July 1, 2017 19:57

ይህን ጥያቄ የምጠይቀው ዛሬ ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ ስለሆነ አይገባውም ይገባዋል የሚል ሙግት ለማንሳት አደለም፡፡ ይልቁንም አዲስ አበባ ሥያሜዋም ፊንፊኔ ይባል መባሉንና ኦሮምኛ እንደ ሥራ ቋንቋ ይጨመር መባሉን ተከትሎ የታሪክ እውነታን በመካድ አቅም ያገኙ ምሁራኖች ነን የሚሉ ግለሰቦች የሚነዟቸውን መዛባቶችን ቢያንስ ለመቀነስ እንጂ፡፡ እዚህ ላይ ምሁራ ነን የሚሉ ያለኩት ሌላው የሕብረተሰብ አካል የፈለገውንም ቢል ከመረጃ እጦትና የሚሰማውን ስለሚያንጸባርቅ እንደመሠረታዊ የእውነት መዛበት መነሻ ስለማላየው ነው፡፡ በተሻለም ምሁር ያልሆኑ ሰዎች ሁኔታዎችን በማዋዛትና በቀልድ ለማስተዋል በሚጠቀም ሁኔታ ሀሳባቸውን ሲያስተላፉ አያለሁ፡፡ አንዳንዴም አደንቃለሁ፡፡ ምሁር ነን ብለው ራሳቸውን በሚገልጡ ሰዎች ግን እጅግ የሚከብድ እውነትን የመካድ ድፍረት ይታያል፡፡ ሕሊና፣ ምሁራዊ ዋጋና ፍልስፍና እንዴት እንደሆነ ባይገባኝም አልተከበሩም፡፡ እርግጥ ነው ምሁር ነን ባዮቹ በአብዛኛው ሀይማኖታዊና ማህበረሰባዊ እሴቶችን አይቀበሉም፡፡ እንደእነሱ እነዚህ አሴቶች አመክንዮዋዊ አደሉም ባይ ናቸውና፡፡ እነዚህን እሴቶች በእነሱ የስነልቦና ውጤት ናቸው ብለው ስለሚገምቱ፡፡ በሌላው አለም ምን እንደሚመስል አላውቅም የኢትዮጵያ ምሁራ ግን አመክንዮ(ሎጂክ) ብዙም ቦታ የለውም፡፡

አብዛኞቹን ትልልቅና መሪ የተባሉት ምሁሮችን ጨምሮ ግን የህዝብን ስነልቦና በመከተል ድራማ ውስጥ ተደብቀው እናያቸዋለን፡፡  ውሸት እንደማንኛውም ማህበረሰብ በእኛ ዘንድም ለዘመናት አብሮ ኖሯል፡፡ ሆኖም ሀይማኖታዊና ማሕበረሰባዊ እሴቶቻችን ከዚያም በላይ ትክክለኛው ሰውኛ ባህሪያችን ውሸትን ጉልበት እንዲያገኝ እድል ሳይሰጠው አፍኖት እንደኖረ ይሰማኛል፡፡ በአንዳንድ ዘመናት ግን ውሸት ጉልበት እያገኘ ብዙ ጥፋቶችን ሲያጠፋ እናየዋለን፡፡ በኢትዮጵያ እንዲሁ ነበር፡፡

የ60ዎቹ ትውልድ የጀመረው የውሸት ችሎታ ግን እስከዛሬም ላንቀለብሰው እየተፈታተነን ይገኛል፡፡ ያ ትውልድ ሀይማኖትን፣ ማህበረሰባዊ እሴቶችን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ መሠረቶችን አጣጥሎና ጥሎ የራሱን ምናብ በሕዝብና አገር ላይ ሊጭን የተነሳ ትውልድ እንደሆነ ነው የማመነው፡፡ ብዙ ጎራ ለይተው ተቧድነው እርስ በእርስም የተጨራረሱበት ምክነያትና እውነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ ፍትህና ኑሮ ለመፍጠር አልነበረም፡፡ ሁሉም የእኔ የሚለውን የራሱንም ምኞች ለማሳካት ሁሉንም አለኝ የሚላቸውን ፍጹም ከስብዕና ጭምር ያፈነገጡ ድርጊቶችን ሲያደርግ ኖሮ የቀናቸውም ሥልጣን ሲያገኙ ያንኑ ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ፍትህና፣ ሕግ አልባነት የተጠናወታቸውን ስግብግብነታቸውን ሲተገብሩ አየን እንጂ፡፡ ሁሉንም የ60ዎችን ቡድኖች አስተውሉ፡፡ ሕወሀት፣ ኢህአፓ፣ ሻቢያን ጨምሮ ሌሎችም አያሌ አንዱም ፍትህና ስብዕና በሚጠይቁት መስፈረት አካባቢ አላለፉም፡፡ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ያለው ሕወሀት በትግራይ ህዝብ ሥም በጫካ በነበረበት ዘመን ሁሉ ለምኞቱ መሳካት የትግራይን ሕዝብ ያለርሕራሄና ሲጨፈጭፍና በረሀብ ሳይቀር ሲያስፈጅ የኖረ እንደሆነ የታወቀ ነበር፡፡ ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ቢሆን ምንም አይገርምም፡፡ ሕወሀት እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ እንጂ ሁሉም የዛን ዘመን ቡድኖች ተመሳሳይ አላማ ነበራቸው፡፡ ያንንም አላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ኢትዮጵያዊ መሠረት ሁሉ ሲንዱ ነው የኖሩት፡፡ የሕዝቡን ማህበረሰባዊና ሀይማኖታዊ እሴቶችን ዋና ኢላማ አድርገው ነበር የዘመቱባቸው፡፡

እንግዲህ ከዛን ዘመን ጀምሮ የመጣው ትውልድና ስልቱ አብዛኛው በውሸትና ስሜተኝነት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ልጅ ሆኜ ሬዲዮና ቴልቪዥን የሚዋሽ አይመስለኝም ነበር፡፡ አሁን ሳየው ግን ጭራሽ እውነት ይነገርበታል ወይ ማለቱ ይቀላል፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባን ልዩ ጥቀም የሚል አዋጅ ያነበበው ጋዜጠኛ የመለስንና የሌንጮን ጥራዝ (ሕገ መንግስት) የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያጸደቁት እያለ ሲያነብ ብዙ ነገር ወደ ሀሳቤ መጣ፡፡ ፍጹ  ውሸት መሆኑ ቀደሜም ንባቡን ሰለማውቀው አልደነቀኝም ግን የኢትዮጵያ ቴልቪዥን በሉት ሬድዮ በቃ እውነት መናገር ድንገት ተሳስቶ ከአልሆነ የሚያሰኝ እስኪመስል ድረስ ነው ውሸትን የሚያወራው፡፡ ውሸትንም በመደጋገም እውነት እንደማይሆን ቢቀበለውም ተደጋግሞ ሲነገረው ሕዝብ ስለሚሰለቸው ከዛ ይተወዋል የሚል እምነት ስላላቸው ይመስላል፡፡ ይህ በፖለቲካው ሂደት ነው፡፡ ብዙም አይገርምም፡፡

የጥፋት ጥፋት እየሆነ የመጣው የምሁራን ሀሰተኝነትና አመክንዮ የለሽ መረጃን የማዛባት አካሄድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዛሬ ለገባችበት አጣብቂኝ ዋነኛ ምክነያት ብዬ የምለውም ይሄው ከምሁራን የሚነሳ ውሸት ነው፡፡ ምሁሮቹን ምሁረ ናቸው በሚል ብዙ ሰው እየተከተለም ገደል እየገባ ነው፡፡

በዚሁ ወደ ተነሳሁበት ልዝለቅ፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ጉዳይ ትልቁ መወያያ እንደመሆኑ ብዙ አወዛጋቢ ነገሮችን እየታዘብን ነው፡፡ አዋጁ በእርግጥም ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ጭራሽ ሌላ ማምከኛ እንደሆን እናውቃለን፡፡ ቀደም ብሎም የነበረና ሄድ መጣ እያለ የተዛባ ታሪክን በሕዝብ ዘንድ ለማስረጽ የሚሞክሩ ቡድኖች አጋጣሚውን አሁንም ለዚሁ ለታሪክ ማዛባት ዕቅዳቸው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ አዲስ አበባም በሉት ሌላው ዛሬ ኦሮሞ የሰፈረበት አካባቢ ከኦሮሞ መምጣት በፊት ሰዎች እንደሚኖሩበት የሚያስታውሰውን ታሪክ ብዙዎች ሊቀብሩት ይሞክራሉ፡፡ አዲስ አበባ ከመመስረቷ በፊት በዛን አካባቢ “የኦሮሞ ሕዝብ” ታሪክ ቢባል 300 ዓመት  ገደማ ብቻ ነው፡፡ ከዛ በፊት ይኖሩ የነበሩ ቢያንስ ዛሬ ኦሮምኛ እያልን የምጠራውን ቋንቋ የማይናገሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ለቦታዎቻቸው ሥያሜ ነበራቸው፡፡ የራሳቸውም ማንነት ነበር፡፡ እውነትን እንናገር ከተባለ እንዲህ ከመሠረቱ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ ይህን የኖረ እውነት እያወጡ ያሉ ቡድኖችን ላስተዋለ ቆይቶ ሌላ ችግር ሊፈጠር እንደሚቻል መረዳት ይቻላል፡፡ በአለፈው ጽኁፌ የዜይን ሕዝብ ታሪክ እንደምሳሌ አንስቻለሁ፡፡ በኦሮሞ ሥም ኦሮሞነትን እያጦዙት ያሉት ቡድኖች ሁሉ  የሌላውን ሕዝብ ታሪክና ማንነት እያጠፉ እንደሆነ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ሥም ብዙ ታሪኮች እየወደሙ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በቅርቡ የዝቋላ አቦንም የኦሮሞ ነበር ሲሉ በመገናኛ ብዙሀን ሳይቀር ሲያስነግሩ ነበር፡፡ ልብ በሉ ዝቋላ በገዳምነት ሲታወቅ ራሱ ወደ 1000 ዓመት ነው፡፡ ዝም እየተባሉና መለማመጥ እስከሚመስል ድረስ ማስታመሙ ስለበዛ የእነዚህ ታሪክ አውዳሚዎች ሴራ እየገዘፈ ነው የሄደው፡፡ የብዙ ነባር ሕዝቦች ታሪክ በእንዲህ ያለ እየወደመ ነው፡፡ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ነባር ሕዝብ ከተባለ ምን አልባት የጉራጌና የሰሜን ሸዋ  ዛሬ አማርኛ እየተናገረው ያለው ሕዝብ የታሪኩ ባለቤት እንደሆነ የበለጠ አሳማኝነት አለው፡፡ ይህ ማለት ዛሬ አሮምኛ የሚናገረው የአካባቢውን ሕዝብ አይመለከትም ማለት አደለም፡፡ ዛሬ እንደሚታሰበው በዚህ ቦታ ላይ የሚኖሩ ጥንታዊ የኦሮሞ ሕዝቦች የሉም፡፡ ይልቁንም ከማንነታቸው ወደ ኦሮምኛ ተናጋሪነት የተቀየሩ ብዙ ሌሎች ሕዝቦች እንዳሉ እናስባለን፡፡ እንዲህ ታሪክ መካካድና የሌለን ታሪክ እየፈጠሩ አገርን መገንባት አይቻልም፡፡ ሁሉም ቆይቶ የሚያነሳው ጥያቄ ነው፡፡ በስሜት ፊንፊኔ የኦሮሚያ ነች ማለት አይቻልም፡፡

ከእነጭርሱም አዲስ አበባ አሁን በአላት የሰው ሕዝብ ብዛትም ሆነ ታሪካዊ የቦታው እውነታ ዛሬ ኦሮሞ ተብሎ ከሚታሰበው ህዝብ ይልቅ ሌሎች መብት አላቸው፡፡ አዲስ አበባን ደጋግመን የኦሮሞ ምድር ነው የሚል አቋም መያዝ ነው ያለብን ብለው የተነሱ የታሪክ አውዳሚዎችን እድል ሊሰጣቸው አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ዛሬ ኦሮሞ እየተባለ የሚታሰበው ቋንቋ ለቦታው መጤ እንጂ መሠረት አልነበረም፡፡ ይህን በእርግጥኝነት መናገር ይቻላል፡፡ በቦታው መሠረታዊ ቋንቋ ምን ነበር ተብሎ ከተጠየቀ  የታሪክ ተመራማሪዎች ሊገልጡት የሚገባ ነው፡፡ አሁን በአለው ነባራዊ ሁኔታ አዲስ አበባ የብዙ ሕዝቦች መኖሪያ ነች፡፡ መስተዳድሯም በዚሁ እውነት ነው ሊመሠረት የሚገባው፡፡ ኦሮሞ በአካባቢዋና የከተማዋም አንድ አካል እነደመሆኑ በቦታው በሚኖር ማንኛውም ተሳትፎ እደማንኛውም ዜጋ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባዋል እንጂ የታሪክ መሠረትነት አለው የሚለውን ሌላ ውዥንብር ማምጣት አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል እንደሚባለው አይነት ነው፡፡

ምሁር መሆን ነገሮችን ማቀድ፣ መወጠንና ለተግባር ምቹ ማድረግን የሚቀይስ ነው፡፡ አሁን ያለውን ችግር ሁሉ የፈጠረው ቢያንስ በተማሪነት ዩኒቨርሲቲ ደጃፍ እስከሚደርስ ቀለም የቆጠረ ነው፡፡ አሁን ኦሮሞን አማራን ሌላውም የራሱን እያከረሩ ታሪክንና የሕዝቦችን እሴቶች እያወደሙ በአሉ ምሁር ተብዬዎች ምክነያት ሕዝብ ከጊዜ ወደጊዜ የከፋ ችግር ውስጥ መግባቱን እያባሰው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ኦሮሞንና አማራን እነደ ትልቅም ሕዝብ ስለሆኑ በኦሮሞነትና አማራነት እየዘወሩት ከአገራዊ ተሳትፎ እያራቁት እንደሆነ በግልጽ እያየን ነው፡፡ በዋናነት የችግሩ ተጠቂ እየሆኑ የመጡት ደግሞ ራሳቸው ኦሮሞና አማራ የሚባሉት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት ስሞች የታጨቁት ሕዝቦች ግን በእርግጥም ብዙ የራሳቸው ማንነት ያላቸው ሕዝቦች ያሉባቸው ናቸው፡፡

ኦሮሞ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሁሉ አንድ ነው ስለሚባል ሌላው በአሮሞ ሕዝቦች መካከል ያለውን ልዩነት ፍጹም ላለማስተናገድ አዳፍኖት ይገኛል፡፡ ባሌና ወለጋ፣ ቦረናና ሸዋ፣ ሐረርና ኢሊ አባቦራ፣ ሌሎችም በባህልም፣   በአኗኗርም እንደማይገናኙ ግልጽ ነው፡፡ በተቃራኒው ሕዝቦች በቋንቋ ከማይመሳሰሉት አዋሳኞቻቸው ጋር የበለጠ ትስስር ያለው ባህላዊ፣ ማህበራዊና ሀይማኖታዊ ትስስር አለ፡፡ ከዚህም አልፎ በደም ሳይቀር በጣም መተሳሰሩ አለ፡፡ ከዚህ በዘለለ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በግልጽ የሚታወቅ አሁን እንዲነገር የማይፈለግ የሌሎች ብዙ ሕዝቦች ማንነት አሁንም አለ፡፡ የዜይን ሕዝብ አንስቻለሁ፣ ዋናው አምቦን ጨምሮ የወንጪና አካባቢዋ፣ ጥቁር እንጪኒ ጉደር አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች የተለየ ማንነት አላቸው፡፡ በታሪክም የጋፋት ሕዝብ ዛሬ አምቦ የተባለውን ጭምሮ ጨለያ ጌዶ፣ ባኮ ምናምን የሚባሉ አካባቢ ይኖር እንደነበር ይወራል(ከተሳሳትሁ የታሪክ ሰዎች ያርሙኝ)፡፡ ግንደ በረትና አካባቢው እኔ የማውቀው የተመዘገበ ታሪክ አለው፡፡ የዚህ አካባቢ ሕዝቦች የጥንታውያን የሸዋ ነገስታት ዘሮች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ይሄው ታሪክ እስከ ጥቁር እንጭኒ የሚዘልቀውን አካባቢ ያካትታል፡፡ የጥቁር እንጭኒና አካባቢው ሕዝብ ራሱን ከጉራጌ ሕዝብ ጋር የሚያይዝበት ታሪክ አለው፡፡ አሁን በኦሮሞነት የታፈነው እንዲህ ያሉ ማንነቶች እጅግ ስለታጨቁ መፈንዳታቸው አይቀርም፡፡ አሁንም ቢሆን ኦሮሞ በሙሉ አንደ ነን ብሎ አያምንም፡፡ የፖለቲካውን ዋነኛ ንትርክ ላስተዋለም እየተንጸባረቀ ያለው ይህ እውነታ ነው፡፡ ወለጋና ሀረር በኦሮሞነት በአንድ እንደሚጠሩት አደለም፡፡

ዛሬ አማራ በተባለው ሕዝብ ከዚህም ግልጽ ብሎ የሚታይ እውነት አለ፡፡ ቢያንስ የአገውን ሕዝብ አማራ በሚል መጠቅለል አይቻልም፡፡ ዝቅ ሲል ግን ሸዋና ጎጃም፣ ጎንደርና ወሎ ሁሉ አማራ በሚል የሚታሰር የራሱ ማንነት የሌለው ሕዝብ አደለም፡፡ ሕዝቡ ከጥንት ጅምሮ የራሱን ማንነት የሚገልጥበት አኗኗርና አወቃቀር አለው፡፡ ሸዋን እንኳን ብናይ፣ ተጉለቴ፣ መርሀቤቴ፣ መንዜ፣ ምናምን እየተባለ ራሱን ይለያል፡፡ ይህ ተፈጥሯዋዊ ነው፡፡ እነዚህ ማንነቶች በአብዛኛው ከአገሩ ጋር እንጂ ከዘር ማንነት ጋር እምብዛም አይገናኙም፡፡ እርስ በእርሳቸው በጋብቻ በሌሎች ማህበራዊ መተሳሰሮች ይገናኛሉ፡፡ መዋቅራቸው ለዘመናት አስማምቷቸው ኖሯል፡፡ በውስት ያለው ማህበራዊ እሴትና የማንነት መገለጫዎች ግን ትልቅ ዋጋ አላቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ እያወደመ የመጣው የዚህኛው ትውልድ ብሄረሰብ እጅግ የታጨቀና በዛው ልክ የእሱን ቋንቋ ከማይናገሩ ጋር እያራራቀ የመጣ ነው፡፡

በመሆኑም ኢትሐዮጵያን የዜጎቿን መብት የምታከብር አገር ለማድረግ መጀመሪያ መፍረስ ያለባቸው ብሄረሰብ በሚል የታጨቁ መዋቅሮች ናቸው፡፡ ወለጋን በወለጋነቱ ጎጃምን በጎጃምነቱ፣ ባሌንም በባሌነቱ ወሎንም እንደዛው እንደድሮው መመለስ ካልተቻለ መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ የፍትህ አገር አትሆንም፡፡ አሁን አንዱ ብሄር ሌላውን ለመጫን ነው እሽቀድምድሙ እንጂ ስለዜጎች መብት ማንም አያስብም፡፡

ታሪክ እንደታሪክነቱ ለመዝገብ ይሆናል፡፡ ሸዋ በሸዋነት ቢደራጅ እደተባለውም ልዩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተሞክሮን ማየት ይቻል ነበር፡፡ ቋንቋ፣ ባኅል ምናምን በዚህ ዘመን ትልቅ ጉዳዮች አደሉም፡፡ እነሱን ማክበር አለምአቀፋዊ መብት እንጂ አገሮች ስለፈቀዱና ስላልፈቀዱም አደለም፡፡

ነገረሮችንም ለአስተዳደር ቀና ያደርጋል፡፡ ዛሬ ምሁር ነን የሚሉትን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት የአሜርካው ዋና ከተማ ዋሽንግተን አማርኛን ጨምሮ ብዙ ሌሎች ቋንቋዎች በሥራ ቋንቋነት እያገለገሉ እንደሆነ እያያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዛ ያለ አሰራር ለመፍጠር ሲባል ዋና ማሰናከያ ሆኖ እናየዋለን፡፡ አዲስ አበባ ኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቋንቋዎችንም ማስተናገድ የሚያስችል መዋቅር ቢኖራት በእርግጥም የአገሪቱ ዋና ከተማነቷን ከማሳየቱም በላይ የባህል ጥንካሬንም የፈጥራል፡፡ የብዝሀ ባህል ከተማ ትሆናለች፡፡ አዲስ አበባን ለኦሮሞ የሚለው አእምሮ ግን እውነትን ለመቀበል የማይወድ እንደሆነ ከወዲሁ በግልጽ ሊነገረውና ለ26 የለመደበትን የውሸት ጉዞ ማቋረጥ ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባ የአዲስ አበባዎች ነች፡፡ ቦታዎቿም ሆኑ መንገዶቸቿ ታሪካቸው ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ብቻ አልተያያዘም፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሞ ምሁር ነን እንደሚሉት ባለጌ ሥያሜዎችን ያጠፋች የታሪክ አውዳሚነት የሚንጸባረቅባም ከተማ አደለችም፡፡ ብዙ የአካባቢ ሥያሜዎቿ በእርግጥም በኦሮምኛ ነው የሚታወቁት፡፡ ለምን ሆኑ ብሎ የተከራከረ ያጠፋም የለም፡፡ ለምንስ፡፡ ሥያሜዎቹ ድሮ ሲጠሩበት ነበር በዛው ቀጠሉ፡፡ አሁን ግን በሌላ ስም ያሉ ቦታዎችን የግድ ወደ ኦሮምኛ እንቀይራለን ሲባል ሌላ ታሪክ ማውደም ነው የሚሆነው፡፡ ልክ የዝዋይን ከተማ ባቱ እንደተባ ሁሉ፡፡ ዝዋይ ሥያሜዋን ከሀይቁ ሀይቁ ደግሞ ስያሜውን ከዜይ ሕዝቦች እንዳገኘ እውነታን ተክዶ ነውና የዝዋይን ሥም ባቱ የተደረገው፡፡ የዚህ አይነት አካሄድ አላማው የሕዝብን ታሪክ ከማውደምና ሕዝብም አንዱ በሌላው ላይ እንደይተማመን ከማድረግ በዘለለ ኢኮኖሚያዊ ተጽኖም ሊኖራ ይችላል፡፡ ሥምና ታሪክ ሲቀየር ብዙ ወጭ ይወጣል፡፡ ሊያውም ለጥፋት፡፡

ሰሞኑን አንደ ፕሮፌሰር ተድላ የተባሉ ሰው መጀመሪያ እስኪ ሰው ነን ከሚለው እንጀምር ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ መልካም ነው እንደዛ ማለት ቢቻል፡፡ ግን የሰው ተፈጥሮ እንደዛ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ሕዝቡ የራሱ የሆነ የማንነት መገለጫዎች አሉት፡፡ አሁን ያለው ማንነት እየተባለ የሚውጠነጠነው ምሁር ተብዬዎች በሕዝቡ ላይ የጫኑበት እንጂ የትኛውም ሕዝብ በተፈጥሮ ሂደት ያጣው አደለም፡፡ ሕዝብ በአኗኗር ሂደት በሚተሳሰርበት ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ እሴቶች የራሱን ማንነት ይገልፃል ማንም ሳይጫነው፡፡ አሁን ምሁር ነን የሚሉት የፈጠሩለት ማንነት ግን የሕዝቡን የራስ ማንነት በግዙፍ ማንነትን በማይገልጹ መጠርንፎች የታሰረ ቆይቶ የሚፈነዳ አይነት ነው፡፡ የሕዝብ ትንንሽ ማነነቶች ለግለሰብ መብትም ቅርብ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ለሰው፡፡ ሲገዝፉ ግን የማይመሳሰሉ ማንነቶች በግድ ሲለሚታጨቁ ሁሌም ነጻነት የለም፡፡ አገር በሚለው ሕዝብን አንድ ማድረግ ይቻላል ግን ትንንሽ ማንነትን በማፈን ፈጽሞ አይቻልም፡፡

እደግመዋለሁ እነዚህ ማንነቶች ለግለሰብ መብት በጣም የቀረቡና ሰው ከልቡ የእኔ የሚላቸው ናቸው፡፡ ከዛ እስኪ ምሁር ነን የሚሉት የሚያዋጣ ከሆነ ኦሮሞና አማራን ከእነዚህ በኋላ ያምጡዋቸው፡፡ ማንም ዞር ብሎ አያያቸውም፡፡ ያኔ ሁሉም አገሬ በሚላት ኢትዮጵያ አገሩን፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶቹን በግዙፍነት የሚናፍቃቸውና የሚንከባከባቸው ይሆናል፡፡ እኛ እንደውም እንደመታደል ሆኖ የቀደሙ ማነነቶቻችን ከዘር ጋር ባለመገናኘታቸው ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ኢጆሌ ባሌ ማለት የባሌ ልጆች አማራ ኦሮሞ፣ ምናምን አያውቁም ነበር፡፡ የባሌ ልጅነት እንጂ፡፡ ኢጆሌ ጂማ፣ ኢጆሌ ሻምቡ የሚለው ከዘር ጋር አልነበረም፡፡ ከሌሎች ጋርም ሲገናኙ እርስ በእርስ አንዱ የአንዱን ማንነት ለማወቅና በማድነቅ እንጂ አንደዛሬው በመጠላላት አልነበርም፡፡ ያኔ አንኳን ከአገር ተሰደው በሰው አገር ይቅርና ከየክፍለአገራቱ ተሰባስበው በሚገናኙበት የትምህርት ተቋማት በሚኖራቸው ግንኙነት በሚፈጠር ጓደኝነት እስከትልቅ መዛመድ የደርሱ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ በብሄረሰብ ሥም አጥተናል፡፡ የብሄረሰቡ አከፋፈል አጋጣሚውን ለራሳቸው ሴራ ለሚጠቀሙ እየተመቸ ከጊዜ ወደጊዜ እኛን እያዘቀጠ ነው፡፡ ትውልድን ለማዳን እውነታን መጋፈጥ፡፡

አመሰግናለሁ!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!

አሜን!

ሰርጸ ደስታ