Skip to content
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና ዳንኤል ሺበሺ፣ በድጋሚ
ለብይን ተቀጠሩ!
-
[ የመምህር በቀለ ገርባ የዋስትና ጉዳይ ዛሬም መፍትሔ ሳይሰጠው በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል ]
ለ10 ወራት አገሪቱን በወታደራዊ ዕዝ እንድትመራ ያደረገው፣የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ በሕግ የገደበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዛሬው ዕለት መነሳቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋችኋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳንኤል ሺበሺ ለጥቅምት 29/2010 ዓ.ም በተለዋጭ ቀጠሮ ለብይን ተቀጠሩ ። በዛሬው እለት በቦሌ ክፍለ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ብይን ለመስማት ቀርበው የነበረ ቢሆንም፣ ብይን ስላልደረሰ በሚል ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። ፍ/ቤቱ በተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ሕግ በዝግ ችሎት ያቀረባቸውን የሰው ምስክር አድምጦ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበር ቢሆንም ፍ/ቤቱ “ብይኑ ተሰርቶ አልደረሰም” በማለት ለጥቅምት 29/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ በዚህ ክስ እያንዳንዳቸው አምሳ ሺህ ብር ዋስትና ማስያዣ እንዳቀረቡ ይታወቃል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመምህር በቀለ ገርባ የዋስትና መብታቸውን በተመለከተ በተደጋጋሚ ቀጠሮ ተይዞበት የነበረው ጉዳይ ዛሬም መፍትሔ ሳይሰጠው በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ሊሰጥ ችሏል። መምህር በቀለ ገርባ የተመሰረተባቸው የሽብር ወንጀል ክስ ወደ መደበኛ የወንጀል ሕግ ተቀይሮ እንዲከላከል ውሳኔ መሰጠቱ የሚታወቅ ነው። በዚሁ መሠረት መምህር በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄያቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄ የከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ እና አስተያየት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም ፤ ፍርድ ቤቱ አሁንም በድጋሚ የቀረበለትን የዋስትና መብት ጥያቄ ውሳኔ መስጠት ያልቻለ ሲሆን፤ያፊታችን ማክሰኞ ነሀሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ሰጥቷል ።
(ይድነቃቸው ከበደ)
Like this:
Like Loading...