7737 ተከሰዋል፤ በ3 ክልሎች 709 ሸማቂዎችንና የታጠቁ ሀይሎች ተይዘዋል፣ 97 አዳዲስ በድምሩ 303  የፍተሻ ኬላዎች አሉ 

ሰሞኑን የአስቸኳይ አዋጁ ጊዜ መጠናቀቅ ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም መሰረታዊ የሚባሉት የመሰብሰብ፣ የመቃወም፣ ሰላማዊ ሰለፍ የማድረግ፣ የመሳሰሉት መብቶች ቀደም ሲልም ግድብና በመመሪያ የታጠሩ በመሆናቸው ብዙም ለውጥ እንደማያመጣ አስተያየት የሰጡ፣  ውሳኔውን ከተለያየ ጫና የመነጨ አድርገው የሚመለከቱ፣ በተቃራኒው የአዋጁ መነሳት ከአዋጁ በፊት የተፈቀዱ መሰረታዊ መብቶች ስላልነበሩ የአዋጁ መነሳት ምንም ይዞት የሚመጣው ነገር የለም። አሁንም ቢሆን ኮማንድ ፖስቱ ስራውን ይሰራል። ለውጭው ዓለም ፍጆታ ይውላል። የሚሉ በአንድ ወገን ያሉት ናቸው።

በሌላ ወገን መንግስትን ጨምሮ አስችኳይ ጊዜ አዋጁ አገሪቱን ከመፈራረስ መታደጉን፣ ዜጎች በሰላም ውጥተው መግባት እንዲችሉ ማድረጉን፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማስቻሉን፣ የተስተጓጎሉ አካሄዶችና ልምዶች እንዲቃኑ ማድረጉን በመጠቆም የአዋጁን ጠቃሚነት ያጎላሉ። አያይዘውም የአዋጁ መነሳት ለውጪው ማህበረሰብና ለጋሽ አገሮች፣ ብሎም ለቱሪስቶችና ጎብኚዎች ብስራት መሆኑን ያመላክታሉ። በአገር ውስጥም ቀላል የማይባል የስነ ልቦና ሃይል እንደሚሰጥ ያሰምሩበታል። የፋና ዘገባ እንደሚከተለው ይነበባል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ከመስከረም 28 2009 ጀምሮ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አነሳ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብሄራዊ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ ለምክር ቤቱ የአዋጁን የ10 ወራት አፈፃጸም አቅርበዋል።

በዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ለማስቆም በየደረጃው ካሉ የመስተዳደር አካላት እና ከህዝቡ ጋር በመሆን በሰራው ስራ ተፈጥሮ የነበረውን ሁኔታ መቀልበስ ተችሏል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

አዋጁ እንዲታወጅ መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ መደረጉን የጠቆሙት አቶ ሲራጅ፥ በአንዳንድ አካባቢዎች የቀሩ አነስተኛ ስራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር እንደሚቻል መረጋገጡን አንስተዋል። ኮማንድ ፖስቱ ቀሪ ስራዎችን በየአካባቢው ያለው የፀጥታ ሀይልና ህዝብ ጋር እንደሚሰራም ነው የገለጹት።

በሁከትና ብጥብጡ የተሳተፉ አካላት እንደፈፀሙት የወንጀል ሁኔታ በህግ እንዲጠየቁ አልያም የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ወደ ህዝቡ እንዲቀላቀሱ መደረጉንም አመላክተዋል። በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልሎች እና አዲስ አበባ በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 21 ሺህ 109 ዜጎች ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው በሁለት ዙር በሶስቱም ክልሎች በተዘጋጁ የማሰልጠኛ ማዕከላት ስልጠና መውሰዳቸውን ነው አቶ ሲራጅ የጠቆሙት።

በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈው ወንጀል ስለመፈፀማቸው በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጦባቸው በኦሮሚያ ክልል 4 ሺህ 136፣ በአማራ ክልል 1 ሺህ 888፣ በደቡብ ክልል 1 ሺህ 166 እና በአዲስ አበባ 547 በአጠቃላይ 7 ሺህ 737 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ነው ብለዋል።

ኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን ስምና የሚቆዩበትን ቦታ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በየጊዜው ማሳወቁን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ መርማሪ ቦርዱ ከተጠርጣሪዎች አያያዝ ጋር ያሉ ጉድለቶችን በመለየት እንዲታረሙ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ከህብረተሰቡ እና የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀትም የታጠቁ አሸባሪዎችን፣ ፀረ ሰላም ሀይሎችንና ነውጠኞችን ለመቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም በኦሮሚያ 325፣ አማራ 275፣ ደቡብ 109 በድምሩ 709 ሸማቂዎችንና የታጠቁ ሀይሎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም አብራርተዋል። ባለፉት አስር ወራት የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሳይታወክ እንዲቀጥልና የኢንቨስትመንት ተቋማት ያለአንዳች ስጋት ስራቸውን እንዲያከናውኑ መደረጉንም ነው አቶ ሲራጅ ያነሱት።

ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠርም በተመረጡ አካባቢዎች 97 አዳዲስ ኬላዎችን በማቋቋምና 196 ነባር ኬላዎችን የማጠናከር ስራ ተሰርቷል፤ በዚህም 2 ሺህ 732 የጦር መሳሪያዎች፣ 181 ቦምቦችና ሁለት የግንኙነት ሬዲዮኖች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል። ሪፖርቱን ያደመጠው ምክር ቤቱ ለአስር ወራት የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ አንስቷል።

ዜናው የፋና ሲሆን ከዜናው ላይ በመውሰድ ርዕሱ ተቀይሯል፣ ፎቶ ከዝግጅት ክፍሉ

ከዛጎል ዜና የተወስደ