July 18, 2017 06:42

እስካሁን 572,488 ህገ ወጥ የውጭ ዜጎች ሳውዲን ለቀዋል
*
ከሳውዱ የወጡት ኢትዮጵያውያን 100 ሽህ አልደረሱም
*
በሳውዲና በኢትዮጵያ የተፈረመው የስራ ስምምነት አሳስቧል

የሳውዲ የምህረት አዋጅ የሶስት ወር የጊዜ ገደብ ተገባዶ አንድ ወር ተጨምሮ የተራዘመው ጊዜ ሊገባደድ የቀሩት ቀናት ብቻ ናቸው ። የሳውዲ መንግስት በተለያዩ ሀገር ኢንባሲና ቆንስሎች ጋር እገዛ እያገኘ በጀመረው መጠነ ሰፊ 1 ሚሊዮን ህጋዊ መኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎችን ሊያስዎጣ የጀመረው ዘመቻ የወጣው ዜጋ ሲሰላ ከታሰበ ከታለመው ግማሽ ያህሉ 572,488 ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ይፋ ሆነዋል ። ከሳውዲ መውጣት ከሚጠበቅባቸው የውጭ ሀገር ዜጎች በቁጥር 400 ሽህ በመሆን ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ ኢትዮጵያውያን እንመደባለን። 400 ሽህ ይደርሳል ከተባለው መኖሪያ ፈቃድ አልባ ወገን መካከል እስካሁን ሳውዲን ለቀው የወጡት 100 ሽህ ስለመሙላታቸው የተጨበጠ መረጃ ያለው የለም ። የተዝረከረከና በማዕከላዊነት የማይሰራጨው የሪያድ ኢንባሲና የጅዳ ቆንስል በተናጠል የሚሰራጨው መረጃ እስካሁን ወደ 100 ሽህ ኢትዮጵያውያን የመጓጓዣ ሰነድ እንደወሰዱ ያስረዳል ። ከዚህ ባለፈ በትክክል ምን ያህል ወደ ሀገር ገብተዋል ለሚለው የተደራጀ መረጃ አላየንም ።

በምህረት ከወጡት የተመለሱት …

ምህረት አዋጁ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ወደ ሳውዲ የተመለሱ ዜጎች ስለመኖራቸው ተጨባጭ መረጃ መመልከት ጀምረናል ። በምህረት አዋጁ ወደ ጎረቤት ኤርትራ የተመለሱ ወገኖች ባሳለፍናቸው ቅርብ ቀናት በህጋዊ የስራ ውል ወደ ሳውዲ መመለሳቸውን መረጃ በግል ደርሶኛል ። ይህንን መረጃ የሚያረጋግጠው ሌላ መረጃም ከሳውዲ መንግስት የፓስፖርት ጀዋዛት መስሪያ ቤት ተሰራጭቶ ዛሬ ማለዳ ተመልክቻለሁ ። የተሰራጨው መረጃ እንደሚያስረዳው ሳውዲን በምህረት አዋጁ የለቀቁ 12,000 የውጭ ዜጎች ወደ ሳውዲ በህጋዊ የስራ ፈቃድ መመለሳቸውን ያስረዳል ። ይህ ሰናይ መረጃ ነው !

አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ኢትዮጵያዊ …


በኢትዮጲያ እና የሳውዲ አረቢያ የሠራተኛ ስምሪት ድርድር ግንቦት አጋማሽ በጅዳ ከተማ በስምምነት መጠናቀቁ በቅርብ አውቃለሁ ፡፡ የተፈረመው የስራ ስምምነት ለወራት በስራ ላይ ስላልዋለበት እክል የተጨበጠ መረጃ ማግኘት አልተቻለኝም ። የስምምነቱን በተግባር አለመዋል በርካቶች በሀገር ውስጥና በሀገር ውጭ እያሳሰበ ነው። በምህረት አዋጁ የስራ ስምምነቱ ወደ ሳውዲ ለመመለስ ተስፋ አድርገው ወደ ሀገር የገቡት ስምምነቱ ባለመጀመሩና የኑሮው ጣራ መንካትን እያጣቀሱ እያማረሩ ይናገራሉ ፤ ለሳውዲው ተመላሽምቢሆን የሚያሰራጩት አሉታዊ መረጃ ሳውዲ የቀረው ህገ ወጥ ቆርጦ እንዳይመለስ አድርጎታል ማለት ይቻላል ። ተመላሹ ተስፋ የጣለበት የስራ ስምምነት ተተግብሮ አለማየት ሳውዲ ያለው እንዳይወጣ እንቅፋት ብቻ አልሆነም ። ዜጎች በከፋው የየመን በርሃ ወደ ሳውዲ እንዲሰደድ እያደረገውም ነው። በተሰጠው የሳውዲ የምህረት አዋጅ ከሳውዲ በአየር በርው ወድ ሀገር የተመለሱ አሁንም በእግራቸው ገስግሰው በየመን በኩል ሳውዲ እየገቡ ነው። ይህን እውነት ሊሴ ፓሴ ሰነዳቸውን በአይኔ በብሌኑ ተመልክቸ አረጋግጫለሁ። ዛሬ ህገ ወጡ ብቻ ሳይሆን ህጋዊው ሳይቀር ለመውጣትም ሆነ ለመግባት ተቸግሯል ። ቢያንስ የተባለው ስምምነት ወደ ተግባር መገባት ቢጀምር በየመን ለመሰደድ ያኮበኮበውን አለያም ሳውዲ ላይ በቋፍ ያለው ዜጋ ጥያቄ በመመለስ መታደግ ይቻላል ባይ ነኝ ። ይህም ከሌለው አማራጭ ያለው አማራጭ ስለሆነ መሰደድን የፈቀደ ቢያንስ ህጋዊ ሆኖ መሰደድ ይችላል …

በመጨረሻዎቹ ቀናት …

በምህረት አዋጁ የመጨረሻ ቀናት የሪያድ ኢንባሲ አጠናክሮ የጀመረውን መረጃ የማሰራጨት ስራ አርግቦታል። መረጃ ቅበላውን ቢያቆምም አገልግሎቱም ሆነ ምክክሩ እየተካሄደ ስለመገኘቱ ግን እሰማለሁ ። የሪያድ ኢንባሲ በመረጃ ቅበላው ሲቀዘቅዝ የጅዳ ቆንስል በመረጃ ቅበላው ተግቶ ሰንብቷል ። ዜጎች በተለያዩ የምእራብ ሳውዲ የምዝገባ ማዕከላት ሰነድ እየወሰዱ በሰላም ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ጉትጎታውን አሁን ገፍቶበታል። የሚምን የሚሰማቸው አግኝተው የተመላሹ ቁጥር ከፍ ባይልም ግልጋሎ ትና መረጃ ቅበላው አለመቋረጡ የሚያበረታታ ነው ።

ወድ ሃገር ላለመመለስ በቂ ምክንያት ሊኖርዎ ይችላል ፤ ወደ ሀገር ለመመለስ አቅሙና ፍላጎቱ ካለዎ ግን ወደ ሀገር መግባት ይመከራል

ቸር ያሰማን

ነቢዩ ሲራክ


ሐምሌ 10 ቀን 2009ዓም