June 25, 2017

በህዝብ ተቃውሞና ትግል የተወጠረው የጎሰኞች ስብስብ የሆነው የህወህት/ኢህአዴግ አፋኝ አገዛዝ ከዓመት በፊት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞና አመጽ ለማፈንና ብሎም ለማጥፋት የጊዜያዊ አዋጅ ማወጁ የሚታወቅ ነው። አዋጁና አዋጁን ተከትሎ በህዝቡ ላይ የሚወሰደው ግድያ፣ አፈና፣ እስራት…ወዘተ በደቡብና በመካከለኛው ያገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ለጊዜው የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ የገታው ቢመስልም በአገሪቱ ሰሜናዊ ግዛቶች በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋና በወሎ የህዝቡን ትግል ሊያዳፍነው ቀርቶ መቋቋም አልቻለም።  ስለሆነም ሌላ ተጨማሪ የእልቂት እርምጃ ለመውሰድ በይፋ በማወጅ ተንቀሳቅሷል።

የኢትዮጵያን ህዝብ በሀይል ለማንበርከክና ህገሪቱንም ለመበታተን በእቅድ ደረጃ ያስቀመጠው መሆኑ ግልጽ ሲሆን ያንን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የጥፋት አዋጁን በጎንደር፣ በጎጃምና በአካባቢው ላይ ይፋ አድርጓል።

ይህንንም የጥፋት አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግም

1ኛ በአየርና በእግረኛ ሜካናይዝድ ጦር የተሟላ ያገሪቱን የመከላከያ ሃይል ያሳተፈ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር በጎንደርና በአካባቢው አስፍሮ በመንቀሳቀስ ላይ ነው።

2ኛ አልበገር ያለውን ህዝባዊ ትግል ለማዳከም ህዝቡን ትጥቁን እንዲፈታና እጁን እንዲሰጥ ቤቱን እየበረበረ፣ እየደበደበና እየገደለ በማስገደድ ላይ ተሰማርቷል።

3ኛ ህዝቡ ትግሉን ካላቆመ የመጨረሻ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት የሚያሳስብ የሽብር ማስጠንቀቂያ ከመስጠትም አልፎ በተግባር እየገለጸው ሄዷል።

እንዳለፈው ጊዜ በጋዜጣዊና በሬዲዮ መግለጫ ሳይሆን ያገሪቱ ቱባ ባለስልጣኖች የመንግስታቸውን እቅድ በይፋ በግልና በመንግስታዊ መስመራቸው እየገለጹ ነው፤ ለዚህም ከሁለት ቀናት በፊት የአገዛዙ ቁንጮ ባለስልጣን የሆነው ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የተሰጠውን መግለጫ እንመልከት፦

«በሃገራችን በቅርቡ ተከስተው የነበሩ ብጥብጦች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻል ሁኔታ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህም ሊሆን የቻለበት ዋነኛ ምክንያት መንግስት ለህዝቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠቱና ነውጥ ፈጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ በማቅረቡ ነው።ነገር ግን አሁንም ቢሆን በአንዳንድ ክልሎች ያልረገቡ ነገሮች ይታያሉ። ከነዚህም መካከል ጎንደር ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። መንግስታችን ይህንን አካባቢ ለማረጋጋት ያለውን አቅም በሙሉ አሟጦ በመጠቀም ላይ ቢሆንም ጥረቱ ሙሉ በሙሉ ሊሳካ አልቻለም።በዚህም ሳቢያ በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ የጎንደርን አካባቢ ሙሉ በሙሉ ከጦር መሳሪያ ነጻ ለማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረ በመሆኑ በአካባቢው የምትገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ለሰላምና ለመቻቻል ሲባል የጦር መሳሪያዎቻችሁን በየአካባቢያችሁ ለሚገኙ የሚሊሽያ አመራሮች በማስረከብ ለሰላም የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ አሳስባለሁ።»

ከዚህ በላይ የሰፈረውን የባለስልጣኑን የሽብር መልእክት ስናይ መንግስት ነኝ ባዩ ቡድን አልበገረ ያለውን የጎንደር ህዝብ ለማንበርክከክ ቆርጦ እንደተነሳ እንገነዘባለን።  የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ቀላሉና ሰላማዊ መፍትሄ ሆኖ ሳለ የዚህ ዓይነት ትዕቢት፣ ሽብርና የጭፍጨፋ ስልት ይበልጥ ሁኔታውን ያባብሰዋል እንጂ አያበርደውም።  ከአንድ መንግስት ነኝ ከሚል ቀርቶ ከተራ ሽፍታ የሚጠበቅ የጥፋትና የሽብር መልእክት አይደለም።  ህዝብን እንደጠላትና አሸባሪ ቆጥሮ የሚንቀሳቀስ ሃይል ወይም መንግስት እራሱ አሸባሪ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ይህን አረመኔያዊ የአገዛዙን ሽብር እያወገዘ ለዓለም ማህበረሰብ፣ ለመንግስታትና ለሰብአዊ መብት ተቋማት በህዝቡ ላይ የሚሰነዘረውንና ለመሰንዘር የሚቃጣውን ዛቻ ከዝግጅቱ ጀምሮ እንዲያወግዙት ይጠይቃል።  ኢትዮጵያውያን ድርጅቶችና ስብስቦችም ሃይላቸውን አሰባስበው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ይህንን የጥፋት ዘመቻ አንዲያክሽፉ ጥሪ ያደርጋል።  የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ይህንን አገዛዙ ለአረመኔያዊ ድርጊቱ የሚያደርገውን ዝግጅት ለማጋለጥ፣ የሕዝብን ትግል ለመደገፍና የአገዛዙን እኩይ ተግባር ለማምከን በጋራ እንቁም።  አንድነት ኃይል ነውና።

የመንግስት ሽብር በተባበረ የህዝብ ትግል ይከሽፋል!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)