July 22, 2017

(GM Melaku and Veronica Melaku)

“እስከ 19ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የሚባለው ሀገር እስከ ደብረ ብርሃን የነበረው ነው፤ ከሱ በስተደቡብ የነበረው በኢትዮጵያ ነገስታት ስር አልነበረም፡፡” ይህን ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ናቸው።

ዶ/ር ነጋሶ

ታሪክ ከዘመናት በፊት የነበረ ሁኔታን የሚያትት የትምህርት ዘርፍ ነው። የታሪክ ተመራማሪ ልክ እንደ ኬሚስት በላብራቶራ ታሪክና ታሪክን አጋጭቶ አዲስ ታሪክን አይፈጥርም። እስከማውቀው ድረስ የታሪክ ተመራማሪ ተቀዳሚ ተግባር ሂደቱ ተፈጸመ የተባለበትን ቦታና ሁኔታን የሚያትቱ ጽሁፎች ከሌሎች ተዛማጅ ጽሁፎች ጋር ማመሳከር፤ በወቅቱ ተፈጠረ የተባለን ክስተትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ የዘረመል ወይንም ስነ አጽም ግኝቶች ካሉ ማፈላለግ እና የጽሁፉን ተአማኒነት ማረጋገጥ ነው። ከዚያ ሁሉ ድካም በሁዋላ የራስን እይታ ለተጠቃሚ ማድረስ እንጂ የአንድን አገር ንጉስ ከሌላ አገር ንጉስ ጋር አፋጭተህ በወቅቱ ያልነበረ ንጉስ አትፈጥርም። በአጭሩ ታሪክ ተአማኒነቱን ተጨባጭ በሆኑ ነገሮች ታረጋግጣለህ እንጅ ተለዋጭ ሌላ ታሪክ በቤተ ሙከራ አትፈጥርም። በመሰለኝ ተጀምሮ በመሰለኝ የሚደመደም አይነትም አይደለም! ታሪክ ታሪክ ነው!

ዶ/ር ነጋሶ ባለፈው ዓመት “የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበርኩ ጡረተኛ ብሆንም በነበረኝ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ምክንያት ተገቢውን እንክብካቤ እየተደረገልኝ አይደለም፤ አሁን ታምሜ እንኳን በአግባቡ የምታከምበት ሁኔታ አልተመቻቸልኝም፤ ምቹ የሆነ መጠለያንም ተነፍጌያለሁ ሲሉ ማማረራቸው የሚታወስ ነው። አሁንም ቢሆን መንግስት ተብየው የሚገባኝ የሚሉትን ክብካቤ ቢያደርግላቸው የምንጠላው ጉዳይ አይደለም። ከዓመት በኋላ ደግሞ አሁን ያለው “ህገ መንግስትም” ሆነ በክልሎች አወቃቀር ወቅት ህወኃት ተወካይ አልነበረውም ብለው ክው አደረጉን። “ህገመንግስቱም” ሆነ የመሬት ክፍፍሉ የተከወነው በኦነግ፣ ሻዕብያ እና ህወሃት አማካይነት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ሆኖ እያለ ዶ/ሩ አይናቸውን በጨው አጥበው ህወኃት ተወካይ አልነበረውም አሉን። ይህ አዲስ አድማስ ላይ የሰፈረው ቃለ መጠይቃቸው ካለው የተአማኒነት ጉለት በተጨማሪ እርስ በርሱ የሚጣረስ በመሆኑ የማሰብ እና የማመዛዘን ችሎታቸው የወረደበትን ሁኔታ ታዝቤያለሁ። ሲጀምሩ አምደ ፅዮን ለዘመቻ ሐረር ድረስ ወርዷል ይሉና ወረድ ብለው ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ኢትዮጵያ እስከ ደብረብርሃን ነበረች፤ ከደብረብርሃን በስተደቡብ የነበረው በነገስታቱ ስር አልነበረም ይሉናል።

አምደፅዮን በ14ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የኢትዮጵያ ነጉሥና ወሰነ ግዛቱም ሐረር ድረስ መሆኑን እየታወቀ ያን ማለታቸው የአይን ቅንድባችን ከፍ እንድናደርግ አስገድዶናል። የዶ/ር ነጋሶ የአማራ ነገስታቱ ኢትዮጵያ ከ19ኛው ክፍለዘመን በፊት ከደብረ ብርሃን ተሻግራ አታውቅም ትርክት አማራ ከደብረ ብርሃን ማዶ አያገባውም የሚል ይዘት ያለው ነው። በተለይ ይህ የሆነው የአዲስ አበባ የባለቤትነት ካርድ በተመዘዘበት ማግስት መሆኑ ደግሞ አንዳች ርካሽ የፖለቲካ ንግድ እንዲገኝበት ታስቦ የተደረግ እንጅ አንዳችም ታሪክን በታሪክነቱ የማስተማር ዓላማ የለውም። ለመሆኑ ከደብረ ብርሃን በስተደቡብ የተሰሩት አያሌ እድሜ ጠገብ ገዳማት ማን እንደሰራቸው ለዶ/ሩ ጠይቁልኝ እስኪ?

ከአምደ ፅዮን በፊትም ሆነ በኋላ እስከ ግራኝ ወረራ ጊዜ ድረስ የአማራ የሰለሞናዊ ሥርወ መንግስት ነገስታት ወሰነ ግዛት ከደቡብ በኩል ከምድር ወገብ 3 ድግሪ ኬክሮስ፤ በሰሜን 18 ድግሪ ኬክሮስ፤ በምስራቅ 13 ድግሪ ኬንትሮስ እንዲሁም በምዕራብ 48 ኬንትሮስ እንደነበር “ The Glorious Victories of Amde Seyon, King of Ethiopia” የተሰኘው የ GWB Huntingford መጽሐፍ ያትታል። ይህን ግልፅ በሆነ ቋንቋ ለማስቀመጥ ያክል አዲስ አበባ (በረራ) በ9 ዲግሪ ኬክሮስ በስተሰሜን ትገኛለች። አንድ ዲግሪ 116 ኪሎሜትር ነው። የአምደጽዮና የመካከለኛው ዘመኗ ኢትዮጵያ የደቡብ ጠረፍ 3 ዲግሪ ኬክሮስ ከሆነ ከአዲስ አበባ 6 ዲግሪ በስተደቡብ (696 ኪሎሜትር ድረስ) የነገስታቱ ወሰን እንደነበር ነው። በሰሜንም በምዕራብም በምስራቅም በዲግሪ የተቀመጡት ሲሰላ የአምደ ጽዮኗ ኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል ከ26 አመት በፊት የነበረችው ባለ ጀበና ቅርጿን ኢትዮጵያ ሆና ነው የምናገኘው።

አምደ ጽዮን የንግስና ስሙ ገብረመስቀል የሆነ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ የሰሎሞናዊ ስርወ መንግስት ንጉሥ ነበር። ከ1314-1344 ዓ.ም በዘለቀው ዘመነ ግዛቱ እጅግ ብርቱ የሚባል የጦር ሰራዊት የገነባ ንጉሥም ነበር። በሁለት የተከፈለው የጦር አደረጃጀቱ ከዘመኑ ጋር የዘመነም ነበረ። የመጀመሪያውና በንጉሡ ሸንጎ የሚመራው የማዕከላዊው የጦር ሰራዊት ሲሆን “ቀስተ ንብ (ተናዳፊ ንብ)”፣ “ተኩላ” ወዘተ በሚባሉ ክፍለ ጦሮች የተከፈለ ነበር። ሁለተኛውና የንጉሡ ማዕከላዊ ሰራዊት አደጋ በሚጋረጥበት ጊዜ ብቻ የሚጠራው የአካባቢው ሚሊሻ ነበር። በአምደ ፅዮን ዘመነ ግዛት ዕድሜው ቀስት ለመወርወር እና ጦር ለመስበቅ የደረሰ ወንድ ልጅ በሞላ ወታደር ነበር። የአምደ ፅዮን ጀግንነት ሰባት ገፅ በሚሆን የንጉሡ መወድሰ ዜማ (National Anthem ሊባል ይችላል) በሚገባ ተገልጿል። ንጉሡ ቀስት ወርውሮ በጠላት አይኖች መካክል የሚሰካ አልሞ ተኳሽም ነበር። እጅግ ሲበዛ ፈሪሃ እግዚአብሄር የነበረው ሰውም ነበር።

የአምደ ፅዮኗ ኢትዮጵያ ለጥቁር አፍሪቃውያን ኩራትም ነበረች። ወቅቱ አውሮጳውያን የባሪያ ንግድን ለመጀመር የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ አፍሪካን መውረር የጀመሩበት ጊዜ ስለነበር Richard Reid የተባለ ሰው “Warfare In African History” በሚል መጽሐፉ ላይ በወቅቱ ለአውሮጳውያን የአፍሪካ ጉዞ ዋነኛ ተግዳሮት የነበረው በሽታ እና መጥፎ የአየር ንብረት (ሀሩር) እንጅ ከነዋሪው የገጠማቸው አንዳች ነገር እንዳልነበረና ይህን የአውሮፓውያን ወረራ የመከቱት የኢትዮጵያ ነገስታት እና በአትላንቲክ ዳርቻ በኩል ይገኝ የነበረው የሞሮኳውያን ስርወ መንግስት ብቻ እንደነበር በገፅ 78 ላይ ጠቅሶታል። ይህ የሆነው ደግሞ በአምደፅዮን በአባቱ ወደም አራድ እና እሱን በተከተሉት ሰይፈ አራድ እና አጼ ዳዊት የግዛት ዘመን ነበር። ስለነገስታቱ ኢትዮጵያ Frederick Douglass የተሰኘ የጥቁር መብት ተከራካሪ ሐምሌ 5 1862 እ.ኤ.አ (July 5, 1862 GC) “July 04 ለባርያው ምኑ ነው?” በተሰኘ እጅግ ብዙ ሰው በተከታተለው ንግግሩ “የፈረጠሙ የብረት እግሮቹም ሆኑ የዛሉ የቻይኖች እግር እኩል እይታን ሊሰጣቸው ይገባል። አፍሪካ ተነስታ ያልተሸመነ ልብሶቿን ታጠልቃለች ኢትዮጵያም እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች” ሲል የነገስታቱ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተስፋና ኩራትነት መስክሯል። ይህ እንግዲህ ከአድዋም ድል በፊት ነበር።

አምደ ፅዮን በዘመነ ግዛቱ በስሩ የነበሩ የይፋት እና የአዳል ሱልጣኖች ያምፁበት እንደነበርና በተደጋጋሚ እየዘመተ አመጻዎችን ያበርድ እንደነበር የሀኒንግፎርድ መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትም ይህንኑን የሀኒንግፎርድ መጽሐፍ እየጠቀሱ አምደ ጽዮን ስላደረጋቸው ዘመቻዎች “The Ethiopian Boarderlands” በተባለ መጽሐፋቸው በስፋት ጽፈዋል። እነዚህ ዘመቻዎች አመጻን የማብረድ እንጂ ፈጽሞ የመስፋፋት ዘመቻዎች እንዳልነበሩ ሀኒንግፎርድ፣ መቅሪዝ እና ፕ/ር ፓንክረስት በተደጋጋሚ “የአዳል አማጽያን” (the Rebels of Adal)፤ “የይፋት አማጽያን” (The rebels of Ifat) ሲሉ መጥቀሳቸው አንድ ማስረጃ ነው።

ንጉሥ አምደጽዮን ካንዴም ሁለቴ ለግብፁ የማምሉክ ሱልጣን አል-ናስር ሙሀመድ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ልኮ ነበር። የዚህ መንስኤ ደግሞ አል-ናስር በወቅቱ የግብፅ ክርስትያኖችን ያሰቃይ፣ ያሳድድና ያስር ስለነበር ነው። ሁለት ጊዜ መልዕክተኞችን ልኮ ሡልጣኑን “ከምግባርህ ካልተቆጠብቅ የአባይን ወንዝ አቅጣጫ አስቀይሬ ህዝብህን በረሃብ እንደምጨርሰው እንዳታውቅ ይሁን” የሚል መልዕክት እንደላከ ተግልጿል። ይህን ተከትሎ የግብጹ አል-ናስር የይፋት ሱልጣኖችን እንዳነሳሳበትና በተደጋጋሚ ለይፋትና ለአዳል ሱልጣኖች አመፅ ከጀርባ የአል ናስር እጅ እንደነበረበት ይነገራል። በመጨረሻ ግን ሡልጣኖቹ ስለተሸነፉ አል ናስር ተስፋ ቆርጦ ከንጉሡ ጋር እርቀ ሰላም እንዳወረደም ተገልጿል። በሀኒንግፎርድ መፅሀፍ ዘይላ ወደብ በንጉስ አመደ ፅዮን ስር እንደነበረችና ወጪ ገቢ ንግድን በዚያ በኩል ይቆጣጠር እንደነበረ በሰፊው ተጽፏል። እንደ ሀኒንግፎርድ ያሁኑ አፋር በአዳሎች ስር የነበረ ሲሆን ከሌሎች አዳሎች ጋር ለአምደፅዮን ይገብሩ እንደነበር ሰፍሯል።

አምደፅዮን በዘመነ ግዛቱ ከኢፋት፣ ከአዳል፣ ፈጠጋር፡ ዳዋሮ እና አፋር ላይ በተለያየ ጊዜ ተቃውሞ ቢገጥመውም ከባሌ ግን ምንም አይነት ተቃውሞ እንዳልነበረበት ፕ/ር ፓንክረስት ይገልጻሉ። ይህ የሆነው ደሞ “ከአምደ ፅዮን የጦርነትንና የአመራር ብቃትን የተቀባሁ ነኝ” በሚለው በጋራድ አሊ ትመራ ስለነበር ነው። ጋራድ በወቅቱ ባሌን ያስተዳድሩ ለነበሩ ይሰጥ የነበረ ማዕረግ ነበር። የሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ባሌ ላይ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረው በአፄ ዳዊት ዘመን ነበር።

(Richard Pankhurst, The Ethiopian Borderlands, page 71-71)።

ንጉሥ አምደ ፅዮን የአዳል ሡልጣኖችን የደመሰሱበትን የመጨረሻ ጦርነት ከማድረጋቸው በፊት ጦራቸውን ሰብስበው የተናገሩትን አስነብቤ እጨርሳለሁ።

…በዚያን ወቅት ንጉስ ገማልዲን ከብዙ የከበሩ ስጦታዎች ጋር ወደ አምደ ፅዮን ቀርቦ “በስምህ እፀልያለሁ ንጉስ ሆይ፤ አሁን ወደ መናገሻህ እንድትመለስ ይሁን፤ እኔን ሾመህኛልና እንደፈቃድህም አደርጋለሁ።ከዚህ በፊት እንዳየነው በተደጋጋሚ የአዳሎችን ምድር ድምጥማጡን አጥፍተሃል። ቀሪውን ተውልን! የቀረነው በንግድ ካንተ ጋር እንተሳሰር ዘንድ፤ ሁላችንም በዚህ ምድር (በአዳል) ያለን ያንተ ተገዥዎች ነንና ዳግም በምድሩ ላይ ክንድህን አታንሳ።”

አምደፅዮን በቁጣ የሚከተለውን መለሰለት

“ወደ መናገሻየ የምመለሰው በውሾችና በጅቦች ተነክሸ፤ እርኩስ መንፈስ በተጠናወታቸው የእፉኝት ልጆች ተዋርጀ አይደለም። አመፀኞችን ሳላንበረክክ ወደ መናገሻየ የምመለስ ከሆነ በወለደችኝ በናቴ ስም ሴት ሆኜ ልጠራ..” ይህን ካለ በሁዋላ ንጉሱ በዕለተ ሰኔ 28 ሰራዊቱን ሰብስቦ..

“በምስራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብ፤ በትግሬ፣ በጎጃም፣ በዳሞት፣ በሀድያ በሁሉም በተዋጋሁባቸው ቦታዎች በእግዚአብሄር ሃይል አሸንፌያለሁ። የጠላቶቻችን ሰራዊት ከሊቅ እስከ ደቂቅ መሪዎቹን ጨምሮ ገሚሱን ገድለናል፤ ገሚሱን ምርኮ ገሚሱንም ቁስለኛ አርገን ድልን ተቀዳጅተናል። አሁንም በነዚህ አማፅያን ፊት አትፍሩ፤ በመካከላችሁ መከፋፈልን አስወግዱ፤ ያ ሲሆን ፈጣሪም ከጎናችን ሆኖ ይዋጋልናል። ቀስት እና ደጋን ይዘው ቢመጡ ቀስትና ደጋን እናንተም ጋር መኖሩን አትዘንጉ።”

ወረድ ብሎም…”በሉ አሁን ጎራዴያችሁን ሳሉ፤ልባችሁንም አጀግኑ፤ በመንፈስ አትፍሩ ነገር ግን እምነታችሁን በፈጣሪ ላይ ጣሉ። ብርታትና ጀግንነታችሁን ወደኋላ ጥላችሁት መጥታችኋል፤ አሁን ግን ከፊት አስቀድሙት የፍርሃትን ስሜትም ከላያችሁ ላይ አራግፉ። እኔ ዝናብም ይሁን ሐሩር አማጽያኑን ሳናበረክክ ወደ መናገሻየ ላልመለስ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በህያው እግዚአብሄር ፊት መሀላ አለብኝ….” ሲል ንግግሩን ጨረሰ። ጦርነቱንም በድል ተወጥቶ በቦታው የሹም ሸር ፈፅሞ ወደ መናገሻው በሠላም ተመልሷል።

(The Glorious Victories of Made Seyon, king of Ethiopia, G.W.B Huntingford, page 69-71)

እኛም ንጉሥ ሆይ ሽህ አመት ይንገሱ!

ዘላለማዊ ክብር ይገባዎታልና እንላለን።

 

C