June 30, 2017

የግል ምልከታዬ !

============

* የተራዘመው የምህረት አዋጅ

* 90 ቀኑ ምህረት አዋጅ አስተምሮቱ ..

* አጭሩን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም ..

* የበረራ ፈቃድ እና የአሻራ አሰጣጡ ተጠያቂ ማነው?

* በቂ ድጋፍ ለማድረግ የሰው ሃይልን ስለማደራጀት ..

* ስራው በማን ነው የሚሰራው? የዲፕሎማቶች  ?

   መኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ሳውዲን በ90 ቀን ውስጥ ለቀው እንዲወጡ የተሰጠው ቀነ ገደብ ለ30 ቀናት ተራዝሟል ። በሳውዲው ንጉሳዊ ቤተሰቦች አመራሮች ይሁንታ አግኝቶ በሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ማምሻውን በፖስፖርት የበላይ ዳይሬክተር በሜጀር ጀኔራል ሱሌማን የህያ  ይፋ የሆነው መረጃ ይፋ ይፋ ሆኗል። ይፋ የሆነው የምህረት አዋጅ የ90 ቀኑ የምህረት አዋጅ ካለቀበት እአአ ከሰኔ 25 ጀምሮ እስከ ቀጣዩ ሐምሌ 25 ቀን 2017 ድረስ የሚቆይ እንደሆነው ታውቋል ። ፖስፖርት የበላይ ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ሱሌማን የህያ በተሰጠው ተጨማሪ አንድ ወር ህጋዊ መኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸው አስፈላጊውን መስፈ ርት አሟልተው ሳውዲን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል ።

90 ቀኑ ምህረት አዋጅ አስተምሮቱ …

=========================

  90 ቀኑ የምህረት አዋጅ መኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ለመግባት ፍላጎት አለማሳያታቸው ይጠቀሳል ። እውነታውን ለማስረዳት ዛሬ ላይ ቀላሉ ማሳያ 400 ሽህ ህገ ወጥ ኢትዮጵያውያን ባሉባት ሳውዲ ወደ ሀገር ለመግባት ሰነድ  በመውሰድ የተመዘገቡትና ሀገር የገቡትን ቁጥር ማየት በቂ ነው።  የምህረት አዋጁን ለመጠቀም መቶ ሽህ ያህል ኢትዮጵያውያን ሰነድ ወስደዋል። ከተመዘገቡት 100 ሽህ ዜጎች መካከል እስከ 50 ሽህ ወደ ሀገር ገብተዋል ። ይህ እንግዲህ ባሳለፍነው ሶስት ወር በተደረገው መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ አይደለም። ከሚያስፈራ ፣ ከሚያሸብር ፣ ከሚያንቀጠቅጠው የመንግስታችን ምክርና ዝክር ቅስቀሳ በላይ የሳውዲና የኢትዮጵያ የሰራተኛ አቅርቦት ስምምነት የተመዘገነው ውጤት መገኘቱን መካድ የማይቻል እውነት ሆኗል ።

አጭሩን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም …

    ዛሬ ላይ የሁላችንም ድጋፍ አግኝተው ወደ ሀገር መግባት የሚፈልልጉ ቢያንስ በግምት ተጨማሪ 150 ሽህ ዜጎች አይጠፉም  ። እናም ወደ ፈተናው ሳንገባ በመጨረሻዎቹ የምህረት አዋጅ ሳምንታት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ያልተጠበቀ የበረራ እጥረት በተሰናከልንበት አካሄድ መነታረኩ አይበጀንም ። ከተሰጠው 30 ቀን የቀረን 25 ቀን ብቻ ነው ። አጭሩን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም 100 ሽህ ዜጋ ሊወጣ ቢዘጋጅ ማድረግ ስለሚኖርብን ማስላቱ ይበጅ ይመስለኛል ።

የበረራ ፈቃድና የአሻራ አሰጣጡ ተጠያቂ ማነው?

 የዚህ ስሌት ውጤት በ25 ቀን 100 ሽህ ዜጋ ለማስወጣት በቀን 400 ሽህ ዜጋን ለመሸኘት የአየር በረራ ዝግጅት ስለመኖሩ ማደራጀት ይገባል።  ኃላፊነቱን ለመሸከም የኢትዮጵያ አየር መንገድንም ሆነ የሳውዲንና የተቀሩትን አየር መንገዶች ማዘጋጀትና ማደራጀት ይገባል። ከዚሁ በተያያዥ ለአዳዲስ ተመዝጋቢዎችና አሻራ ግልጋሎት ጠያቂዎች የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ከሳውዲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች  ደረጃ መመካከር ቀዳሚ ተግባር መሆን ይገባዋል። ይህን አድርጎ ማስተካከል ካልተቻለ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት የሳውዲ መንግስት ስለመሆኑ ማሳወቁ ተገቢ ይመስለኛል ። “ውጡ” በ90 ቀናት ያየነውን አይነት ቢሮክራሲ መውጫ በሩን ከዘጋጉት ለሚፈጠረው መጓተት ኃላፊነቱን ሊወድስዱ እንደሚገባ በማያሻማ ቋንቋ ሊነገራቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ሰው ሊወጣ ፈልጎ ” የአየር ማረፊያ እጥረት አለ ፣ አሻራ ማድረግ በኮታ ነው !” እያሉ ዜጋውን ማመስ  ከላይ የተጠቀሰውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ እንዳይቀጣ እክል መሆኑን ማስረዳት ይገባል።

ስራው በማን ነው የሚሰራው? የዲፕሎማቶች  ?

     ከላይ ያነሳኋቸውን በሳውዲና በኢትዮጵያ መንግሰት በኩል መደረግ ያለባቸው ስራዎች ከወዲህ ከተሰሩ ቀጣዩ የእኛ የዜጎች ጉዳይ ይመስለኛል። ወደ ራሳችን ጉዳይ ስንገባ … ወደ ወቅታዊውና መደረግ ወዳለበት ገፊ ሀሳብ አተኩረን በተቀናጀ አሰራር እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ሀገር ለመግባት ፍላጎት ያላቸውን ወገኖች ልንደግፋቸው ይገባል በሚለው መስማማት ይገባል።  ስራውን በበቂና በተደራጀ የሰው ሀይል በማሳለጡ ጉዳይ የማከርኳቸው በስውር የማገኛቸው አንድ በሪያድ ኢንባሲ የሚሰሩ ዲፕሎማት ወዳጄ ዛሬም ከውጭ ጉዳይ ወደ ሳውዲ ረዳት ዲፕሎማቶች ይላካሉ ተብሎ እንደሚገመት አጫውተውኛል ። ይህ አዋጭ  አለመሆኑ ለማስረዳት ምክንያቴን ማስረዳት ጠቃሚና ግድ ይሆንብኛል ።  ከዚህ ቀደም ከመጡትና ከቆዩት ከሳውዲ ባህልና ከቋንቋው ያልተዋሃዱት አዳዲስና ነባር ዲፕሎማቶች በየቦታው ተመድበው ሲሰሩ ስራውን የሚሰሩት የመጡት ዲፕሎማቶች አይደሉም ። ይልቁንም ስራው የተሰራውና የሚሰራው ለዲፕሎማቶች በተመደቡተ ሹፊር፣ አስተርጓሚና ጉዳይ ፈጻሚዎች ቢሆንም የዲሎማቶች ሰራ ስራው ተሰርቶ ሲያልቅ ፊርማቸውን ማስቀመጥ ብቻ ነው ማለት ይቻላል።   ዋነኛው ስራ በረዳቶቻቸው መሰራቱን በገሃድ ለምናውቅ ዜጎች የውጭ ጉዳይ የሰው ሃይል ጭማሪ አዋጭ አይመስለኝም ። ይልቁንም ለእነሱ የሚወጣው ከፍተኛ ደመወዝና የበርሃ የወል አበል የሀገርና የህዝብን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ከማባከን ባለፈ ስራውን የሚሰሩትን ቅጥር ሰራተኞች ድጎማና ማነቃቂያ በመሆን የተሻለ ስራ መስራት እንደሚያስችል መጠቆም ግድ ይላል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህንን ጉዳይ ልብ ሊለው ይገባል።

በቂ ድጋፍ ለማድረግ የሰው ሃይልን ስለማደራጀት …

    ነዋሪውን በምዝገባ፣ በሰነድ ዝግጅት ፣ በስነ ስርአት ማስከበር ፣ ትራንስፖርት በማቅረብ ፣ አሻራ በማሰጠትና በመሳሰሉት ድጋፎች ነዋሪውን ጥሪ አድርጎ ማስተባበር ይቻላል። ሰውም ለዚህ መሰል ድጋፍ ቀናኢ መሆኑን ተመልክተናል። በነዋሪው መካከል አረብኛ አቀላጥፈው የሚናገሩትን ታዳጊና ጎረምሶች ልጆቻችን ቋንቋና ባህሉን አሳምረው ስለሚያውቁት የተሻለ ስራ መስራት ይችላሉ። ከሳውዲ መስሪያ ቤቶች ጉዳይ ማስፈጸም ቢመደቡም ዲፕሎማት የሚያስንቁ ተቆርቋሪ ዜጎችን ናቸውማ ተማሪዎቻችን በሰፊው በማደራጀት የተሻለ ስራ መስራት ይቻላል ።

    ማህበር ፣ ድርጅት ሊግ ኮሚኒቲና ሌላም ሌላ ታማኝ አደረጃጀቶች ባሳለፍናቸው 90 የምህረት አዋጅ ቀናት የሰሩት ስራ የሚደነቅና የሚያስመሰግን ነበር። ያም ሆኖ በጉልበት ከተሰራው ስራ ራዕይ ይዞ አስልቶ መስራት የሚችሉትን ባለሙያ ኢትዮጵያውያን ባሉነት ሀገር የቀረውን ነዋሪ ማግለሉ አልጠቀመም ካለፈው እንማር ።  ማህበር ፣ ድርጅት እየተጠሩ የመጣውን ሰው አስታውሳችሁ የዜጋውን ፍላጎት የምትረዱ ይመስለኛል ። በእርግጥም ሰው በጥሪው ባይሳተፍ አልፈርድበትም ። እኔም የዚህ ህዝብ አካል ነኝና ለሀገራዊው ድጋፍ ጥሪ የማህበር ፣ የድርጅት ጥሪ ተጠይፊው ነበር። በእርግጥም ስለ ትልቅ ህዝብና ሀገር እየሰሩ ግልጋሎቱን ማህበር ፣ ድርጅትና ምንቴስ እያሉ መለየቱ አዋጭ እልነበረም።  ይህን የተሳሳተ አሰራር ዛሬ ከተገነዘብነው ለነገ ይጠቅመናል  ። ካለፈው የጎላ ስህተት ከተማርነበት ከነዋሪው መካከል መፍትሔ አስልተው የሚያቀርቡ በጎ ፍቃደኞችን ማቅረብ ተገቢ ነው። ዜጎችን ሳይለያዩ  በኢትዮጵያዊ ባንዴራ ጥላ ስር በማደራጀት ወደ ስራ መግባት ጊዜው የሚጠይቀው መፍትሔ ነው ብዬ አምናለሁ።

አጭር ጊዜ ተሰጥቶ ለምን ጊዜ እናጠፋለን ?

============================

     የስራ ሰአትን በሚመለከት የጅዳ ቆንስል እሁድ ሰነድ መስጠት እንጀምራለን ያለውን ውሳኔ በመከለስ በአስቸኳይ ቢቻል ከዛሬ አርብ ጀምሮ ምክክሩን ጀምሮ ከቅዳሜ ጀምሮ ሰነድ መስጠት መጀመር አለበት። የአሻራ መስጫው ጊዜ ከእሁድ ሲጀመር ወደ ቦታው ዜጎችን ለማመላለስ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ኮሚኒቲው የትራንስፖርቱን ኃላፊነት አደራጅቶ ማስጀመር ተገቢ ይመስለኛል።  እንደ አስፈላጊነቱ ከበጎ ፈቃደኛው ነዋሪ በተጨማሪ ለአጭር ጊዜ ጊዜያዊ ሰራተኛ በመቅጠርና ለቆንስል ለኢንባሲ ሰራተኞች ድካም ተገቢውን የላብ ዋጋ ከፍሎ ስራውን በፈረቃ በ24 ሰዓት የሚሰራበት መንገድ ማፈላለግ የተሻለ ውጤት ማምጣትና ወደ ሀገር የሚገቡትን ዜጎች በሰላማዊ መንገድ በክብር መሸኘት ይቻላል ።  ለዛሬው መሰረታዊ በምላቸው ጉዳዮች ያደረግኩትን ዳሰሳ በዚህ አበቃለሁ  !

   በህብረትና በአንድነት በተቀናጀ አሰራር የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ! አጭሩን የተራዘመ የምህረት ጊዜ ለመጠቀም ከላይ ያነሳኋቸውን ሀሳቦች ለመፍትሔው ገንቢ ሀሳብ ናቸው ብዬ አምናለሁ ። በተሻለ አሰራር የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሁላችሁን ዜጎች ጥቆማ፣ ሀሳብና አስተያየት ስራውን ለማሳካት ከፍ ያለ ግብአት ይኖረዋልና የሚመስለንን ጠቃሚ ሀሳብ ማንሸራሸር የማስበው ከሁላችንም ይጠበቃል።

ቸር ያሰማን   !

ነቢዩ ሲራክ

ሰኔ 22 ቀን 2009 ዓም