July 20, 2017

(.)

ትናንትና የልደት በአሌን በማስመልከት ከወዳጆቼ አንዱ ወይም አንዲቱ ሰርፕራይዝ ያደርገኛል/ታረገኛለች ብየ ብጠብቅ ብጠብቅ ወፍ የለም:: ግን ተስፋ አልቆረጥኩም:: ባካባቢየ ወደሚገኝ አንድ ያበሻ ሬስቶራንት ሂጄ ተቀመጥሁ:: ያዘዝኩት ሰላጣ እስኪመጣ ፌስ ቡኬን ለኮስኩ:: አንዱ በቀጥታ ካዲሳባ online ላይ ጠመደኝ::

ስንት አመትህ ሆነህ ማለት ነው በውቄ?”

ሰላሳ ሰባት!”

ትክክለኛ እድሜህን የማትናገረው ትንሽ በዛ ብለው ግብር እንዳይጥሉብህ ፈርተህ ነው?”

ትክክለኛው እድሜየን ስንት ገምተኸው ነው?” አልሁት::

እንጃ ! ብቻ ፎቶህን ሳየው ያልማዝ ኢዮቤልዩ ሊከበርለት የሚገባ ፊት ነው ያለህ”

ስነስርአት!” አልኩ በንዴት ጦፌ::

ራስህ ስነስርአት!! ቀለም በወፍ ላባ እያጣቀስክ ግጥም የፃፍህ ሼባ ሰላሳ ሰባት ነኝ ስትል ትንሽ ሼም ነገር አይቆነጥጥህም? ?”

Blocked

ከጀርባየ የተቀመጡ ሁለት ተስተናጋጆች ወሬውንና ምግቡን ጎንለጎን ሲያስኬዱት ሰማሁ::

ብላ እንጂ!” ይላል አንደኛው

ዘጋኝ ባክህ! እኔ ፍቅር ሲይዘኝ ካንድ ክትፎ በላይ መብላት አልቺልም”

ከጥቂት ደቂቃ በኃላ ዘፈን ተጀመረ:: አየ !! ዘፈን ሚሊኒየም አዳራሽ ቀረ!!

የመዝፈኛይቱ መድረክ በጣም ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ ዘፋኙ በእናቱ የሽንኩርት መክተፍያ ላይ ቆሞ የሚዘፍን ይመስላል::

ከዘፋኙ ጀርባ ኪቦርድ ተጨዋቹ አቀርቅሯል:: የሙዚቃ ተጫዋች ሳይሆን የመንደር ልብስ ሰፊ ነው የሚመስለው::

ከጎኑ የግእዙን አስር ቁጥር የሚመስል ሰውየ ባለ እጄታ ሳንዱቅ የመሰለ ግብዳ ጊታር ተሸክሞ ቁሟል:: ከጊታሩ የሚመነጭ ድምፅ አልሰማሁም:: የሆነ ባልደረባው ” ሽንቴን ሸንቼ እስክመጣ ይህንን ጊታር ይዘህልኝ ቆይ” ብሎት የሄደ ነው የሚመስለው:: በመድረኩና በተመጋቢው ማሃል መለስተኛ ዙ ሃያዘጠኝ የሚመስል ድምፅ ማጉያ ተጠምዷል:: የዘፋኙን ድምፅ ብቻ ሳይሆን ሀሳቡን ሳያጎላው አይቀርም::

በሩ አጠገብ ጠብደል አፍሮ አሜሪካዊ እልፍኝ አስከልካይ ተከምሯል:: ሰውነቱ ግዙፍ ሲሆን ዘለግ ያለ ፂም አለው:: ካንገት በታች ነፃ ትግል ታጋይ ካንገት በላይ አቡነ አረጋይነው ማለት ይቻላል: : የሚረብሽ ተስተናጋጅ ፍለጋ አይኑ በየማእዘኑ ይንከራተታል:: ብዙ አልቆየም:: አንድ stress የተጫወተበት አጭር ሰካራም ወደመድረኩ መጥቶ “ካሽ ስላልያዝኩ ነው! በክሬዲት ካርድ ብሸልምህ ይደብርሃል?” እያለ ዘፋኙን መበጥበጥ ጀመረ::

አስከልካዩ በኮሌታው አንጠልጥሎ ይዞት ወጣ:: ሳየው የመኪና ቁልፍ እንጂ ሰው ከነ ጭንቀቱ ያንጠለጠለ አይመስልም:: ከብዙ ዘመን የቅምቀማ ልምዴ እንደተረዳሁት ከረጅም ቀምቃሚዎች ይልቅ አጫጭር ቀምቃሚዎች ፈጥነው ይሰክራሉ:: ምክንያቱም አልኮል ረጅም ሰው ጭንቅላት ላይ ለመድረስ ብዙ ርቀት መራመድ አለበት::

ሂሳብ ከፍየ እጄን ታጥቤ ልወጣ ሽንትቤት ገባሁ:: ከጀርባየ ሁለት ሰዎች ጎንለጎን ቆመው ይሸናሉ::

አንደኛው አርፎ በመሽናት ፋንታ በድንበርተኛው ሸኚ ላይ አስተያየት አይሉት ጥያቄ ሰነዘረ::

ፍሬንድ በመጥረቢያ ነው እንዴ የተገረዝከው?”

ድንገት ስልኬ ጠራ:: አደይ ናት:: አደይ የዛሬ አራት አመት አብራኝ መጥታ ጥገኝነት የጠየቀች ባለንጀራየ ናት::

Birthday boy የት ነው ያለኸው?” አለቺኝ

ያለሁበትን ተናገርኩ::

እንዳትወጣ ጠብቀኝ”

እንሆ በመጨረሻ!!!

ይሄን ላልማዝ ኢዮቤልዩ የታጨ ፊቴን ለሰርፕራይዝ አሰናድቼ ጠበቅሁ:: ምንም ማድረግ አይቻልም:: እድሌ ነው:: ወንዶች ይታገሉህ ሴቶች ያገልግሉህ ተብየ የተፈጠርኩ ነኝ::

ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ አደይ መጣች

ትንሽ ስናወጋ ቆየና ከቦርሳዋ የሆነ ጥቅል አወጣች :: I knew it ይላል ፈረንጂ!!?

ምን የመሰለ I phone 7 ከፊቴ ቦገግ አለ::

እንዴው ቆይ ምን አሳሰበሽ ” ብየ ልጠመጠምባት ስል ቀደመቺኝ::

ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ይህን ስልክ ለታናሽ ወንድሜ ትሰጥልኛለህ””