(በጌታቸው ሺፈራው)

የወልቃይታ አማራ ማንነት ጥያቄ ያነሱ 12 ግለሰቦች ‹‹የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄን እንደሽፋን ተጠቅመው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 32 (1) ሀ/ለ፣ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3/(1፣2፣4) ስር የተደነገገውን ተላልፈው አርበኞች ግንቦት ሰባት አባል በመሆን በመደራጀትና የጦር መሳሪያ በመታጠቅ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የአካባቢው ነዋሪ ላይ ከባድ ስጋት ፈጥረዋል›› በሚል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ ከጎቤ መልኬና ከኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጋር በመገናኘት ወልቃይት ውስጥ የሚገኙትን የመንግስት ደጋፊዎችና የትግራይ ተወላጆችን የሰፈራ ቦታ በመለየት ጥቃት ለመፈፀም ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ በተለይ ከኮሌኔል ደመቀ ዘውዱ ጋር በመገናኘት የወልቃይት አማራ የማንነት ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው መንግስትን በትጥቅ ትግል ሲያስወግዱ እንደሆነ እና የወልቃይት ኮሚቴ አባላት እየታሰሩ በመሆኑ የመንግስት ደጋፊዎች ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ተልዕኮ ወስደዋል በሚል ተከሰዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአርማጭሆና ወልቃይት ከሚገኙ የግንቦት ሰባት ታጣቂዎች፣ እንዲሁም በክሱ የግንቦት 7 አመራር ነበር ከተባለው ጎቤ መልኬ ከሚመራቸው 80 ያህል ታጣዊዎች ጋር ጫካ በመግባት፣ ወልቃይት ውስጥ ከነበረ የመንግስት ጦር ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የትግራይ ተወላጆችና ባለሀብቶች የሰፈራ መኖሪያ ካምፖች ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል ተከሰዋል፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ወልቃይት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆኑ መኖሪያቸው ሰ/ጎንደር ጠገዴ ወረዳ የሆኑ ሁለት ተከሳሾች ‹‹እኛንም የወልቃይት ጥያቄ ይመለከተናል›› ብለው አብረው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጠበቃ የደንበኛቸው ጉዳይ በሌላ ፍርድ ቤት እየታየ ባለበት ሁኔታ በዚህ ክስ ‹‹የሽብር ቡድን አመራር›› ተብለው መጠቀሳቸው የኮሎኔሉን በህግ ፊት ንፁህ ሆኖ የመታየት መብት የነፈገ መሆኑን በመግለፅ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ በሌሎች ክሶች ላይም ኮሎኔሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የተጠቀሱ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ አቤቱታቸውን በክስ መቃወሚያ ማቅረብ እንደሚችሉ አሳውቋል፡፡ በዚህ የክስ መዘገብ የተከሰሱት፡-

1. ጎይትኦም ርስቀይ ሙሉ
2. ደርሶ ተስፋሁን አሰፋ
3. አዱኛ ድምቃ ገ/እግዚያብሄር
4. ሀጎስ በላይ ፈረደ
5. መከተ መብራህቱ ደምለው
6. ግደይ አሰፋ አብርሃ
7. መብራቱ ደምለው በየነ
8. ማሙዬ አርኮ ብርሀኔ
9. አስቻለው አብርሃ ሰዓሉ

10. ብርሃኑ ፈረደ ሀደራ
11. መላኩ ረዳ እና
12. ላቀው ብርሃኑ ናቸው፡፡