June 25,2017

ኢህአዴግ አልቀበልም ያላቸውን አጀንዳዎች በመደገፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መነጋገሪያ አጀንዳዎችን አጸደቁ፤ የአጅንዳ ጉዳይ ተዘጋ

June 25, 2017

የተለያየ ስያሜ የተሰጠው የድርድር አጀንዳ ቀረጻ ተቋጨ። ኢህአዴግ በዋና ጉዳዮች ላይ እንደማይደራደር አቋሙን ይፋ ሲያደርግ ተደራዳሪ የተባሉት ድርጅቶች ተቀብለውታል። በኢትዮጵያ የፖለቲካና የህሊና እስረኛ የለም የሚለውን ጨምሮ አገሪቱ ላይ ስጋት ያጣለውን አንቀጽ 39፣ የመሬት ፖሊሲ፣ የድንበር ጉዳይ፣ የሕገ መንግስት ማሻሻያና የአስቸኳይ አዋጁን በተመልከት ንግግር የለም። ፋና እንደዘገበው በዚሁ የኢህአዴግ አቋም ሁሉም ድርጅቶች ተስማምተዋል።

ኢህአዴግ በብሂራዊ መግባባት ጉዳይ፣ በምርጫ ህግ፣ በጸረ ሽብር ህግና በተደጋግሚ በውጪ ረዳት አገሮች ሲወተወትበት የነበረውን የበጎ አድራጎትና የማህበራት ማደራጃ አዋጅና መሰል ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ወስኗል። ድርድሩን የተከታተሉ ” ይህ ድርድር ሳይሆን አስቀድሞ ኢግአዴግ እንዳለው ውይይት ነው” ሲሉ ድርድሩ ወደ ውይይት ዝቅ አለ ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ለዚሁ ውጤት ፓርቲዎቹ አስቀድመው ሲባሉና ሲወዛገቡ መቆየታቸው በርካቶችን ያሳዘነ እንደነበር ከጅምሩ የተወሳ ሲሆን በኢትዮጵያ የህሊናና የፖለቲካ እስረኛ እንደሌለ መቀበል ድርጅቶቹን የሚያሳጣ እንደሆነ፣ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ ላይ በልዩነት በመውጣት ሪኮርድ ማስመዝገብ አለምቻላቸው የችግሩ ሰለባ በሆኑትና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በህዝብ ዘንድ እንደማያስከበራቸው ከወዲሁ እየተጠቆመ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ቢያንስ የመነጋገርን ባህል ማዳበሩ እንደ ቀላል ሊወሰደ እንደማይገባ በተደጋጋሚ የሚገልጹ አሉ። መንግስት ይህን ያህል አልፎ መሄዱ ሊያስመሰግነው እነድሚገባ እንዚሁ ክፍሎች ያምናሉ። በውይይቱ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያላቸው እንደ ኦፌዴን፣ በጥቅሉ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ አለመካተታቸውን ግን ሁሉም ቢቃወሙትም፣ ቢኖሩም ዋጋ የለውም አስቀድመው ራሳቸውን ማግለላቸው አግባብ ነው የሚሉም አሉ።

አሁን ለንግግር የሚቀርበው የፓርቲዎች ስነ ምግባር በድርድሩ ያልተሳተፉትን የሚያገል እንዳይሆን ከወዲሁ ስጋት አለ። በሌላ በኩል ግን ኢህአዴግ አሁን ከተወያያቸው ፓርቲዎች ጋር ለምርጫ ቢቀርብ ምርጫ ቦርደን ቢያፈርስም ከማሸነፍ የሚያገደው ነገር እንደሌለ ትዝብት አለ። ፋና የሚከተለውን ዘግቧል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ ባካሄዱት 13ኛ ዙር ውይይት በይደር ባቆዩዋቸው ረቂቅ የድርድር አጀንዳዎች ላይ ሀሳብ ከተለዋወጡ በኋላ ለድርድር የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተስማምተዋል። በዚህም መሰረት የምርጫ ህጎች እና ተያያዥ ጉዳዮች በድርድር አጀንዳነት ከፀደቁት መካከል ይገኙበታል።

በዚህ አጀንዳ ስርም፦

የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ

1999 .ም የምርጫ ህግ

2002 .ም የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ይበኙበታል።

አዋጆች እና ተያያዥ ህጎች የሚለው አብይ የድርድር አጀንዳም በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር ሊካሄድበት ፀድቋል።

በዚህ አብይ አጀንዳ ስርም፦

የፀረ ሽብር ህግ

የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት ህግ

የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ

የታክስ አዋጅ

የመሬት ሊዝ አዋጅ እና የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታ በንኡስ የድርድር አጀንዳነት ፀድቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፦

የዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ ተቋማት አደረጃጃት

ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመስራትና ሀብት የማፍራት መብት ከክልል መንግስታት ህጎች አንጻር

ወቅታዊ እና ኢኮኖሚ ወለድ የህዝብ ጥያቄዎች

ብሄራዊ መግባባት

የፍትህ ተቋማት አደረጃጀት እና አፈጻጸም አዋጆችም በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የፀደቁ አጀንዳዎች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት ሀሳብ መነሻነት ኢህአዴግ በፀረ ሽብር ህግ እና በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ እንዲሁም በፓርቲዎች ምዝገባ አፈጻጸም ላይ ከህግ ውጭ በቁጥጥር ስር የዋሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እና አባላት ካሉ በአዋጆቹ ላይ በሚደረግ ድርድር ሊቀርብ ይችላል ብለዋል።

ውድቅ የተደረጉ ረቂቅ የድርድር አጀንዳዎች አሉ

1.የህገ መንግስት ማሻሻያ

ኢህአዴግ በህገ መንግስቱ ማሻሻያ እንዲረግባቸው በተጠየቁ ሶስት አንቀጾች ማለትም አንቀጽ 39፣ አንቀጽ 46 እና አንቀጽ 72 አልደራደርም ሲል አቋሙን አሳውቋል።

2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳ ላይ ኢህአዴግ ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆና ስለአዋጁ መደራደር አይቻልም በማለቱ ውድቅ ተደርጓል።

3 የመሬት ስሪት ፖሊሲ

የመሬት ስሪት ፖሊሲን በተመለከተ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳ “የመሬት ስሪት የኢህአዴግ ልዩ ፖሊሲ በመሆኑ መሬት የህዝብ እና የመንግስት ነው የሚለው አቋም ለድርድር አይቀርብም በማለቱ” ውድቅ ተደርጓል።

4. የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የድንበር ወሰን

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የድንበር ወሰን በፓርቲዎች ድርድር ሳይሆን በሀገራት መንግስታት መካከል የሚከናወን በመሆኑ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳ ውድቅ ተደርጓል።

5. የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች

የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች አሉ” ተብሎ በፓርቲዎች የቀረበው ረቂቅ የድርድር አጀንዳ ላይ “የህግ እንጂ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኛ የለም” የሚል ሀሳብ ከኢህአዴግ በመቅረቡ አጀንዳው ለድርድር አልበቃም።

ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ “አልደራደርበትም ያለው ረቂቅ አጀንዳ፤ ህጋዊ እና ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ በውጭ ሀገር ሆነው እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሳተፉ” የሚለውን ነው።

ይህንን አጀንዳ ያቀረቡት አምስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አጀንዳው ለድርድር አለመቅረብ ላይ ተስማምተዋል። በመጨረሻም ፓርቲዎቹ ለድርድር የመረጧቸው አጀንዳዎች ቅደም ተከተል፣ የድርድር ጊዜ ሰሌዳ እና የድርድር መጀመሪያ እና መጨረሻ ጊዜ በአደራዳሪ ኮሚቴው ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ በመስማማት የዛሬው ውይይታቸውን አጠናቀዋል።