JULY 26, 2017

130 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የቆሼ የቆሻሻ ክምር መደርመስ አደጋ ከተከሰተ አምስት ወራት ቢያስቆጥርም፣ በወቅቱ ከአደጋው ተርፈው ዕገዛ ይደረግላቸዋል ተብለው የነበሩ የአደጋው ተጎጂዎች ቃል የተገባላቸው ድጋፍ በመዘግየቱና ከዚህ በፊት ሲሰጡ የነበሩ ድጋፎች በመቋረጣቸው ችግር ውስጥ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡

ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የቆሼ ተጎጂዎች፣ ያሉበትን ሁኔታ ለመገናኛ ብዙኃን ለምን ተናገራችሁ ተብለው በአካባቢው ሹማምንት ጫናዎች እንደደረሱባቸው ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በወጣቶች ማዕከል ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ የአደጋው ተጎጂዎችን በማናገር ዘገባ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ እነሱም ችግራቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹በጊዜው መረጃ ለምን ሰጣችሁ ተብለን ጫና ደርሶብናል፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያናገራቸው ተጎጂዎች አስረድተዋል፡፡

ሌላው ቢቀር ጋዜጣውንና አብሮ የወጣውን ፎቶግራፍ ይዘው መጠለያው ጣቢያ ድረስ ሹማምንቱ እንደመጡና ጫና እንዳደረሱባቸው፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ተጎጂዎች ገልጸዋል፡፡

‹‹ሌላው ቢቀር በሪፖርተር በወጣው ዘገባ ምክንያት ለሳምንት ያህል ይቀርብልን የነበረው ምግብ ተቋርጦ ነበር፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ሐምሌ 8 ቀን 2009 .. በኮልፌ ቀራኒዮ የሚገኘውን በተለምዶ የወጣቶች ማዕከል በሚባል የሚታወቀውንና ወደ 90 የሚጠጉ ተጎጂዎች በጊዜያዊነት መጠለያ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘውን ሥፍራ የጎበኘ ሲሆን፣ በመጠለያው ሕፃናት፣ አራስ የታቀፉ እናቶችና ዕድሜያቸው የገፉ አዛውንቶች እየኖሩበት ነው፡፡

በወቅቱ ሪፖርተር ካገኛቸው ተጎጂዎች መካከል መረጃ ለመስጠት ያላቸውን ሥጋት የገለጹ ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ ካሉበት ችግር የበለጠ ምንም ሊመጣ እንደማይችልና መረጃ ለመስጠትም ምንም እንደማይፈሩ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

መጠለያ ጣቢያው ውስጥ ያሉት ተጎጂዎች በሁለት ክፍሎች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ አንደኛው ውስጥ 66 ሰዎች ሲጠለሉ፣ እነዚህ ሰዎች የሚኖሩበት አንድ ክፍል ሙሉ ለሙሉ በቆርቆሮ የተሠራ በመሆኑ ለብርድና ለዝናብ መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህ ክረምት ልጆቻችን ለጉንፋንና ለሌሎች በሽታዎች ተጋልጠዋል፤›› ብለዋል፡፡

ሐምሌ 8 ቀን በተደረገው ጉብኝት ከዚህ ቀደም ይቀርብ የነበረው ምግብ ከተቋረጠ ሁለት ሳምንታት እንደሞላው፣ በዚህም ሳቢያ እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹እኔ በደሜ ውስጥ የኤችአይቪ ቫይረስ አለ፡፡ መድኃኒት ለመውሰድ የግድ ምግብ ያስፈልገኛል፤›› ሲሉ አንድ እናት ተናግረዋል፡፡ በመጠለያ ጣቢያው ከነበሩት ቤተሰቦች ውስጥ 54 ያህሉ ቂሊንጦ የሚገኘው የ10/90 ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንደሚዛወሩ ቢነገራቸውምና የቤቶቹ ቁልፍ ቢሰጣቸውም፣ አሁንም ድረስ ቤቶቹን ማግኘት እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡

ግንባታቸው የተጠናቀቀው የ10/90 ቤቶች ተጎጂዎች በሚሰጣቸው ገንዘብ የውስጥ ማጠናቀቂያ ሥራቸው ተከናውኖ ይገባሉ ቢባልም፣ ገንዘቡ አሁንም ድረስ ለሁሉም ተጎጂዎች ባለመሰጠቱ ቤቶቹን አስጨርሰው መግባት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ገንዘቡ እንደሚሰጠን ተነግሮን የባንክ ቁጠባ ደብተር የተከፈተልን ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ አብዛኞቻችን ገንዘቡን አላገኘንም፤›› ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው አንድ እናት ከሁለት ሳምንት በፊት ሁለት መንታ ልጆች እንደተገላገሉ፣ ነገር ግን በቂ የምግብ አቅርቦት ስለሌለ እንደተቸገሩ ሪፖርተር ማየት ችሏል፡፡ እኚህ እናት ሕፃናት ልጆች ይዘው አጠገባቸው የሚረዳቸው እንደሌለ፣ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች የመጠለያው ነዋሪ ለሪፖርተር ተናግራለች፡፡

ከተከሰተ አምስት ወራት ያስቆጠረው የቆሼ አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ 592 ያህል ሰዎችን አፈናቅሏል፡፡ በወቅቱም የተለያዩ አካላት ተጎጂዎችን ለመርዳት የተለያዩ የዕርዳታ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በገንዘብ ብቻ 95 ሚሊዮን ብር ያህል የተሰበሰበ ሲሆን፣ በዓይነት ግምታቸው 7.5 ሚሊዮን የሚደርስ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የአልባሳትና የቤት ቁሳቁስ በገቢ ሞዴል ተሰባስበዋል፡፡ እንዲሁም በዓይነት ከተሰበሰቡት 2.03 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የንፅሕና መጠበቂያና የተለያዩ ግብዓቶች ለተጎጂዎች ተሠራጭተው እንደነበር፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሪፖርት ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በተጨማሪ በቆሼና አካባቢው ይኖሩ የነበሩና ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ ነዋሪዎች፣ ንፋስ ስልክና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍላተ ከተሞች ወደሚገኙ የመንግሥት ቤቶች እንዲዛወሩ ተደርገዋል፡፡

 ‹‹አሁን ሰዎች በጣም በተመቻቸ ሁኔታ እንዳለን ያስባሉ፣ ነገር ግን እውነታው ይኼ አይደለም፤›› ሲሉ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚኖሩ ሌላ እናት ተናግረዋል፡፡

      ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ለሪፖርተር ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው፣ ‹‹ነዋሪዎቹ መረጃ በመስጠታቸው ጫና ደርሶብናል ያሉት በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከክፍያ መዘግየት ጋር በተያያዘ ችግሩ እንዳለ አምነው፣ ይህ የሆነው ክፍያ ለመፈጸም ሲሞከር ይገባኛል ባይ በመብዛቱና አንዳንድ ወደ ፍርድ ቤት የሄዱ ጉዳዮች በመኖራቸው መዘግየቱ እንደተከሰተ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የሚቀርበው ምግብ መቋረጡን፣ ይህም የሆነው የተሰበሰበው ዕርዳታ በማለቁ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡

አሁን በጣቢያው ከሚገኙ 26 አባ ወራዎች መካከል ዘጠኝ የሚሆኑት ክፍያ ተፈጽሞላቸው ከመጠለያ ጣቢያው እንዲለቁ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርተር በዳዊት እንደሻው