እንደሚታወቀው ሰሞኑን ከግብር ተመን ጭማሪ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አከባቢዎች ተቃውሞና አድማ እየተካሄደ ይገኛል። በእርግጥ አብዛኞቹ የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን የተቃውሞው መንስዔ ከፍተኛ የግብር ጭማሪና መፍትሄውም የተመን ቅናሽ ይመስላቸዋል። ነገር ግን፣ የግብር አወሳሰኑ እና የሕዝቡ ብሶትና አቤቱታ የሚያሳየው ሌላ ነገር ነው። የግብር ጭማሪ የተወሰነበት አግባብ የፀረ-ሽብር ሕጉ ከፀደቀበት ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ይህና ሌሎች ተመሣሣይ ችግሮችን በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው በሌላ ሳይሆን የፀረ-ሽብር ሕጉን በማስወገድ ነው። ምክንያቱም፣ የግብር ተመን አወሳሰን እና የፀረ-ሽብር ሕጉ አተገባበር በሀገሪቱ መንግስትና ሕዝብ መካከል ያለው ማህበራዊ ውል (Social Contract) ከመፍረሱ ጋር በቀጥታ የተያያዘነው፡፡ በዚህ ፅኁፍ የ“Jean-Jacques Rousseau” – “The Social Contract and Discourses [1761]” መፅሃፍ ዋቢ በማድረግ የግብር አወሳሰኑ እና የፀረ-ሽብር ሕጉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ግፅታዎች መሆናቸውን በዝርዝር ለማሳየት እሞክራለሁ።

 

ስዩም ተሾመ

“Jean-Jacques Rousseau” የመንግስት መሰረታዊ ዓላማ የሕዝብን ሕልውና ማረጋገጥ ነው ይላል። በዚህ መሰረት፣ የግብር ተመን አወሳሰንም ከዚሁ መሰረታዊ ዓላማ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ “the State as a body aiming at the well-being of all its members and subordinates all his views of taxation to that end” በማለት ይገልፃል። በመሆኑም፣ መሰረታዊ ፍላጎትን ለማሟላት የሚያስፈልገው ገቢ ከግብር (ከታክስ) ነፃ መሆን አለበት፡፡ በተቃራኒው ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ባለሃብቶችና የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ግብር ሊጣል ይገባል።

በእርግጥ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት በቤተሰብ ሊመሰል ይችላል። ነገር ግን፣ እንደ “Rousseau” አገላለፅ፣ መንግስት ወግ-አጥባቂ (patriarchal) ወላጅ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም፣ የመንግስት ህልውና የተመሰረተው በብዙሃኑ ፍቃድ (General Will) ላይ ስለሆነ የቤተሰቡን አባላትን ነፃነት መጋፋት አይችልም። በዚህ መሰረት፣ የመንግስት ሕልውና የሚረጋገጠው ስራና አሰራሩን ከሕዝብ ነፃነት ጋር እንዲጣጣም በማድረግ ነው። በመሆኑም፣ የመንግስት ዋና ዓላማ ራሱን ከዜጎች ነፃነት ጋር የተጣጣመ ማድረግ “reconciling its existence with human liberty” እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ከመንግስት ተግባራት ዋናው ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ማድረግ ነው። ይህንንም ባለሃብቶች ያከማቹትን ሃብትና ጥሪት በመቀማት ሳይሆን ያልተገባ የሃብት ክምችት እንዳይፈጠር በማድረግ ነው፡ መንግስት ለድሆች ሆስፒታል ከመገንባት ይልቅ ድህነትን ለማስወገድ መስራት አለበት። በአጠቃላይ ከመንግስት አስተዳደር፣ በተለይ ደግሞ ከግብር ተመን አወሳሰን እና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮችን “Rousseau” እንደሚከተለው ይገልፃል፡-

“…the encouragement of the arts that minister to luxury and of purely industrial arts at the expense of useful and laborious crafts; the sacrifice of agriculture to commerce; the necessitation of the tax-farmer by the maladministration of the funds of the State; and in short, venality pushed to such an extreme that even public esteem is reckoned at a cash value, and virtue rated at a market price: these are the most obvious causes of opulence and of poverty, of public interest, of mutual hatred among citizens, of indifference to the common cause, of the corruption of the people, and of the weakening of all the springs of government.” Jean-Jacques Rousseau, The Social Contract and Discourses [1761]: Online Library of Liberty, Page 219.

 

ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች በኢህአዴግ መንግስት አስተዳደር እና በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ በግልፅ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። አዲሱ የግብር ተመን አወሳሰን፣ የመንግስት የበጀት አጠቃቀም፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሰራር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፣ የሙስና እና ብልሹ አሰራር መስፋፋት፣ የፍትህ ስርዓቱ ውድቀት፣ ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ እየጠፋ አምባገነንነት መስፈኑ፣ በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት፣ …ወዘተ የኢህአዴግ መንግስትን በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነትና ተቀባይነት አሳጥቶታል። ሕዝቡ በገዢው ፓርቲና በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ያለው ተስፋ ተሟጥጦ በማለቁ፣ ብሶትና አቤቱታውን በአመፅና አድማ እየገለፀ ይገኛል። ይህን ችግር ከሥረ-መሰረቱ ለመከላከልና ለማስወገድ ዋናው ነገር የዜጎችን ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ እንደሆነ “Rousseau” እንደሚከተለው ይገልፃል፡-

“Such are the evils, which are with difficulty cured when they make themselves felt, but which a wise administration ought to prevent, if it is to maintain, along with good morals, respect for the laws, patriotism, and the influence of the general will. But all these precautions will be inadequate, unless rulers go still more to the root of the matter. There can be no patriotism without liberty, no liberty without virtue, no virtue without citizens; create citizens, and you have everything you need; without them, you will have nothing but debased slaves, from the rulers of the State downwards. To form citizens is not the work of a day; and in order to have men it is necessary to educate them when they are children.” Jean-Jacques Rousseau, The Social Contract and Discourses [1761]: Online Library of Liberty, Page 219.

 

ከላይ እንደተገለፀው፣ በአጠቃላይ የመንግስት አስተዳደርን ለማሻሻል፣ በተለይ ደግሞ ከግብር አወሳሰንና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ የዜጎችን ነፃነት (liberty) እና እኩልነት (virtue – equality) ማረጋገጥ የግድ ነው። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት ራሱን እንደ ወግ-አጥባቂ አባት ሳይሆን እንደ ሁሉን-ቻይ እናት ሆኖ ሕዝቡን ማገልገል ይጠበቅበታል። በዚህ ላይ “Rousseau” እንዲህ ብሏል፡-

“Let our country then show itself the common mother of her citizens; let the advantages they enjoy in their country endear it to them; let the government leave them enough share in the public administration to make them feel that they are at home; and let the laws be in their eyes only the guarantees of the common liberty. These rights, great as they are, belong to all men: but without seeming to attack them directly, the ill-will of rulers may in fact easily reduce their effect to nothing. The law, which they thus abuse, serves the powerful at once as a weapon of offence, and as a shield against the weak; and the pretext of the public good is always the most dangerous scourge of the people.” Jean-Jacques Rousseau, The Social Contract and Discourses [1761]: Online Library of Liberty, Page 219.

 

በአጠቃላይ፣ በኢህአዴግ መንግስት እና በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በዘላቂነት ለመቅረፍ የዜጎችን ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ የግድ ነው። ይሁን እንጂ፣ “መብትና ነፃነት ይከበር!” በማለት ድምፃቸውን ያሰሙ አካላት በሙሉ እየተከሰሱ ለእስራትና እንግልት፣ እንዲሁም ስደት እየተዳረጉ ያሉት ደግሞ በፀረ-ሽብር ሕጉ አማካኝነት ነው። ከሞላ-ጎደል ሁሉም ጋዜጠኞች፥ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጦማሪያ፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥ ተቃውሞና አቤቱታ ለማሰማት አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ዜጎች፣ ሌላው ቀርቶ “የግብር ተመን በዛብን!” በሚል አቤቱታና ቅሬታቸውን የሚገልፅ ነጋዴዎች ሳይቀር የሚከሰሱት የፀረ-ሽብር ሕጉን በመጥቀስ ነው። በፀረ-ሽብር አዋጁ አማካኝነት በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል ደግሞ በሙሉ “Rousseau” እንዳለው “የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር” በሚል ሰበብ ነው።

በመጨረሻም፣ የግብር ተመን ማስተካከያ የአጭር ግዜ መፍትሄ ነው። የችግሩ ሥረ-መሰረት ያለው ግን የዜጎቹን ነፃነትና እኩልነት የማያከብር መንግስታዊ ስርዓት ነው። ስለዚህ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የመጀመሪያው እርምጃ የፀረ-ሽብር ሕጉ ማስወገድ ነው። ያም ሆነ ይህ ግን፣ የግብር ጭማሪ እና የፀረ-ሽብር ሕጉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ግፅታዎች ናቸው! ሁለቱም የተፈጠረበትን መሰረታዊ ዓላማ የሳተ መንግስት በሕዝብ ላይ የሚፈፅማቸው ግፍና በደሎች ናቸው! የሁለቱም መንስዔ የዜጎች ነፃነትና እኩልነት የማያረጋግጥ ስርዓት ነው። መፍትሄውም የሁሉንም ዜጎች ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ ነው።