መንግስቱ ሙሴ

የካሳ/ገዱ አራንባ እና ቆቦ ንግግሮች እና የክህደት ትረካወች

የወልቃይት ጉዳይ በአባይ ወልዱ እና በወያኔ የማይለወጥ ፖሊሲእነቱ

ስብሰባው የወያኔ የጦርነት አዋጅ በሚመስል፣ ደግሞም ነው ስብሰባ የተባለውን ወያኔ አሁንም አዲስ ያልሆነ እና የቆየ ጸረ ኢትዮጵያ በይበልጥም ጸረ አማራ የሆነውን የሦስት ቀናት ቆይታ ዘግተዋል። ገዱም ሆነ ካሳ ስለ አጠቃላይ ሁኔታው ለመዘርዘር ዙሪያ ገቡን ከዞሩ በኋላ በተለይም ካሳ እንዴት ከኢሕአፓ እርሱ እና ጓደኞቹ ዘር እና አጥንት ቆጥረው እንደከዱ እና ከሕወሐት እንደተደባለቁ ታሪካዊ የሆነ አይነተኛ ክህደቱን ለመሸፈን ኢሕአፓ ውስጥ ሊያታግል የሚችል ሁኔታ በማጣት ወደ ሕወሐት ሄደን የጋራ ትግል አደረግን ይላል። የካሳ ተክለብርሀንን ውሸት ማንም ከመናገሩ በፊት እራሱ ጨርሶታል። በኋላም አማራ ያልሆኑት እነ በረከት/አዲሱ/ታደሰ/ተፈራ ዋለዋ/ሕላዊ ዮሴፍ በአንድ ጀንበር በወያኔ የአማራ ታርጋ ተለጥፎላቸው እና በወያኔ ተጠምቀው በአዴን እንደሆኑም ገልጾታል። “የሚያታግል ሁኔታ ኢሕአፓ ውስጥ በማጣታችን” ብሎ ባለበት አንደበቱ “ኢሕአፓ” ኢትዮጵያዊ አጀንዳ የነበረው እና ስለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ዴሞክራሲ በአገሪቱ መስፈን የሚታገል እንደነበር መካድ አልቻለም። ክህደት አደረግን እና እኛ በዘር ልጓም ተስበን ወይንም ጠባብ ብሄርተኛ አስተሳሰብ የነበረን ከእናት ድርጅታችን ከወያኔ ተደባለቅን ማለት ግን ተስኖት ዙሪያጥምጥም ቢጓዝም እራሱን ገላጭ በሆነ መልክ ብዙ ስድብ እና ውግዘት በትግሉ ግዜ ደረሰብን ብሎም ያለቅሳል።

ከበለሳ የተነሱት የነ በረከት/ታደሰ/ታምራት ከሀዲ ቡድን ግን የብዙ ታጋይ ኢትዮጵያውያንን ደም አፍሠው እና በትግል የተገኙ ትጥቆችን እና ገንዘብ ተሸክመው ቁጥራቸውን ከፍ አርገው እና ብዙ የተወናበዱ ጨምረው ትግራይ እንደገቡ ግን አልገለጠውም። በወያኔ እና በኢሕአፓ መካከል ግጭት ነበር በሚል አቅልሎት ያለፈው አነጋገር ውሾቹ እና ከሀዲወቹ የነ በረከት/ካሳ/ሕላዊ/ታደሰወች ቡድን የወያኔ የውስጥ ሰላይ፣ በመሆን ብዙ ወራት ያስቆጠረ ተግባር መፈጸማቸውን፣ ለብዙ የያን ግዜ ኢትዮጵያዊ ታጋይ ወጣቶች በሕወሐት እና በሻብያ መሰዋት በውስጥ አርበኝነት ማገልገላቸውን በቀጥታም ባይሆን በዙሪያው ገልጾታል።

አባይ ወልዱ የተዘፈነለትን ስብሰባ። እዚህ በማህበራዊ ሚዲያ ገዱን ሰማይ ሊያስነኩ የሞከረለቱን የመቀሌ ቆይታ በቂጡ አስቀምጦታል። እንዲህም አለ የማንነት ጥያቄ የሕዝብ ጥያቄ ሳይሆን የጠላቶቻችን ነው። ጠላቶቻችን ተጠቀሙበት። ለመጠቀም ያበቃቸው ዋነኛ ጉዳይ እንደ አባይ ወልዱ አባባል በሁለቱ ድርጅቶች አመራር ክፍተት መፈጠሩ ነበር አለን። እንደገባኝ እና እንደምረዳው መጀመሪያ በሕወሐት መካከል መለያየት መኖሩን አናውቅም ነበር። ከሆነ አሁን ቆሟል ማለት ነው? የዚህ ስብሰባ አላማም ይህን ክፍተት ለማጥበብ፣ በትግራውያን ላይ ወደፊትም ሊደርስ የሚችል ማነኛውንም ችግር ከወዲሁ እንዳይከሰት ለማድረግ ሕዝብን የሚያማልል የወያኔ ድራማ ወይንም ማስፈራራት፣ አለያም ለማስጠንቀቂያ የተላለፈበት ለመሆኑ የመቋጫ የአባይ ወልዱ ንግግር ፍርጥም ባለ መልኩ አሳይቶናል። አባይ ወልዱ ወልቃይት ትግራይ ናት። የወልቃይት ጉዳይ በፌደራሉም፣ በኢሕአዴጉም፣ መልስ ያገኘ ስለሆነ ማንም የሚያገባው የለም ብሎታል። ይህን የሕወሐት የፖሊቲካ ቢሮ ሰብሳቢውን አባባል የነቀፈም፣ የተቃወመም ወይንም በተለየ ሀሳብ ያቀረበም የበአዴን ባንዳ የለም/አልነበረም። የአባይ ወልዱ የወልቃይት ጥያቄ ብሎ ነገር የለም ያለውን ካድሬወች በሞቀ ጭብጨባ ሲዘጉት ግን አየን ሰማን። ስብሰባው ሌላ ቀርቶ ግብረገብነት እንኳን የጎደለው እንደነበረ ተስተውሏል። እኔ እንደተረዳሁት እና የስብሰባውን መንፈስ እንዳስተዋልሁት እነ ገዱ ተጽፎ የተሰጣቸውን ያነበቡበት። እንደፈረደባቸው የወያኔን የገዳይ ቡድን ሀውልት አበባ ጉንጉን ያስቀመጡበት ድራማ ነበር። ወያኔ ደግሞ የጦርነት አዋጅ በሚመስል ማንገራገር እና መፎከር ብጤ ያሳየችበት ለመሆኑ የአባይ ወልዱን አነጋገር በጥሞና ላደመጠ የሚረዳው ጉዳይ ነው።

የእንቶፈንቶው ካሳ ተክለብርሀን አነጋገር ግን የሚገርም እና በጣም ውሸት ከአድርባይነት የተቀላቀለበት እንደነበር ማየት ችያለሁ። ኢሕአሠን የኢሕአፓን ሰራዊት ሦስቱ ኃይሎች ወያኔ/ሻብያ/ሱዳን መጀመሪያ ጎንደር በኋላም ጎጃም ላይ በተባበረ ሀይል መጨፍጨፋቸው ግልጽ ነው። በኢሕአፓ በኩል ደግሞ ልክ ቴወድሮስ እንዳደረጉት ምንም እንኳን በውጭ ሐይሎች የተቀነባበረ ጸረ ኢትዮጵያ ጦርነት እና ግዙፍ ቢሆንም የኢሓፓ መሪወች እስከ ሰራዊቱ ፊት ለፊት ገጥመው ወደቁ እንጅ ሽሽት ወይንም አገር ክህደት አለማድረጋቸው ታሪክ ዛሬ ብትደበዝዝ ወደፊት ጉልህ ቦታ እንደምትሰጠው ግልጽ ነው። እናም ካሳ ተክለብርሀን የተባለ የወያኔ አባል። ኢሕአፓ ውስጥ የሚያታግል ሁኔታ በማጣታችን ያለው ገና ትግሉ በተጀመረ በሦስት አመቱ የበለሳ ወይንም በግዜው ሦስተኛው ሪጅናል ሰራዊት በኢሕአፓ ተብሎ ከሚጠራው ከባቢ ከድተው እና ሰራዊቱን በሀሰት እና ወያኔያዊ ውዥንብር በትነው ነበር ወደ ትግራይ የተጓዙት። መልሰው ከ14 አመታት በኋላ ጎንደር እና ጎጃም ወያኔን መሪ እና ሹንባሽ በመሆን የኢሕአፓን ሰራዊት አብረው ጨፍጭፈው አስጨፍጭፈው እንዳለፉ ግልጽ ነበር።

ለመጭው ተብሎ ወደጎንደር የተቀጠረለቱ ይህ ስብሰባ ለመገምገምም የማይመች፣ ምንም አዲስ ነገር ያላየንበት፣ የእጅ ነሽወች መልመጥመጥን የወያኔን የጦር ሰበቃን ያሳየን ሆኖ ተዘግቷል። ከእባብ እንቁላል እርግብ አይጠበቅም። የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ አማራው ቆርጦ ተነስቷል እንጅ ከጠላቱ አንዳችም የሚጠብቀው እና ለ26 አመታት ካየው የተለየ እንደማይኖር ግጥም አርጎ ያውቀዋል። ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ በኩልም የተለየ ቀርቶ የተለሳለሰ አንዳች እንደሌለ አሳይቶናል። ትግሉ ደግሞ በአለው ፍመት እና ግለት እየቀጠለ ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!