June 26, 2017 16:55

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ታሪክ ገዝፎ የወጣ የመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ ነበር። ፓርቲው በዘመኑ ፋሽን የነበረውን የሶሻሊዝም ርዕዮተዓለም አንግቦ ከታች እስከላይ ድረስ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ለማሰባሰብ የቻለ የደርግን ወታደራዊ አስተዳደር ከማንም በላይ የፈተነ ኃይል ነበር። እንደ እኔ እምነት ከሆነ በ1967 ዓ.ም ክረምት ላይ በተካሄደው የድርጅቱ ስብሰባ በገጠር የትጥቅ ትግል ለማካሄድ በሽምቅ ተዋጊነት የሰለጠኑትን ተዋጊወች እየመራ ወደበረሀ የገባው የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበረው ብርሀነመስቀል ረዳ ከሀላፊነት ቦታ ተነስቶ በውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ውስጥ እንደተራ ሰራተኛ ሲመደብ የኢሕአፓ ውድቀት ሀ ብሎ የጀመረው ያኔ ነበር። ከአያያዝ ጉድለት ሁነኛው ወዳጅ ቀንደኛ ጠላት ሊሆን እንደሚችል ያስተማረን አንዱ ክስተት የነብርሀነመስቀሉ የ1967ቱ የስልጣን አመዳደብ ሁኔታ ነበር።

የትኛውም ፓርቲ በቅድሚያ ማድረግ የሚኖርበት እያንዳንዱ አባል የመተዳደሪያ ደንቡን ጠንቅቆ እንዲያውቀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት እና ለአመራር የሚታጩት ሰዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ነጥቦችን በግልጽ ማስቀመጥ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ወደአመራር የሚመጡትም ሆኑ ከአመራር የሚነሱት ሰዎች የህሊና ዝግጅት እንዲያደርጉ የጥንቃቄ ስራ መሰራት አለበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በድብስብስ የሚደረግ ምርጫ በግለሰቦች ዘንድ የመበለጥ ስሜት ይፈጥር እና ወደጥፋት ሊመራ ይችላል። ብርሀነመስቀል ከአመራርነት ቦታው ሲነሳና በዝቅተኛ ቦታ ሲመደብ የተሰማው የመጠቃት ስሜት ነበር። በዚህም ምክንያት እሱና ተከታዮቹ ከመኤሶን ባልተናነሰ መልኩ የኢሕአፓን ወሳኝ ሰዎች ለደርግ በማጋለጥ የድርጅቱን ውድቀት ዕውን አደረጉ።

ኢሕአፓ ከገበሬው እስከምሁር ማሰባሰብ የቻለ ድርጅት ሆኖ እያለ፣ ከሲቪል እስከወታደራዊ ተቋሞች ዘልቆ ገብቶ ቁልፍ ሰዎችን አቅፎ እያለ፣ ነገር ግን በራሱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ያለውን ሁኔታ አቻችሎ መሄድ አቅቶት አሉኝ የሚላቸውን ወሳኝ ሰዎች በአፈንጋጮች ጠቋሚነት አስበልቶ ወደሞት አዘገመ።

መንግስትን ታግየ የስርአት ለውጥ አመጣለሁ ብሎ የተነሳ ማንኛውም ድርጅት ከእንዲህ አይነት ውድቀት ትምህርት ቀስሞ በቅድሚያ የራሱን አባላት ገርቶ መያዝ ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ከመተዳደሪያ ደንቡ ጀምሮ እስከተግባራዊ ክንዋኔወች ድረስ ግልጽ በሆነና ዲሞክራሲያዊ አሰራርን በተላበሰ መልኩ መፈጸም ይኖርበታል። የመተዳደሪያ ደንቡ አሻሚ አለመሆን፣ የዴሞክራሲያዊ አሰራር መስፈን፣ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት አግባብ ግልጽ መሆን፣ ግጭቶች እና አለመጣጣሞች የሚፈቱበት መንገድ ተቀባይነት ያለው መሆን፣ ጥርጣሬወች የሚጣሩበት አሰራር መኖር፣ የአንድን ድርጅት ጥንካሬ የሚያጎለብቱ እና በአባላቱ መሀል ግንኙነትን እና መተሳሰብን የሚያዳብሩ ይሆናሉ። የነገር ጫፍ ይዞ ዕውነቱን ለማጣራት መስራት ገንቢ ሲሆን የነገር ጭራ ይዞ ማውራቱ ጥላቻን የሚወልድ አፍራሽ ተግባር ነው። ማንኛውንም ሀላፊነት በጥንቃቄ ለመስራት መቁረጥ፣ ከዚህ አልፎ ለሚከሰት ግድፈት ስህተትን ማመን፣ ይቅርታ መጠየቅና መቀበልን ባህሪ ማድረግ ያስፈልጋል።

ማንኛውም ሰው ሙሉ አይደለም። በመሆኑም ጠንካራ ጎናችንን እያጎለበትን ድክመቶቻችንን እንድናስወግድ በጥላቻና በንቀት ሳይሆን በቅን ልቦና ልንተራረምና ልንደጋገፍ ይገባል። ተያይዘን አላማችንን ከግብ ለማድረስ የምንችለው በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ጓዳዊ ግንኙነት ስንመሰርት ነው። የአማራ ድርጅቶች ቀዳሚ አላማ በአማራው ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቃት መመከት ብሎም ማስወገድ ነው። አማራው አደጋ ውስጥ ነው። ይህን አደጋ ለመቀልበስ የውጪ ኃይል ይደርስልናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። በስውርና በግልጽ የሚፈጸመው ግፍ መቋጫ የሚያገኘው ጥፋት እየተፈጸመበት ያለው ኃይል ነቅቶ ራሱን ሲከላከል ብቻ ነው። ለዚያም ነው አማራው በማንነቱ መደራጀት አስፈላጊ የሚሆነው። የአማራ ትግል ለዴሞክራሲ የሚደረግ ትግል ሳይሆን የህልውና ትግል ነው። ማንኛውም አማራ ለራሱና ለወገኑ ህልውና ሲል፣ ዘሩን ለማስቀጠል ሲል፣ ልዩነትን አስወግዶ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ይኖርበታል።

ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰነዘሩትን ትችቶች መገምገም አስፈላጊ ቢሆንም ዋናውን አላማችንን ግን የሚያስቀይስ ሊሆን አይገባም። አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር ለሚሰነዘሩት ትችቶችና ነቀፌታወች ሁሉ መልስ መስጠት ተገቢ አይደለም። ትልቁ ነገር የራስን ግድፈትና ስኬት እየገመገሙ ከድክመቱም ከጥንካሬውም ትምህርት በመውሰድ ለቀጣዩ ስራ የተሻለ ስልት መንደፍ ነው። ምላሽ ወይም መግለጫ ሊሰጥባቸው ይገባል በሚባሉ ነገሮች ላይ የሚቀርበው የቪዲዮ፣ የኦድዮ ወይም የጽሁፍ ምላሽ በቁምነገሩ ላይ ብቻ ያተኮረ፣ በጅምላ የማይወነጅል፣ አስተማሪ፣ የተገራና ተመልካችን የማያስቀይም እንዲሆን ያስፈልጋል። አሉባልታ ለሚያናፍሱና ተራ ስድብ ለሚሳደቡ ሰዎች ምላሽ ለመስጠት ተራ እሽኮለሌ ውስጥ መግባት ልክ አይደለም። እንዲህ ሲሆን ወዳጅን ጠብቆ ከማቆየት አልፎ ጠላት የነበረን በመማረክ ተቃዋሚን ማዳከም ይቻላል።

ያ ትውልድ የሚል መጠሪያ የተሰጠው የ1950ወቹና የ1960ወቹ ትውልድ በየሚያምንበት ቡድን ተሰልፎ በጽናት ታግሏል። ያ ትውልድ የሰራቸው ግድፈቶች እንዳሉ መካድ አይቻልም። እንደሻዕቢያ፣ ወያኔ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ሶማሌ አቦ ያሉት ማዕከላዊ መንግሥቱን አዳክመው ሀገር ለመበተን የተሰለፉት የጎሣና የሀይማኖት ድርጅቶች ዛሬ በምንገኝበት አሳፋሪ የታሪክ ወለል ላይ አስቀምጠውናል። እንደ ኢሕአፓና መኤሶን ያሉት ሀገራዊ ድርጅቶችም ቢሆኑ እርስ በርስ ከመራኮት ጀምሮ በፈጸሟቸው ጥፋቶች አሁን ለምንገኝበት ሁኔታ ያበረከቱት ድርሻ አለ። ያም ሆኖ በገንጣይ አስገንጣይ ረድፍ ተሰልፈው የተዋጉትም ቢሆን ለአላማ በጽናት መቆምን እና መስዋዕትነት መክፈልን አስተምረውናል።

ያ ትውልድ ወደትግሉ መድረክ የገባበት ያ ወቅት የሶሻሊዝም አስተምህሮ ጉልበት አግኝቶ በመላው አለም እንደፋሽን ብርቅ የሆነበት ጊዜ ስለነበር በርዕዮተአለሙ ላይ የሚስተዋሉት ችግሮች የትውልዱ ችግር ተደርገው ሊወሰዱ አይገባም። ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች! የዓለም ወዛደሮች ሁሉ ተባበሩ! የሚሉት የወቅቱ መፈክሮች የሶሻሊዝም ስርአት አራማጅ የነበሩትን ሀገሮች በጸረ ኢምፔሪያሊዝም ትግል ያስተባበረ ነበር። ለዚያም ነበር የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ የሶማሊያን ወራሪ መንግሥትና የሻዕቢያን ተገንጣይ ኃይል ለመመከት የየመን፣ የኩባና የራሽያ ወታደሮች በኢትዮጵያ ምድር ደማቸውን ያፈሰሱት።

ሶሻሊዝም በተግባር መዋል የሚችል ስርአት ቢሆን ኖሮ ከሚቃወመው በላይ የሚደግፈው እንደሚበልጥ አሁንም በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ነገር ግን በወዛደሩ ስም ወደስልጣን የመጡት ፓርቲወች አላማውን በሳተ መልኩ አምባገነናዊነትን ስላሰፈኑ እና የከበርቴው ስርአት አራማጆች በጽናት በመታገላቸው ብዙ የተከፈለበት ሶሻሊዝም እንደቀልድ ፍርክስክሱ ሊወጣ ቻለ።

የአሁኑ ትውልድ ያለፈውን ትውልድ ከመክሰስ እና ከመውቀስ ወጥቶ ከድክመቱም ከጥንካሬውም ትምህርት መውሰድና ለተሻለ ነገር መስራት ይኖርበታል። ዛሬ ላይ ቁጭ ብሎ በዚያ ትውልድ ላይ መሳለቅ እወክለዋለሁ የሚለው ሕዝብ ዛሬ በወያኔ እየተሰራበት ያለውን ግፍ ወደጎን ብሎ በሚኒሊክ ጊዜ ተፈጽሟል ብሎ ላለው በደል እንደሚያለቅሰው ኦነግ መሆን ነው።
ኢሕአፓ ትክክል ነው ብሎ ባመነበት መስመር ተሰልፎ ከባድ መስዋዕትነት የከፈለ ድርጅት ነው። አሁንም ቢሆን የሕዝብን ጩኸት ከመጮህና ከመታገል አልቦዘነም። የግንቦት 7ቱን ፕ/ር ብርሀኑ ነጋን ጨምሮ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል የወያኔን እኩይ አገዛዝ እየተናነቁ ያሉ የዚያ ትውልድ አባላት ብዙ ናቸው። እኒህ ሰዎች እየከፈሉት ያለውን መስዋዕትነት አቅልሎ ማየት አልፎ ተርፎም ከሳሽና ወቃሽ ሆኖ መቅረብ ፍጹም ስህተት ነው።

የዚያ ትውልድ ሰዎች እስካሁን ድረስ በትግል ላይ እንዲቆዩ የተገደዱት ኃላፊነቱን ሊረከብ የሚችል አዲስ ትውልድ ጎልቶ ሊወጣ ባለመቻሉ ክፍተቱን ለመሙላት ነው ብሎ ማሰብ ይቻላል። በአዲስ ኃይል የተዋቀረ የተጠናከረ ድርጅት ሲፈጠር የዚያ ትውልድ አባላት እፎይታ አግኝተው ምክር በመስጠትና ልምድ በማካፈል ይወሰናሉ። ከነዚህ የትናንት ወጣቶች የዛሬ አዛውንቶች በጎ ተሞክሮወችን እና የአላማ ጽናትን መውረስ እና ያጠፏቸውን ጥፋቶች አለመድገም ተገቢ ነው። ከዚያ ባለፈ የችግሮች ሁሉ ምንጭ እንደነበሩ አድርጎ መውቀሥና በጸረ ሕዝብነት መክሰስ ትክክል  አይደለም።

ኢሕአፓና መኤሶን ወደትግል ሲገቡ ኢትዮጵያ ችግር አልባ ሀገር አልነበረችም። በዘውዳዊው አስተዳደር የብዙሀኑ ጭሰኛ መሆን እጅግ መጥፎው ነገር ነበር። አንድ ደጃዝማች የባለብዙ ጋሻ መሬት ባለቤት ሆኖ በመሬቱ ላይ የሰፈሩት ሰዎች መሬት አልባ ጭሰኛ መሆን እጅግ ከባዱ ነገር ነበር። ጭሰኝነቱን ተከትሎ የነበረው የጉልበት ብዝበዛና የመብት ጥሰት ዛሬ ላይ ቁጭ ብለው እንደሚያስቡት ቀላል አልነበረም። በዚያን ወቅት መሬት ላራሹ ብሎ የተነሳው ወጣት በምንም ስሌት በጸረ ሕዝብነት ለመክሰስ አይታሰብም። ጥፋቶች የተፈጸሙት አንድም በርዕዮተአለሙ ግድፈት ሌላም በልምድ ማነስ እንጅ በጸረ ሕዝብነት በመሰለፋቸው አልነበረም። ስለዚህ ድክመቶችን አርሞ ጠንካራ ጎኑን የበለጠ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ኃይል ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ወዳጅና ጠላትን መለየት ተገቢ ነው። አሁን ዋናው የአማራ ጠላት ወያኔና ሌሎች አማራን እንጠላለን የሚሉ ድርጅቶች ናቸው። ለኢትዮጵያ አንድነት የሚታገሉ ድርጅቶች በምንም ስሌት የአማራ ጠላት ሊሆኑ አይችሉም። በአንድነት ስም የተደራጁ ኃይሎችም የአማራውን እንቅስቃሴ እንደስጋት ከማየት ወጥተው ተባብሮ ለመስራት መዘጋጀት አለባቸው። እያልሁ ያለሁት የአማራ ታጋይ ድርጅቶች እና የአንድነት ኃይሎች ግብግብ ውስጥ መግባታቸው ፍጹም ስህተት ነው ነው። የአማራ ድርጅቶች የአንድነት ስጋት ሊሆኑ አይችሉም፤ የአንድነት ኃይሎችም ለህልውናቸው የሚዋደቁትን አማሮች ቢቻል መደገፍ እንጅ መሰናክል ሊሆኑባቸው አይገባም። የአንድነት ኃይሉ እና የአማራ ድርጅቶች ቢተባበሩ ይጠቅማል ሲባል የአማራውን የትግል እንቅስቃሴ እንዲዋጥ መፍቀድ ማለት አይደለም። አማራው የብዙ ኃይሎች የጥቃት ኢላማ እንደሆነ ለአፍታም መዘንጋት አያስፈልግም። ስለዚህ የአማራው ትግል ወደኋላ መመለስ የለበትም። ይህንን የተቀጣጠለ እምቢኝ ባይነት ይበልጥ እያቀጣጠሉ መሄድ ካልተቻለ ከበረደ በኋላ እንደገና መልሰን ነፍስ እንዝራበት ቢባል የሚከብድ ይሆናል።

እንደሚመስለኝ የአማራ ድርጅቶች የሚታገሉት በአማራው ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመቀልበስ፣ እንደማንኛውም ዜጋ እኩል መብት እንዲኖረው ለማስቻል እንጅ የስልጣን ተፎካካሪ ሆነው ለመውጣት አይደለም። በጎሣ ተደራጅቶ ለስልጣን መፎካከር አግላይና አንድነትን የሚሸረሽር የሀገር አደጋ እንደሆነ ብዙወችን ያስማማል። የአማራው በዘር መደራጀት ከሌላው የሚለየው መጥፋት አለበት ተብሎ የተወሰነበት በመሆኑ ነው፤ የጥቃት ኢላማ በመሆኑ ራሱን ለመከላከል መደራጀት ስላለበት ነው። በዚህ ከተስማማን ጥቃትን ለመከላከል የግድ ወደአንድ ታላቅ አማራዊ ኃይል መሰባሰብ ይበጃል። የተለያዩ ድርጅቶች አሉ ማለት ድርጅቶችን አንድ የማያደርጓቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ ማለት ነው። የተደበቀ ፍላጎት ከሌለ በስተቀር የአማራ ድርጅቶች አላማና ግብ አንድ ነው። በአንድ ማዕከላዊ አመራር ስር ያሉ ክፍሎች በየአካባቢው እንዲቋቋሙ ማድረግ ሕዝቡን ለማሰባሰብ ይረዳል፤ በተጨማሪም የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ የፉክክር መንፈስ ስለሚፈጥር ትግሉን ለማፋፋም ይጠቅማል። ለምሳሌ የጎጃም፣ የጎንደር፣ የወሎ፣ የሸዋ በሚል የሚቋቋሙት ክንፎች/ ክፍሎች በየራሳቸው ሰዎች እየተመሩ በ “አማራ የህልውና እና የነጻነት ፋኖ ድርጅት” ስር እንዲውሉ ቢደረግ ጠቀሜታው ብዙ ነው። እንደወያኔ ያለ አንድን ዘር ለማጥፋት ታጥቆ በተነሳ መንግስት ስር የወደቀ ተጠቂ ሕዝብ ተደራጅቶ ራሱን መከላከል ካልቻለ መጥፋቱ የማይቀር ይሆናል። አማራው በራሱ ክልል ሳይቀር የራሱ ባልሆኑ ሰዎች ተረግጦ እየተገዛ እንዳይቀጥል፣ በተለያዩ ስልቶች ቀስ በቀስ ከመኖር ወደአለመኖር እንዳይሸጋገር ብቸኛው መፍትሄ ጠንካራ ድርጅት መፍጠር ነው። በየክልሎች ተበትነው የሚኖሩት አማሮች መብት ሊከበር የሚችለውም ለመብታቸው የሚታገል ጠንካራ ኃይል ሲኖር ብቻ ነው።

ከዚህ በፊት ደጋግሜ ለመግለጽ እንደሞከርሁት የአማራው ትግል የትኛውንም አማራ የሚያገል ሊሆን አይገባም። እያንዳንዱ አማራ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት “የምከፍለው መስዋዕትነት ለራሴና ለቤተሰቤ ነው” ብሎ እንዲያምን ማድረግ ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት። በዘሩ ምክንያት ከመገለልና መድልዖ የዘለለ የዘር መጥፋት ሰለባ እንደሆነ የተረዳ አማራ በምንም ስሌት የጠላት መሳሪያ በመሆን በራሱና በቤተሰቡ ላይ ጥፋት እንዲፈጸም ተባባሪ ሊሆን አይፈቅድም። በኢሕዴን ስር ያሉት አማሮች ከሚታሰበው በላይ ለአማራው ትግል ጠቃሚወች ናቸው። ከላይ እስክታች ድረስ ባለው አደረጃጀታቸው ተጠቅመው መረጃ ከማቀበል ጀምሮ በቀጥታ ተሳትፎ እስከማድረግ የዘለቀ የተግባር ስራ በማከናወን ግዙፍ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ ይችላሉ። እንኳን የዘር ሰለባ የሆነ ሕዝብ ይቅርና በዘሩ ላይ የተቃጣ ጥቃት ያልተፈጸመበት ወያኔ እንኳ በትግሉ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ነው በሚል ብቻ በተለያየ የስልጣን ደረጃ በነበሩ በርካታ ትግሬወች ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲቸረው እንደነበር ይዘነጋል!

አማራነት አንድነት፣ መቻቻል፣ አስተዋይነት፣ ፍቅር፣ ለጠላት አለመንበርከክ፣ ሀገር ወዳድነት መሆኑን በአንደበትም በተግባርም ማስመስከር ያስፈልጋል። እያንዳንዱ አማራ ዕኩል የባለቤትነት መብት ከተሰጠው ለድርጅቱ ተዋጊም ሰላይም ሆኖ እንደሚያገለግል ማመን ይኖርብናል። ነገር ግን ባለማወቅም ይሁን በጥቅም ተገዝቶ ለጥቃት የሚያጋልጥ ሰው ቢኖር ጉዳት ሳያደርስ የሚጋለጥበትና የሚመከርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ነው። ጥንቃቄ የጎደለው አያያዝ፣ ወከባ፣ ከራስ ውጪ ያለውን ሁሉ በጥርጣሬና በክፉ አይን ማየት፣ ገንቢም ተገቢም አለመሆኑ ታምኖ መጀመሪያ ሁሉም ራሱን ማረቅ ይኖርበታል። ማንኛውም ሰው ሀሳቡን በግልጽ የማንሸራሸር ዕድል ቢሰጠው ማትረፍ ይቻላል። የሚሰጡት አስተያየቶች፣ ሀሳቦች፣ትችቶች፣ ነቀፋወች፣ ውንጀላወች፣ ትክክል ካልሆኑ እና መልስ መስጠት ቢያስፈልግ ክብርን በጠበቀ መልኩ መመለስ ይቻላል። ይህን ማድረግ ራስን ማስከበር፣ ለሌላውም ጥሩ ምሳሌ መሆን ነው። መጥፎ ቃላት ከጥሩ ሰዎች አይወጡም።

አክቲቪስት አቻምየለህ ታምሩ “በአማራ መደራጀት ጉዳይ” በሚል ያወጣውን ጽሁፍ አስመልክቶ ብዙ ውርጅብኞች እየወረዱበት ነው። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ትምህርት መውሰድ ያለብን ከሁሉም በመሆኑ ከወያኔም የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ወያኔ ካቅሙ በላይ ሆኖ ፈንድቶ ሲወጣበት ካልሆነ በስተቀር ችግሮቹን የሚፈታው ማንም ሳያውቅ ውስጥ ለውስጥ ማለትም በራሱ ነው። በትንሽ በትልቁ መናቆር፣ ቅሬታን አደባባይ ላይ እያወጡ ማስጣት ንቃቃት/መሰነጣጠቅ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆንና እንደኢሕአፓ ሁሉ ውድቀትን ያስከትላል። አቻምየለህ አማራ ብሔር አይደለም አለ ተብሎ ሲሰደብ ብሎም እንዲጠረጠር ሲደረግ ለተመልካችም ቢሆን ይቆረቁራል። ከዚህም በላይ የአማራውን ትግል የሚከፋፍል ሆኖ ያልተፈለገ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። አቻምየለህ አንድ ሰው ላይሆን ይችላል። እንደትንሽና ቀላል ነገር የምንናገራቸውና የምናደርጋቸው ነገሮች ትልቅ ጥፋት ሊያመጡ ይችላሉ። ለዚያም ነው የምንናገረውን እና የምናደርገውን በቅድሚያ ማሰብ የሚኖርብን። እንደዚያ ካላደረግን ከታሪክ ሳንማር ከወዳጅ መሀል ጠላት እየፈጠርን ከነሰነቅነው አላማ ወደገደል እንገባለን።

በመሰረቱ ብሔር አንድ ወጥ ትርጉም ያለው ቃል አይደለም። የብዙ ነገሮች መመሳሰልና አንድነት ያለው ሕዝብ መጠሪያ አድርገው የሚወስዱ ወይም የሀገር ተለዋጭ ስም አድርገው የሚጠቀሙበት አሉ። ታዲያ ብሔር ማለት ሀገር ማለት ነው ብሎ ቢል ይህን ያህል በብስጭት የሚያወራጭ መሆን አይኖርበትም። መማማር ሲቻል፣ በጨዋ ደንብ መተራረም ሲገባ ወዳጅ ጠላት እስኪታዘብ ድረስ ወዲያና ወዲህ ቆሞ “አሎ ሉሎ” እያሉ መወራረፍ ፍጹም ስህተት ነው።

ሞረሾችም እኮ የአማራ ነገድ እንደሚሉ ነው የሚታወቀው። ጎሣ፣ ነገድ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ የሚሉትን ቃላት ለአንድ ሕዝብ መጠሪያ እያፈራረቁ የሚጠቀሙ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፤ እኔም ከነዚህ ሰዎች አንዱ ነኝ። ታዲያ ትክክል ካልሆንሁ ስህተቴን አንስቶ ማስተማር ሲቻል በስሜ አንቀው ይዘው መሬት ለመሬት እየጎተቱ ቢያሰቃዩኝ ተገቢ ነው? ብዙ ቃላቶች አንድ ወጥ ትርጓሜ የላቸውም፤ ያም ሆኖ የጠብ መነሻ ሊሆኑ አይገባም።