August 2, 2017 

በዘንድሮው የሰሜን አሜሪካ እና የአውሮፓ ስፖርት እና ባህል ፌስቲቫሎች ላይ የቦይኮት (እቀባዘመቻዎች ተነስተው ነበር። የዘማቻዎቹን ውጤቶችም  አይተናቸዋል። በዚች አጭር ጽሁፌ የማተኩረው በውጤቶቹ ላይ አይደለም።  በሲያትሉም ሆነ በሮም ዝግጅቶች ላይ ስለነበርኩ፣   የቦይኮት ዘመቻዎቹ ከጅምሩ ጥቅም እና ጉዳቶችን አመዛዝነው ነበር ወይ የሚለውን በጥቂቱ ለመፈተሽ እሞክራለሁ። በዚህ ርዕስ ላይ ስጽፍ  አዋራ እንደሚነሳ አምናለሁ።  በጉዳዩ ላይ እጅግ ብዙ ሰዎች ሲወያዩ ብታዘብም በፍርሃት ይሁን በሌላ ምክንያት ሃሳባቸውን በአደባባይ ለመናገር ግን ሲደፍሩ አይታይም።    ሃሳባቸውን በድፍረት የሚሰነዝሩ ወገኖችም  ቦይኮት ስለሚደረጉው ብዙዎች ዝምታን ቢመርጡ አይደንቅም።  “አህያ የለኝ ከጅበ አልጣላ” ብሎ ሃሳቡን በነጻ ለመግለጽ የሚሞክር ደግሞ ይሰደባል።    በሳይበሩ አለም፣  ወቅትን እየጠበቀች  በምትነደው እሳት ላይ ማን ቤንዚን እንደሚጨምርበት አሁን ግልጽ ሆኗል። አንዳንዶቹን የቦይኮት ዘመቻዎች ማን እንደሚጠራው እንኳን አይታወቅም። ምክንያቱም ሃላፊነቱን የሚወስድ አካል ስም እና አድራሻ የላቸውም። አንድ ሾልኮ የወጣ መረጃ  የሚጠቁመን  ገዥው ፓርቲ ሰባት ሺ የሳይበር ላይ አጥቂዎችን የወር ደሞዝ እየከፈለ አሰማርቷል። …

ምስል – ፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ at Kingstowne Starbucks @kinfu

በቨርጂንያ ግዛት በምትገኝ፣ ኪንግስታውን ስታርባክስ በራፍ ላይ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ  ሲጋራውን እንደ ሲኖትራክ ጭስ እያቦነነ ተቀምጧል። የወቅቱ ሙቀት በጭስና በአልኮል ደከምከም ያለ ሰውነቱ ላይ ተጨምሮበት የሉሲን አጽም አስመስሎታል። ከሁለት ባለግዜዎች ጋር ጠቀምጦ ህወሃትኛ ወጉን በነጻነት ይሰልቃል – የሞት ሞቱን።  ከዚያ አለፍ ብሎ ያለው ሞል ውስጥም ሆነ ስቶር ገባን። እዚያ  የምናገኛቸው ሸማቾች ደግሞ (በሙሉ ማለት ይቻላል) ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ናቸው።  “የባለስልጣናቱ  ዘመድ አዝማዶች ” መሆናቸው ተነገረን።

በባንክ ብድር ሳይሆን ካሽ በማውጣት ዘመናዊ ቪላ ቤቶች የመግዛት አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያውያን ሚሊየነሮች።  የአካባቢው ነዋሪ እንደነገረን ከሆነ እነዚህ  ምንጩ ያልታወቀ ሚሊየነሮች ያንን መንደር ሁለት አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ነው ገዝተው የሰፈሩበት። በአሁኑ ሰዓት በዲሲ፣ በቨርጂንያ እና በሜሪላንድ ግዛቶች የመኖርያም ሆነ የንግድ ቤት አከራዮቹ እነሱው ሆነዋል። ልብ በሉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪ በአምስት ዓመታት ግዜ ዉስጥ ብቻ  ከኢትዮጵያ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ 10 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወደ ዉጭ እንዲወጣ ነግረውናል።… ይህን ጉዳይ ለግዜው በዚህ ልተወውና ወደ ቦይኮቱ ልሂድ።…

ይህንን ሰው (እንድርያስን) የዲሲው ግብረሃይል አለየውም እንዴ?” ሲል አብሮኝ ከነበሩት አንዱ ጠየቀ። የስርዓቱ ቀንደኛ አማካሪ በቨርጂንያ ግዛት ውስጥ በግላጭ ተገኝቶ በዋዛ እንደማይታለፍ ሁሉም የሚያውቀው ነው። እንድርያስ እሼቴ እንዲህ በግላጭ እና በነጻነት ያለምንም ተቃውሞ ተቀምጦ በመገኘቱ እድለኛ ነው።

ግብረሃይሉ  በ”ቦይኮቱ” ጉዳይ ላይ ተጠምዷል። በእርግጥም የኳሱ “ቦይኮት” ነገር ሁሉንም ወገኖች ያግባባ አልመሰለም። ምክንያቱም ፍትሃዊነቱ፣ አድሏዊነቱ እና የፖለካ ጠቀሜታው በአግባቡ መፈተሹ አከራካሪ ስለሆነ ይመስለኛል። ይቅርታ የሚጠይቁ አርቲስቶች አሉ፣ ይቅርታ የማይጠይቁ አርቲስቶችም አሉ፣  ይቅርታ ቢጠይቁም ተቀባይነት የማይኖራቸው አሉ… ።  የዚህን ጉዳይ ቅድመሁኔታ እና መስፈርቱ እንዴት እና በማን እንደሚወጣ ግልጽ አይደለም። አልያም ሁሉንም የሚያግባባ አይደለም።  ቦይኮት (ማዕቀብ) የሰላማዊ ትግል  አንደኛው መንገድ ነው። ሁሉም ተሳታፊ ሲስማማበት፣ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ሲያመዝን እና ወቅቱን የጠበቀ ሲሆን ደግሞ በተግባር ሲተረጎም ውጤታማ ይሆናል።  ማን በምን መስፈርት ቦይኮት እንደሚደረግ ሕብረተሰቡ ተስማምቶ ሲፈቅድ እንጂ አንድ ቡድን በግል ጉዳይም ይሁን በቅናት ተነሳስቶ  ሲሰራው ችግሩ እዚያ ላይ ይሆናል። በአመክንዮ እንጂ  ከጥላቻ ለመሆኑ መስፈርቱ የሁሉምም ይሁንታ ሲያገኝ ይመስለኛል። ሃመልማል አባተ ይቅርታ ብላ ትቀላቀል ዘንድ፣ ፋሲል ደሞዝ ከራዳሩ ውጭ ይሆን ዘንድ፣ የአስቴር አወቀ ጉዳይ በዝግ ችሎት ይታይ ዘንድ… ከመድረክ ጀርባ ያሉ ጀብዱዎችን ታዝበናል።

Artist Gossaye Tesfaye

ጎሳዬ ተስፋዬ በስፖርት ፌዴሬሽኑ ለስራ ተጋብዞ የመጣ ድምጻዊ ነው። ጉዞው ግን ቀላል አልነበረም። አያሌ ውጣ ውረዶችን አልፎ ስራውን ለወገኑ ሊያሳይ ብቅ ሲል እመንገዱ ላይ የኬላ ፍተሻ ገጠመው። እዚያው ላይ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠው – አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለፈጸመው በደል ይቅርታ እንዲጠይቅ። ጎሳዬ ይህችን ትንሽ የ”እለት ጸሎት” አይነት ነገር ለማድረግ ምን ገዶት።  በመጀመርያ ለ”ይቅርታው” ሙሉ ፈቃዱን ገልጾ ነበር።  ከጥቂት ግዚያት በኋላ ያማከራቸው ወገኖቹ በጉዳዩ ሳይስማሙ ቀሩ።… አርቲስቱ  ሁለት አማራጭ ነበረው። ይህን አድርጎ ከአውሬዎች ጥርስ ውስጥ መግባት፣  ወይንም ደግሞ ይህንን ሳያደርግ የሚያገኘው ጥቅም መቅረት። ምርጫው ላይ ብዙም አላንገራገረም።   በመሪር ሃዘን ሁለተኛውን አማራጭ በመውሰድ አድናቂዎቹ ጋር ላለመገናኘት ወሰነ። እርግጥ ነው።   ይህ ድምጻዊ ወያኔ አይደለም። የስርዓቱ ደጋፊም አይደለም። ሙያውን ተገን በማድረግ  የዳሽን ቢራ ማስታወቂያ በሰሩ ሰዎች ሰለባ ግን መሆኑ አይካድም። “የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ” በሚል ለሕዝብ የላከው ደብዳቤ አንጀት ይበላል።  የገዛ ወገኖቹ በዚህ ሁኔታ ስራውን እንዳይሰራ ሲያደርጉት በጭንቅላቱ ምን ሊመላለስ እንደሚችል ለመገመት አያስቸግርም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎቹስ ስሜትም ግምት ውስጥ አልገባም።  እንዲህ እያልን…የሃገር ቅርስ የምንላቸውን፣ በሚሊዮን ሕዝብ ልብ ውስጥ ያሉ ወገኖችን እየገፋን ለወያኔ ጉልበት መሆናችንን የተገነዘብነው አይመስለንም።

ቦይኮቱን የሚጠሩት ወገኖች ከሃገርፍቅር ስሜት ወይንም በአገዛዙ የበደል  ስራ ላይ ካላቸው  የተነከረ አቋም የተነሳ መሆኑ ግልጽ ነው። ሕዝቡም ቢሆን በህወሃት የግፍ አገዛዝ ላይ ብሶት አለበት። ይህንን ብሶት ያንገፈገፈውን ህዝብ በስሜት በማንሳት ለተግባር (ሞብ) መጥራት እጅግ ቀላል ይሁን እንጂ  ሁሌ ጠቃሚ አይሆንም። ሞብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝንበት ግዜ ይኖራል። ለዚህ ነው የማህባራዊ ሳይንስ ጠበብቶች  የህዝብ ስሜት ብቻውን ሲሆን አደጋ እንዳለው የሚነግሩን።  ስሜት ከአመክንዮ ጋር ሲሆን ብቻ ነው ውጠታማ የሚሆነው።