July 18, 2017 ታሪካዊ መረጃ እና ፎቶ ግራፍ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) የቀዳማዊ ኃይለስላሴ 125ኛ የልደት በአል በሚቀጥለው ሳምንት፣ July 23, 2017 ዓ.ም. በተወለዱበት መንደር፤ በኦሮሚያ ክልል፤ ሐረርጌ ውስጥ በኤጄርሳ ጎሮ መንደር ውስጥ በድምቀት ይከበራል። ይህ የልደት በአል ከመከበሩ በፊት ግን፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መልካም የሚሰኝ ዜና ለዝግጅት ክፍላችን ደርሷል። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በተወለዱበት ኤጄርሳ ጎሮ፤ ሃውልታቸው፣ ሙዚየም እና ቤተ መጽሃፍት የሚገነባ መሆኑ ታውቋል።

 

ይህን ትልቅ ፕሮጀክት አስመልክቶ መረጃውን ያደረሰን

ሙሉጌታ ኃይሌ፤ እንደገለጸው ከሆነ… ፕሮጀክቱ ቤተ መጽሃፍ፣ ሙዚየም እና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫን ያካትታል። የፕሮጀክቱ ዲዛይን የተዘጋጀው በመሃመድ አህመድ እና ባልደረቦቹ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት መስሎ እንዲሰራ ነው የታቀደው። ከዚህ በተጨማሪ ግን… በኢራን የቴህራን ዩኒቨርስቲ አማራጭ ዲዛይን ለማቅረብ ቃል መግባቱ ተገልጿል። በአገር ውስጥ የሚገኙ የህንጻ ዲዛይነሮች የተሻለ ፕሮጀክት ቢያቀርቡ የሚቀበሉ መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ ኃይሌ ገልጸዋል።

 

በኢትዮጵያ፣ በአፍሪቃ እና በአለም የፖለቲካ መድረኮች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መታሰቢያ ሃውልት እና ህንጻ የሚያርፈው፤ 23ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ሲሆን፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በጎበኟቸው አገሮች ብዛት መጠን የሚሰሩ ማረፊያ ክፍሎች ይኖሩታል። በያንዳንዱ ማረፊያ ውስጥም ከጎበኙት አገር ጋር በተያያዘ፤ ያገኙት መታሰቢያ የታተሙ ጽሁፎች እና ፊልሞች ይኖራሉ። ለምሳሌ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ1955 ጃፓንን ሲጎበኙ፤ አሳሂ ሺምቡን የተባለ ታዋቂ የአገሪቱ ጋዜጣ፤ “ታላቅ የተከበረች ነፍስ ወደዚህ አለም መጣች!” ብሎ ነበር መሪ ዜናውን የሰራው። ወደፊት ጎብኚዎች እንዲህ እና ይህን የመሳሰሉ ጽሁዎች የታተመባቸውን ስራዎች ጭምር ይጎበኛሉ።

 

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአለም ደረጃ የፈጠሩት አስተዋይ ፖለቲካም ለሁልግዜም ሲጠቀስ የሚንር ነው። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንግግር በሊግ ኦፍ ኔሽን ሲቀርብ ብዙም እድል ሰጥቶ ያዳመጣቸው ሰው አልነበረም – 1936። በኋላ ላይ ግን ይህ “ትናንሽ አገራት ሲጎዱ፤ ዛሬ ምንም ምላሽ ካልሰጣቹህ፤ ነገ በያንዳንዳቹህ ላይ ሃይለኛ እየመጣ ያጠፋችኋል። ስለዚህ አንድ መሆን አለብን” የሚል ይዘት ያለውን ንግግራቸውን ተከትሎ፤ የአለም ህዝብ መተባበሩን ትቶ በጃንሆይ ንግግር ላይ አሾፈ። ብዙም ሳይቆይ ግን… አዶልፍ ሂትለር በመላው አውሮፓ አምባገነን ሆኖ ብዙ ጥፋቶችን አደረሰ። ይህ ከሆነ ከብዙ አመታት በኋላ፤ የግርማዊነታቸው አባባል እንደትንቢት ተቆጥሮ የተባለው ሁሉ ሆነ። የግርማዊነታቸው አርቆ አስተዋይነትም በአለም መድረክ ምስክርነት አገኘ።

 

በአፍሪካ ደረጃም የአፍሪካ አንድነትን ከመመስረት ጀምሮ፤ የአፍሪቃ አገራት በፍቅር እና በሰላም እንዲኖሩ ይሰብኩና ይመክሩ የነበሩ ንጉስ ናቸው። በኢትዮጵያ ደግሞ የትምህርት መስፋፋት እና የሰለጠነ አስተሳሰብ እንዲኖር አድርገዋል። በጣልያን ወረራ ወቅት ከአገር ውጪ እና ወደአገር በመመለስ፤ ታሪክ የማይዘነጋው አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል። አሁን በትውልድ መንደራቸው የሚገነባው ሙዚየም፣ ቤተ መጽሃፍት እና ሃውልታቸው… የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ሰብዕና የሚያጎላ እና የኢትዮጵያን ታሪክ ህያው አድርጎ የሚያቆይ ይሆናል።

Emperor Haile Selassie’s 125th birthday will be celebrated on July 23, 2017 at his birth place, Ejersa Goro