JULY 21, 2017

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ወደ ጵጵስናው የመጡት ብዙ ጫና ተደርጎባቸው ነበር፡፡ ከጵጵስናው ይልቅ በሶርያውያን ገዳም መኖርን ይመርጡ ነበር፡፡ ሺኖዳ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ምኞታቸው እንደ አባ ገብረ ክርስቶስ በበረሓ መኖር ነበር፡፡ የወቅቱ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ ግን ገዳሙን እንዲረዱ ወደ ሶርያውያን ገዳም ላኳቸው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የገዳሙ አበው ሺኖዳ ለገዳሙ መሻሻል የሚሠሩትን ሥራ አልወደዱትም፡፡ የኢትዮጵያዊው የገብረ ክርስቶስ (አብዱል መሲሕ) ደቀ መዝሙር የነበሩት ሺኖዳ (በጥንቱ ስማቸው አባ እንጦንስ) ግን መከራውን ሁሉ ተቋቋሙት፡፡ በመጨረሻም አቡነ ቄርሎስ ገዳሙን እንዲያስተዳድሩ በጫና ሾሟቸው፡፡ በኃላፊነታቸው ላይ እያሉ ግን እርሳቸው ለገዳሙ መሻሻል የሚሠሩትን ሥራ ያልወደዱ መነኮሳት ተነሡባቸው፡፡ ለፓትርያርኩም ከሰሷቸው፡፡ ፓትርያርኩም አባ እንጦንስን ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ጠሯቸው፡፡ ሺኖዳም ከሳሾቻቸው ትክክል እርሳቸው ግን ስሕተት መሆናቸውን ገልጡ፡፡ ይህ ፈተና የመጣውም በእርሳቸው ድክመት እንጂ በከሰሷቸው አባቶች ምክንያት እንዳልሆነ ተናገሩ፡፡ ስለዚህም ከኃላፊነት እንዲነሡና ወደ በረሓ ገብተው በምናኔ እንዲኖሩ የፓትርያርኩን ፈቃድ ጠየቁ፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ ግን ውሳኔያቸውን በማግሥቱ እንደሚያሳውቋቸው ነግረው በመንበረ ፓትርያርኩ እንዲቆዩ አደረጉ፡፡

በማግሥቱ ሴፕቴምበር 30 ቀን 1962 ዓም አቡነ ቄርሎስ አቡነ እንጦንስን ለውሳኔው ጠሯቸው፡፡ አባ እንጦንስም ወደ በረሓው የሚመለሱበትን ቀን እየናፈቁ ጠበቁ፡፡ አቡነ ቄርሎስም እጃቸውን በአቡነ ሺኖዳ ላይ ጭነው ‹የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮትና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳስ› አድርገው ሳያስቡት ሾሟቸው፡፡

ይህ በተፈጸመ ሰሞን የትምህርት ቤት ጓደኛቸውና የብዙ ጊዜ ወዳጃቸው ጀርመናዊው ፕሮቴስታንትና በካይሮ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የኮፕቲክ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ዶክተር ሜናድረስ (Dr. Otto Meinardus) ‹እንኳን ደስ ያለዎት› የሚል የደስታ መግለጫ ደብዳቤ ላከላቸው፡፡ ብጹዕ አቡነ ሺኖዳም ደብዳቤውን በደስታ ከተቀበሉ በኋላ የሚከተለውን መልስ ላኩለት፡፡

ሰላምና ጸጋ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይሁንልህ፡፡ ስለ ላክህልኝ የደስታ መግለጫ መልእክት ምስጋናዬን አቀርብልሃለሁ፡፡ ወዳጅነትህንና ፍቅርህን መቼም አልዘነጋውም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ላለው (ለጵጵስናው ሹመት) ጊዜ የኀዘን መግለጫ እንጂ የደስታ መግለጫ አይስማማውም፡፡ አንድ መነኩሴ ጸጥታ የነገሠበትን በረሓ ትቶ ውጥንቅጡ ወደ በዛ ከተማ ሲገባ እንዴት እንኳን ደስ ያለህ ይባላል? በክርስቶስ እግር ሥር መቀመጧን ትታ እኅቷ ማርታ ወደምትደክምበት የማድቤት ሥራ ስትመለስ ማርያምን ማነው እንኳን ደስ አለሽ የሚላት? ለእኔ ይህ አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ እኔ ጵጵስና የተሾምኩበትን ቀን የማስታውሰው በኀዘንና በልቅሶ ነው፡፡ እውነት ለመናገር የምናኔና የጸሎት ሕይወት ከማንኛውም መለኪያ በላይ ነው፡፡ ከኤጲስቆጶስነትም ሆነ ከጵጵስና ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ወዳጄ ሆይ እውነተኛው መቀባት (ለጵጵስና መቀባት ሳይሆን) ልብን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ አድርጎ መቀባት ነው፡፡ እርሱ በመጨረሻው ቀን የሚጠይቀን ማዕረጋችንን ሳይሆን ንጹሕ ልባችንን ነውና፡፡ ይህንን የምጽፍልህ በዋዲ – ኤል – ናትሩን፣ ባሕር – ኤል – ፋሬግ ከሚገኘው ከምወደው ዋሻዬ ውስጥ ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ በዚህ ቦታ እስከ ጥምቀት በዓል ድረስ ለመቆየት አስባለሁ፡፡ ከዚያም ወዲያ ወደ ካይሮ እመለሳለሁ፡፡

ለተሾሙት ጳጳሳት በየአካባቢው የሚደረገውን ድግስ ስመለከት ይህ ትዝ አለኝ፡፡

Otto Friedrich August Meinardus, Two Thousand Years of Coptic Christianity,1999, p. 5

 ዳንኤል ክብረት