July 5, 2017 14:58

. አባ ተክለ ሃይማኖት፥ ያለተወዳዳሪ መቅረባቸውን በመቃወም፣ የሲኖዶሱ ሕግ እንዳይፈርስ አሳስቤያለሁ፤

. በክልሉ መንግሥት ማሳሰቢያ ከመረጥን፥ ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳል፤ ቅ/ሲኖዶስም እንደሌለ ያስቆጥራል፤

. አስመራጩ ክፍል፥ ማሳሰቢያውን አልተቀበለውም፤ ተሰርዟል” የሚል መልስ ሲሰጠኝ፣ ዝም ብያለሁ፤

. ማሳሰቢያዬ፥ ቤተ ክርስቲያኔን መጠበቅ እንጂ መካድ አይደለም፤ የሚያስመሰግነኝ እንጂ አያስተቸኝም፡፡

******

. በዶ/ር አባ ኃ/ማርያም ምርጫ፥ እንዳንሳሳት ወይም ጥራት ያላቸውን እንዳናጣ የመጠንቀቅ አቋም ነበረኝ፤

. በሰዓሊተ ምሕረቱ ጉዳይ፣ ባለሥልጣናቱን ትቶ በዶ/ሩ ላይ ያነጣጠረው ተቃውሞ፣ ግራ አጋብቶኝ ነበር፤

. በሃይማኖት የማይገናኙን፣ ከቢሮ ወይም ከአዳራሽ ውጭ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲገቡ አይፈቀድም፤

. ቢገቡ፥ ቀኖና ይጣሳል፤ ምእመናንም ቢቃወሙ አይፈረድባቸውም፤ እኔም ተቃውሟቸውን እጋራለሁ፤

. የሰዓሊ ምሕረቱ [ቀኖናዊ ጥሰት]ወደፊት እንዳይደገም እንወያይበታለን፡፡

******

. ለሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ የክህነት አባታቸው ነኝ፤ ቅስናም ኾነ ቁምስና በኢየሩሳሌም የተቀበሉት ከእኔ ነው፤

. የአሁኑን ምርጫ እግዚአብሔር በዕጣ ለተወዳዳሪያቸው ሰጠ፤ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደሚሾሙ ተስፋ አለኝ፤

. ለቅዱስ ሲኖዶሳችን ጥንካሬ የሚሰጡ ተጠያቂ ሊቅ በመሆናቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይፈልጋቸዋል፡፡

******

. መ/ር ዘመድኩን ያሰራጨው፣ ከሰይጣን የተላለፈለትን የሐሰት ምስክርነት ነው፤“ስም ማጥፋት” ነው፤

. የምመልሰው፥ ሃይማኖቴን ስለነካብኝና ምእመናን እንዳይሰናከሉ፤ እርሱም እውነትና ሐሰቱን እንዲለይ ነው፤

.በ81 ዓመት ዕድሜዬ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኔ ህልውና የተጋደልሁትን ሳይሸሽግ ስለመሰከረልኝ አመሰግነዋለሁ፤

.የሰው ልጅ ከምንም በላይ፣ ሃይማኖቱን እንደ ዓይኑ ብሌን ጠብቆ መኖር ይገባዋል፤
እኔም ሃይማኖቴን ከሚነኩብኝ ጨፍጭፈው ቢገድሉኝ ምርጫዬ ነው፡፡

******

 

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፱፻፲፩፤ ቅዳሜ፣ ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)

ባለፉት ሳምንታት በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ላይ የተላለፉ መጣጥፎችን አንብቤ ስለነበር፤ ብፁዕነታቸውን ልጠይቃቸው ወደድሁ፡፡ ቀርቤም መስቀል ከተሳለምሁ በኋላ፥ ጥያቄ አለኝ፤ አልኋቸው፡፡ ስለ ምን ጉዳይ? አሉኝ፡፡ ባለፉት ሳምንታት እርስዎን በሚመለከት የተላለፉ መጣጥፎች ነበሩ፤ ሰምተዋቸው ከሆነ፡፡ እውነቱንና ሐሰቱን ሊያብራሩልኝ ይፈቅዳሉን? አልኋቸው፡፡ እርሳቸውም ሳያንገራግሩ፥ እንዴታ! ምን ከፋኝ፥ በሰፊው እገልጽልሃለሁ፤ ብለው ንግግራቸውን በእግዚአብሔር ቃል ጀመሩ፡፡ “ቃሉም ብፁዕ ውእቱ ዘኢተዐቅፈ ብየ = በሐሰት ምስክር በእኔ ያልተሰናከለ ብፁዕ ነው” (ማቴ.11፥5)፤ “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመሰክር፤ ይላል እግዚአብሔር” የሚል ነው፡፡ ዘጸ.20፥16

ንግግራቸውንም በማራዘም ሲናገሩ፤ “እኔ አባ ቀውስጦስ፣ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በመሆኔ፥ በሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ሐሳብ የመስጠት መብት አለኝ፡፡ ስላለኝም በአስመራጭ ኮሚቴ የቀረቡ ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት፣ እንደ ነገ የምርጫ ድምፅ ልንሰጣቸው ተዘጋጅተን ሳለን፥ በዋዜማው የስም ማጥፋት ዘመቻ የጀመሩ ሰዎች እንዳሉ ሰማሁ፤ በእጅጉ አዘንሁ፡፡ እንዳንሳሳት፤ ለቤተ ክርስቲያናችንም ጥራት ያላቸውን ሰዎች እንዳናሳጣት በማሰብ፣ በማግሥቱ ጉባኤው በጸሎት እንደ ተከፈተ እጄን አውጥቼ ማሳሰቢያ ሰጠሁ፡፡

የመጀመሪያ ማሳሰቢያዬ፦ ለኑፋቄው ማረጋገጫ ያለበትን ተጠርጣሪ አንድ ላይ ሆነን እናስወግደው፡፡ ያለማረጋገጫ የንጹሐን አባቶችን ስም አጥቁረን እናስወግድ ብንል ግን፤ ቤተ ክርስቲያንን ብቁ ሰው ማሳጣት ይሆንብናል፤ ጠመንጃ ተኩሶ ሰው እንደ መግደል ያስቆጥርብናል፡፡ በንጹሕ ደም ውስጥ እጃችንን እንዳናስገባ እንጠንቀቅ፤ የሚል ነው፡፡ ይህ፣ ራሳችንን ከፍርድ ለማዳን፤ ቤተ ክርስቲያንንም እግዚአብሔር በሚወደው መንገድ ለመምራት የሚያስችል ሐሳብ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን መካድ አይደለም፡፡

ሁለተኛው ማሳሰቢያዬ፦ አባ ተክለ ሃይማኖት ያለተወዳዳሪ ቀርበዋል፡፡ ተቀምጦ የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ይቸግራል፤ እንደሚባለው ነገ ከነገ ወዲያ ወገን ያለው ያለተወዳዳሪ ልመረጥ ቢል የሲኖዶሱን ሕግ ያፈርስብናል፤ አንድ ተወዳዳሪ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ በክልሉ መንግሥት በቀረበ ማሳሰቢያ ወይም ጽሑፍ የምንመርጥ ከሆነ፤ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጎዳል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስንም እንደሌለ ያስቆጥራል፤ ስል፤ የአስመራጩ ክፍል፥ “ጽሑፉን አልተቀበለውም፤ ተሰርዟል፤” የሚል መልስ ሲሰጠኝ ዝም ብያለሁ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ እንጂ መካድ አይደለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ማሳሰቢያዬ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስተች አልነበረም፡፡

ነገር ግን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለኝን ተቆርቋሪነት የጠላብኝ ጥንተ ጠላቴ ሰይጣን፣ ፍልስጣ፣ የጽድቅ ጠላት የቀናውን ሐሳቤን አጣምሞ፥ ያላልኩትን አለ፤ ብሎ በሐሰት መስክሮብኛል፡፡ በዚህም ጠላት ሰይጣን ብዙ ምእመናንን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ አድርጓል፡፡ ይህንንም የሐሰት ምስክርነቱን አጠናክሮ የገደል ማሚቶ ላደረገው፥ ዘመድኩን ለተባለው ሰው አስተላልፎለታል፡፡ ይህ ግለሰብ ከጠላቴ የተላለፈለትን የሐሰት ምስክርነት ልዋል ልደር ላጣራ ሳይል ስሜን አጥፍቶ አሰራጭቷል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ባለው በሰማንያ አንድ ዓመታት ዕድሜዬ ስለ ቤተክርስቲያን ህልውና በመጨነቅ የተጓዝሁበትን የተጋድሎ ጎዳና ሳይሸሽግ ስለ መሰከረልኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ የሚገርመው ግን ደቂቃ ሳይቆይ ቃሉን ለውጦ በመቃብር ውስጥ ሆኖ “ቤተ ክርስቲያንን ክዷል” ብሎ በሐሰት መመስከሩ ነው፡፡

እውነት ለመናገር፣ ለአንተ ለጠያቂዬ መልስ ልሰጥህ ፈቃደኛ የሆንሁት፤ ሃይማኖቴን ስለነካብኝና፤ ልጆቼ ምእመናን ይህን ሰምተው እንዳይሰናከሉ፤ እርሱም እውነትና ሐሰቱን ለይቶ እንዲያውቅ እንጂ፤ ሌባ፣ ወንበዴ፣ ቀጣፊ፣ አጭበርባሪ፣ ሴሰኛና ነፍሰ ገዳይ ቢለኝ ኖሮ፤ ከምንም ባልቆጠርኹት ነበር፤ ምክንያቱም፣ በዜና አበው ላይ እንዳነበብኹት፦ “አንድ ቅዱስ አባት ቆመው ሲጸልዩ፥ አንድ ክፉ ሰው ሰይጣናዊ ፈታኝ፦ ሌባ፣ ወንበዴ፣ ቀጣፊ፣ ሴሰኛ፣ ነፍሰ ገዳይ አላቸው፡፡ እርሳቸውም ዝም አሉት፡፡ መናፍቅ ከሐዲ ቢላቸው ግን፤ “አይደለሁም አይደለሁም” ብለው ጮሁ፤ ይላል፡፡ ይህም የሚያሳየው የሰው ልጅ ከምንም በላይ ሃይማኖቱን እንደ ዓይኑ ብሌን ጠብቆ መኖር እንደሚገባው መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም እኔም ሃይማኖቴን ከሚነኩብኝ ጨፍጭፈው ቢገድሉኝ ምርጫዬ ነው፡፡ እንደሰማሁት፣ ዘመድኩን የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋም ምሩቅና ተቆርቋሪ እንደሆነ ተነግሮኛል፡፡ እንዲህ ከሆነ፣ እኔ ቤተ ክርስቲያንን ሳልክድ፤ ሁለተኛም፥ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተናገርኩትን ተገኝቶ ሳይሰማ ሳያውቅ ከእኔም ጠይቆ ሳይረዳ በእኔ ላይ የሐሰት ምስክርነት መስጠት ሰዎችም የተሳሳተ ግንዛቤና እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ የለበትም ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ልጅ ከሆነ በዚህ ንስሐ እንዲገባ እመክረዋለሁ፤” ሲሉ መልሰውልኛል፡፡

ጥያቄዬን በመቀጠል፣ ብፁዕ አባታችን፥ ከላይ የተዘረዘረው ቸግር መነሻው በሰዓሊተ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ የተባለው ችግር ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር ካለ አሁንም ቢገልጹልኝ አልኋቸው፤

ብፁዕነቸው ሲመልሱም፦ እኔ፣ ተፈጸመ የተባለውን ነገር አላውቅም ነበር፤ ነገር ግን፣ ለኤጲስ ቆጶሳቱ ምርጫ ሁለትና ሦስት ቀን ሲቀረው በዶክተር አባ ኃይለ ማርያም ላይ የተቃውሞ ድምፅ ተሰማ፤ ምክንያቱ ወይም መነሻው ምንድን ነው? ብዬ ስጠይቅ፤ አባ እንግዶቹን ሲቀቡ፣ ከእንግዶቹ አንዱም አባን ሲቀባቸው የሚያሳይ ምስል ታየ፤ ተባለ፤ ቆይቶ፤ ደግሞ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራንና ሌሎችም ባለሥልጣናት ከእንግዶቹ ጋር በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ቆመው ለእንግዶቹ በሳፋ ውኃ ቀርቦላቸው እየቀዱ ሲያፈሱ የሚያሳይ ምስል ታየ፤ ተባለ፡፡ ይህ የተንኰለኛ ቅንብር ይኹን አይኹን ባላውቅም አስደነገጠኝ፤ በእጅጉም አሳዘነኝ፡፡ ተቃዋሚዎችም፣ የሃይማኖት ልዩነት ያላቸውን ሰዎች አጅበው የገቡትን ባለሥልጣናት ትተው ዶክተሩን ብቻ ሲቃወሙ ከመሰማታቸው(ከመደመጣቸው) በቀር ሌሎችን ባለመቃወማቸው ግራ ተጋባሁ፤ ምክንያቱም፣ ቤተ ክርስቲያናችን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አባል መሆኗ ባይካድም፤ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር ግኑኝነታችን ቢቻል በኢኮኖሚ ለመረዳዳት ተቻችሎ ኑሮን ለመግፋት አንዱ የሌላውን መንጋ እንዳይነጥቅ ተመካክሮ በሰላም ለመኖር እንጂ፤ በሃይማኖት ግኑኝነት የለንም፡፡ ከቢሮ ወይም ከአዳራሽ ውጭ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲገቡ አይፈቀደም፡፡

በውጭ አገር ግን አብያተ ክርስቲያናት የሃይማኖት ልዩነት ሳይገታቸው፤ አልፎ አልፎ ይገናኛሉ፡፡ ይህም በኢየሩሳሌም እንደሚደረግ ዐውቃለሁ፡፡ በአገራችን ግን ይህ አልተለመደም፤ ምእመናን ቢቃወሙ አይፈረድባቸውም፤ እኔም ተቃውሟቸውን እጋራለሁ፤ ምክንያቱም መናፍቃን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ከገቡ የቀኖና ጥሰት ይከተላል፤ ሃይማኖትንም ይጎንጣል፤ ወደፊት እንዳይደገም እንወያይበታለን፤” ብለዋል፡፡

እኔም ጥያቄዬን ስላልጨረስሁ፣ ብፁዕ አባታችን፥ መጣጥፉ አባ ኃይለ ማርያም ከእርስዎ ቤት እንደሚገቡ እንደሚወጡ ሌሊትም ከእርስዎ ጋር እያደሩ እንደሚመክሩ ይናገራል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው? አልኋቸው፡፡

ብፁዕነታቸው በመገረም ሲመልሱ፦ “ይህ ፍጹም ውሸት ነው፡፡ አባ ኃይለ ማርያም ከእኔ ቤት የሚገቡበትና የሚወጡበት፣ ከእኔ ጋርም እያደሩ የሚመክሩበት አንዳችም ምክንያት የላቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአጋጣሚ ከመንገድ ላይ እንኳን ተገናኝተን አናውቅም፡፡ ወደ ፊት በአገልግሎት ብንገናኝ፥ በእርሳቸውም ሆነ በእኔ ላይ ማዕቀብ የሚጥል የለም፡፡ ለመሆኑስ ከሰው እንዳይገናኙ ያወገዛቸው ነፃነታቸውን የገፈፈው ማነው?” ብለዋል፡፡

ስለ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራስ ምን ይላሉ? አልኋቸው፤ ሲመልሱም፦ “ለሊቀ ሊቃውንት አባ ዕዝራ ከኔ የሚቀርባቸው ወንድም ወይም አባት ያለ አይመስለኝም፡፡ ዕድል ገጥሞኝ፤ በኢየሩሳሌም ቅስናም ሆነ ቁምስና የተቀበሉት ከእኔ ነው፡፡ የክህነት አባታቸው መሆኔን በሕይወት ታሪካቸው ላይ አቅርበውታል፡፡ የአሁኑን ምርጫ እግዚአብሔር በዕጣ ለተወዳዳሪያቸው ሰጥቷል፡፡

እርሳቸውም ጉባኤያቸው እንዳይመክን ተተኪ መምህር ያዘጋጁ እንጂ፣ ለሲኖዶሳችን ጥንካሬ የሚሰጡ ተጠያቂ ሊቅ በመሆናቸው ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይፈልጋቸዋል፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደሚሾሙ ተስፋ አደርጋለሁ፤” ሲሉ ለጥያቄዬ መልስ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ስለ ምእመናን ያላቸውን አስተያየት ሲገልጹ፦ ምእመናን ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውና ቀኖና ቤተ ክርስቲያናቸው እንዳይዛባ በቤተ ክርስቲያን ያልተለመደ ሥራ ወይም ሥርዓት ሲያዩ ተቃውሞ ማሰማታቸው የሚደገፍ ነው፤ በእጅጉም ያስመሰግናቸዋል፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ፣ መናፍቃን ባቀናበሩት ሤራ አንዳንዶች ምንም በማያውቁት መንገድ ሰይጣን ዲያብሎስ የዘራውን የሐሰት ምስክርነት አምነው የንጹሐን አባቶቻቸውን ንጹሕ ስም እያጠፉ፥ መስቀላቸውን አንሳለምም፤ አባቶቻቸንም አንላቸውም፤ እያሉ በድፍረት ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡

መስቀሉ የክርስቶስ ነው፤ እኛም ልጆቻችን የምንላቸው አማኞችን እንጂ ከሐዲዎችን አይደለም፤ ባይሳለሙም አባቶቻችን ባይሉንም ጉዳቱ የራሳቸው ነው፡፡ እኛ እኮ ቀደም ሲል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ክፉ ስም ያወጡላችኋል፤ ደስ ይበላችሁ” ስላለን፤ አይከፋንም፡፡ እነሱ ግን የሚጎዱት ባለማወቅ ስለሆነ እናዝንላቸዋለን፡፡ ስለዚህም፣ “በወንድምህ ላይ በሐሰት አትመስክር” ብሎ ሕግ የሠራ እግዚአብሔር እንዳይፈርድባቸው በሐሰት ከመመስከር ይጠንቀቁ፡፡ በማያውቁት ነገር በመናፍቃን ቅጥረኞች እየተገፉ ሌላውን ኰንነው በሥራቸውም ሆነ በእምነታቸው እንደ ፈሪሳዊ አይመጻደቁ፥ ፈርዶ የሚኮንን፣ ፈርዶ የሚያጸድቅ እግዚአብሔር መኖሩን ይወቁ እላለሁ፤” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

እኔም በበኩሌ የብፁዕነታቸውን ምክር ተቀብለን እንጠቀምበት እላለሁ፡፡
************
መምህር ዘመድኩን በቀለ፣ ስለ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ተጋድሎ ከሰጠው ምስክርነት መካከል፣ በፀረ ማርያም – ሰባክያን ነን ባይ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰርጎ ገቦች ላይ ያላቸውን ጽኑ አቋም በታወቀው ርቱዕ አንደበት በመግለጽ፣ ቀናዕያን ኦርቶዶክሳውያን ከመድረክ እንዲያስወግዷቸው ያስተላለፉትን ጥብቅና ቆራጥ አባታዊ መመሪያ የሚያስታውሰው ይገኝበታል፡፡

ጊዜው፥ ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲኾን፤ ወቅቱም፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 34ኛው ዓመታዊ ስብሰባ የሚያካሒድበት ሦስተኛ ቀን ውሎ ነው፡፡ የዕለቱ የስብሰባው መክፈቻ የነበረውና በአጠቃላይ ጉባኤው የጋራ መግለጫ ላይ የሰፈረው የብፁዕነታቸው ትምህርት፣ በቅዱስ ጳውሎስ የሮሜ ክታብ ምዕ. 8 ላይ የተመሠረተ ሲኾን፤ መልእክቱም የሚከተለው ነበር፡-

ቅዱስ ሲኖዶስ/ሰበካ ጉባኤ የተመሠረተው በሐዋርያት ነው፤ ለሃይማኖቱ ቀናዒና አስተዳደር ዐዋቂ የነበረው ቅዱስ እስጢፋኖስም ተሹሞ ሰፊ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ እርሱን ቢገድሉትም፣ ፰ሺሕ ተከታዮቹ ተነሥተው፣ የበለጠ ተደራጅተው አገልግሎቱን አስፋፍተዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. የራሷ ፓትርያርክ ኖሯት፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሰበካ ጉባኤ ተጀምሮ፣ በ፶ ሳንቲም የተጀመረውን አስተዋፅኦ፣ ዛሬ በመቶ ሚሊዮን መቁጠር ችለናል፡፡ ይህን ብር ግን፣ ቤተ ክርስቲያን ትገልገልበት፤ ትክክለኞቹ አገልጋዮቿም ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ሰበካ ጉባኤ የሚጠናከረው በስብከተ ወንጌል ነው፡፡ ስብከቱን ደግሞ ምስጢር ዐዋቂዎች ሊሰብኩት ይገባል፡፡ “ክርስቶስን እንሰብካለን”፤ “አባት የሌለው አባት አብ ብቻ ነው”፤ ምስጢረ ሥጋዌው ሳይገባቸው፣ ዕውቀቱ ሳይኖራቸው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንረከባለን፤ የሚሉ በየበረንዳው የሚያንዣብቡ ሰባክያን ነን ባዮች፣ በፍጹም ቤተ ክርስቲያንን ሊደፍሯት አይችሉም፡፡ እስከ ደም ጠብታ እንታገላለን፤ ቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ነች፤ ማርያምን የማይሰብክ/የሚቃወም/ ሰባኪ ካለ ከመድረክ እንድታስወግዱት በእግዚአብሔር ስም አደራ ብዬ እማፀናችኋለኹ፤” ሲሉ ለጉባኤው ትምህርተ ወንጌል እና አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡