July 4, 2017 16:40

የብሔር/ብሔረሰቦች መብት ይከበር ብሎ የተነሳው ኮምኒስታዊ የተማሪ እንቅስቃሴ በትግራይ በኩል ብሔረሰባዊ የትጥቅ ትግሉን በተሳካ ሁኔታ ካገባደደ በሁዋላ መንደሮችንና ከተሞችን ሳይቀር በዘር ግንድ ላይ በተሰመረ ድንበር ክልል (አጥር) ገድቦ አገሪቱን ወዳልታወቀ ጥፋት አቅጣጫ ይዟት መጓዙን ቀጥሏል። ለወያኔ ሹማምንት እና የጎጥ ካድሬዎች የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሰረታዊው የሰብአዊ መብት መረጋገጥ እና የህግ በላይነት ሳይሆን የትኛው ብሔረሰብ በየትኛው ‘ክልል’ የበላይ እና የበታች ይሆናል የሚለው ጉዳይ ሆኗል።

ዜጎች ዘራቸውን ሳይሆን ዜግነት በሚፈቅደው ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት ተጠቅመው አገራቸውን ብለው ከትውልድ ትውልድ በቆዩበት ፣ ወልደው ስመው ፣ ድረው ኩለው ፣ አሳድገው ለወግ አብቅተው ባረጁበት ስፍራ ሁሉ ማን አለቃ ማን ምንዝር ፣ ማን ከንቲባ ማን ግብር ከፋይ ፣ ማን መጤ ማን ባላገር ፣ ማን ልዩ ተጠቃሚ ማን ተርታ መንገደኛ… ምን ቀረ? ማን ወርቅ ማን መዳብ እንደሆነ ዘር ላይ የተመረኮዘ ድልድል ቀርቦ ሁሉም በጎጥ መስፈርት እንዲለካ እንዲመዘን ሆኗል። ከህወሀት የፖለቲካ ፕሮግራም ጋር የተዳቀለው የወያኔ ህገ መንግስት ይህ እንዲሆን ግድ ብሏል።

ይህን የምለው አዲስ አበባ የማን ናት ብለው ከፊሉ የዘር ሀረግ እየቆጠሩ ሌሎቹ ጥንታዊ አድባራት ስም እየጠሩ ከሚሟገቱት ካንዳቸውም ጋራ የማልስማማ መሆኔን ለማመልከት ነው። አዲስ አበባ የራሷ የበቃ ታሪክ ያላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የክፉም የደጉም ቀን መናኸሪያ ናት።
አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊነት ነው። ወያኔ ከምርጫ 97 አንስቶ በተቀነባበረ ስልት በከተማይቱ የሚያራምደው ፖሊሲ ያንን ኢትዮጵያዊነት ማኮላሸት ነው። ነዋሪዎች በልማት ስም ተፈናቅለዋል ፤ ለብዙ አሰርት አመታት በእድሩም በደጀ ሰላሙም ተቀራርበው የገነቡት መተሳሰር ተበጣጥሷል ፣ ወላጆች ሲፈናቀሉ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል ፤ አዛውንት እና አቅመ ደካሞች ጠዋሪ እና ሲታመሙ ጠያቂ እንዲያጡ ተበይኖባቸዋል። ዛሬ ደግሞ እስከናካቴው አዲስ አበባ የሚባል ከተማ የለም ተብለዋል።

አዲስ አበባ ፊንፊኔ ትሆናለች ምክንያቱም ቁምነገሩ ነዋሪዋ ማን ነበር አሁንስ ማን ነው የሚለው ሳይሆን አቀማመጧ የኦሮሞ ህዝብ ዙርያውን ከቦ መኖሩ ግምት ውስጥ መግባቱ ነው። ይህን መሰረት ያደረገ አዲስ አዋጅ ተረቆ በሚንስትሮች ፀድቆ ጨዋታው ወደ ወያኔ 99% ፓርላማ ሜዳ ተልኳል… ሰነድ የጨበጠ ወይንም በአፈ ታሪክ እንኳ ፊንፊኔ የሚባል ከተማ ኖሮ ባያውቅም አዋጁ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ‘መጤ’ የሚባሉ ዜጎችን ለይቶ አድሏዊ ስርዓት ለማስፈን መወጠኑን ያረጋግጣል።

ትንሽ ስለ ‘ፊንፊኔ’

እኔ እሰከማውቀው ድረስ የኦሮሞ ህዝብ አዲስ አበባን ፊንፊኔ በሚል መጠሪያ አያውቃትም። እንደ አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ኢትዮጵያዊ መናገር የምችለው ፊንፊኔ የሚባል አጠራር የሰማሁት ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ወዲህ ነው። በማጠያየቅ እንደተገነዘብኩት ደግሞ ይህን ስያሜ ለከተማይቱ ያወጡት እነ ሌንጮ ለታ የኦነግን ፕሮግራም ሲቀርፁ በነበረበት ሰነድ ነው። እነኝህ ሰዎች ከወለጋ ቄለም እና ደምቢዶሎ መጥተው አዲስ አበባን ፊንፊኔ ናት ሲሉ ምን ታሪካዊ መሰረት ይዘው እንደሆነ የሚነግረኝ አላገኘሁም። ይሁንና ላንድ አፍታ ወጣ ብለው እኔ የተወለድኩበትን አካባቢ ህዝብ ቢያነጋግሩ ኖሮ ፣ እውን ለኦሮሞ ለህዝብ ታሪክ እና ባህል አክብሮት ቢሰጡ ኖሮ ምናልባት እንደ ወትሮው ‘ሸገር’ ይሏት ነበር። የሸዋ ኦሮሞ በራሱ ቋንቋ ሀሳብ ሲለዋወጥ አዲስ አበባን ሸገር ይላታል። የሚያወራው በአማርኛ ሲያነሳት ግን ያው አዲስ አበባ ይላታል።

አፌን በፈታሁበት እና የእረኝነት እድሜዬን ባገባደዱኩበት ጅባትና ሜጫ ፣ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ የኖርኩበት ጨቦ ፣ በቾ እና አመያ ፣ አጠቃላይ የምእራብ ሸዋ ኦሮሞ ህዝብ በራሱ ቋንቋ አዲስ አበባን ‘ሸገር’ እያለ ሲጠራት መቆየቱን የሚያስተባብል የለም። ወግ ያለው ጥናት ቢደረግ የዚህ አጠራር መሰረት ምን እንደሆነ ማውቅ የሚቻል ይመስለኛል። ዛሬ ድረስ ብዙ ያራዳ ልጆች ጭምር አዲስ አበባን ሲያቆላምጧት ሸገር ማለታቸው አለምክንያት አይደለም። አጠራሩ ከኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኑ የተወረሰ መሆኑም አይጠፋውም። ይኼ እንግዲህ የህዝብን ባህላዊ እና ታሪካዊ መስተጋብር የሚያንፀባርቅ አሻራ ነው – የህዝብ መፈቃቀር። ይህም ሆኖ የአዲስ አበባን ታሪካዊ መሰረት የጨበጠ ስም መቀየር የሚያስፈልግበት አንዳችም ሰበብ የለም።

እጅግ ሁዋላ ቀር መገናኛ ተንሰራፍቶ በቆየባት አገራችን እያንዳንዱ መንደር ወይንም ቀዬ ፣ አካባቢ እና ሰፈር እዚያው ነዋሪ በሆነው ህዝብ ትርጉም ሊስጠው በሚችል መልኩ ስም ሲወጣ ቆይቷል። ይኼ እኛ አገር ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር በኖረባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚደረግ ነው። መንደሮች ወይንም አካባቢዎች ስም የሚወጣላቸው በጭፍን ወይንም የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ በፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ አልነበረም። ለአካባቢው ነዋሪ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ስያሜ ይወጣል። አባ ጅፋር ወልቂጤ የሚል ስም ሲያወጡ ያካባቢውን ገበሬ ማማከር አላስፈለጋቸውም።

አዲስ አበባ የተቆረቆረችው ደግሞ በዘመኑ አገር እና ህዝብ የማሳደር ሀላፊነት ትከሻቸው ላይ በወደቀ የራሷ ዜጎች ነው። ያኔ አዲስ አበባ የሚለው ስያሜ ይበልጥ ትርጉም ይሰጥ የነበረው ለነዋሪው እና አከባቢው በቅርብ ርቀት ላለው ህዝብ ነበር ማለት ይቻላል።

ሐረር ወይንም ደምቢዶሎ የሚኖር ኦሮሞ በዚያን ዘመን ስለ አዲስ አበባ ታሪካዊ ስፍራ የሚያውቀው ወይንም እንዲያውቅ የሚጋብዘው ምክንያት አልነበረም። መቀሌ እና ሽሬ የሚኖር ትግሬ ፣ ጎጃም እና ጎንደር ነዋሪ የሆነ አማራ ምናልባትም እድሜውን ሙሉ ያችን አዲስ አበባን ላይጎበኛት ይችላል። ዘመን ሲለወጥ እና የመገናኛ አገልግሎቱ ፣ የልማት አውታሩ እየሰፋ ሲሄድ ዩንቨርሲቲ ለመማር አለበለዚያም ዘመድ ለመጠየቅ ወይንም ስራ ፍለጋ… ምናልባት ይጎበኛት ይሆናል። ለሱ አዲስ አበባ ማለፊያ ማግደሚያ ደማቅ ያገሬ ርዕሰ ከተማ እንጂ ሌላ አልነበረችም። ሲመጣ ተቀብላ ታስተናግደዋለች ፣ ሲሄድ የማይረሳ ትዝታ አስታቅፋ ትሸኘዋለች።

በመሰረቱ ዛሬ አገሪቱን የሚያስተዳድሩት የጎጥ ጦር አበጋዞች አዲስ አበባን የሚያውቋት ቁምጣ እና ሸበጥ ታጥቀው በወረሯት ጊዜ ነበር። ስለ ነዋሪዋ መስተጋብር ፣ ስለ ህዝቡ አኗኗር ፣ ስነልቡና እና ከአካባቢው ህዝብ ጋር ፀንቶ ስለቆየው ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው ግንዛቤ ዚሮ ነበር ማለት ይቻላል። በምርጫ 97 ወቅት የደረሰባቸውን ሽንፈት አስተውሎ መሪያቸው “አዲስ አበባ ውስጥ የዘር ፖለቲካ አይሰራም” ወደሚል ድምዳሜ መድረሱንና ካድሬዎቹ አደረጃጀት ስልት በመቀየር የወጣት ፣ የሴት ሊግ እያሉ እንዲያሰባስቡ ቀጭን መመሪያ መስጠቱ ያስታውሷል። ወቅቱ አዲስ አበባ ለጎጥ ፖሊቲካ አልመችም ብላ ድምፁዋን ከፍ አድርጋ ያስተጋባችብት አጋጣሚ ነበር።

በመሆኑም አዲስ አበባ ስለ ስሟ ማንነት ቆርቁሮት ፣ እንደ ችግር ተቆጥሮ ጥያቄ ያቀረበ ወገን እንዳለ ተሰምቶም አያውቅም። ዛሬ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ፋይዳ ያለው ጠቀሜታ እና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ብትሆንም አገሪቱ የምትመራው ደግሞ በዘር ማንነት ላይ በተደራጁ የጦር አበጋዞች ስለሆነ ዘረኛ ልዩ ጥቅም ፣ ልዩ መብት የሚባል ፈሊጥ ተቀስቅሶ ከተማይቱ ላይ ተዘምቷል። ገበያ ፣ ገንዘብ እና ስልጣን ያሰከራቸው የጎጥ ጦር አበጋዞች ለስልጣናቸው ዕድሜ ማርዘሚያ ሌላ የዘር መስፈርት እያዘጋጁላት ነው።

መሰረታዊ ሰብአዊ መብቱን በታጠቀ ወራሪ ጦር የጨፈለቁትን ህዝብ ዛሬ ልዩ መብት ልናጎናፅፍህ ነው የሚል አዋጅ ያስነግራሉ።

አዲስ አበባ ዘር አላት?

አባ ጅፋር ከጂማ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ እርፍት አዳር የሚያደርጉባትን መንደር ‘ወልቂጤ’ ብለው ሰይመዋል። ትርጉሙ ‘እኩል በኩል’ ማለት ሲሆን ይኸውም ያች መንደር በጅማ እና አዲስ አበባ መካከል እኩል ርቀት ላይ መሆኗን ለማመልከት እንደነበር ይታወቃል። ወልቂጤ በመሰረቱ የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ መንደር አልነበረችም ፣ አሁንም አይደለችም።

ትናንትም ሆነ ዛሬ ነዋሪዎቿ ስሟን ለመቀየር የሚያስገድዳቸው ምክንያት አልታያቸውም። ነገ የሚመጣውን ለመተንበይ ግን የዘመኑ ፖለቲካ አያያዝ አይፈቅድም። አባ ጅፋር እንደ አላፊ አግዳሚ እንግዳ ድንኳናቸውን ተክለው ከማደር በላይ የመንደር ስም ሰጭ ማን አደረጋቸው ብሎ ያኮረፈ ወይንም ጥያቄ ያነሳ ወገን እስከ ዛሬ መኖሩን አላውቅም። እስከ ዛሬ ድረስ የአባ ጅፋርን ነብስ ይማርና ወልቂጤ ለማንም ሳትሸጥ ሳትለወጥ አለች። ያው እንደቀድሞው ለፍቶ አዳሪ እና ታታሪ ህዝብ እየኖረባት ነው።

የወያኔው ረቂቅ አዋጅ እንዲህ ይላል “ከተማዋ ፊንፊኔ ተብላ በመቆርቆሯ…”። እንዲያው በሞቴ ፊንፊኔ የሚባል ከተማ መቼ እና በማን ተቆረቆረ? ብለን ብንጠይቅ እኛ የቅርብ ነዋሪዎቿ የሆነውን ኦሮሞዎች ቀጥቅጠው እየገዙን ባሉት የትግራይ የጦር አበጋዞች ዘንድ ያስገምተን ይሆን?

ትንሽ የቤተሰብ ታሪክ ላክልበት – አያቴ ቀኛዝማች ጉተማ ፊጤ አዲስ አበባ መርካቶ አራተኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1911 አካባቢ አንድ መንደር ቆርቁረዋል። ዘመዶቼ እንደነገሩኝ አውቶቡስ ተራ እስከ ፋሲል መድሀኒት ቤት የነበረው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ንብረትነቱ የአያቴ ነበር። ፋሲል መድሀኒት ቤት ጀርባ ቀበሌ 32 ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ግቢ ውስጥ ለራሳቸው መኖሪያ ትልቅ ቪላ እና ዙርያውን ደግሞ የሚከራዩ ቤቶች አንፀዋል።

የዚያ ሰፈር ነዋሪዎች ሊያረጋግጡ እንደሚችሉት (የልማት ተፈናቃይ ሆነው ገሚሱ ጎዳና ላይ እየተኙ ነው) አያቴ ከሰሯቸው ውስጥ አብዛኞቹ ሳር ክዳን ቤቶች ነበሩ። የመጨረሻው የሳር ክዳን ቤት በቆርቆሮ የተተካው ብታምኑም ባታምኑም 1964 እንደ እኛ አቆጣጠር ነበር። የመርካቶን የመጨረሻ ሳር ጎጆ አቶ ሀይሌ ቱሬ የሚባሉ ትጉህ ዜጋ ይኖሩበት ነበር። በመርካቶ የሳር ቤት አሻራ የቆየው እስከ እኛ ዕድሜ ጊዜ ድረስ ነበር ለማለት ነው። ታዲያ  በሰፈሩ ህብረተሰቡን ያሰባሰበው ትልቁ ማህበር ‘ጉተማ ፊጤ’ እድር እየተባለ እስከ ደረግ ዘመን ማብቂያ ድረስ ይጠራ እንደነበር አስታውሳለሁ። ቀኛዝማች ጉተማ አፄ ሀይለስላሴን ተከትለው ሰገሌ ፣ ሁዋላም ማይጨው የዘመቱ ብዙ ቤተዘመድ ጦርነቱ ላይ አጥተው የተመለሱ አገራቸውን የሚወዱ ዜጋ ነበሩ። የሞቱት በ1951 አካባቢ ነው። አዲስ አበባ እያንዳንዷ መንደር ገብታችሁ ብታስሱ የሳቸውን አይነት ተመሳሳይ ታሪክ ታገኛላችሁ።

እንደ እኔ አያት ሁሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ መንደሮች የመጡ ዜጎች በሙያቸው ፣ ጥበባቸው እና ባገኙት መስክ ተሰማርተው አዲስ አበባ ላይ አዲስ ህይወት ገንብተዋል። ዘር የማትቆጥረው አዲስ አበባ ዶርዜውን ፣ ትግሬውን ፣ አማራውን እና ኦሮሞውን አጎራብታ በአንድ ማህበር ፅዋ አቋድሳ ፣ በሀዘን ጊዜ ለመፅናናት አቀራርባ ፣ በሰርግ ጊዜ አንድ መድረክ ላይ ዳንኪራ አስረግጣ ፣ በክፉ በደጉ ሁሉ አቅፋ ደግፋ አስተናግዳቸዋለች። ያንን ፅኑ መሰረት ላይ የቆመ ታሪካዊ ማንነት ለማፍረስ ከትግራይ በረሀዎች ጦር ሰብቀው የመጡ ወራሪዎች ዘምተውበታል።

በኔ እምነት አንድን ከተማ ወይንም አካባቢ ላንድ ዘር ልዩ መጠቀሚያ የማድረግ ዝንባሌ የሚመነጨው ፀረ-ኢትዮጵያ ከሆነው የህወሀት ማኒፌስቶ ብቻ ነው። ተጨባጭ ታሪክን ክዶ ፣ የህዝብን በጎ ታሪክ አዋርዶ ለጠባብ የድርጅት አላማ ሲባል አገርን ለጥቃት ማመቻቸት የህወሀት ማኒፌስቶ መርህ ነው። ኢትዮጵያ የህወሀት የጥፋት ኢላማ ሁና ቆይታለች – አሁንም የተቀየረ ነገር የለም።

እንጂ የከተሞች እና ክፍለ አገራት ባለቤትነት ዘር ላይ የተመረኮዘ ታሪካዊ መሰረት አላቸው ከተባለ ከአዲስ አበባ ይለቅ አስመራ ወደ ታሪካዊ ባለቤቷ እንድትመለስ ለምን አይታገሉም። ያቺ ከተማ በማን ተቆረቆረች። ከትግራይ ወይንም ትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ ጋር ያላትስ ታሪካዊ ግንኙነት ምንድነው? በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የኢትዮጵያም ጭምር ገዢ አሳዳሪ የነበሩት ርዕሰ ከተማቸው መቀሌ የነበረው አፄ ዮሐንስ እና ራስ አሉላ አስመራ ላይ ምን ሲያከናውኑ ቆዩ?
ህወሀት ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሲረዳ እና የትግራይን ድሀ ልጅ ምፅዋ እና ናቅፋ ከሻቢያ ጎን አሰልፎ ሲማግድ ታሪካዊውን የትግራይ ህዝብ አሻራ እና የኢትዮጵያን መሰረታዊ ማንነት እየፋቀ መሆኑን ሹክ ያለው አልነበረም ማለት ነው። እንዲያው ይኼ ጥንት እነ እገሌ ኖረውበት ነበርና ዛሬ ስያሜውም ባለቤትነቱም መቀየር አለበት ሲባል የዚህ አይነቱ አመክንዮ በቅድሚያ ተግባራዊ መሆን ያለበት የተፃፈ ሰነድ ጭብጥ ታሪክ ባላቸው እንደ አስመራ ባሉት ላይ ቢሆን አይሻልም ነበር? ጥያቄዬ ለህወሀት ነው እንጂ ለዛሬዎቹ የአስመራ ልጆች አይደለም።

ልዩ ጥቅም በአዋጅ

አዲስ አበባ ዙርያ ያለው ዜጋ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሟላልህ የከተማይቱ ስም ፊንፊኔ በሚል ከተቀየረ በሁዋላ ነው የሚል መልዕክት ያዘለ አዋጅ ነው። የንፁህ ውሀ መጠጥ አገልግሎት የምታገኘው ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎትህ የሚረካው ፣ ሆስፒታል ገብተህ የምትታከመው አዲስ አበባ ወደ ፊንፊኔነት ስትቀየር ነው የሚል መልዕክት አዋጁ ውስጥ ሰፍሯል። በሙስና እና ስግብግብ ዘራፊዎች እጅ ወድቃ ለነዋሪዎቿ ሲኦል የሆነችው አዲስ አበባ ለራሷ አሮባት በዙርያዋ ነዋሪ ለሆኑ ገበሬዎች የተትረፈረፈ አገልግሎት የምታቀርበው ስሟ ሲቀየር ብቻ ነው። ይኼ ነው የአዋጁ ይዘት።

አዲስ አበባ በወያኔ ዘመን እንኳን የአካባቢውን ገበሬ ፍላጎት ልታረካ ለራሷ የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት የላትም ፣ የኑሮ ውድነት አብዛኛውን ነዋሪ ከሰውነት ተራ አውጥቶት የሚገኝ መሆኑን የዕለት ዘገባዎች ሳይቀሩ ይመሰክራሉ፣ የመብራት መቆራረጡ ፣ የውሀ ወረፋ ፣ የህክምና አገልግሎት እጦት ፣ የትምህርት ቤቶች ጥራት መውደቅ ፣ ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር… ስንቱ ይነገራል። ወያኔ የያዘው ውሀ ከባዶ ጣሳ ወደ ተቀደደ ጣሳ ማገላበጥ ነው።

በዚህ ሳምንት ይፋ የሆነ ሪፖርት የሚከተለውን አስፍሯል…
አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ “የትምህርት ጥራቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ አሽቆልቁሏል” በሚል ርዕስ ስር እንደዘገበው “… የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል በሚል ከእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቅርቡ የተደረገው ይሄው ጥናት፤ የተማሪዎችን የአስተሳሰብ አቅም ከሌሎች አገራት ጋር በማነፃፀር ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡ “በኢትዮጵያ የሚገኙ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ፣ አሜሪካና ሲንጋፖር በመሳሰሉ የአደጉ አገራት ከሚገኙት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ ጋር እኩል ነው…” ይላል።

ይህን አይነቱን አሳፋሪ የስራ አፈፃፀም የታቀፈ ስርዓት የአንዲትን ታሪካዊ ርዕሰ ከተማ ስም ለመቀየር አዋጅ ያረቃል። አገሪቱ ወደተረጋጋ ሰላም እና ዕድገት የምትጓዝበትን ትልም ሳይሆን ዜጎች ዋስትና በሌለው ጥቃቅን ጉዳይ ላይ እንዲራኮቱ ተንኮል ይሸርባል።

አናሳዝንም ወይ? ነው ያለው ሙዚቀኛው!

ወያኔ የአዲስ አበባን ስም ለመቀየር ብሎ ባወጣው አዋጅ ሰበብ የተነሳው አተካሮ ሌላው አሳዛኝ ትርኢት ነው። ትርኢቱን በብዙሀን መገናኛ መድረክ ላይ የሚያራግቡት አብዛኞቹ ያው የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ግብረ ሀይል ካድሬዎች ቢሆኑም በዚህ ከፋፋይ መረብ ውስጥ ጥልቅ ብለው አቧራ የሚያስነሱ ቅን ዜጎችም እንዳሉ ማስተዋል ይቻላል። ገሚሱ ለኦሮሞ ህዝብ መብት ተሟጋች ሆነው ግፋ ወደፊት የሚሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ አዲስ አበባ የአማራ እንጂ የማንም አይደለችም በሚል እጅግ አሳፋሪ ሙግት የገጠሙ ናቸው። ሁለቱም ተቃራኒ ወገኖች አርቆ አስተዋይነት የነጠፈባቸው ግን የሚያስከትሉት ጥፋት መዘዙ አገሪቱን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። በመካከሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያወገዙ መስሎ አንድን ህዝብ በጅምላ የሚረግሙ እና የሚያበሻቅጡ ወገኖች አሉ።

አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊ እንጂ ምንም ልትሆን እንደማትችል ሁሉም ወገን ጠንቅቆ ሊረዳው የሚገባ ይመስለኛል። አዲስ አበባ ላይ ያነጣጠረው የወያኔ ጥቃት ስም በመቀየር ብቻ የሚገታ መስሎ ከታየን እጅግ አድርገን ተሳስተናል። ጥቃቱ ኢትዮጵያን ከገፀ-ምድር ለመፋቅ ወያኔ የጠነሰሰው የረጅም ጊዜ አላማ አካል ነው። መዋጋት ካስፈለገ ልንዋጋ የሚገባን ህዝብ ላይ የተጫነውን የወያኔ ፖለቲካ ሰነድ ነው። እነሱ በማያሻማ ቋንቋ አላማቸውን ነድፈው አስቀምጠዋል ፤ እያንዳንዷ የሚወስዷት እርምጃ ወደ አላማቸው ግብ የሚወስድ አውራ ጎዳና ነው። ይህን በንፁሀን ዜጎች ደም የበከተ የጥፋት ጎዳና አንድ ላይ ተሰልፈን መዝጋት ካልቻልን አዲስ አበባችን ብቻ ሳትሆን እኛም ማንነታችን ይጠፋል።