June 28, 2017

የማለዳ ወግ… ይድረስ ለሚመለከታችሁ ባለስልጣናት

==============================

* ለአንባሳደር አሚንና ለአንባሳደር ውብሸት ባላችሁበት

* ቅጅ /ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ወርቅነህ ገበየሁ

መረጃን ማቀበሌ ወንጀል ሆኖ ” የነቢዩ ሲራክ ልጆች ከሚማሩበት የጅዳ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት እንዲታገዱ ” የሚለው የካድሬዎች ሀሳብ ያን ሰሞን ቀርቦ እንደነበር በድጋሜ በማረጋገጤ አዝኘ ነበር ያደርኩት ።  … ስለ እውነት ለመናገር ፣ ስለ እውነት እየተገፉ መኖር ግድ ይላል ብዬ የሚሰራው ባይደንቀኝም በዘመነ ኦሪት እንኳ ባልታዬ ህግ ልጆች በአባታቸው ” ወንጀል ” ስማቸው ሲጠራ መስማት ልቤን በሀዘን ሰብሮት አድሯል  🙁 እናም ሁሉንም ለመርሳት ልጆቸን እረፍት ወደ ማይሰማ ወደ ማይናገረው ቀይ ባህር ይዣቸው ዘና ልበል ብዬ ማልጀ ስነሳ ሌላ አሳዛኝ መረጃ ደረሰኝ ። መረጃው እንዲደርሰኝ ያደረገው ደግሞ አንድ አደር ባይ ወዳጄ ነበር ፣ ወዳጄን እኔን ያመመኝ አሞት ስለማያውቅ የዜጎች ጉዳይ አግብቶኝ የተገፊውን ድምጽ ሳሰማ ” ሥራ ፈት ነህ  !” እያለ ያላግጥብኝ ነበር። ዛሬ ግን የራሱ የሆነች እህት በሪያድ አየር መንገድ ለቀናት በደረሰባት እንግልት ተደናግጦ” አገር ይያዝ” ጩኸት አሰማኝ  ። ቀጠለና ዜጎች እየተሰቃዩ ነው የታላችሁ በማለት ከጅዳ ቆንስል እስከ ሪያድ ኢንባሲ ሹም ወዳጆቹን ጨምሮ መረጃውን እኔው ጋር አድርሶታልና አዘንኩ … ደጋግሞ ሲደውልልኝና መረጃ ሲሰጠኝ ዝም ብየ ሰማሁትና ለመሆኑ እኔ ስናገር ሥራ ፈት እያልክ  አልነበር?  ዛሬ ችግሩ በዘመድህ መጥቶ መናገር መናደድ ጀመርክ?   እስከ አሁንስ የት ነበርክ ? ማለቴ አልቀርም ። እሱ ግን አፈረ ፣ እኔም  ያፈረውን አድርባይ  ወዳጄን መጎሻሸሙን አልወደድኩትም …በወዳጄ ዛሬ መቆርቆር አላዘንኩም የሰጠኝን መረጃ ተከትዬ ያሰባሰብኩት እውነት ግን በእርግጥም ያስከፋል ። ይህን መልዕክት እንድጽፍ ላችሁ ያነሳሳኝ ጉዳይም ይኸው የደረሰኝ መረጃ ነው ።

  ላለፉት ሶስት ወራት ሌት ተቀን ግሩም በሆነ ዝግጅት የከረመው የኢንባሲና የቆንስል መረጃ ቅበላ በመቋረጡ የተከተለውን ውዥንብር እንደ ዜጋ ታዝቤያለሁ ። የኢንባሲና የቆንስል መረጃ ቅበላ በማቆሙም ቦታውን ባልተካም በመረጃ እጦት ስደተኛው እንዳይንገላታ ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት የምችለው ለማድረግ ሞክሬያለሁ ። አሁንም የምቀጥለው በዚሁ መንፈስ ነው  … የኢንባሲና የቆንስል ለመረጃ የተዘጋው በር ከተከፈተ እኔ ብዙም ላይክና ሸር ፈላጌ ዝር ላልል ቃል ልግባላችሁ  ! ብቻ ለዜጋው መረጃ ያስፈልገዋልና የተዘጋውን በር ክፈቱለት ለማለት  ለመማጸንና ለመምከርም ጭምር ነው ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ችግር በጅዳና በሪያድ አየር መንገዶች እየተንገላታ ያለው ሰው ለቅሶ ዛሬም ደርሶኛል ። በምህረት አዋጁ መራዘም ዙሪያ በሚናፈሰው መረጃ ለሚዋልለው ዜጋ እያደረጋችሁ ያለውን ጥረትና እውነቱን አስረዱት ።  ”  የምህረቱ ጊዜ አብቅቷል !” ተብሎ በሳውዲ ፖስፖርት ፖሊሶች እንዳይሳፈሩ መመለስ ስለመጀመሩ ጉዳይ ግልጽ መረጃ ከእናንተ ይጠበቃል ።  ከቀናት በፊት በጀዛን ትናንት ደግሞ በጅዳ አንዳንድ ተመላሾች ” የምህረቱ ጊዜ አብቅቷል !” ተብለው በፖስፖርት ፖሊሶች እንዳይሳፈሩ ተከልክለው እንደነበር ከጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች በግል መረጃውን አረጋግጫለሁ። በዚህና በዚያ  በተለያዬ አቅጣጫ የሚሰማው መረጃ ብዙዎችን ግራ እያጋባ ይገኛል ። በሚሰራጩት መረጃዎች ፣ እየተደረገ ስላለው ጥረትና  ተዛማጅ የተመላሽ ዜጎች ጉዳይ በሳውዲ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች በምህረት አዋጁ ወቅት ያደርጉት እንደነበረው ሳያቋርጡ መረጃን ሊሰጡ ይገባል የሚለው የብዙ ወዳጅ ተከታዮቸ መልዕክት ነው ። በእርግጥም ወቅታዊ መረጃን ሲሰጡ ከርሞ አሁን በወሳኙ ጊዜ ማቋረጥ  በመቶ ሽዎች የሚቆጠር ዜጋ ብቻ ሳይሆን በመላ አለም ያለው ሚሊዮን ሀገር ወዳድ እንዳይረጋጋ ያደርጋል ። በውል የተጠና የመረጃ ቅበላው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በሪያድ የኢትዮጵያ ኢንባሲ እና የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት በወሳኙ ጊዜ ያቋረጣችሁትን የመረጃ ቅበላ ትቀጥሉ ዘንድ እመክራለሁ  !  በየአየር ማረፊያዎች ቀንና ማታ ቀርቶ ለሰአታት መቋቋም በሚከብደው ደረቅ ሀሩር ጸሃይ ሙቀት እየተለበለበ ያለው ወገን ያለበትን ሁኔታ መከታተልና መደገፍ ፣  መረጃ ፣ ማብራሪያ በሉት ምክር ካስፈለገ በቦታው እየተገኙ መስጠት ተገቢ ነው እላለሁ !

ይህን ምክር እንድጽፍ ያነሳሳኝ መታበይ እንዳይመስላችሁ ። በቂ ምክንያት አለኝ  ” ላለፉት ሶስት ቀናትበሪያድ አየር መንገድ አውላላ ሜዳ ላይ ተሰቃየን ” በሚል የሚደርሱኝ መረጃዎች እጅግ  ውስጥን ይረብሻሉ  🙁  እናንተም በዚህ ዙሪያ ምንም አይነት ወቅታዊ መረጃ ስለማታቀርቡ በእንግልት ላይ ያሉ ዜጎች  የመረጃ እጦት ሌላ ፈተና እንደሆነባቸው መረዳት ችያለሁ ! እባካችሁ ዜጎች መረጃን  ከእናንተ ከህዝብና መንግስት አገልጋዮች የማግኘት መብታቸውን አለንና እሱኑ መብት አክብሩልን   !

 የግርጌ ማስታወሻ

====∞===== = ለወዳጆቸና ለተካታታዮቸ ፣ ይህ መልዕክት ለኃላፊዎች እንዲደርስ Share እና Like ማደረጋችሁን አትዘንጉ ፣ ሁላችንም  ስለተገፉት ዜጎች ድምጽ መሰማትና መፍትሔ ማግኘት መትጋት ግድ ይለናል  !

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር

ነቢዩ ሲራክ

ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓም