድ ነው።

በራስ-ወዳድነት (Egoism) የተመሰረተ የብሔርተኝነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት ሳይሆን የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም በዋናነት የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም ብሔር ተወላጆችን ልክ እንደ አውሬ በመመልከትና በኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ጭካኔ የተሞላ ነው። ታዋቂው ፈላስፋ “Jean Jacques Rousseau” እንዲህ ያሉ በበታችነትና በራስ-ወዳድነት ስሜት የናወዘ የፖለቲካ አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች ያለ ምንም ምክንያት ወይም ጉዳት ወደ ፍፁም አውሬነት ሊቀየሩ እንደሚችሉ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…men who neither valued nor compared themselves could do one another much violence, when it suited them, without feeling any sense of injury. In a word, each man, regarding his fellows almost as he regarded animals of different species, might seize the prey of a weaker or yield up his own to a stronger, and yet consider these acts of violence as mere natural occurrences, without the slightest emotion of insolence or despite, or any other feeling than the joy or grief of success or failure.” WHAT IS THE ORIGIN OF INEQUALITY AMONG MEN, AND IS IT AUTHORISED BY NATURAL LAW?, 1754, Trans. by G. D. H. Cole.

በአጠቃላይ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፍፁም ስህተት ከመሆኑ በተጨማሪ የአውሬነት መገለጫ ነው። በማንኛውም ግዜ ቦታ ቢሆን በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሀገርን ወደ የእርስ-በእርስ ጦርነት የሚያስገባና ጨቋኝ ስርዓት በመዘርጋት የሚቋጭ የድኩማኖች መንገድ ነው። በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅ አውሬነት መገለጫ ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት የሚደርግ ሕዝባዊ ንቅናቄና ትግል እንዴት መጀመርና ምን መሰረት ማድረግ እንዳለበት በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።