13 July 2017 13:56

በ  ጋዜጣው ሪፖርተር 

የጣና ሃይቅን ከእምቦጭ አረም ባልተናነሰ መልኩ በሃይቁ ዙሪያ ካሉ ሆቴሎች የሚመነጨው ፍሳሽ እንደሚያሰጋው ተነገረ፡፡ አሁን ላይ የእምቦጭ አረምን ከስሩ ለማጥፋት በሰው ሃይል የተከፈተው ዘመቻ ዘላቂ መፍትሄ ባለመሆኑ ከጎንደር እና ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ምሁራን አረሙን በተመለከተ ሳይንሳዊ ምርምር እያደረጉ መሆናቸውን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ተናግረዋል፡፡

27 በላይ ደሴቶችን የያዘው የጣና ሃይቅ ዙሪያ ገብ አሁን ላይ በደቡብ ጎንደር በከፍተኛ ሁኔታ መንስኤው ባልታወቀ የእምቦጭ አረም እየተወረረ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፤ ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ባለፈ የክልል እና የፌዴራል መንግስትም ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተሉት እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የእምቦጭ አረምን ከመሠረቱ በማጥፋት ግን ሳይንሳዊ ምርምር እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ ከሀገር አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ የአለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጣና ሃይቅ በተለይም ለባህርዳር ከተማና አካባቢዋ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የሥነምዕዳር ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የእምቦጭ አረም መስፋፋት አሳሳቢ መሆኑን ያስታወሱት የከተማዋ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ፤ ከአረሙ ባልተናነሰ በከተማዋና በጣና ዙሪያ የተገነቡ ሆቴሎችና እየተስፋፉ በሚገኙ የልማት ስራዎች ምክንያት ከሐይቁ ባለፈ የአባይ ተፋሰስንም የሚጎበት እድል እንዳለ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ሆቴሎች ፍሳሻቸውን ወደሃይቁ እንዳይለቁና የሃይቁ ዳርቻም እየተደለደለ ለግንባታ እንዲውል መደረግ የለበትም ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ይህንንም ለመከላከል የከተማ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ እና ከአማራ ክልል ቅርስ ጥበቃ ቢሮ ጋር በመሆን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደመፍትሄ ከቀረቡት ሃሳቦች መካከል በጣና ሃይቅ ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች እና የህንፃ ግንባታዎች በከተማ አስተዳደሩ ጥብቅ የዲዛይን ክትትል እየተደረገባቸው፤ የሃይቁን ደህንነት የማይጎዱ መሆናቸው በጥናት እንዲረጋገጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡