19 Jul, 2017

ነአምን አሸናፊ

ቅዳሜ ሐምሌ 8 ቀን 2009 .. 13ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን 6 ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ያከናወነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ ዶ/ር ሚሊዮን ቱማቶን ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንዲመሩት ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ፡፡

/ር ሚሊዮን የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የቀድሞውን ሊመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን በመተካት ነው የተመረጡት፡፡ የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ሊቀመንበር ናቸው፡፡

በጠቅላላ ጉባዔ መገኘት ከሚገባቸው 80 የአራቱ የመድረክ አባል ድርጅቶች ተወካዮች 66 ያህል መገኘታቸውን አዲሱ አመራር በዕለቱ ለሪፖርተር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በዕለቱ የአዳዲስ አባላት ምርጫ ከማከናወን በተጨማሪም፣ የፓርቲው የአንድ ዓመት የሥራ ክንውንና እንቅስቃሴን የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደተካሄደበትም መድረክ አስታውቋል፡፡

በዕለቱ ከሊቀመንበሩ በተጨማሪ የሌሎች የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ተከናውኗል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ጎይቶም ፀጋዬ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ ሙላቱ ገመቹ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፣ ወ/ሮ ራሔል ባፌ የፋይናንስ አስተዳዳር ኃላፊ፣ እንዲሁም አቶ ካሳዬ ዘገየ ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡

በተጨማሪም መድረክ አዲስ የኦዲትና ቁጥጥር አባላትን ምርጫ አካሂዷል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ዓለሙ ኩየራን ሰብሳቢ፣ አቶ ክንፈ ገብረ ዮሐንስን ጸሐፊ፣ እንዲሁም አቶ ለገሰ ላንቃሞን አባል አድርጎ መርጧል፡፡

በተመሳሳይ እሑድ ሐምሌ 9 ቀን 2009 .. ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ማኅበረ ዴሞክራሲና ደቡብ ኅብረት አንድነት ፓርቲ፣ ስያሜውን ወደ ኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) መቀየሩን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ከዚሁ በተጨማሪም አዳዲስ የሥራ አስፈጻሚና አመራር አባላትን ምርጫ አከናውኗል፡፡ በዚህም መሠረት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን በሊቀመንበርነት፣ አቶ ጥላሁን እንደሻውን በምክትል ሊቀመንበርነት፣ እንዲሁም ሃምሳ አለቃ በቀለ ጊዴቦን የኦዲትና ቁጥጥር ኃላፊ በማድረግ መርጧል፡፡

መድረክ መጠሪያውን ወደ ኢሶዴፓ የቀየረውን ፓርቲ ጨምሮ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (አረና)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ ድርጅት ነው፡፡