26 Jul, 2017
By መላኩ ደምሴ

በስማቸው ይጠሩ የነበሩ መታሰቢያዎች ወደ ቀድሞ መጠሪያቸው እንዲመለሱ ተጠየቀ
በአፍሪካ ኅብረት 29ኛው የመሪዎች ጉባዔ ሐውልታቸው እንዲታነፅ የተወሰነላቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ሳይሆን የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) በተመሠረተበት የአፍሪካ አዳራሽ (የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን) ፊት ለፊት እንዲቆምላቸው ጥያቄ ቀረበ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 125ኛ የልደት በዓል እሑድ ሐምሌ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ሲከበር ነው፣ በክብር እንግድነት የተገኙት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጥያቄውን ያቀረቡት፡፡ የእሳቸውን ጥያቄ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ እንግዶች አስተጋብተውታል፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ንጉሠ ነገሥቱ ለአገሪቱ ያደረጉዋቸውን ዋና ዋና የሚባሉ አስተዋጽኦዎች በማውሳት ሐውልታቸው መቆም ያለበት አሁን የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት በሚገኝበት (የቻይና መንግሥት ባስገነባው) ሳይሆን፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተመሠረተበት የአሁኑ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ወይም የቀድሞው የአፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት ክፍት አደባባይ ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ይህንን ጥያቄ ለመንግሥት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር አማካይነት መቅረብ እንዳለበት አሳስበው፣ ውጥኑ ይሳካ ዘንድም አስፈላጊው ነገር መደረግ ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ግርማ እንዳሉት፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲመሠረት በማድረግና የመጀመሪያው ጉባዔውም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ የአፍሪካ አዳራሽ ይባል የነበረውን ሕንፃ አስገንብተዋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 29ኛው የመሪዎች ጉባዔ ሐውልታቸው እንዲገነባ መወሰኑን ያመሠገኑት አቶ ግርማ፣ ሐውልቱ መቆም ያለበት ግን በአሁኑ የኅብረቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መሆን የለበትም ብለዋል፡፡ ከአፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለው ክፍት ሥፍራም የሐውልቱ መቆሚያ እንዲሆን ጥያቄው ለመንግሥት መቅረብ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድም ማኅበሩን በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡ የሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊዎችም በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡

የቀድሞውን ፕሬዚዳንት የሚያጠናክር ሐሳብ ያቀረቡት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሥራ ሚኒስትር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ናቸው፡፡ ራስ መንገሻ በ1951 ዓ.ም. አንድ ቀን አፄ ኃይለ ሥላሴ አስጠርተዋቸው ለሚመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሕንፃ መገንቢያ ቦታ እንዲመርጡ፣ ፕላኑን እንዲያወጡና በጀቱን እንዲያቀርቡ እንዳዘዙዋቸው አስታውሰዋል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት ከባለሙያዎች ጋር ሆነው ጥናታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ቦታ ተመርጦ የሕንፃው ግንባታ በወቅቱ ዋጋ አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ሥራው እንዲጀመር ያዛሉ፡፡

በወቅቱ ሕንፃውን ገንብቶ ለመጨረስ ሦስት ዓመት እንደሚፈጅ፣ ነገር ግን በቶሎ ማለቅ ስላለበት በቀን ስምንት ሰዓት የነበረውን ሥራ 24 ሰዓት በማድረግ በአንድ ዓመት መጨረስ እንደሚቻል መተማመን ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ግንባታው ተጀምሮ ከታሰበው በታች በዘጠኝ ወራት ከአሥር ቀናት ገንብተው ማስረከባቸውን ራስ መንገሻ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጥረትና ድካም የተደረገበት የንጉሠ ነገሥቱ ውጤት ስለሆነ ሐውልታቸው በዚያ ሥፍራ መቆም አለበት ብለዋል፡፡ ከተሳታፊዎችም ከፍተኛ የጭብጨባ ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት እንዲቆምበት የተፈለገው ሥፍራ በደርግ ዘመን የሌኒን ሐውልት የነበረበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ሥፍራ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ ሐውልት እንዲቆም መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ አደራ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

ከሐውልቱ ማቆም ጎን ለጎን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስም የተሰየሙ ነገር ግን በደርግ መንግሥት የተለወጡ ማስታወሻዎች እንዲመለሱ ተጠይቋል፡፡ ነዋሪነታቸው በውጭ አገር የሆኑት የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአገሪቱን ትምህርት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ንጉሠ ነገሥት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) ጨምሮ በስማቸው ይጠሩ የነበሩ ስያሜዎች ወደ ቀድሞ መጠሪያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በተደረገው ውይይት ተሳታፊ የነበሩ እንግዶችም ይህንኑ ጥያቄ አንፀባርቀዋል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ከአልጋ ወራሽነት እስከ ሙሉ እንደራሴነትና ንጉሠ ነገሥትነት ከ58 ዓመታት በላይ አገልግለው፣ ያለምንም መታሰቢያ መቅረታቸው ለመንግሥትም ሆነ ለአሁኑ ትውልድ ዕዳ ነው ተብሏል፡፡ ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት፣ ለትምህርና ለሥነ ጥበብ መስፋፋት፣ ለአስተዳደርና ለፍትሕ መሻሻል፣ ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ጉልህ ሥፍራ እንዲኖራት ያደረጉት አፄ ኃይለ ሥላሴን ያለ ማስታወሻ ማስቀረት አይገባም ሲሉም አስተያየታቸውን የሰጡ አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በደርግ መንግሥት እየተነቀሉ በየሥርቻው የተጣሉ ሐውልቶቻቸው ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው ነው የተባለው፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ካህናት ዓባይነህ አበበ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ስም ህያው አድርጎ መዝለቅ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ላለፉት 22 ዓመታት በስማቸው የተቋቋመው መታሰቢያ ማኅበር በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ፣ በሃያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ችግረኛ ወጣቶች በስኮላርሽፕ እያስተማረ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ እስካሁንም 308 ተማሪዎችን በመቀበል 259 ተማሪዎች በሕክምና፣ በምህንድስና፣ በጤና መኮንነት፣ በነርስነት፣ በሕግና በልዩ ልዩ መስኮች ማስመረቅ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ጥረት ማገዝ ተገቢ ስለሆነ ለማኅበሩ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ዘርፍ ላደረጉት ተግባር የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ የአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት አባት መሆናቸው አፅንኦት ተሰጥቶበት ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ለዚህ ዓላማ እንዳዋሉት ተገልጿል፡፡ ለትምህርት ከነበራቸው ልዩ ትኩረት የተነሳም በአንድ ወቅት ለእሳቸው ሐውልት ለመቅረፅ ገንዘብ ሲሰባሰብ፣ ‹‹ከሐውልት ይልቅ የአዕምሮ ሕንፃ ይበልጣል፤›› በማለት ትምህርትን ማስቀደማቸው ተወስቷል፡፡ የተሰባሰበው ገንዘብም ለትምህርት ቤት ግንባታ እንዲውል ማዘዛቸው ተነግሯል፡፡ ከአባታቸው የወረሱትን የቀድሞ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ለአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መስጠታቸው ተብራርቷል፡፡ የተሰበሰበው ገንዘብም ለትምህርት ግንባታ እንዲውል ማዘዛቸው ተነግሯል፡፡ ከትምህርት በተጨማሪ የኪነ ጥበብ ዘርፍን በማስፋፋት፣ ዘመናዊ አስተዳደርና ሕገ መንግሥት በመዘርጋት፣ ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል በማደራጀትና በማብቃት መሰል  ተግባራት ተወድሰዋል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ጥበብና ሥልጣኔ ከፋች እንደነበሩም ተተንትኗል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1884 ዓ.ም. በቀድሞው ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በኤጀርሳ ጎሮ ነው የተወደሉት፡፡ ከ14 ዓመታቸው ጀምሮ ከአውራጃ አስተዳዳሪነት በጀመሩት የሥልጣን ጉዞ ንጉሠ ነገሥት ሆነው ኢትዮጵያን ለ58 ዓመታት መርተዋል፡፡ በ1966 ዓ.ም. በተካሄደው አብዮት ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ከሥልጣን አውርዶአቸው ከገደላቸው በኋላ መቃብራቸው ሳይታወቅ፣ በኢሕአዴግ ዘመን ነበር ከተቀበሩበት አልባሌ ሥፍራ አፅማቸው ወጥቶ መጀመሪያ በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም፣ ከዚያም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲያርፍ መደረጉ ይታወሳል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር በ1987 ዓ.ም. በመቋቋም በ1991 ዓ.ም. ከፍትሕ ሚኒስቴር ፈቃድ በማግኘት ላለፉት 22 ዓመታት መንቀሳቀሱ ተወስቷል፡፡ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ነገር ግን በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ ተማሪዎችን በስኮላርሽፕ እያስተማረ ማስመረቁንና አሁንም መቀጠሉን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡ ማኅበሩን በቋሚነት የሚደግፉ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦችን ማግኘት ባለመቻሉና በውስን አባላት ድጋፍ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ችግረኛ ተማሪዎችን መርዳት አለመቻሉን አሳውቋል፡፡ ማኅበሩን የሚደግፉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ቁጥር ማነሱን፣ ለጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ደመወዝ የመክፈል አቅም በማነሱ የሥራ ኃላፊዎች መቀያየራቸው፣ የራሱ የሆነ ቢሮ ስለሌለው በኪራይ እያፈላለገ ከቦታ ቦታ መቀያየሩ፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለሕዝብ ራሱን ማስተዋወቅ አለመቻሉ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ንጉሠ ነገሥቱ ለአገር ልማትና ዕድገት ያደረጉትን ፈለግ በመከተል የማኅበሩ አባልና አጋር እንዲሆኑ፣ ትውልዱን በትምህርትና በሥነ ጥበብ ለማነፅ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ማኅበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

SOURCE    –      Home