26 Jul, 2017 

By ዘመኑ ተናኘ

በአዲስ አበባ በቀን ገቢ ግምት ሳቢያ ተዘግተው የነበሩ የንግድ መደብሮች ሥራ ጀመሩ፡፡

ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2009 .. በአዲስ አበባ በተለይም መርካቶ ውስጥ የሚገኙ የንግድ መደብሮች ተዘግተው መዋላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሪፖርተር ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 .. በመርካቶና ሌሎች አካባቢዎች ተዟዙሮ ባደረገው ቅኝት መደብሮቹ ተከፍተው ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ ተዘግተው ከነበሩ የንግድ መደብሮች መካከለ አልፎ አልፎ የተዘጉ እንዳሉም ማየት ተችሏል፡፡

በመርካቶና በአካባቢው በተደረገው ቅኝት ግን ብዙዎቹ የንግድ መደብሮች የተለመደ ሥራቸውን መቀጠላቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ሲካሄድ የነበረው የቀን ገቢ ግምት ተጠናቆ ለነጋዴው ይፋ ሲሆን፣ በተነሳው ተቃውሞ የንግድ ተቋማት እየተዘጉ መሆናቸው ታወቀ፡፡

የምሥራቅ ጎጃም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች የሕዝብ ግንኙነት ሁነት ማደራጃና ማኅበራዊ ክትትል የሥራ ሒደት ዋና አስተባባሪ አቶ ጋሻዬ ጌታሁን እሑድ  ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በቀን  ገቢ ግምት ምክንያት በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በሸበል በረንታ ውስጥ የሚኖሩ ነጋዴዎች ለተከታታይ ሦስት ቀናት የንግድ ተቋማቸውን ዘግተው ነበር፡፡

ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር በተያያዘ በተነሳው ተቃውሞ ነጋዴዎች ሙሉ በሙሉ  ዘግተው መሰንበቻቸውን ጠቁመዋል፡፡

በምሥራቅ ጎዳም ዞን ከ8,000 በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱ እንዲገቡ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ከ30 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ጋሻዬ፣ በዞኑ በሚፈለገው መጠን ግብር እየተሰበሰበ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ኃላፊ አቶ ሽፈራው አየለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ተቃውሞ በዞኑ ወዳሉ ሌሎች ከተሞችም ተስፋፍቷል፡፡ ‹‹ከሸበል በረንታ የጀመረው ተቃውሞ በአሁኑ ወቅት ወደ ሞጣና ቢቸና ተሸጋግሮ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ሙሉ በሙሉ ዘግተዋል፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የዞኑ መንግሥት ምን ዕርምጃ እየወሰደ ነው ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ የተሟላ መረጃ የለኝም፤›› በማለት ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

የክልሉ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መንገሻ ፈንታው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልሉ በዚህ ዓመት 50,494 ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ የግብር ሥርዓት ማስገባት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

አቶ መንገሻ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ከስብሰባ ሲወጡ ለሪፖርተር እንደሚገልጹ ቃል ቢገቡም፣ ከዚያ በኋላ ለሁለት ቀናት ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል የተነተሳው ተቃውሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ መምጣቱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 .. በባህር ዳር ከተማ የተወሰኑ የንግድ መደብሮች ተዘግተው እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘመኑ ተናኘ‘s blog 

anon

መኑ ተናኘ