June 24, 2017

(በአቻምየለህ ታምሩ)

የሪፖርተሩ መስራች አማረ አረጋዊ የታላቋን ትግራይ ሪፑብሊክ ለመመስረት ጫካ የገባ ፋኖ ነው። ወያኔ አዲስ አበባ እንደገባ በኢሳያስ አፈወርቂ ትዕዛዝ የተካሄደውን የመለስ ዜናዊ፣ የፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ የዶ/ር መኮንን ቢሻውና የእንድርያስ እሸቴ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መርቷል። ከዚያ ከወያኔ ወጣሁ አለና ሪፖርተርን መሰረተ።

የቁርጡ ቀን ሲመጣ ሪፖርተር ጋዜጣ ከአይጋ ፎረምና ትግራይ ኦንላይን ቀጥሎ እንደ ሩዋንዳው ሬዲዮ ሚሌ ኮሊንስ ዝቅተኛውን የጋዜጠኝነት መስፈርትን የማያሟሉ የትግራይ ፋሽስታዊ ብሔርተኞች በኢትዮጵያ ምድር የዘር ማጥፋትና እልቂት እንዲካሄድ ቤንዚን የሚያርከፈክፉበት የፕሮፓጋንዳ ምድጃ ነው።

የአማረ አረጋዊው ሪፖርተር ጋዜጣ በዛሬው (06/21/2017) እለት ባሰራጨው የዜና ዘገባው ከአንድ ዓመት በፊት ወያኔ ቀለብ የሚሰፍርላቸው ምንደኞች በማህበራዊ መገናኛዎቻቸው ይፋ ያደረጉትን አዲስ የወያኔ ካርታ በጥቅም ላይ አውሏል። ይህ የወያኔ ካርታ ከተግባራዊነቱ በመለስ ምንም ያልቀረውን አማራና ኦሮሞን ዙሪያውን በማነቅ በሱዳንና በጎንደር-ወለጋ መካከል እየተዋሰነ ቤንሻንጉል የሚባለውን ክልል ጠቅልሎ ጋምቤላን በማቀፍ በመለስ ራዕይ መሰረት የምትመሰረትዋን “ከመረብ እስከ ባሮ የተዘረጋች የታላቋ ትግራይ ሪፑብሊክ” ፍኖተ ካርታን የሚያሳይ ነው።

በዚህ ዘገባው ተጋዳላይ አማረ አረጋዊ ድርጅቱ ወያኔ በ1968 ዓ.ም. ባወጣው ማንፌስቶ ያቀደውን “ታላቋ ትግራይን” የመመስረት አላማ ከፍጻሜ በማድረስ ረገድ “የመለስ ራዕይ” እየተባለ ሲንቆለጳጰስ ከከረመው የነ አባይ ፀሐዬና ስዩም መስፍን ፕሮግራም ቀድሞ ለመገኝት የቆረጠ ይመስላል።

አማረ አረጋዊ ባሳየን የወያኔ ካርታ መሰረት ለሺ ዘመናት ሲዋሰኑ የኖሩት ጎጃምና ጎንደር ከሱዳን ጋር አይዋሰንም። ወለጋም ከሱዳን ጋር አይዋሰንም። ከሱዳን ጋር የሚዋሰነው ከትግራይ ክልል ጋር እንዲዋሰን የተደረገው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚባለው ክልል ነው። ከትግራይ ክልል ጋር እንዲዋሰን የተደረገው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ በሱዳንና በወለጋ መካከል እየተዋሰነ ከጋምቤላ ክልል ጋር በቀጥታ እንዲዋሰን ተደርጓል።