July 9, 2017

(አለምነህ ዋሴ)

አማሮች የጥንተ ታሪካቸው ምሥክርና አሻራ የሆኑ ጥንታዊ ገዳሞቻቸውና በውስጣቸው የሸከፉትን ለበርካታ ክፍለ ዘመናት አንዳንዴም እስከ 2500 አመታት የዘለቁ ቅድመ ክርስትና፣ እምነትና ታሪክን የሰነቁ፣ የነገስታቶቻቸውን ታሪክና አፅም ጠብቀው ያቆዩ፣ እፁብ ድንቅ የታሪክ ኃውልቶችን ከቦ የያዘ ጣና።

ጣና እንቦጭ በተባለ ባይተዋር አረም ክፉኛ መወረሩ ይሰማል። ከደቡብ እስከ ሰሜን ጫፍ የአማሮች መናገሻ ከተማ ውቧን ባህርዳር ከመሳጯ የጎንደሯ ጎርጎራ ጋር ያስተቃቀፈ ጣና። ከአንድ የዘር ግንድ የፈለቁ ሥለመሆናቸው በሳይንስ የተመሰከረላቸው 15 አይነት የአሳ ዝርያዎችን አትረፍርፎ የሚመግብ ናይል ፐርችን ጨምሮ እንኳን በዘመናዊ በጀልባው ቀርቶ አማሮች “ባርካ” በሚሉት ግዙፍ ጀልባ ከሰሜን ወደ ደቡብ ከደቡብ ወደ ሰሜን እንዲሁም ወደ ምስራቅ የጎንደር ግዛቶች የሚጓጓዙበት የሚንሸራሸሩበት የኢትዮጵያ ሚስጥራትን የሸከፉ ከ30 በላይ ደሴቶች ጎብኝተው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሚታደስባቸው ቅዱስ ኃብቶች ማህደር ነው ጣና።

ጣና የኢትዮጵያ ባህር ነው። መሬት ቁልፍ (“ል”ን ጠበቅ) ለሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የባህርን ስፋትና ጥልቀት፣ የውኃን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንደዚሁም የመዝናኛ ልኬት ፋይዳ ሚና የታላቅነት ተምኔት በተግባር የሚያሳያቸው እንዲያጣጥሙ ትልቅ እድል የሚከፍትላቸው፣ በውል የሚያስጨብጥ ብርቅ የተፈጥሮ ኃብታችን ነው ጣና። ጣና የኢትዮጵያ ባህር ነው።

የጣና ልጅ ተብለህ የምትጠራበት በዓለም ታሪክ ለሽህ ዓመታት የተወደሰ! የተዘመረ! አሳሾች ሕይወታቸውን ቤዛ አድርገው ሊያዩትና ሊዘግቡለት የተንደረደሩለት ብቻ ሳይሆን ከረጋ ጥቅሙ ከማይነጥፍ ሕይወቱ የተቀዱ ብዙሃን እንደ መለኮታዊ ኃይል ቆጥረው ያመለኩት የሀገራችን ኢትዮጵያ የሃይቆች ሁሉ ሃይቅ በሰው ልጅ ትርክት ውስጥ ደግሞም መሣ የለሽ አዳኝ የሕይወት ምንጭ ነው ጣና። የኢትዮጵያ ባህር ነው ጣና።

ጣና ሃይቅ

የሰው ልጅ የህልውናው መሰረቱ የሆኑትን ውሃና አፈር ቀላቅሎ የሚንደረደር ነው ጣና። የሕይወት ውሃ ነው ጣና። ጣናኮ ጊዮን ነው። ጊዮን እግዚአብሄር ምድርን ያለባላ ሰማይን ያለ ካሥማ ሲፈጥር ምድርን ሙሏት ብሎ የሰውን ልጅን ሲዘራ ባርኮ ከፈጠራቸው አራት የውኃ ምንጮች መካከል አንዱ ጊዮን ነው።

የሰው ልጅ በኤደን ገነት ሳለ እባብ ሳያሳስተው በፊት ይኖርበት ይንፈላሰስበት ዘንድ ከገነት ዙሪያ ካፈለቃቸው ምንጮች ከአራቱ አንዱ ነው ጊዮን። የበረሃ ፍሬዎችን ወንድሞቻችንን ግብፃዊያንን በሕይወት ያኖረ በዛ ጭው ባለ ገዋ መሬት ላይ ሕይወት የዘራ! ሕይወት የከሰተ! ሕይወት ያፈራ! ምድሯን እንዲሞሏት ያስቻለ! ከላይ ከሰማይ የተፈቀደለት! የተባረከ! አጥጋቢ ዝናብ የማያጣ ለም አፈር እየቆነጠረ ቁልቁል ለረዥሙ ወንዝ ያሰኘውን ርቀት ፈፅሞ ግብፅን አኑሮ ሜዲትራኒያንን እስኪቀላቀል ድረሥ በዙሪያው የከተሙ ሸለቆውን ተከትለው ሕይወታቸውን ወይንም የህልውናቸውን ድንኳን ለተከሉ ጥቁር፣ ቡኒ፣ ነጭ፣ ክርስትያን፣ ይሁዲ፣ ሙስሊም፣ አረመኔ ኃይማኖት የለሽ ለሁሉም እንደ ማንነታቸው ሁሉ ሳያዳላ ሕይወት ይዞ የሚነጉድ የሕይወት ባህር ምንጭ ነው ጣና።

የትኛውም የአለም ወንዝ የጣናን ያህል ሊመሰከርለት አይችልም። ውኃና አፈር ቀላቅሎ የሚሄድ ብቸኛ ወንዝ ነው። ግዑዝ አይደለም በዚህ የተነሳ። ጣና ነብሥያ ያለው ህያው ነው። ጣና ካንተም ሕይወት በላይ ነው። ጣና እንደ ሀገር ወዳዶቹ ሩሲያውያን እንደ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ትርክታቸው በነደደ የጠላት ፍላፃ ፊት በናዚ ጎራዴ ፊት ቆመህ ከዚህስ በኃላ እጣ ፈንታዬ ሞት ይሆናል እንጅ ወደ ኃላዬ ፈቅ አልልም። ከኃላዬ ሞስኮ ናት እንዳሉት ጣና ሞስኮ ናት። ጨርቄን ማቄን ሳትል የምትሰለፍለት ሕይወት ነው። ጣናኮ መተንፈስ ተስኖታል፤ ታንቋል።

ከሜትር በላይ የሚዘልቅ ውኃ ገብ ዘንዶ ተክል ከሰራ አካሉ ጋር ተጣብቷል። ከጠቅላላ አካሉ አንድ ሰባተኛውን ተጠምጥሞበታል። ጣና የትናንትና የዛሬ ወይም የቅርቡ ነገ ብቻ ውሉ የተቋጠረበት እስትንፋስህ እንዳይመስልህ። ጣና ዘላለምህ ነው፣ ህይወትህ! ውበትህ! ቅድሥናህም ነው። የጣና ልጅ ነኝ ስትል የሥእብናህን ሰላም፣ ትሁትነት፣ ታላቅነት፣ አይበገሬነት፣ ደግነት፣ አመንጭነት፣ ባለቅኔነት፣ ተንታኝነት፣ ዜመኛነት፣ አዋቂነት፣ ደራሲነት፣ ሁሉንም የሚነግረኝ ውስጠትህን ነው ጣና።

ጣና 7 አዲስ አበባን የሚያክል ግዙፍ መልካአዋ ሆኖ የተንሰራፋ ውጫዊነቱን ያሃል ከውስጥህ የሚፈስ የስብእናህ የባህሪህና የተምኔትህ ውኃ ልክ የሆነ ውስጥህም ነው። ያን የሚያሃል ግዙፍ አካል ባንተ ጭብጥ ሰውነት ውስጥም ነው። አሁን ያንተነትህ አንድ ሰባተኛ እንቦጭ በተባለው በዚህ ባይተዋር አረም ተወሯል !ታንቋል! መተናፈስ! መላወስ! መረብ መጣል! መንሳፈፍ! መጎብኘት! አይቻል ዘንድ (በሂደት ማለት ነው) ካሁኑ አንድ ሰባተኛ አካልህ ዐይንህ እያዬ በአረም ተውጧል። ባለፉት አምሥት አመታት ውስጥ ጣና የኢትዮጵያ ባህር ከጠቅላላ ቆዳ ስፋቱ የግዙፏን አዲስ አበባ ያህል ያሃል አካሉ በመሰሪ ባይተዋር አረም ቁጥጥር ሥር ውሏል።
ከፀሃይ ንጋትና ከጀንበር ጥልቀት ጋር የሚቀያየረው ጠይም መልኩ አበባ በሚመሥል መሰሪ አረንጓዴ አረም ተውጦ አረንጓዴ ዳስ ወይንም ጨፌ ሆኗል። እንድትጨነቅ እንድትሸበር ሳይሆን እንድትተጋና ጀግና እንድትፈጥር ነው።

ናይልኮ ጣና ነው። ናይልኮ ትኩሥ ውኃ ነው። ደምኮ ነው። በዐይንህ በብረቱ እያየኸው በጣና መስታወት ገፅ ላይ እንደሰለጠነ እንደ አንድ ታላቅ የሰላም ሰራዊት ቀስ ብሎ ሰልፉን ሳያዛንፍ እየተመመ በለሆሳስ የሚወጣና ጥቂት ኪሎሜትር በለሆሳስ ከተጓዘ በኃላ 400 ሜትር አፋፍ ላይ ሲደርስ ቁልቁል 40 ሜትር እየተወረወረ በሚፈጥረው ፏፏቴ በቀስተ ደመና ቅስት ውስጥ ውኃው ጢስ ሆኖ እየበራዬ ለዐይን ትንግርት ለልብ ልክ የለሽ ምስጠት ሆኖ የዙሪያውን እፀዋት ህልውና በቅርብና በርቀት ታድጎ፣ ውኃ አጠጥቶ፣ እነሱን ለማጠጣት ተበትኖ ለዐይን ትርዒት ሆኖ እግረ መንገዱን እንደ ግዙፍ ቦይንግ አውሮፕላን ወደ አየር የመነሳት እንድርድሮሽ በሙሉ ሞተሮቹ እያጓራ በሚከንፍበት እዛ ጫፍ ለሚጠብቁት ግብፆች ውኃንና አፈርን አዝሎ ደረስኩላችሁ ብሎ በሸለቆ መንገድ ውስጥ መገማሸር የሚጀምርበት አፍዝ አደንግዝ የተፈጥሮ ቅያሥኮ ነው ጣና።

ጣና ፈጣሪ አምላክ በእሳት ላንቃ እጣቶቹ በእሳተ ገሞራ ብዕሩ የኢትዮጵያ ሰው ራሱን ኑሮ ሌሎችንም እንዲያኖር ታስቦና ታቅዶ የተሰራ አስገራሚ ህያው ቅያስኮ ነው። ጣናኮ ሚስጥር ነው ወንድሜ። አሁን አለም ዐይኑ ተገልጦለት እንጀራህን እየተሻማ መብላት እንደጀመረ ሁሉ ውሎ አድሮ ወግና ባህል ያለውን እስክስታንም እንዲሁ ይጨፍርበታል። ደስታውን ይገልፅበታል። ቅኔህ ይገባዋል።

እያደር የኢትዮጵያ አያሌ ሚስጥሮች የሚቆፈርባቸውና የሚገለፅባቸው ደሴቶች ከጠላት ወረራ እየጋረደ እየመገበ እያዝናና እያኖረ መቀበሪያቸውም የሆነ “አገውእማህ” እኮ ነው ጣና። የጣና ልጅ እኮነህ አንተ። ኢትዮጵያዊ ስትሆን የጣና ልጅ ነህ። ይህን ከጊዜ መጀመር ጋር የጀመረ ምንነትና ማንነትን አንድ ሰባተኛ አካል የወረረው አረም እንቦጭ መሠሪ ነው። ይህ በፈረንጅ አፍ Water hyacinth ተብሎ የሚጠራ አረም የታወቀ የወንዞች! የግድቦች! የኃይቆችና የመሥኖዎች ፀር ነው። ያለ አንታርክቲካ በስተቀር ያልደረሰበትና ያልወረረው የውኃ አካል አታገኝም።
የውኃ ከባቢን የማውደም መቅሰፍትነቱን ለመቋቋም በያመቱ በአለም ዙሪያ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስወጣ ነቀርሳ ነው። ካልተቆጣጠርከው ይቆጣጠርሃል። Water hyacinth ከውኃው አካል ጋር ተያይዘው የለሙ የተፈጥሮ ተክሎችንና እነሱ ላይ የሚመኩ እፅዋቶችን ህልውናቸውን ያከስማል። ልብ አድርግ ጣና ላይ አያሌ የአእዋፋት አይነቶች አሉ፤ ሌላ ቦታ የማይገኙ ጭምር።

ወደ ባህሩ ውስጥ ሊደርስ የሚገባውን የፀሃይ ብርሃን ገድቦ ያስቀራል። የውኃውን የኦክስጅን መጠን ያመናምናል። የሙቀቱን መጠን ይለዋውጠዋል። በውኃው አካል ላይ ያለውን የተፈጥሮ የጋዝ ልውውጥ ይቀንሰዋል። የአረሙ ውኃ ዘለቅ ሰውነት ቅጠሎቹን ለማጠጣት በስሩ የሚመጠው ውኃ በዛ የውኃ አካል ላይ የፀሃይ ሙቀት ከሚያስከትለው ትነት በላይ የውኃውን መጠን ይቀንሰዋል። ይህን አረም እንደ ብሄራዊ አደጋ ቆጥረን በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ለዘለቄታው አብረን የምንጋፈጠው ብሄራዊ አደጋ ነው። የማንዘናጋበት ፈተና ነው። በአምስት አመት እድሜ አዲስ አበባን ያህል የውኃ አካል ከሸፈነ ቀሪውን ሥሌት ለየራሳችሁ እተወዋለሁ።
ጊዜ የለንም ጊዜ የሚያገለግለው ለአረሙ ነው። አልሞኒቶር የተባለው የግብፅ ጋዜጣ እንደዘገበው ይህ Water hyacinth ተብሎ የሚጠራ እምቦጭ አረም የግብፅ አመታዊ የናይል ውኃ ድርሻን በሂደት አስር በመቶ ያሃሉን የማባከን አደጋ መጋረጡን ዘግቧል። አሁን አስዋንና መስኖዎችን በሸፈነበት ደረጃ በያመቱ አስራሶስት ቢሊዬን ሜትር ኪዩብ ውኃ ያባክናል ወይንም አረሙ ለራሱ ይጠጣዋል። ልብ አድርጉ አስዋን ላይ አስር ቢሊየን ኪዩብ ውኃ በትነት ይባክናል። ከዚህ ላይ ሦስት ቢሊዬን ሜትር ኪዩብ ውኃ ደግሞ በዚህ አረም የተነሳ የሚያባክነውን የውኃ መጠን ጨምሩበት። እንደ አልሞኒተር ዘገባ የግብፅን የውኃ ሃብት አደጋ ላይ የጣለው ይህ አረም ለረዥም ጊዜ የኖረ ነው፤ ይታወቃል በተለያየ ደረጃ በተለያየ ስፋት።

ይሁንና እንዲህ ተስፋፍቶና የአገሪቱን የውኃ አቅርቦት አደጋ ላይ ለመጣል በሚችል መልኩ የተስፋፋው ግን ከአስዋን ግድብ መሠራት ጋር ነው። ከአስዋን በፊት የናይል ጎርፍ ይህን እንቦጭ የተባለ አረምንና ሌሎችን ተክላ ተክሎችን በኃይል እያዳፋ ጠራርጎ ወስዶ ሜዲትራያን ባህር ውስጥ ይከታቸው ነበር። ወንዙ ራሱን በራሱ የሚያክምበት ጥበብ ነበረው። አስዋን ግን ውኃውን አቁሮ እየተቆጣጠረ እየከፈተና እየዘጋ የሚቆጣጠር ከመሆኑ የተነሳ አረሙ እድልና ጊዜ አገኝቶ ወበራ።

አሁን አገሪቱ በትነት ከምታጣው በላይ ውኃ ሊያሳጣት እድል ያለው ይህን አረም የህልውና አደጋ አድርጋ በቻለችው መጠን እየተፋለመች ቢሆንም የሚያስወጣት ወጭ ግን ቀላል አይደለም። በማሽን፣ በማጭድ፣ በመድኃኒት ከማጥፋት ባሻገር እሱን ተመግበው ሊያጠፉት የሚችሉ ሥነ ፍጥረታዊ ወታደሮችም በርግጥ አሉ። አውስትራሊያ ለኡጋንዳው ቪክቶሪያ ኃይቅ ወረርሽኝ በስኬታማ መልኩ ተጠቅማበታለች የሚባለው የጢንዚዛ ዝርያ አንዱ ሁነኛ መንገድ ነው። እንቦጭ ለጉማሬዎች የዳሊ ሥጋ ያህል ማለፊያ ምግብ መሆኑ ይነገራል።

ሰብሰብና ክምችት ብሎ ያገኙት እንደሆነ የተከማቸበትን በሙሉ እንክት አድርገው እምሽክ አድርገው ያጠፉታል። ይሁንና አረሙን አጠፋለሁ ብለህ ስንቱን ቦታ በጉማሬ ልታጥለቀልቀው ነው። ነገሩ ፈተና ነው። እስከዛው ግን ወንድ! ሴት! ልጅ! አዋቂ! ሳንል በማጭድ መንግስት ደግሞ ገንዘብ መድቦ በፍጥነት በማሽን ቢያስጠርገው የግድ ነው ብለን እናምናለን። እንቦጭ የጣናን ፍጡራን ዳርቻዎቹን አየር የሚያሳጣ ጀልባ የማያስነዳ የዙሪያው ተክሎችን እንዳይበቅሉ የሚያደርቅና የሚያደርግ፣ ፀሃይ የሚጋርድ፣ ኦክስጅን የሚከለክል በሂደት የመንፈሳዊ ፀጋችንና የቁሳዊ ሃብታችን ምንጭ የሆኑትን ጥንታዊ ገዳሞቻችንም ከሰው ከጎብኝ ሊያርቅ የሚችል ትልቅ ጠላት ነው። እንዋጋው።

የኢትዮጵያን ባህር ጣናን እናድን፤ ዛሬ ሳይሆን አሁን። የጣና ችግር ጀግና ሁነን የምንወለድበት ትልቅ አጋጣሚ እንጅ የምንጨነቅበት አይደለም። በእውቀታችን በገንዘባችን በሥልጣናችን በእምነታችን በሁሉም መንገድ ሥለጣና እንቁም። ቁልል ያለውን ውኃችንን እንመልሰው። ይህንን ክፉ አረም እናስወግድ።