እያንዳንዱ ሰው እንደ አፄ ሚኒሊክ ቅዱስና እርኩስ ነው!
የኢህአዴግ መንግስት ስለ ተቃዋሚዎች ይናገራል። ተቃዋሚዎች ስለ ኢህአዴግ ይናገራሉ። ግማሹ ቴዲ አፍሮ ኮንሰርት እንዳያዘጋጅ ፍቃድ ተከለከለ ይላል። ሌላው የጎሳዬ ተስፋዬን ኮንሰርት ¨Boycott” አድርጉ ይላል። አንዱ ድንገት ተነስቶ ስለ ቀድሞ ታሪክ የሆነ ነገር ይናገራል፣ ከዛ ሕዝቤ ሁላ በጭፍን ተቃውሞና ድጋፍ ያዙኝልቀቁኝ ይላል። ይኸው ነው የእኛ ነገር። ሁሉም ይናገራል። አንዱ በጭፍን የሚደግፈውን፣ ሌላው በጭፍን ይቃወማል። እርስበእርስ መጯጯህ እንጂ መደማመጥና መግባባት ተስኖናል። ሁሉም የራሱን እውነት ለመናገር እንጂ የሌሎችን ለማዳመጥና ለመረዳት ዝግጁ አይደለም።

በእርግጥ እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ትክክል ነው። ሁሉም ሰው የሚናገረውና የሚፅፈው ነገር በተግባር የሚረጋገጥ እውነት ሆነ በቃላት የተለወሰ ውሸት ለውጥ የለውም። ሁሉም ሰው በራሱ እይታ ትክክል የመሰለውን ነው የሚያደርገው። ሰው በጭራሽ ስህተት ለመስራት ብሎ አይሳሳትም። ይሄን ለመረዳት በጣም ቀላል ነው። ለምሳሌ፣ እርስዎ፥ አንቺ ወይም አንተ እስኪ ዛሬ የተናገራችሁትን ወይም ያደረጋችሁትን ነገር መለስ ብላችሁ አስቡ። እውነትም ሆነ ውሸት መናገር ያለባችሁን ተናግራችኋል አይደል? አምናችሁበትም ይሁን ሳታምኑበት የሆነ ተግባር ፈፅማችኋል። ከቦታ (space)፣ ግዜ (time) እና ምክንያት (cause) አንፃር ሲታይ የፈፀማችሁት ድርጊት ለራሳችሁ ትክክል ነው። በ“phenomenologist epistemologyፅንሰሃሳብ መሰረት፣ እያንዳንዱ ሰው የሚፈፅመው ተግባር ሌሎች ሰዎች በእሱ ቦታ ቢሆኑ የሚፈፅሙትን ተግባር ስለሆነ ድርጊቱ ሁልግዜም ትክክል ነው፡

Man chooses and makes himself by acting. Any action implies the judgment that he is right under the circumstances not only for the actor, but also for everybody else in similar circumstances.”

እኛ ለራሳችን የምንሰጠውን ግምት ሁሉም ሰው ለራሱ ይሰጣል። እኛ በምንናገረውና በምንፅፈው ነገር ላይ ትክክል ነን ብለን እንደምናስበው ሁሉም ሰው በራሱ፥ ለራሱ ትክክል ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው በመካከላችን አለመግባባት የተፈጠረው? ለምን እያንዳንዱ ሰው በራሱ ትክክል መሆኑንና የእሱን እውነት ተቀብለን ለመረዳት ጥረት አናደርግም? በአጠቃላይ፣ እርስበእርስ ከመጯጯህ ባለፈ መደማመጥና መግባባት የተሳነን ምክንያቱ ምንድነው?

አወዛጋቢ በሆኑ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች ዙሪያ ተነጋግሮ መግባባት የተሳነን ሌሎች ሰዎች፣ በተለይ የቀድሞ መሪዎች ስህተትን አውቀውና ፈቅደው እንደፈፀሙት ስለምናስብ ነው። እኛ በራሳችን “ባለማወቅ” ስህተት ልንሰራ እንደምንችል እናውቃለን። አወዛጋቢ የሆኑ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶችን ሌሎች ሰዎች በስህተት ሳይሆን አውቀውና ፈቅደው፤ በክፋትና ምቀኝነት ወይም ሌሎችን ያለ አግባብ ለመጉዳትና ራሳቸውንን ለመጥቀም ብለው እንደፈፀሟቸው እናስባለን። ለእኛ ሲሆን “ሳናውቅ በስህተት…” የምንለውን ለሌሎች ሲሆን “አውቀው በድፍረት እንደፈፀሙት” እናስባለን።

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ ሁሉም ሰው በራሱ “ትክክል” ብሎ ያመነበትን ነው የሚፈፅመው። እኛ “ስህተት ነው” ብለን የምንቃወመው ተግባር ከድርጊት ፈፃሚዎቹ ቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር ሲታይ ግን ትክክል ነው። በእርግጥ ትክክክኝነቱ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛ ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ እኛም እነሱ በነበሩበት ቦታ (space)፣ ግዜ (time) እና ምክንያት (cause) ላይ ብናስቀምጥ አሁን የምንቃወመውን ተግባር ሳናዛንፍ ደግመን እንፈፅመዋለን።

የሰው ልጅ ሁሉንም ነገር በራሱ አውቆና ፈቅዶ ያደረገው ይመስለናል። ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች በሰዎች ነፃ ፍላጎትና ፍቃድ (will) የተደረጉ ይመስሉናል። ይህ ግን ከቦታ፥ ግዜና ምክንያት አንፃር ከድርጊቱ ወይም ክስተቱ ያለንን ርቀት ወይም የግንዛቤ እጥረት ከመጠቆም የዘለለ ትርጉም የለውም። ምክንያቱም፣ ሌሎች ሰዎች በፍቃዳቸው ያደረጉት የመሰለንን ነገር ቀርበን ወይም በጥልቀት ስናውቀው ምርጫና አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንደተፈፀመ እንረዳለን።

የሰው ልጅ አንድ በጣም አስቂኝ ባህሪ አለው። የሌሎች ሰዎችን ተግባር አግባብነት ወይም ትክክለኝነት የሚፈርጀው “እኔ ብሆን ኖሮ እንደዛ አላደርግም ወይም እኔ ብሆን ኖሮ እንደዚህ አደርግ ነበር” በሚል እሳቤ ላይ ተመስርቶ ነው። ይህም በሞራላዊ ወይም ምክንያታዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ሰው ራሱን በድርጊት ፈፃሚው ቦታ (space)፣ ግዜ (time) እና ምክንያት (cause) ቢያስቀምጥ አሁን “እንዴት እንደዚህ አደረገ?” እያለ የሚቃወመውን ተግባር ሳያዛንፍ ይደግመዋል። የሰው ልጅ ይህን እውነት ሺህ ግዜ በተግባር አረጋግጦታል፡፡ ነገር ግን፣ ይህን ሃቅ አምኖ መቀበል ሞቱ እንደሆነ “Leo Tolstoy” እንዲህ ሲል ገልፆታል፡–    

“…series of experiments and arguments proves to him that the complete freedom of which he is conscious in himself is impossible, and that his every action depends on his organization, his character, and the motives acting upon him; yet man never submits to the deductions of these experiments and arguments. However often experiment and reasoning may show a man that under the same conditions and with the same character he will do the same thing as before, yet when under the same conditions and with the same character he approaches for the thousandth time the action that always ends in the same way, he feels as certainly convinced as before the experiment that he can act as he pleases.” War And Peace: EP2|CH8, Page 1159.

ዛሬ ላይ የምንቃወመውን ተግባር ከተፈፀመበት ቦታና ግዜ፣ እንዲሁም የተፈፀመበትን ምክንያት ጠንቅቀን ስናውቅ ምርጫና አማራጭ በሌለበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ አንደተፈጸመ እንገነዘባለን። ምርጫና አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የተፈፀመ ተግባርን “ትክክል” ወይም “ስህተት” ብሎ መፈረጅ አይቻልም። ምክንያቱም፣ አንድን ተግባር ትክክል ወይም ስህተት ብሎ ለመፈረጅ በቅድሚያ አማራጭ መኖር አለበት። አማራጭ በሌለበት ምርጫ ሊኖር አይችልም። አማራጭ በሌለው አስገዳጅ ምርጫ የተፈፀመ ተግባርን ትክክል ወይም ስህተት ብሎ መፈረጅ አይቻልም። ድርጊት ፈፃሚው ያደረገው እኛም በእሱ ቦታ ብንሆን የምናደርገውን፥ ያለ ማዛነፍ የምንፈፅመውን ነው።

በተለያዩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እርስበእርስ ከመጯጯህ ባለፈ መደማመጥና መግባባት የተሳነን ለዚህ ነው። የቀድሞ ሆኑ የአሁን መሪዎች የሚፈፅሟቸው ተግባራት አውቀውና ፈቅደው፥ ሌሎችን ለመጉዳት ወይም ራሳቸውን ለመጥቀም አስበው ይመስለናል። ከዚያ በኋላ “እከሌ ጀግና ነው! እከሌ ባንዳ ነው! አፄ ሚኒሊክ ቅዱስ ነው! አፄ ሚኒሊክ እርኩስ ነው!” እያልን እንጯጯሃለን፡፡ እያንዳንዱ ሰው በአፄ ሚኒሊክ ቦታ ላይ ቢሆን እሱ ያደረገውን ሳያዛንፍ ይደግመዋል! ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ሰው እንደ አፄ ሚኒሊክ ቅዱስና እርኩስ ነው!

iopian Think Tank Group