“የኢህአዴግ መንግስት ጨካኝ ወይስ ጨቋኝ” በሚለው ፅሁፍ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰድ በዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ተመልክተናል። በዜጎች ላይ እንዲህ ያለ የጭካኔ እርምጃ የሚወስደው ደግሞ እንደ ጨቋኝ ስርዓት የእኩልነት ጥያቄን ተቀብሎ ማስተናገድ ስለማይችል እንደሆነ በዝርዝር ተገልጿል። ስለዚህ፣ አምባገነናዊ መንግስት ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ የሚወስደው የሕልውና ጉዳይ ስለሆነበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ “የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካ” በሚለው ፅሁፍ እንደተገለፀው፣ ሁሉም አምባገነን መንግስታት በጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚዎች ላይ የሆነ ኢ-ፍትሃዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የእነዚህ አካላት እንቅስቃሴ ከዜጎች የፖለቲካ መብትና ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለሆነ ነው።

የጨቋኝ ስርዓት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፈልን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የቆመ ነው። ስለዚህ፣ የጨቋኙ ስርዓት ሕልውና ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እንዳያነሱ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው። ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ የማያነሱት ስለራሳቸው ሆነ ስለሌሎች ሰዎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት መረጃና ግንዛቤ ከሌላቸው ብቻ ነው። የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ከእነሱ የበለጠ መብትና ነፃነት እንዳለውና የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆነ ካላወቁ በስተቀር የእኩልነት ጥያቄ አያነሱም። በዚህ መሰረት፣ የተወሰኑ ሰዎች፥ ቡድኖች ወይም ማህብረሰብ ከእነሱ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆኑ ሲያውቁ፣ ወይም ደግሞ ማግኘት ከሚገባቸው በታች እያገኙ እንደሆነ ሲያውቁ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ ማንሳት ይጀምራሉ።

ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እንዲያነሱ በቅድሚያ ስለ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው እና ስለ መንግስት ስራና አሰራር ማውቅ አለባቸው። በተለያዩ አከባቢዎች ያለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከራሳችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዞ ማየትና መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ ዜጎች ስለራሳቸው መብትና ነፃነት፣ ስለ መንግስት ስራና አሰራር፣ በሌሎች አከባቢዎች ስላለው ጥቅምና ተጠቃሚነት ማወቅ አለባቸው። ይህ እንዲሆን ደግሞ፤ በተለያዩ አከባቢዎች ስላለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ትክክለኛ ሃሳብና መረጃ የሚያቀርቡ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች፣ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትንታኔ የሚቀርቡ የፖለቲካ ልሂቃንና ጦማሪያን (ፀኃፊዎች)፣ ስለ ዜጎች መብትና ነፃነት መከበር የሚወተውቱ የፖለቲካ መሪዎችና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች መኖር አለባቸው። እነዚህ አካላት በንቃት በሚንቀሳቀሱበት ሀገር ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውንና ነፃነታቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ፥ ይጠይቃሉ።

በአጠቃላይ፣ የጨቋኝ ስርዓት ሕልውና ዜጎች እውነታን እንዳያውቁና እንዳይጠይቁ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ፣ ዜጎች ትክክለኛ እውነታውን እንዳያውቁና እንዳይጠይቁ ለማድረግ ከመንግስት በስተቀር ሌሎች መናገርና መፃፍ የለባቸውም። ከመንግስት አፈ-ቀላጤዎችና ቃል-አቀባዮች ውጪ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን ከማዳመጥ የዘለለ ሚና ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ለዚህ ደግሞ ስለ መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት የሚናገሩ፥ የሚከራከሩ፥ የሚያስተምሩ፥… ወዘተ፣ በአጠቃላይ ከስርዓቱ መሪዎች ፍላጎትና ምርጫ ውጪ የሆነ ማንኛውም ዓይነት ሃሳብና አስተያየት የሚሰጡ ግለሰቦች፥ ቡድኖችና ተቋማት መወገድ አለባቸው።

በዚህ መሰረት፤ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ መኖር የለበትም፣ በእውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃና ትችት የሚቀርቡ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መኖር የለባቸውም፣ የዜጎች መብትና ነፃነት እንዲከበር የሚወተውቱ የፖለቲካ መሪዎችና የመብት ተሟጋቾች መኖር የለባቸውም። በአጠቃላይ፣ በጨቋኝ ስርዓት ስር የሚኖሩ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እንዳይጠይቁ ለማድረግ በቅድሚያ እንዳያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ኢትዮጲያ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ “Anti-Terrorism Law (2009)”፣ እንደ ስዋዚላንድ (Swaziland) በ¨Suppression of Terrorism Act (STA)”፣ እንደ አንጎላ (Angola) “በState Security Law”፣…ወዘተ በመሳሰሉ አፋኝ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች አማካኝነት የግል ሚዲያዎችን፣ ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያንን፣ የመብት ተሟጋቾችንና የፖለቲካ መሪዎችን እስራትና ስደት ደብዛቸውን ማጥፋት ያስፈልጋል።

ለምሳሌ፣ “CPJ” የተባለው የጋዜጠኞ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጲያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ በወጣ የመጀመሪያ አምስት አመታት ውስጥ ብቻ 57 ጋዜጠኞች ሀገሪቱን ለቅቀው ወጥተዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት አመታት ውስጥ ነፃና ገለልተኛ የሚባል ሚዲያ ከሞላ-ጎደል ጠፍቷል፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቭል ማህበራት “የሉም” በሚባሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፣ ከታዋቂ እስከ ጀማሪ ፖለቲከኛ በሽብር ወንጀል ተከሰው ታስረዋል፣ ከዚያ የተረፉት ሀገር ለቀቅው ተሰድደዋል።

ይህ ሁሉ ግፍና በደል የኢትዮጲያ ሕዝብ መብቱንና ነፃነቱን እንዳያውቅና እንዳይጠይቅ ለማድረግ ሲባል የተፈፀመ ነው። ምክንያቱም፣ የኢህአዴግ እድሜ ሕዝብ እንዳያውቅና እንዳይጠይቅ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። በዚህ መሰረት፣ የኢትዮጲያ ሕዝብ መብቱን ማውቅና መጠየቅ ሲያቆም የኢህአዴግ እድሜ ይረዝማል፣ ሕዝብ መብቱን ማውቅና መጠየቅ ሲጀምር የኢህአዴግ እድሜ ያጥራል። “ታዲያ ምን ይሻላል?” የሚለውን በሌላ ግዜ እንመለስበታለን።