July 21, 2017

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን የቀን ገቢ ግምት መሠረት ያደረገው አዲሱ የግብር ትመና በህብረተሰቡ ዘንድ ከባድ ቁጣ እየቀሰቀሰ ነው። የቀን ገቢ ግምት መጨመር ጋር በተያያዘ የተነሳው የሥራ ማቆም አድማ በኦሮሚያ ክልል በሻሸማኔ፣ጅማ፣ ወሊሶ፤ በቡሌ ሆራና በአምቦ ከተማዎች ቀደም ብሎ የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገሮች አድማሱን እያሰፋ ነው። በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ በአንድ አንድ አካባቢዎች የሥራ ማቆም አድማ ተጀምሮ እንደነበረ የተለያዩ መረጃዎች እያመላከቱ ነው።የቀን ገቢ ግምት የሚደረገዉ «የግብር ከፋዮችን የንግድ እንቅስቃሴ መሠረት ባደረገ እና በገቢ መርማሪዎች የህሊና ዳኝነት ላይ ተመስርቶ» እንደሆነ የገቢዎች ባለስልጣን ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ ነጋዴዎች እንደሚገልጹት ከሆነ የቀን ገቢ ግምት እጅግ በጣም የተጋነነ ከመሆኑ ባሻገር ነጋዴዎችን ከንግድ ሥራ የሚያስወጣ ሚዛናዊ ያልሆነ የገቢ ግምት እንደሆነ በተለያየ መንገድ እየገለፁ ይገኛሉ።
በኦሮሚያ ክልል የቀን ገቢ ግምት መጨመር ጋር በተያያዘ የተነሳው ሥራ የማቆም አድማ በተመለከተ ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ “ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ ያላቸውን ቅሬታ በዚህ አግባብ ቢገልጹ ምንም ክፋት የለውም!” በማለት ከቪኦኤ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ታክስ ፕሮግራም ልማት ስራዎች ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ ” በተናጥል እንጂ በቡድን አቤቱታ ማቅረብ የለም፤” በማለት የነገዴዎችን አቤቱታ ያጥላሉት ባለስልጣኗ፣ ወ/ሮ ነፃነት አበራ ሲሆኑ፤ ሴትዮይቱ የሰጡት መግለጫ የአገዛዙ ሥርዓት ከደነገገው የቡድን መብት ጥበቃ እርዮተ አለምና ፅንሰ ሃሳብ ጋር የሚጋጭ ንግግር እንደሆነ እየተገለፀ ነው። ከዚህም በላይ ነጋዴዎች ለሚያቀርብት አቤቱታ እና ቅሬታ የወ ሮ ነፃነት አበራ ምላሽ ነጋዴዎችን አስቆጥቷቸዋል ። የንግዱ ማህበረሰብ የራሴ የሚለው (ነፃ እና ገለልተኝ )ወኪል ማህበር የለውም በመባል በሰፊዉ ይታማል።


ይድነቃቸው ከበደ