July 17, 2017 15:53

ደብረ ብርሃን

1/ደብረ ብርሃን

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደብረብርሃን ከአዲስ አበባ 130 /ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡የተቆረቆረችውና ስያሜዋን ያገኘችው ደግሞ ከ500 አመት በፊት በ1446 .ም አካባቢ በአፄ ዘርአያእቆብ /1426-1460./ ነበር፡፡

ከተማዋ ድሮ ደብረኢባ በመባል የምትታወቅ ሲሆን የንጉሱ የግራ በአልቴሃት /ግራ በአልቴሃት ከንጉሱ ሶስት ሚስቶች የአንደኛዋ የክብር ስም ነው/ ርስት ነበረች፡፡ በ1440ዎቹ መጀመሪያ ንጉሱ ጐብኝተዋት ደስ ስለተሰኙባት ተጉለት የነበረውን መናገሻ ወደዚያ አዙረው የድንኳን ከተማቸውን ከተሙባት፡፡ በኋላም ቤተመንግስት አሳንፀውና ባለወርቅ ጉልላት የነበረውን የስላሴ ቤተክርስቲያን አሰርተው ቆረቆሯት፡፡

ተአምረ ማርያም” የተሰኘ የጥንት ድርሳን የከተማዋን ስያሜ ከአንድ ተአምራዊ ሁነት ጋር አያይዞ ይገልፀዋል፡፡ በ1446 .ም በክርስትና ሃይማኖት ካህናትና በጥቂት የሃይማኖቱ ተከራካሪዎች መካከል ክርክር ይነሳል፡፡ ንጉሱና የካህናቱ አለቆች በተገኙበት አንድ እለት በጉባኤ ክርክሩ ተካሄደ፡፡ በመጨረሻም “እስጢፋኖሳውያን” በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ተከራካሪዎች አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ተጠይቀው አሻፈረን በማለታቸው ከፍተኛ ቅጣት ይደርስባቸዋል፡፡
ይህ በሆነ በ38ኛው ቀን መጋቢት 10/1446 .ም ረዘም ላለ ጊዜ / ምናልባትም ለቀናት/ የቆየ ቦግ ያለ ብርሃን ከሰማይ ይወርዳል፡፡ የብርሃኑ መውረድ ለእስጢፋኖሳውያን ስህተተኛነት ለካህናቱ ደግሞ ትክክለኛነት ምስክር ነው በሚል ተተርጉሟል፡፡ ስለዚህ ብርሃን መውረድ የንጉሱ ዜና መዋእልም ያትታል፡፡ በዚህ ሳቢያ ንጉሱ የስፍራውን ስም ደብረብርሃን /የብርሃን አምባ/ በማለት ሰይመውታል፡፡

አፄ ዘርአ ያእቆብ ከንግስና ዘመናቸው 14 አመት የሚሆነውን በደብረብርሃን ከተማ እንዳሳለፉና አብዛኛዎቹን የሃይማኖትና የፍልስፍና ድርሰቶቻቸውን የፃፉት በዚሁ ከተማ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዘመኑም ደብረብርሃን ከፍተኛ የትምህርት ማእከል የነበረች ሲሆን በንጉሱ ትእዛዝ በርካታ የሃይማኖት መፃህፍት የትርጉም ሥራ ተከናውኖባታል፡፡

2/አንጎለላ ከተማ

አንጎለላ ኪዳነ ምህረት

አንጎለላ ከተማ የምትገኘው ከደብረብርሃን ከተማ በስተምእራብ 10 /ሜ ርቀት ላይ ነው፡፡ በንጉስ ሳህለ ስላሴ /1805-1840/ .ም እንደተመሠረተች የሚነገርላት ሲሆን በሸዋም ሁለተኛዋ ከተማ ነበረች፡፡

ያለውጤት የቀረ ቢሆንም ንጉስ ሣህለ ስላሴ የውጭ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከእግንሊዝ /1834/ እና ከፈረንሳይ /1835 ./ መንግስታት ዲፕሎማቶች ጋር የንግድና የወዳጅነት ውል የተፈራረሙት በዚሁ በአንጎለላ ከተማ ነው፡፡የዳግማዊ ምኒሊክ የትውልድ ቦታ በሆነችው በዚችው በአንጎለላ ከተማ ታሪካዊቷ የአንጐለላ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ትገኛለች፡፡

በቤተክርስቲያኗ ዳግማዊ ምኒሊክ ክርስትና የተነሱባት ከመሆኗ በተጨማሪ በአድዋ ጦርነት ህይወታቸውን ለአገራቸው መስዋእት ያደረጉት የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ገበየሁ አጽም በክብር አርፎበት ይገኛል፡፡ የጀግናው አጽም ከተቀበረበት የአድዋ የጦር አውድማ ከሰባት አመታት በኋላ እንዲመጣ ተደርጎ በክብርእንዲቀመጥ የተደረገውም አጼ ምኒሊክ ራሳቸው ባሰሩት ሳጥን መሆኑ ይነገራል፡፡

የአንጐለላ ከተማ ከፍተኛ የከተማነት እንቅስቃሴ የተካሄደባት ቦታ በመሆኗ ልዩ ዋጋ የሚሰጣቸው የስነ ህንፃ ቅርሶች ፍርስራሽ ይገኝባታል፡፡ ከ150 አመታት በላይ እድሜ እንዳስቆጠረ የሚገመተው የንጉስ ሣህለ ስላሰ ቤተመንግስት ፍርስራሽ በተለይም በስሩ የሚገኘው አስገራሚው የቤተመንግስቱ የምድር ቤት አሠራር ዓይንን የሚማርክና የጥንት አባቶቻችንን የፈጠራ ውጤት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡

3/አንኮበር

1733 .ም በሸዋው ነጋሲ በመርዕድ አዝማችአ ምሀ እየሱስ /1733-1767 ./ የተመሰረተችው አንኮበር ከደብረብርሃን ምስራቃዊ አቅጣጫ 42 /ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡


አንኮበር ከአጼ ይኩኖአምላክ /1262-1277 ./ ዘመን ጀምሮ ለIትዮጰያ ነገስታት ማረፊያነት አገልግላለች፡፡ አፄ አምደጽዮን የድንኳን ከተማቸውን እንደተከሉባት ይነገራል፡፡ አፄ ልብነድንግል ደግሞ በተሻለ ሁኔታ የባለወልድ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ጀምረው እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡

የከተማነት ታሪኳ የጐላው ግን የሸዋ ስርወ መንግስት በመንዝ በማንሰራራት /1665-1881 ./ የመስፋፋት እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወደ እንጦጦ እስከዞረበትና በኋላም አዲስ አበባ እስከተቆረቆረችበት ጊዜ ድረስ በቀዝቃዛ አየሯ የምትታወቀው አንኮበር ለስድስት የሽዋ ነገሥታት በማዕ ከልነት አገልግላለች፡፡አንኮበር የሸዋ ነገስታት ቋሚ መናኸሪያ ለመሆን የበቃችው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስልጣን በያዙት
ንጉስ ሳህለ ስላሴ / 1806-1840 ./ ነበር፡፡

ንጉሱ የእ ጅ ባለሙያዎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያበረታቱ በመሆኑ በርካታ የእደጥበብ ሥራዎች ይከናወኑባት ነበር፡፡ በቤተመንግስት የሚተዳደሩ ከ1000 በላይ አናጺዎችና ግንበኞች በተለይም ባሩድ ቀማሚዎች፣ የጦር መሣሪያ ሠራተኞችና አንጥረኞች በወቅቱ ነበሩባት፡፡ የንጉስ ሳህለስላሴ ወራሽ ኃይለመለኮት ዘውድ በጫኑበት ዘመን አንኮበር በአጼ ቴዎድሮስ /1855-1868 ./ ሠራዊት ከመወረሯ በፊት ሹማምንቱ ቤተመንግስቱን አቃጥለውታል፡፡ አጼ ቴዎድሮስም በቦታው ድንኳን ጥለው ጥቂት ቀናት ቆይተዋል፡፡በተካሄደው ጦርነትም አንኮበር ክፉኛ መጐዳቷን መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡ በ1870ዎቹ ከሚኒሊክ መመለስ በኋላ አንኮበር እንደገና ተቋቁማ የጥንት ማእረጓ ተመልሷል፡፡

ዛሬ በአንኮበር ከአጼ ምኒሊክ ቤተመንግስት ፍርስራሽ በተጨማሪ በተለያየ ዘመን የተሰሩ አምስት አብያተ ክርስቲያናትና ዘመናዊ ሎጅ ይገኛሉ፡፡ እነሱም ፡አንኮበር ጊዮርጊስ በ1733 .ም በአምሃ እየሱስ፣ አንኮበር ማርያም በ1767 .ም በአስፋው ወሰን፣ አንኮበር ሚካኤል በ1817 .ም እና አፈር ባይኔ ተክለሃይማኖት በ1821 .ም በንጉስ ሳህለስላሴ፣ አጼ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ በ1875 .ም የጋብቻ ሥነስርአታቸውን ሲፈጽሙ ቅዱስ ቁርባን የተቀበሉበት የመድሃኒአለም ቤተክርስቲያን በ1772.ም ሥራው ቢጀመርም በ1846 .ም በንጉስ ሃይለመለኮት የተሰሩ ናቸው፡፡

ረጅሙን የዞኑን ተራራ ተንተርሳ የምትገኘው የቁንዲ ከተማ ሌላዋ ታሪካዊ ቦታ ናት፡፡ ከተማዋ የተመሰረተችው በመርእ ድ አዝማች ወሰን ሰገድ /1800-1805 ./ ነው፡፡ አንኮበር ለመድረስ 10 ኪሎ ሜትር ሲቀር በምትገኘው ቁንዲ የሚገኘው ቤተመንግስት በግንብ የተከበበ እንደነበረ በዙሪያው የሚታየው ፍርስራሽ ያረጋግጣል፡፡ የቁንዲ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንም የዚያን ዘመን የእደ ጥበብ ውጤት ያንፀባርቃል፡፡

4/ አልዩ  አምባ

የአንኮበር ታሪክ ሲዘከር የስምጥ ሸለቆ አካል የሆነችው የአልዩ አምባ ከተማና የአብዱል ረሱል የሙስሊም መቃብር ስፍራ አብረው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከአንኮበር ከተማ 12 /ሜ ያህል ቁልቁል ተወርዶ የምትገኘው አልዩ አምባ እንደ ሐረር በግንብ የተከበበች ስትሆን በምስራቅ፣ በደቡብና በምእራብ በሮች አሏት፡፡

ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በኢ ትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊ ከሚባሉት የቀረጥ ኬላዎችና የንግድ ማእከል አንደኛዋ ነበረች፡፡ የፈረንሳይ ዲፕሎማት ሮቺ ሄሪኮርት እንደፃፈው ከ1500 እስከ 1700 የሚጠጉ ግመሎች የአገር ውስጥ ምርት ወደውጭ ያጓጉዙባት ነበር፡፡

1834 እና 1835 .ም በአገራችን መጀመሪያ የሆነው የቀረጥ ውል የተፈረመው በአልዩ አምባ ገበያ መሠረት ነው፡፡

በከተማዋ ከፐርሽያ / Iራን/ ፣ ከህንድና ከአረብ አገሮች የሚመጡ በርካታ የውጭ አገር
ዜጎች ይኖሩባት እንደነበርም ጎብኝዎች ጽፈውላታል፡፡ በአጼ ምኒሊክ ዘመን የቀረጥ መስሪያ ቤት ሲከፈት በአልዩ አምባ የጉምሩክ ጽ/ቤት ስራውን እንዲጀምር ተደርጎ ነበር፡፡ ስልክም ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ከእ ንጦጦ እስከ አልዩ አምባ ድረስ መስመር ተዘርግቶለት ነበር፡፡ አልዩአምባ የተዳከመችው የባቡር ሃዲድ በከተማዋ ማለፍ ባለመቻሉና ወደ ድሬዳዋ በመዛወሩ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዛሬ የአልዩ አምባ ገበያ አብዛኛዎቹን አርጎባዎች ይዞ የአፋርንና አማራ ብሔረሰቦችን ያገናኛል፡፡

5/ሳላይሽ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት

የአጼ ምኒሊክ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲሆን የሚገኘውም በሀገረ ማርያምና ከሰም ወረዳ ኮርማሽ ከተማ ነው፡፡ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ ዋናውን መንገድ ተከትሎ 50 /ሜ ከተጓዙ በኋላ ወደግራ በመታጠፍ 13 /ሜ ርቀት ላይ የኮርማሽ ከተማ ይደረሳል፡፡ ግምጃ ቤቶቹ በቁጥር 14 ናቸው፡፡አሰራራቸው ደግሞ በእንቁላል ቅርጽ ነው፡፡ በ1890 .ም ከአድዋ ድል ማግስት ለጦር መሣሪያ ማከማቻነት ተብለው የተሰሩ ሲሆን የቦታው ስትራቴጂያዊ /ስልታዊ/ የተፈጥሮ አቀማመጥ የጐብኝን ቀልብ ይስባል፡፡ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቶቹ ቀደም ሲልም ለአፈንጋጭ ባለሥልጣናት እስር ቤት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከእስረኞቹ መካከልም ልጅ እያሱ ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ታሪካዊ ግንብ ቤቶች ለመንግስት መስሪያ ቤቶች በጽህፈት ቤትነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ይዘታቸውን ሳይለቁ የጥገና እድሳት ሥራ ተሠርቶላቸዋል፡፡

6/የአቡኑ ከተማ ሰላ ድንጋይ

የአቡኑ ከተማ ሰላድንጋይ ከደብረብርሃን በስተሰሜን 72 /ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ለ38 አመታት የኢ ትዮጵያ ፓትሪያርክ የነበሩት ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ መንበረ ጵጵስናቸው በዚችው በሰላ ድንጋይ ነበር፡፡ በ1875 .ም በአቡነ ማቴዎስ የተሰራው የሰላድንጋይ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በ25 አመቱ በመብረቅ ቢፈርስም እንደገና በ1900 .ም በአጼ ምኒሊክ ልዩ ትእዛዝ ተሰርቶ ሚያዚያ 30 ንጉሱ ባሉበት በአቡኑ ተባርኳል፡፡ የቤተክርስቲያኑ ህንፃ የውስጥ አሰራር ውበት አይንን የሚማርክና የዘመኑን የህንፃ ሥራ ልዩ ችሎታ የሚመሰከር ነው፡፡ በውስጡም ከግብጽ ሀገር የመጣውን የአቡነ ማቴዎስ መቀመጫ ጨምሮ በርካታ የታሪክና የባህል ቅርሶች ይገኙበታል፡፡

ሰላድንጋይ የንጉስ ሳህለ ስላሴ የትውልድ ሥፍራም ናት፡፡ በእናታቸው በወይዘሮ ዘነበወርቅ እንደተሰራችና በስማቸውም የምትጠራው ሰገነት ከተሰራች 150 አመትአስቆጥራለች፡፡ ስላድንጋይ የአብዛኛዎቹ የሸዋ ነገስታት ሚስቶችና እቁባቶች መቀመጫ ስለነበረች የወይዘሮዎች ከተማ በመባልም ትታወቃለች፡፡ ከሰላድንጋይ አቅራቢያ ከ1433 /1434/ /ም በአጼ ዘርAያቆብ የተተከለችው ደብረምጥማቅ ቤተክርስቲያንና ብዙ መነኮሳት የሚገኙባት የፃድቃኔ ማረያም ከፊል ዋሻ ደብር ይገኛል፡፡

7/ባልጭ አማኑኤል

ባልጭ አማኑኤል ቤተክርስቲያን የሚገኘው ከደብረብርሃን 260 /ሜ ርቆ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባልጭ ከተማ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ የተመሰረተው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በAጼ ገላውዲዎስ ሲሆን አጼ ምኒሊክ በ1870ዎቹ አሳድሰውታል፡፡

በቅድስቱ ግድግዳ ላይ የተሳሉት ጥንታዊ የፈትል ስእሎች ከመንፈሳዊ መግለጫነት ባሻገር ደጃዝማች ምኒሊክ በልጅነታቸው በአጼ ቴዎድሮስ ሲማረኩ፣ በ1857 .ም ከመቅደላ ሲያመልጡና በኋላም በፍቼ ከተማ ከአጼ ዮሐንስ /1864-1881 ./ ጋር ያካሄዱትን ስምምነት የሚገልጹ ናቸው፡፡ በመካነ ፈውስነቱ በአገራችን ስሙ እየገነነ የመጣው የሸንኮራ ዮሐንስ ፀበልም የሚገኘው ከባልጭ ከተማ የ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ ነው፡፡ ፀበሉ ቀደም ሲል በሽተኞችን ያድን እንደነበር ይነገር እንጅ ቀሳውስትና የፀበሉ አስተዳዳሪዎች ግን ከ1957 .ም ጀምሮ ዝናው እንደታወቀ ይናገራሉ፡፡

ፀበሉ የሚገኝበት አካባቢ ዳገታማና ቁልቁለት በመሆኑ ከአዲሱ ዩሐንስ ቤተክርስቲያን ህንፃ አጠገብ ሆኖ ሲመለከቱት የአካባቢውን አስደናቂ መልክአምድራዊ አቀማመጥና በተፈጥሮ ውበት የታደለውን የመስህብ ሥፍራ ማየት ያስደስታል፡፡

8/ወፍ ዋሻ ደን

በሰሜን ሸዋ ከሚገኙ የተፈጥሮ መስህብ ስፍራዎች መካከል የወፍ ዋሻ ደን አንዱ ነው፡፡ ደኑ አምስት ወረዳዎችን፡ጣርማበር፣ ቀወትን፣ አንኮበርን፣ ላሎማማንና ጌራቀያን የሚያካልል ሲሆን 16925.5 ሄክታር የቆዳ ስፋት አለው፡፡ ደኑ ጎሽ ሜዳ፣ ወፍ ዋሻና ጓሳ በተባሉ የጉብኝት ሥፍራዎች የተከፋፈለ ነው፡፡ ጐሽ ሜዳ ከደብረብርሃን በ30 /ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

በቀወት በኩል 12 /ሜ ጥርጊያ መንገድ አለው፡፡ ከአራት የማያንሱ ብርቅዬ አዕ ዋፋት የሚገኙበት ጐሽሜዳ ከጭላዳ ዝንጀሮና ከምኒሊክ ድኩላ ከብርቅዬ እንስሳት በተጨማሪ አነር፣ ሚዳቋ፣ ጉሬዛና ሰስ ከመሳሰሉት ሌላ በአለም በየትኛውም ስፍራ የማትገኘው “አንኮበር ሴረን” ወፍ ብቸኛ መገኛም ነው፡፡ ከደብረብርሃን ወደ ደብረሲና 15 /ሜ በዋናው መንገድ ተሂዶና ወደ ምሥራቅ 14 /ሜ ገባ ብሎ እይታው የሚጀምረው ወፍ ዋሻ ደን በክረምት ወራት አዕዋፋት ስለሚበዙበት የወፎች መሸሸጊያ /ዋሻ/ ተብሎ ይጠራል፡፡

ከጎሽ ሜዳ ባልተለየ መልኩ ማራኪ ሲሆን በደብረሲና በኩል 7 /ሜ የክረምት ከበጋ ጥርጊያ መንገድ አለው፡፡

ጓሳ የሚገኘው በመሀል ሜዳ መዳረሻ ላይ ነው፡፡ ስያሜውን ያገኘውም በአካባቢው በብዛት ከሚበቅለው የጓሳ ሳር ነው፡፡ ቦታውን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ወርቃማው ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እፅዋትና ከአስራ አራት የማያንሱ በአገራችን ብቻ የሚገኙ አዕዋፋት ያሉበት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአካባቢው የመሬት አቀማመጥ ማራኪ መሆኑ ነው፡፡

በመሠረት አስማረ

አማራ ቴሌቪዥን