የሀበሻ ቤተክርስቲያን እና መስጂድ የአትሂዱ ዘረኛና የኋላ ቀር ፖለቲካ  – ግርማ ካሳ

አንድ ፓልቶክ ክፍል እንግዳ ሆኜ ቀርቤ ነበር። አዲስ አበባን ያካተተ ሸዋ የሚባል አዲስ ክፍለ ሃገር/ክልል አስፈላጊነት ዙሪያ ሐሳብ እንድሰጥ ነበር የጋበዙኝ። ኦሮሞዉም፣ አማራው፣ ሁሉም እኩል የሆኑባት ፣ አማርኛና አፋን ኦሮሞም የሥራ ቋንቋ የሆነበት ክልል መኖር የበለጠ ኦሮሞዉን እንደሚጠቅምም ነበር ለማሳየት የሞክርኩት። በዚህ መሐል ዉጭ ያሉ የኦሮሞ ጠባብ አክራሪዎችና ኦህዴዶች በኦሮሞ ስም እየነገዱ ኦሮሞዉን እየጎዱ እንደሆነ ለማሳየት ሞከርኩ። ይሀን ምስኪን ሕዝብ ፣ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እያጣሉትና እያራራቁት በሁሉም መስፈርት ተጎጂ እንዳደረጉት አስረዳው።

ክሶስት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ አንድ ጸያፍ፣ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ የማይመልስ ሰነድ ወጥቶ ነበር። ሰነዱ ከነለማ መገርሳ ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጽ/ቤት እንደወጣ ጠቀስኩ። ኦሮሞ ነኝ ያሉ አንድ የክፍሉ ታዳሚ፣ ሰነዱ ከኦህዴድ እንደወጣ ምን ማስረጃ እንዳለኝ ጠየቁኝ። “ሰነዱ በኦሮሞ ስም የወጣ ግን የኦሮሞን ሕዝብ የሚሳደብ ሰነድ ነው “ ብለውም ኦሮሞዎች ይሄን ሊጽፉ እንዳማይችሉ በመግለጽ ነበር በሰለጠነ መልኩ የሞገቱት። እኔም ቀጥተኛ መረጃ እንደሌለኝ አስረድቼ ያሉኝን circumstantial ፣ ተዛማጅ መረጃዎችን በማቅረብ ሰነዱ ከነ አቶ ለማ መገርሳ ቢሮ እንደወጣ ለማሳየት ሞከርኩ። አንዱ ትልቁ መረጃዬ ሰነዱን በተመለክተ የፌዴራል መንግስት ቃል አቀባይ አቶ ነጋሪ ሌንጮ “እኛ አናውቀውም” ቢሉም፣ የክልሉ መንግስት ቃል አቀባይ ግን እንኳን ሰነዱን ሊክዱ፣ አንደውም አንድ ሰነድ ለፌዴራል መንግስቱ እንዳቀረቡ በይፋ ማመናቸው ነበር።

ይህ ሰነድ ለፌዴራል መንግስት ከቀረበ በኋላ ከታወቁ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ከአቶ ብርሃነ መስቀል አበበ በቀር ብዙ የኦሮሞ ብሄረተኞች ሲቃወሙት አልሰማሁም። ለምን ቢባል በይዘቱ ይስማማሉ ብዬ ስለማስብ። አቶ ብርሃን መስቀልም ተቃዉሟቸው ያሰሙት ለምን አዲስ አበባ በኦሮሚያ መንግስት ስር አልሆነችም በሚል ነበር።

አለምነህ ዋሴ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ዉይይት ከተደረገበት በኋላ፣ እነ ለማ መገርሳ ያቀረቡት ሰነድ water down ሆኖ፣ አንድ ሌላ ረቂቅ በሚኒስተሮች ምክር ቤት ጸደቀ። በሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ኦህዴድ በ extension የኦሮሞ ብሄረተኞች ከሕወሃት፣ ደሃዴን እና ብአዴን ተለይተው ለብቻቸው የቆሙበትና የተሸነፉበት ሁኔታ ነው የነበረው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያረቀቀው ሰነድ፣ ኦህዴድ መጀመርያ ካዘጋጀው ሰነድ በጣም ስለወረደባቸው፣ ጊዜም አልፈጀባቸውም የኦሮሞ ብሄረተኞች ጠንካራ ተቃዉሞ ማሰማት ጀመሩ። እነ ጃዋር መሐመድ በሚቆጣጠሩት የኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ፣ በለማ መገርስ ትከሻ የሌላውን ማህበረሰብ ፍላጎት ለመጨፍለቅ ሲሰሩ ቆይተው ሳይሳካላችው ሲቀር ፣ ረቂቅ አዋጁ ኦሮሞዉን ከአማራውና ከአዲስ አበባ ህዝብ ለማጣላት ነው በሚል የሌላው አሳቢ ለመምሰል እየሞከሩ ነው። የሚያስገረመው ግን ሌላው ማህበረሰብ እንደ ጃዋር ያሉትን ሰዎች ማወቅና መረዳት አለመቻሉ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ብሄረተኛ የሚባለው ሃይል እነርሱን እያባባለና ማጎዘፍና መለማመጥ ምን እንደሚፈይድላቸው ሊገባኝ አልቻለም።

በፓልቶክ ጥያቄ የጠየቁኝ ኦሮሞ ታዳሚ፣ “ሂትለር ጀርመኖችን እንደማይወክል፣ እነ ጃዋርም ኦሮሞን አይወኩልም” ነበር ያሉኝ። እዉነታቸውን ነው። አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞችን ማባባል ሳይሆን ፖለቲካቸው የከሰረ ፣ የኦሮሞ ማህበረሰብ የማይመጥን፣ ሕዝቡን የጎዳ መሆኑን aggressively ማሳየትና ማስተማር ያስፈልጋል። ሂትለር በመርዛማ ፖለቲካው ብዙ ጀርመኖችን አስቶ ነበር። እነዚህም ሰዎች ያሳቷቸው፣ በዘር በሽታ የበከሏቸው፣ ብዙ ወጣቶች አሉ። እነርሱን ከነዚህ ቢላሾች መዳፍ ማውጣት አለብን። አለበለዚያ ይዘዋቸው ገደል ነው የሚገቡት።

እስቲ ለጃዋርና መሰሎቹ አፍቃሪዎች፣ እነርሱን ሆይ ለምትሉ፣ ጃዋር በቅርብ ከተናገራቸው አባባሎች የተወሰኑት አብሮ በተያያዘ ቪዲዮ ይከታተሉ።

ስለጃዋር ስንጸፍ አንድ ግለሰብን አይደለም እያየን ያለነው። ጃዋር የኦሮሞ ፈርስት ንቅናቄ መሪ ነው።፡የኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ ዳይሬክተር ነው። ከርሱ ጋር በተለያዩ ግብረ ኃይሎች የሚሰሩ፣ ከርሱ ጋር በየስብሰባዎች የሚገኙ እንደ ዶር ሕዝቄል ጋቢሳ ያሉ ብዙ ምሁሮች አሉ። እነርሱን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።፡

“ኦሮሞው የራሱ መስጊዶች፣ አብያተ ክርስቲያናትን እድሮችን መስራት አለበት። በየስቴቱ አምስትና አስር ኦሮሞዎች ብንኖር እንኳን መስራት እንጂ ኡእሃበሻ መስጂድና ቤተ ክርስቲያን ሄደን የምንሰግድበትና የምናስቀድስበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

ባለፊት አምስት አመታት ኢትዮጵያ የተሰኝችዉን አገር ለኛም ለነሱም እኩል እንድትሆን ለማጽዳት ያላድረኩት ጥረት የለም። እነሱ ግን የሚሰሙ አይነት ሕዝቦች አይደሉም። እዉነቴን ነው ! ባስተምራቸው፣ ባስተምራቸው ሲብስባቸው እንጂ ሲሻሻሉ አላይም። እዉነቴን ነው የምላችሁ ጭራሽ እየባሰባችው ነው”

“እነሱ ሜዲያ ላይ የምቀርበው በሌላ ነገር ሳይሆን ኤክስፐርት ስለሆንኩ በሞያዬ ምክንያት ነው። ዛሬም ይፈልጉኛል፤ ነገም ይፈልጉኛል። ባይፈልጉኝም እንኳን ተጎጂ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው። ለምን እነርሱ ሜዲያ ላይ እንደምቀርብ ታውቃላችሁ ? ጃዋር መሐመድ የሚባለው የኦሮሞ ልጅ ከማንም በላይ ኦራተር(ተናጋሪ) ነው ተብሎ ሲሰማ እዛ ሩቅ ያለው የኦሮሞ ልጅ ኩራት ይሰማዋልና ራሱን ከፍ ያረጋል”

እነዚህ አባባሎች ኦሮሞን ይወክላሉን ? በኦሮሞ ስም የሚነገሩ፣ የኦሮሞን ማህበረሰብ የሚሰደብና የሚያዋርድ ጸያፍ አባባሎች አይደሉምን ? እንደዚህ አይነት ሰዎች በኦሮሞ ስም ሲነግዱስ የሌሎች (ኦሮሞዎች) ዝምታስ እስከመቼ ነው ?

አሁን ለኦሮሞ ማህበረሰብ ይሄን እላለሁ። ኦሮሞው እድል ፈንታው ከሌላው ጋር ነው።ኦሮሞነት ኢትዮጵያአዊነት ነው። ከሌላው ወገኖች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ይሄ መሬት የኦሮሞ ርስት ነው፣ ያ መሬት የጉራጌ ነው …ከሚለው ፖለቲካ ወጥቶ፣ ሁሉም እኩል የሆኑባት አገር እንድትኖር መስራት ነው የሚሻለው። ዉጭ ያሉ አክራሪዎች፣ ኦህዴዶች፣ ኦነግች የመሳሰሉ በሽተኛ፣ ከኦሮሞ ባህል ጋር ፈጽሞ የማይሄድ አስተሳሰብ ነው ያላቸው። እነርሱን መስማትና በነርሱ ርካሽ ወሬ መታለሉን ማቆም አለበት።የኦሮሞ ባህል የጉድዲፈቻ ባህል ነው። ሌላውን የመቀበል፣ ለሌላው የማሰብ ባህል ነው። የኔ የናንተ የሚል ሳይሆን የኛ የሚል ባህል ነው። የነዚህ ሰዎች ፖለቲካ ግን ፍጹም ከኦሮሞ ባህል የራቀ ነው።