August 2, 2017 – ስፖርት

ስፖርት፤ ሐምሌ 24 ቀን፣ 2009 ..

ማንተጋፍቶት ስለሺ(DW) ከእግር ኳስ ግጥሚያ እስከ የምሽት ዳንኪራ፤ ከባሕላዊ ምግቦችና አልባሳት እስከ ሺሻና ጫት ንግድ ባለፈው ረቡዕ ተጀምሮ ቅዳሜ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ተስተውሏል።

15ኛው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ከረቡዕ ሐምሌ 19 ቀን 2009 ዓም አንስቶ እስከ ቅዳሜ ድረስ በጣሊያን መዲና ሮም ተከናውኗል። በዝግጅቱ የሕጻናት፣ የታዳጊዎች እና የአዋቂዎች እግር ኳስ በአጠቃላይ ከ50 በላይ ቡድኖች እንደተሳተፉ ፌዴሬሽኑ ገልጧል። በአንደኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ግጥሚያ እንደ ዓምናው ሁሉ ዘንድሮም ዋንጫውን የወሰደው የኢትዮo ኖርዌይ ቡድን ነው። ከእግር ኳስ ግጥሚያ እስከ የምሽት ዳንኪራ፤ ከባሕላዊ ምግቦችና አልባሳት እስከ ሺሻና ጫት ንግድ በቦታው ተገኝተን የታዘብነው ነው።

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ፌስቲቫል ከተከናወነበት የዴን ሀጉ ስታዲየም አነስ ባለ ስታዲየም ውስጥ ነበር የተከናወነው የዘንድሮው ፌስቲቫል። በሥፍራው ከተገኘንበት ከዓርብ ከሰአት ጀምሮ ፌስቲቫሉ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ስታዲየሙ ውስጥ በርካታ ታዳሚያን ተገኝተዋል። በየቀኑ ከ2 ሺህ በላይ ሰው በስታዲየሙ መታደሙም ተገልጧል። ከታዳሚያኑ መካከል በተርታ ከተዘረጉት ዳሶች ከአንደኛው አጠገብ ሁለት ወጣቶች አረፍ ብለው እየተመገቡ ነው። «ሁሉም ሰው የተለየ ዓላማ የለውም። የምንመጣው ለመገናኘት፣ ለመጫወት ለመዝናናት እስከሆነ ድረስ ሁሉም ይመጣና በአንድ ፍቅር ባ,ንድነት ኹነን አንድነታችንን የምንገልጥበት ስለሆነ ያ ቢሆን እኛ ደስ ይለናል» ብሏል የለንደኑ ነዋሪ ቢንያም። የረዥም ጊዜ ወዳጁና ጣሊያን ሮም ነዋሪ የኾነው ማስረሻ በበኩሉ በጓደኛው ሐሳብ የሚስማማ መኾኑን በመግለጥ «ሁሉም ሰው የሚመጣው ለመዝናናት ነው፤ ሁሉም አንድ የኾነ ዓላማ ይዞ ነው የሚጣው። ይመስለናል» ሲል አክሏል።

ሜዳው ውስጥ እግር ኳስ ጨዋታ እየተኪያሄደ ከመግቢያው አንስቶ ግራና ቀኝ በተጣሉ ዳሶች ውስጥ የባሕላዊ ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም አልባሳት ሲሸጡ ነበር። ከዳሶቹ ጀርባ ደግሞ ሺሻ የሚያጨሱና ጫት የሚቅሙ ወጣቶች ተኮልኩለው ይታያሉ። እነሱን አልፌ ምግብና አልባሳት ወደሚሸጡት ዳሶች አቀናሁ። ሮም ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የኖሩ ጠየም ያሉ እናት ከፊት ለፊቴ ይታዩኛል። ፈገግታና ተጫዋችነታቸው ይበልጥ ሳበኝ። ወ/ሮ አስናቀች ሥዩም ይባላሉ። ነዋሪነታቸው መዲናዪቱ ሮም ውስጥ ነው። «የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርዓት ያለው ነው፤  ጫጫታ የለ፤ ኹካታ የለ መደሰት ብቻ ነው» ብለዋል። በተርታ ከተጣሉት ዳሶች በአንደኛው ምግብ ከሚሸጡ ባልደረቦቻቸው ጋር ኾነው ነው ያነጋገርናቸው። ያቀረቡት ምግብ በሙሉ ተሽጦ ማለቁንም ሲገልጡ በደስታ ተውጠው ነው። ዳሱ ውስጥ አብረዋቸው ምግብ ሲሸጡ የነበሩት ወ/ሮ ሙሉ ደግሞ ከዛሬ አምስት ዓመት ጋር ሲነፃጸር የዘንድሮውታዳሚ ማነሱን ተናግረዋል። «ጥቂት ሰው ያns, ይመስለኛል፤ በዓሉ ግን ቆንጆ ነበረ» ብለዋል።

15ኛው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ላይ በአንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን  31 የእግር ኳስ ቡድኖች ተካፋይ እንደሆኑ ተገልጧል። ከአደኛ ዲቪዝዮን ኢትዮ ኖርዌይ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም በተጋባዥነት የተገኘው የኢትዮ አበበ ቢቂላ ቡድንን 2 0 አሸንፎ ዋንጫውን ዳግም ወስዷል። የዘንድሮው ዋንጫ የተሰየመው በጀግናው አበበ ቢቂላ ስም ነው።

በሜዳው ኢትዮ ኖርዌይ ፈዘዝ ያለ ሰማያዊ መለያ እና ገምባሌ እንዲሁም ደማቅ ሰማያዊ ቁምጣ ለብሶ ታይቷል።  ኢትዮ አበበ ቢቂላ በበኩሉ ከላይ ቀይ መለያ ሲያደርግ ቢጫ ቁምጣ ከቀይ ገምባሌ ጋር አክሎበታል። የኢትዮ አበበ ቢቂላ ተጨዋቾች ወደ ሜዳ የገቡት መለያቸው ላይ ከጀርባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከፊት የዳሸን ባንክ ምስሎችን አድርገው ነበር።

በፌስቲቫሉ በህጻናት እና በታዳጊ ዘርፍ እያንዳንዳቸው 10 ቡድኖች ተካፋይ ነበሩ። የዘንድሮ የታዳጊዎች አሸናፊ የሆነው የኢትዮ ዙሪክ ቡድን ሲሆን ኢትዮ ሆላንድን የረታው 2-0 ነው።

ለአራት ተከታታይ ቀናት የዘለቀው የባሕልና የስፖርት ፌስቲቫል የተጠናቀቀው በሙዚቃ ድግስ ነበር። ወበቅ በተቀላቀለበት የሮም ምሽት የሙዚቃ ድግሱ የተከናወነው ከቤት ውጪ ገላጣ በሆነ ሥፍራ ነበር። የዘንድሮ የአዋቂዎች የእግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊ የሆነው የኢትዮ ኖርዌይ ቡድን አሰልጣኝ አሳዬ ጥላሁንን እዛው የሙዚቃ ድግስ የተከናወነበት ቦታ ላይ አግኝቼ አነጋግሬዋለሁ። ደስታውን ሲገልጥ «እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ደስ ይላል፤ ከቡድናችን አንጻር ውጤቱን የጠበቅኹት ነበር ያለው አሰልጣኝ አሳዬ ቡድኑን ለአራት ዓመታት በተከታታይ ለፍጻሜ አድርሶ ሁለት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መኾን ችሏል።

አሰልጣኝ አሳዬ ኖርዌው ውስጥ የተማረው ስፖርት ሲሆን ከ21 ዓመት በታች ተጨዋቾች የሚገኙበት ቡድን ይዞም በማሰልጠን ላይ ይገኛል። በስፖርቱ ዘርፍ ከሚያደርገው የማማከር ሥራ በተጨማሪ ኢትዮ ኖርዌይ ቡድንንም በማሰልጠን ላለፉት አራት ዓመታት ለፍጻሜ አድርሷል።

በፌስቲቫሉ ማሳረጊያ ምሽት አርቲስት ጸሐዬ ዮሐንስ እንዲሁም ላፎንቴኖች ማለትም ታደለ ሮባ እና ብርሃኑ ተዘራ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚዎች አቅርበዋል። ዓርብ እለት አርቲስት ሸዋንዳኝ ኃይሉና ልጅ ሚካኤል ታዳሚውን በሙዚቃ አዝናንተዋል። የቅዳሜው ሙዚቃ ድግስ ከሌሊቱ ሰባት ሰአት ጀምሮ የተጠናቀቀው እሁድ ማለዳ ላይ ነበር። በዚህም የዘንድሮው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ፍጻሜ አግኝቷል።

Audio Player
http://www.dw.com/am/a-39912412

 ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

ESCFE festival Rome- Italy, 2017 picture @kinfu

ESCFE festival Rome- Italy, 2017 picture @kinfu

ESCFE festival Rome- Italy, 2017 picture @kinfu