July 28, 2017 –

 ቆንጅት ስጦታው 

ኦነግን በመቀላቀል ስልጠና ለመውሰድ አስበው ነበር የተባሉ ወጣቶች ተከሰሱ

ከተከሳሾቹ መካከል የ16 አመት ታዳጊ ይገኝበታል

(በጌታቸው ሺፈራው)

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኦነግን በመቀላቀል ወታደራዊና ፖሊቲካዊ ስልጠና ሊወስዱ አስበው ነበር በሚል በ5 ወጣቶች ላይ የሽብር ክስ መስርቷል፡፡ አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ ‹‹በውጭና በሀገር ውስጥ በሚገኙ የኦነግ አባላት እና አመራሮች ጋር በስልክ፣ በኢሜል ግንኙነት በማድረግ ተልዕኮ በመቀበል፣ ለኦነግ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት›› ሲንቀሳቀሱ ነበር ሲል ክስ የመሰረተ ሲሆን በውጭ ሀገር በተለይም ኬንያ ሆነው ከተከሳሾቹ ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር ያላቸውን አመራሮች፣ አመራሮቹ ከተከሳሾች ጋር ይገናኙበት ነበር ያለውን ስልክ፣ እንዲሁም ተከሳሾቹ በክሱ ላይ ፈፀሙት ያለውን ተግባር ተከናወነበት የተባለውን ቀን በክሱ ላይ ሳይጠቅስ ቀኑ በውል ተለይቶ ባልታወቀ፣ ስሙ ያልታወቀ፣ ስልክ ቁጥሩ ያልታወቀ እና አልፎ አልፎ ስማቸውን የጠቀሳቸውን ግለሰቦችም የአባቱ ስም ያልታወቀ በሚል አስፍሯል፡፡
በዚህ ክስ መዝገብ የተከሰሱት 1ኛ ፍሮምሳ ቤኩማ፣ 2ኛ ሀጫሉ ሰርቤሳ፣ 3ኛ ዮሴፍ ገመቹ፣ 4ኛ ጌቱ ተስፋ እና 5ኛ ኤባ ቀነዓ ሲሆኑ ተከሳሾቹ ከ16-23 ባለው የእድሜ ጣሪያ ያሉ ናቸው፡፡ 2ኛ ተከሳሽ እና 5ኛ ተከሳሽ ‹‹ኬንያ ሄደው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና ለመውሰድ ከአዲስ አበባ በመነሳት አቃቂን በማለፍ ቱሉ ዲምቱ ላይ በቁጥጥር ስር ውለዋል›› በሚል በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡


ከተከሳቹ መካከል 3ኛ ተከሳሽ ዮሴፍ ገመቹ 16 አመቱ እንደሆነ በክሱ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን አዋቂዎች በሚመረመሩበት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተመርምሮ ክስ ከተመሰረተበት በኋላ በአሁኑ ወቅት አዋቂዎች በሚታሰሩበት ቂሊንጦ እስር ቤት ታስሮ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ ጅብሪል አህመድ ኡስማን የተባለ የ16 አመት ታዳጊ ‹‹ለአራት ወር ያህል የቡድኑን ፖለቲካዊና የጅሃድ ትምህርት፣ የአካል ብቃት ትምህርት፣ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም እና የቦንብ አወራወር ስልጠና ወስዷል›› በሚል በኦብነግ አባልነት የሽብር ክስ እንደቀረበበት ይታወሳል፡፡

ኦነግን በመቀላቀል ስልጠና ለመውሰድ አስበው ነበር የተባሉ ወጣቶች ተከሰሱ
ከተከሳሾቹ መካከል የ16 አመት ታዳጊ ይገኝበታል