July 2, 2017

የቀድሞው የህወሃት ታጋይና በኋላም የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ኤታማጆር ሹም የነበረው ጻድቃን ገብረ ተንሳዔ ከአንድ ዓመት በፊት ‘ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ መውጫ አቅጣጫ አመላካች ሃሳቦች ‘ በሚል አንድ አነጋጋሪ ጽሑፍ አቅርቦ ነበር ።

አሁን በቅርብ ደግሞ ‘ኢትዮጵያን መልሶ የቀይ ባህር ኃይል የሚያደርግ ፖሊሲ ያስፈልጋል’ በሚል ዘለግ ያለ ቃለ መጠይቅ ከአዲስ ዘመን ጋር አድርጎ በድረ ገጾች በድምጽ ተለቆ ለማድመጥ ችለናል።

ፃድቃን የዛሬ ዓመት አቅርቦ የነበረው ጽሑፍ በተወሰነ ደረጃ አነጋጋሪ የነበረ ቢሆንም፣ አንዳንድ ሃሳቡን መሰረት ያደረጉ ትችቶች ከማድረግ ውጭ፣ በአብዛኛው ሀሳቡን ከመሞገት ይልቅ ትኩረት ያሳረፈው ግለ ታሪኩ ላይ ስለነበር፣ በቂና ፍሬያማ ውይይት ሊካሄድበት ሳይችል ቀርቷል።

ዘንድሮም እንደአምና ፣ ፃድቃን ያቀረበው ሃሳብ ጭብጥ ዙሪያ ውይይት ከማካሄድ ይልቅ በአብዛኛው ትችቱ፣ ያለፈ ታሪኩ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ ያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች በጥሞና አጢኖ አስፈላጊውን ውይይት ለማካሄድ አልተቻለም ።

ጻድቃን ማንነቱን ሳይደብቅ የጻፈው ጽሑፍና ቃለመጠይቅ በመሆኑ፣ ስለከዚህ ቀደም አቋሙና፣ ሀገራችንም አሁን ላለችበት ሁኔታ የራሱ ድርሻ አንዳለው የሚካድ ባለመሆኑ፣ በየጊዜው የሚያቀርባቸውን ጽሁፎች የድሮ ማንነቱ ላይ ብቻ በማተኮር አቅልሎ ከማየት፣ ሃሳቡ ላይ አትኩሮት በማድረግ መተቸት ወይንም መሞገት የተሻለው አማራጭ ይመስለኛል።

ለኢትዮጵያ ደህንነት የባህር በር አስፈላጊነትና ፣ ለኢኮኖሚ አንቅስቃሴዋ የወደብ አስፈላጊነት ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ የነበረ ቢሆንም፣ በጠባብ የትግራይ ብሄረተኝነት ተጨፍኖ የነበረው ህውሃት፣ ሃገራዊ እይታ ስላልነበረው (መለስ ባህር በርን አስመልክቶ የኛ እይታ መጀመሪያ ከትግራይ አንጻር ነው ይል አንደነበረው!) ታሪካዊውን የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት አሳልፎ መስጠቱን ያገናዘበ በሚመስል መልኩ አሁን ፃድቃን፣ እንደቀድሞው ኢትዮጵያን መልሶ የቀይ ባህር ኃይል የሚያደርግ ፖሊሲ ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሲሰነዝር፣ በበኩሌ ከረፈደም ቢሆን እንኳን ደህና መጣህ ለማለት እመርጣለሁ።

ጥያቄው ወቅታዊ ከመሆኑም ባሻገር ምንም አይነት ዘለቄታዊ ሃገራዊ ራዕይ ሳይኖረው፣ የመለስን ራዕይ ተግባራዊ እናደርጋለን በሚል በ ዕውር ድንብር ለሚጓዘው የህወሃት መራሹ መንግስትም (አሰብን አስመልክቶ መለስ እኛ ካልተጠቀምንበት የግመል መፈንጫ ሆኖ ይቀራል የሚል ጨቅላና ግብዝ እይታ እንደነበረው መገንዘባቸውንም እንጃ)ማስታወሻና ምናልባትም የማንቂያ ደወል አድርጎም ማየት ይቻላል ።

ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያን ሃገራዊ ጥቅም የሚመለከት ጉዳይ አስመልክቶ የሚነሳን ሃሳብ፣ ማንም ያንሳው ማንም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በስፋትና በጥልቀት መወያየት፣ ተወያይቶም ወደ አንድ አሰባሳቢ አቋም በመድረስ ተጽእኖ ለመፍጠር መታገል፣ ለነገና ለከነገ ወዲያ የሚተው አይመስለኝም።

አበጋዝ ወንድሙ